Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሕወሃት/ኢሓዴግ ምን ያህል እንዳከረረ (ክፍል 2) – ግርማ ካሳ

$
0
0

አገር ውስጥ በሰላም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች አመራር አባላት ናቸው። አብርሃ ደስታ ከአረና፣ ዳንኤል ሺበሺና ሃብታሙ አያሌው ከአንድነት፣ የሺዋስ አሰፋ ከሰማያዊ። ሐምሌ 1 ቀን 2006 ሽብርተኞች ናችሁ ተብለው ተያዙ። ጠበቃዎቻቸው በሌሉበት በድብቅ ፍርድ ቤት ቀረቡ ተባለ። ፖሊስ ዜጎችን ከመያዙ በፊት በእጁ መረጃ ሊኖረው ሲገባ፣ መረጃ ለማሰባሰብ ጊዜ ያስፈልገኛል ብሎ ለ28 ቀናት ቀጠሮ ይጠይቃል። ፍርድ ቤቱ፣ ያለምንም ማቅማማት፣ ምን መረጃ በሌለበት ሁኔታ፣ የታሳሪዎችን የዋስትና መብት ከልክሎ 28 ቀናትም እንዲታሰሩ ያዛል።

tplfከ28 ቀናት በኋላ ሃብታሙ፣ ዳንኤል እና የሺዋስ ነሐሴ 27 ቀን እንደገና ፍርድ ቤት ቀረቡ። አሁንም ፖሊስ ማስረጃ ሳያቀርብ ለ28 ቀን ሁለተኛ ቀጠሮ ጠየቀ። ፍርድ ቤቱ አሁንም፣ ምንም መረጃ ሳይመለከት፣ ፖሊስ ስለጠየቀ ብቻ፣ ዜጎች በወህኒ እንዲቆዩ አዘዘ። አምሣ ስድስት ቀናት መረጃ ሳይቀርብ ዜጎች ሕግ ያስከብራል በሚባለው አካል የሰብአዊ መብታቸው ተረገጠ። እንደገና ለመስከረም 22 ቀን ተቀጠሩ። ነሐሴ 29 ቀን ደግሞ አብርሃ ደስታ ፍርድ ቤት ሲቀርብ የተለየ ነገር አልነበረም። «ተጨማሪ ሰነድ ለማሰባሰብና ምስክሮች ለማቅረብ ጊዜ ያስፈልገኛል» ብሎ ፖሊስ በመጠየቁ ተጨማሪ 27 ቀን ይሰጠዋል።

እነዚህ የታሰሩ ወጣት ፖለቲከኞች የሰሩት አንዲት ወንጀል የለም። ወንጀላቸው ለፍትህ፣ ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ መቆማቸው ነዉ። ወንጀላቸው አገራችውን መዉደዳቸው ነው። የሕወሃት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ግን፣ ሕግን እንደ በተር በመጥቀም፣ ጠንካራ የሚባሉ፣ ተሰሚነት ያላቸውን ወጣት የፖለቲካ አመራሮች በማሰር፣ ሆን ብሎ የተቃዋሚዎችን እንቅስቃሴ ለማሽመድመድ እየሞከረ እንደሆነ ግን ግልጽ ነው።

ከዘጠና ሰባት በኋላ በተፈጠረው ሁኔታ «ቅንጅት ሞቷል፤ የተቃዉሞ እንቅስቃሴውም አልቆለታል» በሚል ሕወሃት/ኢሕአዴጎች ዳንኪራ ሲመቱ እንደነበረ ይታወቃል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የተበታተነዉን አሰባስባ አንድነት በሚል ስም ጠንካራ ፓርቲ እንዲወጣ አደረገች። የአገዛዙ ባለስልጣናት 50 ሰው አይገኝም ያሉት፣ በሜክሲኮ አደባባይ መብራት ኃይል አዳራሽ ያኔ በተደረገው፣ የመጀመሪያው የአንድነት ሕዝባዊ ስብሰባ፣ ከ5 ሺህ ሰው በላይ በመግባቱ አዳራሹ ሞላ። የአዳራሹ በር ተዘግቶ ብዙ ህዝብ እንዲመለስ ተደረገ። በአራት ኪሎ ያሉ ባለስልጣናት ደነገጡ። ሰበብ ፈልገው ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን አሰሯት። ኢንጂነር ግዛቸው ሃላፊነቱን ያዙ። ነገር ግን የፓርቲው እንቅስቃሴ ተዳከመ። አንድነት ተከፋፈለ። በድጋሚ በሕወሃት/ኢሕአዴጎች ዘንድ ፌሽታ ሆነ።

አንድነት ዉስጥ እንደ አንድዋለም አራጌ ያሉ ወጣት አመራሮች መጡ። መጠነ ሰፊ ድርጅታዊ ሥራ መስራት ጀመሩ። ትንሽም ብትሆን አንድነት በአገሪቷ ሁሉ ድርጅታዊ መዋቅሩን መዘርጋት ጀመረ። የአንድነት ጥንካሬ ያሳሰበው ሕወሃት/ኢሕአዴግ እንደገና በትሩን አነሳ። አንድዋለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን የመሳሰሉ ጠንካራ አመራሮች ታሰሩ።

