ሚስቱ አረገዘችበት ፡ ደነገጠ – እንድታስወርደው ጠየቃት አሻፈረኝ አለች፡፡ በጣም ተቆጣ ! ቁጣው ሲውል ሲያድር ቁዘማ ሆነ ፡፡ ቁዘማው ላልተወለደው ልጁ ደብዳቤ እንዲፅፍ አነሳሳው ፡፡
ሁለት ደብዳቤዎችን እንዲፅፍ አነሳሳው ፡፡ ሁለት ደብዳቤዎችን ፃፈ፡፡ የደብዳቤዎቹ ሙሉ ቃል ይሄ ነው፡፡
አንደኛው ደብዳቤ፡-
ልጄ የወገቤ ክፋይ፡-ከኔ ወገብ ከተለያየንበት እንዲሁም ከእናትህ ማህፀን ከተገናኘህበት ሰዓት ጀምሮ እንደምን አለህልኝ እኔ ትወለዳለህ ከሚለው ሀሳብና ሰቀቀን በስተቀር ደህና ነኝ ልጄ ፡፡
ይሄን ደብዳቤ የፃፍኩልህ የፊደልንና የቋንቋን ጣጣ ከማህፀን እንድትጀምረው ለማስገደድ አይደለም ፡፡
ይልቁንስ ለውሳኔ እንዳትቸኩል ከመምጣትህ በፊት ግራ ቀኙን እንድትመረምር ነው፡፡ አሁን ጨቅላ አይደለህም የ3 ወር ጎረምሳ ነህ ! አውራ ጣትህን መጥባት ጀምረሃል፡፡
ጊዜህን እንደጥንቱ በራስ በመቆም ብቻ እንደማታሳልፈው አውቃለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ 6 ወሮች አሉህ ፡፡ በእኚህ ቀሪ ጊዜያት እንድትፋፋባቸው ሳይሆን እንድታስብባቸው እፈልጋለሁ፡፡ ስለሁሉም ነገር አስብ ፡፡
ከመቸኮልህ በፊት አስብ ፡፡ እኔ 40 ዓመት ሞልቶኛል፡፡ ግን በዕውቀትና በጥበብ ካንተ እንደማልበልጥ አውቃለሁ፡፡ ‹‹ ማወቅ ማለት ከውጭ ያለውን መማር ማለት አይደለም፣ ከመወለዳችን በፊት ያለውን ማስታወስ ነው ›› ብሏል ሰውዬው ፡፡
ይህንን ብሂል ያመንኩ ቀን ስቅስቅ ብዬ ነው አለቀስኩ፣ ለካ አባቴ ቄስ ትምህርት ቤት ያስገባኝ ፤ አንደኛ – ሁለተኛ -ሦስተኛ ደረጃ ትምህርት ያስተማረኝ ፤ ባለ ድግሪ ፤ በለ ማዕረግ ያሰኘኝ አልባሌ ቦታ ከምውል ብሎ ኖሯል ፡፡ ስለዚህ ‹‹ የምወለደው ለማወቅ ስለምፈልግ ነው ›› አትበል! ፡፡ እኔ ካንተ አላውቅም ፤ ካንተ አልበልጥም፤ ምናልባት የምበልጥህ በንዴትና በሽበት ብቻ ይሆናል፡፡
ልጄ ወዳጄ የወገቤ ክፋይ እንዳትወለድ የማሳሳብህ ስለምጠላህ አይደለም ! ‹‹እወድሃለው›› – ‹‹እወልድሃለው›› አላልኩም ‹‹እወድሃለው›› ፡፡ ግን የወደድነውን በባዶ ቤት አንጋብዝም ፤ እናትህ ‹‹ ሁላችንም እዚህ ምድር ስንመጣ ዕርቃናችንን ነው ›› ትላለች ፡፡ ብወዳትም አላመንኳትም ፡፡
ጥቂቶች ለብሰው እንደሚወለዱ አውቃለሁ፡፡ ለምሳሌ ከካናዳ የመጣች ጓደኛዬ ስትነግረኝ ካናዶች አንድ ልጅ ሲወልዱ ብዙ ሺህ ብር ከመንግስት ይሰጣቸዋል፡፡ የስካንዲቪያን ሠዎች አርግዘው በታዩ ጊዜ አስተዳደሮቹ ለመጪው ልጅ የሚሆን ቁሳቁስ ፣ ቤት ያሰናዱላቸዋል፡፡
የፈረንጅ ልጆች ስንቅ ሳይዙ ወደዚህች ምድር አይመጡም ! ለፈረንጅ አባቶች ልጅ ክፍት የስራ ቦታ ማለት ነው ፡፡ ሲሳይ ነው ፡፡ ስለዚህ አንድ ካናዳዊት ብታስወርድ እህል የሞላው ጎተራ አቃጠለች ማለት ነው፡፡ እኔ አሁን ውጭ ሀገር ኖሬ አላውቅም ፣ ግን የሰማሁትን ይዤ ብዙ አስባለሁ፡፡
የፈረንጅ ሽማግሎች ጡረታ ሲወጡ በመውለድ የሚጠመዱ ይመስለኛል፡፡ በዕድሜዬ መግፋት ያጣሁትን ደመወዝ በሚስቴ ሆድ መግፋት እመልሰዋለሁ የሚሉ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ የተነሳ እናትህ ‹‹እናትህ ሁላችንም የመጣነው ዕርቃናችንን ነው›› ስትል የባልነቴን ጭንቅላቴን ባወዛውዝላትም አላምናትም፡፡
