ኢሳት ዜና ፦ በ2007ዓ.ም ለሚደረገው ሃገራዊና ክልላዊ ምርጫ ህብረተሰቡ ለተለያዩ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ድምፁን እንዳይሰጥ ለማፈን በሚያስችል ሁኔታ በክልሉ የሚገኙ ሚሊሻዎች ልዩ ተልዕኮ እንደተሰጣቸው ተገለጸ የአማራ ብሄራዊ ክልል መንግስት ሚሊሽያ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ መኳንንት መልካሙ ሰሞኑን ለታማኝ አመራሮች በሰጡት ድርጅታዊ መግለጫ ላይ በያዝነው ዓመት በሚካሄደው ምርጫ ህዝቡ የተለያየ ፅንፍ በመያዝ ገዢው ፓርቲ ላይ ስጋት የሚፈጥሩ ችግሮችን በማስወገድ ሙሉ በሙሉ አሸናፊ ለማድረግ የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ሲናገሩ ተደምጠዋል። አቶ መኳንንት ባለፈው ዓመት ለዚሁ ልዩ ተልዕኮ ከ360 በላይ ለሆኑ የሚሊሽያ አመራሮችና ባለሙያዎች በሁለት ዙር ፤ በወረዳ ደረጃ ላሉ የሚሊሺያ አባላትም ለአምስት ተከታታይ ቀናት በሁለት ዙር ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል። በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ከ3 ሺህ 600 በላይ በሆኑ ቀበሌዎች ላሉ የሚሊሽያ አባላትም ልዩ ተልዕኮውን እንዴት ማሳካት እንደሚችሉ የሚያግዝ ስልጠናዎች መሰጠታቸውን ምክትል ሃላፊው ለታማኝ የስርአቱ ደጋፊዎች ገልጸዋል።
በክልሉ ያሉ የሚሊሽያ አባላት ከህዝቡ የተወጣጡ እና የገዢው መንግስት ደጋፊዎች መሆናቸው ስለሚታመን ጠዋትና ማታ ከህብረተሰቡ ጋር በመገናኘት በየቀበሌው ካሉ ልዩ ልዩ የወጣት፣ የሴቶች እና የአርሶ አደሩ አደረጃጀቶችን በመጠቀም የመራጩን ህዝብ አመለካከት የመቀየር ስራ እንዲሰራ መታዘዙን፣ ይህ አሰራር ህዝቡ ታማኝነቱንና ድምጹን ለገዢው ፓርቲ የሚሰጥ መሆኑን የማረጋገጥ ሂደቱን ሊያሳካ ይችላል ተብሎ እንደታመነበት ለታማኞች ተናግረዋል። በተለያዩ ጊዜያት የተሰጡትን ስልጠናዎች ለማካሄድ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የጠየቀ ቢሆንም፣ ከዚህ ወጪ ውስጥ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ህብረተሰቡ እንዲሸፍን መደረጉን፣ ገንዘብ በእጁ የሌለው ድሃው ህብረተሰብ ሳይቀር በግ ፣ ፍየል ፣ ዶሮና እህል እንዲያዋጣ በማድረግ ለሚሊሺያው ስልጠና መሰጠቱን ባለስልጣኑ ገልጸዋል።
በቀጣይም ተመላሽ ከሆኑ ወታደሮች ውስጥ የተሻለ የድርጅት ፍቅር ያላቸውን በመለየት ወደ ሚሊሽያው የመቀላቀል ስራ እየተሰራ እንደሆነ በዚሁ ዝግ ውይይት ተናግረው ፣ ወታደሮቹ በየገጠር ቀበሌው ሲሰማሩ ልዩ ልዩ ጥቅሞችን ከአርሶአደሩ ሊያገኙ የሚችሉበትን አሰራር ለመዘርጋት ግፊት የማድረግ ሃሳብ ወደ አመራሩ ዘንድ እንደወረደም አስረድተዋል። አቶ መኳንንት የግልና የመንግስት ተቋማት ጥበቃዎችና ሚሊሺያው ከላይ እስከታች የአመለካከት ችግር ያለባቸው በመሆኑ እና ተልዕኮ የሚሰጣቸው ከጸረ ሰላም ሃይሎች በመሆኑ ለአካባቢው ልማት ጠንቅ መሆናቸውን ገልጸዋል። ተከታትለው አንዳንድ ርምጃዎችን ለመውሰድ በአመራሩ መካከል መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል። ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ በዳንግላ ዙሪያ ወረዳ የሚገኙ አንዳንድ አመራሮችና የሚሊሺያ አባላት ሚሊሺያው ከገዢው መንግስት ጥቅም ይልቅ የህብረተሰቡን ጥቅም በማስቀደም ከታሪክ ተወቃሽነት ነጻ እንሆናለን ብለዋል። የድምጽ መረጃውን ለላኩልን የሚሊሺያ አባላት ምስጋናችንን እንገልጻለን።