ብዙም አልቆየም ተወዳጁ እና ተስፍ ሰጪው የሚሊየነሞች ንቅናቄ ተጀመረ። በሌላ በኩል ከመኢአድ ጋር አንድነት የሚያደርገው የውህደት እንቅስቃሴ ትልቅ መነቃቃትን ፈጠረ። የአንድነት ፓርቲ ገዢዎች ከጠበቁት እና ከገመቱት በላይ ገፍቶ ስለሄደባቸው በድጋሚ በትራቸውን አነሱ። በሚሊዮኖች ንቅናቄና በመኢአድ አንድነት ዉህደት ዙሪያ፣ ትልቅ ሚና የነበረው፣ የአንድነት የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ወጣት ፖለቲከኛው ሃብታሙ አያሌውን አሰሩት። በተለይም በደቡብ ክልል ትልቅ ድርጅታዊ ሥራ ሲሰራ የነበረዉን የፓርትቲው ምክትል የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ዳንኤል ሺበሺንም እንደዚሁ። የአንድነት መሪ የሆኑት ኢንጂነር ግዛቸው ፣ ሃብታሙ ከታሰረ በኋላ የሚሊየነኖምችን ንቅናቄ ማስኬድ አልቻሉም። እንቅስቃሴው ባለበት ቆመ። ወደፊትም ቆሞ የሚቀር ይመስላል፣ የአንድነት አባላትና ደጋፊዎች ግፊት አድርገው ፓርቲው ከቢሮ ወደ ሜዳ እንዲወጣ ካላደረጉት በቀር።

በአብዛኛዉ የአገዛዙን በትር የቀመሰው የአንድነት ፓርቲ ቢሆንም፣ ሰማያዊ፣ አረና እንዲሁም ሌሎችም አላመለጡም። የሰማያዊ እና የአንድነት አብሮ መስራት ፣ ብሎም መዋሃድ ፣ የአንድነት እና የመኢአድ መዋሃድ የአገዛዙ ራስ ምታቶች ነበሩ። በተቻለ መጠን ሰማያዊን እና አንድነትን ማራራቅ፣ አንድነት እና መኢአድ እንዳይዋሃዱ ማድረጉን ትልቁ ግባቸው አድርገው ነበር ሲሰሩ የነበሩት። በመሆኑም የሚቆጣጠሩትን ምርጫ ቦርድ ተጠቅመው፣ የመኢአድ እና የአንድነት ዉህደትን ለጊዜው አደናቀፉ። በሰማያዊና በአንድነት መካከል መቀራረብ እንዲኖር ይተጋ የነበረዉን የሰማያዊ ምክር ቤት ም/ሰብሳቢ የሺዋስ አሰፋንም ወደ ወህኒ ወሰዱት።


በሰሜን የሕወሃት እምብርት በሆነችዋ ትግራይ፣ የፍትህና የዲሞክራሲ ድምጽ ሆኖ ሲጽፍ የነበረው፣ የአረና አመራር አባል አብርሃ ደስታ፣ ለሕወሃቶች ትልቅ ራስ ምታት ነበር የሆነባቸው። እነርሱ ጠመንጃ ይዘዋል። እርሱ ግን ብእር ብቻ ነበረች በእጁ። በትግራይ ዉስጥ ትልቅ ንቅናቄ መፈጠሩን፣ የትግራይ ሕዝብ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር አብሮ ለትግል እጅ ለእጅ መያያዙ አስደነገጣቸው። ሕወሃቶች ሊኖሩ የሚችሉት ህዝቡን ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አማራ እያሉ ሲከፋፍሉት ብቻ ስልሆነ፣ ኢትዮጵያዉያንንን የማሰባሰብ ፖለቲካን ይጸየፉታል። በተለይም በአብርሃ ደስታ ግፊት መቀሌ ሰላማዊ ሰልፍ ሲጠራ፣ ሰልፉ እንዳይደረግ መከልከል ሳይበቃቸው፣ የሰልፍ ጥያቄ እንደገና እንዳይነሳ በሚል ነው መሰለኝ አብርሐ ደስታን ከነሃብታሙ ጋር ወደ ማእከላዊ አስገቡት።

እንግዲህ ከላይ የጠቀስኳቸው በሙሉ የሚያሳዩት ሕወሃት/ኢሕአዴጎች ምን ያህል የተጨበጠ ሥራ የሚሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ማየት እንደማይፈልጉ ነው። እነርሱ የሚፈልጉት ዝም ብሎ መግለጫ የሚያወጡ፣ ዝም ብለው የሚያወሩ፣ ዝም ብለው ስብሰባ ማድረግ የሚቀናቸው፣ ከቢሯቸው የማይወጡ፣ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የማያደርጉ፣ ትግሉን ወደ ሜዳ የማይወስዱ መሪዎችን እና ድርጅቶችን ነው። እንደነዚህ አይነት ድርጅቶች እየጠቀሱ የዉሸት መድበለ ፓርቲ እንዳለ ለማሳየት የሚጠቀሙባቸው ድርጅቶች ናቸው።

አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ «የዲሞክራሲ ስርዓት መገንባት ለኛ አማራጭ ሳይሆን ሕልዉናችን ነው» ሲሉ ብዙ ጊዜ ሰምቻቸዋለሁ። ዶር ቴዎድሮስም አዳኖምም አንድ ወቅት ከጆን ኬሪ ጎን ለጎን ቆመው፣ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዲሞክራሲ እንደሚያብብ ነበር የነገሩን። ነገር ግን እያየን ያለው፣ ከመለስ ዘመን በባሰ ሁኔታ ሕወሃት/ኢሕአዴግ እንዳከረረ ነው። አቶ ኃይለማሪያም፣ መለስን አውት ሻይን ለማድረግ ነው መሰለኝ፣ ብዙዎችን በማሰር፣ በማስገደል፣ ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን በመጨፍለቅ በጣም እየተጉ ናቸው።

አንድ ሕወሃት/ኢሕአዴጎች የዘነጉት ነገር ቢኖር ግን ትግሉ፣ የፖለቲክ ድርጅት መሪዎች ብቻ ሳይሆን የሕዝብ መሆኑን ነው። የሕዝብን ኃይል ደግሞ አፍነው ሊቆዩ አይችሉም። ሕዝብ ምንጊዜም አሸናፊ ነው።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>