ከላይ እንዳስነበብኩህ የፈረንጅ ልጆች ለብሰው ይወለዳሉ ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ለወላጆቻቸው ካፖርትና ቀሚስ ይዘው ወደዚህች ዓለም ይመጣሉ ፡፡ የሀበሻ አባት ግን ሚስቱ ስታረግዝ የድሮ ሱሪውን ማሳጠር ይጀምራል፡፡ አለበለዚያ ልጁ ሲወለድ ምን ይለብሳል ? ልጄ ወዳጄ የወገቤ ክፋይ ፡- ይሄ ሁሉ የሆነው በእኔ ጥፋት አይደለም ፤ ጥፋቱ ሁሉ የእናትህ ነው፡፡ እመነኝ ፡፡
የመጀመሪያ ስህተቷ ሴት መሆኗ ነው፡፡ ግዴለም ትሁን ፤ – ለምን ተቆነጃጀች ? – ግዴለም ትቆንጅ ፤ ለምን በደጄ አለፈች ? – ግዴለም ትለፍ፤ ለምን ሠላምታዬን መለሰች ? – ግዴለም ትመልስ፤ ለምን እኔን አመነች ? – ግዴለም ትመን፤ ለምን እሺ ብላ ተሳመች ? – ግዴለም ትሳም፤ ለምን…… ? – ግዴለም አንዴ ሆኗል ! ፡፡ ልወቅሳት አልፈልግም ምክኒያቱም እወዳታለሁ፡፡
እንዲያውም ጥፋተኛው እኔ ሳልሆን አልቀርም ፡፡ የመጀመሪያው ስህተቴ ወንድ መሆኔ ነው ፤ ወንድ ባልሆን ኖሮ ከድንበር አትሻገራትም ነበር ፡፡ ክኒኑን እንደ ቁርስ ምሳዬ ሳላሰልስ እወስደው ነበር ፡፡ የክኒንና የወንድ ዝምድና ግን አይገርምም ? ወንዶች ክኒንን ይሰሩታል – ሴቶች ይውጡታል፡፡ የለም! ስህተቱ የእኔም የእናትህም አይደለም ! ያንተ ነው፡፡ መጀመሪያ ማሰብ ነበረብህ << Think twice before you born once ok! >>
እኔና አናትህ መደሰት መብታችን ነው ለመደሰት ቀን መቁጠር የለብንም ! አንተ መወለድ መብትህ ነው ግን መብትህን ለመጠቀም ጊዜና ቦታ መምረጥ አለብህ ፡፡ አሁን ምን አጣደፈህ? ተው እንጂ ልጄ ጥድፊያ በዘራችን የለም ! ምናልባት ‹‹ዕድገት እየታየ ነው›› የሚል ወሬ ከሰማህ አትመነው ፡፡ ከእናት ሆድ በስተቀር እዚህ ሀገር ያደገ ነገር የለም፡፡
ልጄ በርግጥ ካንተ ጋር እደራደራለሁ፡፡ ካልተወለድክ በጣም ብዙ ነገር ላደርግልህ ቃል እገባለሁ ፡፡ ካልተወለድክ ጥሩ አባት እሆንሃለው፡፡ አስብበት!፡፡ የማነበው መፅሀፍ ላክልኝ ባልከው መሰረት የአቤ ጉበኛን ‹‹ አልወለድም›› ን ልኬልሃለው ፡፡ መልስህን በቶሎ እጠባበቃለሁ፡፡
*****
ሁለተኛ ደብዳቤ :
እምቢ አልክ ! መልዕክትህን አንብቤ ደሜ ፈላ! ግትር ነህ ! ቂል ነህ ! ‹‹ የወፎችን ድምፅ መስማት ስለምፈልግ በቅርቡ እወለዳለሁ›› ብለሃል ፡፡ አትጃጃል፡፡
የሞባይልና መኪና እንጂ የወፍ ድምፅ እዚህ አዲስ አበባ ከየት አምጥተህ ነው የምትሰማው ? ፍላጎትህ ይህ ከሆነ አማዞን መሀል ተፈጠር፡፡ በአጠቃላይ መልዕክትህ ሁሉ ግትርነትህን የሚያሳይ ነው ! ፡፡ እናትህ ልዝብ ጨዋ ናት፡፡ ቤተሰቦቿም ለስላሶች ናቸው፡፡
እኔም ትሁትና ተግባቢ ነኝ ታዲያ ይሄ ግትርነት ከየት መጣ ? በሁለታችንም ደም ውስጥ ግትርነት ከሌለ አንተ ከየት ወረስከው ? መቼም ልጄ ነህ ብዬ ለማመን መልክህን የግድ ማየት የለብኝም፡፡ ጠባይህም ከእኔ የተገኘ መሆኑን ማወቅ አለብኝ ፡፡ ባህሪህ የእኔ አይደለም ፡፡ የእናትህም አይደለም፡፡ ስለዚህ የእኔ ልጅ አይደለህም ፡፡ ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ የምነጋገረው ካንተ ጋር አይደለም ፤ ከእናትህ ጋር ነው ፤ ከእርሷ ጋር ሁሉን እንጨርሳለን፡፡
*****
© በዕውቀቱ ሥዩም