*ጦርነት፣በሽታ፣ድህነት– ለድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ መስፋፋት አስተዋጽኦ አበርክተዋል
“ድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ”የሚለውን አጠራር የተባበሩት መንግስታት ዓለምአቀፍ የህፃናት ፈንድ(ዩኒሴፍ)፤ ልጆች ከትውልድ አገራቸው ድንበር ተሻግረው ወደ ሌላ አገር በመግባትበጉዲፈቻ የሌላ ቤተሰብ አባል የሚሆኑበት ሁኔታ ነው ሲል ይተረጉመዋል
በተለያዩ አገራት ዜጐች መካከል የሚፈፀም ጉዲፈቻ እየጨመረ የመጣው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ጦርነት የተነሳ አያሌ ህፃናት ወላጆቻቸውን በማጣታቸው፤በማሳደጊያዎች ውስጥበአሰቃቂ ሁኔታ ተይዘው ለማደግ ይገደዱ ነበር፡፡ከዚያ የተሻለ ሌላ አማራጭም አልነበራቸውም፡፡
ድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ የተጀመረው የተለያዩ አገራት ወታደሮች የጦርነት ቀጠና በሆኑ የዓለም አገራት መስፈራቸውን ተከትሎ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በበርካታ የአለም ክፍሎች የተነሱ ግጭቶች ለወታደሮች በየአገሩ መስፈር ምክንያት ሆኗል፡፡ በተለይ የተባበሩት መንግስታት ወታደሮች በኮሪያ ጦርነት እንዲሁም የአሜሪካ ወታደሮች በቬትናም ውጊያ ወቅት በርካታ ልጆችን እንደወለዱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በአብዛኛው ጉዲፈቻ የተደረገው ወደ አሜሪካ እና አውሮፓ አገራት ሲሆን የጉዲፈቻ ልጆች ምንጭ አገሮችም ደቡብ ኮሪያ፣ ቬትናም እና የመሳሰሉት ነበሩ፡፡ ከጦርነትና ግጭቶች በተጨማሪም ድርቅ፣ በሽታና ድህነትም ለድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ መስፋፋት ምክንያት ሆነዋል፡፡
ለዚህም ሩሲያ፣ ጉዋቲማላ፣ ቻይና እና የአፍሪካ አገራት ይጠቀሳሉ፡፡
በተለይ ከደቡብ ኮሪያ በርካታ ቁጥር ያላቸው ህፃናት በጉዲፈቻ የተወሰዱ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ በሰሜኑና ደቡብ መካከል በተደረገው በርካታ አገሮች የተሳተፉበት ጦርነት፣ ልጆች ቤተሰባቸውን በማጣታቸው ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በወቅቱ በደቡብ ኮሪያ ሰፍረው ከነበሩ የአሜሪካ ወታደሮች የተወለዱ ህጻናት በመልክ ከአካባቢው ማህበረተሰብ የተለዩ ስለነበሩ፣ለማህበራዊና ስነልቦናዊ ችግሮች ተጋልጠዋል፡፡እነሱ ብቻ ሳይሆኑ እናቶቻቸውም በሕብረተሰቡ ዘንድ መገለል ይፈጸምባቸው ነበር፡፡በጦርነት ሰበብ የተወለዱ ህፃናት በአብዛኛው በጉዲፈቻ የሚወሰዱት ወደ አባቶቻቸው አገር ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ በአባታቸው የዜግነት መብት ስላላቸው ነው፡፡ ይሔም ለድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ መጨመር አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር“በጦርነት ምክንያት የተወለዱ ልጆች በመሆናቸው ልንታደጋቸው ይገባል”የሚለው አስተሳሰብ ድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻን ያስፋፋ ሲሆን “ጉዲፈቻ በአገሮች መካከል መልካም ግንኙነት ለመፍጠርም ይረዳል”የሚለው አመለካከት ስር መስደዱ ሌላው ምክንያት ነው ሊባል ይችላል፡፡
በአሜሪካ ድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ ተቋማዊ በሆነ መልኩ የተጀመረው እ.ኤ.አ. በ1956 ዓ.ም ሆልት በሚባል በጎ አድራጊ ግለሰብ ሲሆን በአሁኑ ወቅት “ሆልት ችልድረንስ ሰርቪስ” በበርካታ አገራትየሚንቀሳቀስና ብዙ ቅርንጫፎች ያሉት የጉዲፈቻ አገልግሎት ኤጀንሲ ለመሆን በቅቷል፡፡ ኤጀንሲው ኢትዮጵያ ውስጥ መስራት ከጀመረም ከሰባት ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡
በተለያዩ አገራት የተከሰቱ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችምለድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
