የ’ዳ ክንድሽ አቅፎኝ
ያሳር ክንፍሽ ኣቅፎኝ
እንቁሽን ስመኘው
ጣጣሽ ብቻ ተርፎኝ
መኖርን ስፈራ – መሞትም ስፈራ
ካየር ንብረት በቀር- ንብረት ሳላፈራ
ወሩ ተጠራቅሞ- አንድ ደርዘን ሞልቶ
እንደባለጌ ልጅ – በሩን በግሩ ከፍቶ
አዲስ ዘመን ገባ::
አዲስ ኣመት ገባ
ያለ መስቀል ወፎች – ያለ አደይ አበባ
በግዜር ሰራሽ ማማ
ቁራ ብቻ ሰፍሯል
የመስቀል ወፍማ
ወይ አገር ለውጧል
ወይ ልብሱን ቀይሯል::
አዲስ ኣመት ገባ
በቄጤማ ምትክ- ቡልኬት ጎዝጉዞ
በቅፍ አደይ ምትክ- ጉንጉን ሽቦ ይዞ
በሉባንጃ ምትክ- አቡዋራ እያጤሰ
በፈንድሻ ምትክ- ጠጠር እያፈሰ::
አዲስ አመት ገባ
አዲስ እንዲህ ዋዛ
ተፈጥሮ በውበት -መንፈሴን ሳይገዛ
በመአዛው ሳይዋጅ
መስከረም መግባቱን- በሬድዮ ልስማው?
እንደ መንግስት አዋጅ: