Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ከንግድ ባንክ ከሰባት ሚሊዮን ብር ላይ በመመዝበር የተጠረጠሩ ኃላፊዎች ተከሰሱ

$
0
0

- ተጠርጣሪዎቹ በጋብቻና በሥጋ ዝምድና የተሳሰሩ ናቸው ተብሏል

CBE_SAበኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው መሥሪያ ቤት በሒሳብ ማስታረቅ ሥራ ክፍል የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅና የሒሳብ አስታራቂ ሲኒየር ኦፊሰርን ጨምሮ 13 ተጠርጣሪዎች፣ ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ከባንኩ የውስጥ ሒሳብ በመመዝበር ወንጀል ተጠርጥረው ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ነሐሴ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት ክስ ያቀረበባቸው፣ የንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት የሒሳብ ማስታረቅ የደንበኞች አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምርአየሁ ተክሌና የሒሳብ አስታራቂ ከፍተኛ ኦፊሰር አቶ ኤፍሬም ወልደተንሳይ ናቸው፡፡

የአቶ ታምራየሁ አማች ናቸው የተባሉት አቶ ንብረት ማሞና እህቶቻቸው ወ/ሮ ትንሳኤ ማሞ (የአቶ ታምራየሁ ሚስት)፣ ወ/ሮ ውዳሴ ማሞ፣ የአቶ ኤፍሬም ወንድም አቶ ሔኖክ ወልደተንሳይና የአቶ ታምራየሁ አክስት ልጅ ናቸው የተባሉት ተጠርጣሪ አቶ ዓለሙ አብርሃም (ያልተያዙ) በዋና ወንጀል አድራጊነት የተጠረጠሩ ናቸው፡፡ በአቶ ንብረት ማሞ ሥራ አስኪያጅነት የሚመሩና አድራሻቸው በሐዋሳ የሆነ ጂቢሲ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ማኅበር፣ ንብረት ማሞ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ድርጅት፣ በአቶ ታምራየሁ ሥራ አስኪያጅነት የሚመራው አዳነና ቤተሰቦቹ የኮንስትራክሽን ማሽነሪ አከራይ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ በአቶ ሔኖክ ሥራ አስኪያጅነት የሚመራው ሔኖክ ወልደተንሳይ ኮንስትራክሽን ማሽነሪ አከራይ ድርጅትና በአቶ ዓለሙ ሥራ አስኪያጅነት የሚመራ ወንድገማኝ ዴዛ ሕንፃ ሥራ ኮንስትራክሽን ድርጅትም በክሱ ተካተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው መሥሪያ ቤት፣ በሒሳብ ማስታረቅ ሥራ ላይ የነበሩት ኃላፊዎች አቶ ታምራየሁና አቶ ኤፍሬም፣ ከሌሎቹ ተጠርጣሪዎች ጋር በሥጋና በጋብቻ ዘመዳሞች መሆናቸውን የሚጠቁመው የዓቃቤ ሕግ ክስ፣ ይኼም ግንኙነታቸው ወንጀሉን ለመፈጸምና ሚስጥሩን ለመጠበቅ መልካም አጋጣሚ ስለፈጠረላቸው፣ የማይገባ ጥቅም ለማግኘትና ለሌሎች ለማስገኘት በማሰብ፣ ከባንኩ የውስጥ ሒሳብ ላይ 7,064,857 ብር መመዝበር በመንግሥት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ገንዘቡ ሊመዛበር የቻለው ሁለቱ የባንኩ ኃላፊዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመጠቀም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው መሥሪያ ቤት የውስጥ ሒሳብ ላይ በመቀነስ፣ በተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፎች መተላለፍ የሚገባቸውን የሒሳብ ማስታረቅ ሥራዎች፣ የሥራ ኃላፊነትን ወደ ጎን በመተው ለጥቅም ሲሉ መመሳጠራቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

በመሆኑም ገንዘቡን በስውር ለመመዝበር እንዲያስችላቸው ከአቶ ንብረት ማሞና ከአቶ ዓለሙ አብርሃም ጋር በጥቅም በመመሳጠር የአቶ ኤፍሬምን የግል መግቢያ ቃል (User Name) እና የሚስጥር ቃል (Password) በሕገወጥ መንገድ በመጠቀም ወጪ ማድረጋቸውን ክሱ ይዘረዝራል፡፡

ሁለቱ የባንኩ ኃላፊዎች የክሬዲት ሒሳብ ትኬት አዘጋጅተው በመፈረምና የባንኩን ሠራተኞች የባንክ ሲስተም የግል መግቢያ ቃልና የሚስጥር ቃል በመጠቀም፣ ገንዘቡን በተለያየ መጠን ወጪ ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

ከባንኩ የውስጥ ሒሳብ ላይ ያላግባብ ወጪ በማድረግ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሐዋሳ ዲስትሪክት ታቦር ቅርንጫፍ፣ አቶ ንብረትና ወ/ሮ ውዳሴ መሥራች በመሆን ባቋቋሙት ጂቢሲ ጠቅላላ ኮንስትራክሽን ስም በተከፈተ አካውንትና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጠመንጃ ያዥ ቅርንጫፍ በሚገኘው ወንድማገኝ ዴዛ ሕንፃ ኮንስትራክሽን ስም በተከፈተ አካውንት፣ በድምሩ 7,064,857 ብር በሕገወጥ መንገድ እንዲዛወር ማድረጋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

አቶ ንብረት የተባሉት ተጠርጣሪ ከወ/ሮ ውዳሴ ጋር በጋራ ባቋቋሙት ድርጅት ስም፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋናው መሥሪያ ቤት ሒሳብ ላይ እየተቀነሰ ሐዋሳ በሚገኘው የባንኩ ታቦር ቅርንጫፍ በሁለቱ የባንኩ ኃላፊዎች አማካይነት ሲተላለፍላቸው እንደነበር፣ በአቶ ኤፍሬም ስም በኅብረት ባንክ መስቀል ፍላወር ቅርንጫፍ በከፈቱት ሒሳብ ሲያስተላልፉ እንደነበር፣ በአቶ ሔኖክ ስም በዳሸን ባንክ መስቀል ፍላወር ቅርንጫፍ ሲተላለፍ እንደነበር፣ በወ/ሮ ትንሳኤ ስም በዳሸን ባንክ ዓቢይ ቅርንጫፍ በተከፈተ ሒሳብ ሲተላለፍ እንደነበርና በሌሎቹም ግለሰቦችና ድርጅቶች ስም በተለያዩ ባንኮች በተከፈቱ አካውንቶች ገንዘቡን ሲያስተላልፉ እንደነበር ክሱ ይገልጻል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተለያዩ አካውንቶች ወጥቷል የተባለውን ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ የተለያዩ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች፣ ደረቅ የጭነት ማመላለሻ ገልባጭ መኪና፣ ጅምር ቤት፣ የቤት አውቶሞቢሎችና ሌሎች ንብረቶችን መግዛታቸውንና በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስለው በማቅረብ ሲገለገሉበት እንደነበር ክሱ ያስረዳል፡፡

በአጠቃላይ ተጠርጣሪዎቹ ሁለት ክስ የቀረበባቸው ሲሆን አቶ ታምራየሁ፣ አቶ ኤፍሬም (ያልተያዙ)፣ አቶ ንብረት፣ አቶ ሔኖክ፣ ወ/ሮ ትንሳኤ፣ ወ/ሮ ውዳሴ (ያልተያዙ)፣ አቶ ዓለሙ (ያልተያዙ) በመንግሥት ላይ ጉዳት በማድረሳቸውና ያላግባብ ተጠቃሚ በመሆናቸው በዋና ወንጀል አድራጊነትና በልዩ ወንጀል ተካፋይነት በፈጸሙት በሥልጣን ያላግባብ መገልገል ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

በሌላ በኩል ሁሉም ተጠርጣሪዎች ያገኙትን ገንዘብ ሕገወጥ አመጣጡና ምንጩን በመደበቅና በመሸፈን፣ ሕጋዊ አስመስሎ ለማቅረብና ከወንጀል ተጠያቂነት ለማምለጥ፣ የገንዘቡን እንቅስቃሴ ሰውረው በማዘዋወር በፈጸሙት፣ በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሙስና ወንጀልም መከሰሳቸውን ክሱ በዝርዝር ያስረዳል፡፡

Source:: Ethiopian Reporter


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>