በሮማኒያ የቻችስኩ መንግስት ፖሊሲ /Ceausescu’s Policy/ እያንዳንዷ ሩማንያዊት ሴት፣ቢያንስ አምስት ልጅ የመውለድ ግዴታ ተጥሎባት ነበር፡፡ አንዳንድ ቤተሰቦች ታዲያበድህነት የተነሳ የወለዷቸውን ልጆች ማሳደግ ስለማይችሉ ህጻናት ማሳደጊያ ውስጥ ለማስገባት ይገደዱ ነበር፡፡ የቻችስኩ መንግስት እ.ኤ.አ. በ1989 ዓ.ም በወደቀ ማግስት፣በአገሪቷ ውስጥ ከስድስት እስከ ስምንት መቶ የሚደርሱ የህፃናት ማሳደጊያዎች ነበሩ፡፡በእያንዳንዱ ማሳደጊያም ከ100ሺ እስከ 300ሺ የሚገመቱ ህፃናትእንደነበሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በማሳደጊያዎች ውስጥ ያሉ ህፃናት ሁኔታበመገናኛ ብዙሃንበሰፊውይነገር ስለነበር፣ አሁንም “ልጆችን ልንታደጋቸው ይገባል” በሚል ዓላማ፣የምእራቡ አለም ድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻን ማድረጉን ቀጠለበት። በተመሳሳይ ሁኔታ በሩሲያ በነበረው ከፍተኛ የሆነ ድህነት የተነሳም ከ300ሺ በላይ ህፃናት ማሳደጊያ ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡ ይሄን ተከትሎም የድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ ሊጨምር ችሏል፡፡
በቻይና አሁንም ድረስ የሚተገበረውና የህዝብ ብዛትን ለመቀነስ በመንግስት የወጣው አንድ ልጅ ብቻ የመውለድ ፖሊሲ፣ ዜጎች ጉዲፈቻ እንዳያደርጉ ከተቀመጠው ክልከላ እንዲሁም ህብረተሰቡ “ወንድ ልጅ ቤተሰቡን ይጦራል” በሚል ለሴት ህፃናት ባለው አሉታዊ አመለካከት የተነሳ፣ ብዙ ልጆች በተለይም ሴት ልጆች ማሳደጊያ ውስጥ እንዲገቡ ተገደዋል፡፡
የኤችአይቪ/ ኤድስ መስፋፋትምለድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ መጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከሰሃራ በታች ባሉ የምስራቅ አፍሪካ አገራት 12.3 ሚሊዮን ህፃናት በኤድስ ምክንያት ወላጆቻቸውን እንዳጡ ይገመታል፡፡ ሆኖም በአፍሪካ ድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ እንደሌሎች የዓለም አገራት በብዛት አልተለመደም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በአህጉሪቱ ልጆችን በቤተዘመድ የማሳደግባህል መኖሩ ሳይሆን እንደማይቀር ይገመታል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ የአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ግንወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት በቤተዘመድ የማሳደግ ሁኔታ መቀጠሉ በእጅጉ የሚያጠራጥር ነው፡፡ እናም በአፍሪካ ድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ እየተስፋፋ እንደሚመጣ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
ድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ፤ ዝምድና በሌላቸው ሰዎች መካከል የሚደረግ የጉዲፈቻ ዓይነት በሚለው ዘርፍ የሚመደብ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ጉዲፈቻ ልጁ የተፈጥሮ ልጅ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን በጉዲፈቻ አድራጊዎችናበጉዲፈቻ ተደራጊ መካከል የድንበር፤ የቀለም፣ የባህል፣ የዘር፣የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልዩነትምየሚስተዋልበት መሆኑ ነው፡፡
የድንበር ተሻጋሪ ጉዲፈቻ፤ መንግስት ወላጅ ለሌላቸው ህጻናት ከሚያቀርበው አማራጭ የእንክብካቤ መንገዶችአንዱ ሲሆን ጉዲፈቻው ፐብሊክ /public adoption/ በሚለው ዘርፍ ይመደባል፡፡ ይህም ለጉዲፈቻ የሚቀርቡት ልጆች ዕጣ ፈንታየሚወሰነው በሚመለከተው የመንግስት አካል መሆኑንያመላክታል።
ምንጭ፡ አዲስ አድማስ