Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ጅራፍ ራሷ ገርፋ ራሷ ትጮሃለች (አስገደ ገ/ስላሴ ወ/ሚካኤል)

$
0
0

‹‹ብርሃኑ በርሄ የህወሓት አባል ነው›› 
አስገደ ገ/ስላሴ ወ/ሚካኤል (ከመቀሌ)

 

አስገደ ገ/ስላሴ ወ/ሚካኤል

አስገደ ገ/ስላሴ ወ/ሚካኤል

የአረና ሊቀ መንበርና ሌሎች አመራሮች ባለፈው ሃምሌ 18-20/2006 ዓ.ም በተካሄደው መደበኛ የማ/ኮሚቴ ስብሰባ በጠንካራ አባላቱና አመራሮች በተወሰደው ህገ- ወጥ እርምጃ ጥፋታቸውን ለመሸፈን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መፅሄቶችና ማህበራዊ ድረ-ገፆች የስም ማጥፋት ዘመቻ ተዘምቶብን እንደሰነበተ የሚታወስ ነው። እኛም ግብረ መልስ ስንሰጥ ቆይተናል። አሁን ደግሞ የስም ማጥፋትና ውሸታም ተግባራቸው ቀይረው በሌላ መልክ ወንጀላቸውን ለመሸፈን እየሞከሩ ነው። 

መነሻየ በነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ነሃሴ 2/2006 የአረና ሊቀመንበር ብርሃኑ በርሄ በሰጠው ቃለ ምልልስ እኛን በተመለከተና አጠቃላይ የትግል ሂደቱን መሰረታዊ ስህተት በመሆኑ ዋና ዋና ነጥቦችን በመለየት መልስ ለመስጠት ተገድጄለሁ። 

ብርሃኑ በርሄ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ገዢው ፓርቲ በሰላማዊ መንገድ በምርጫ ውድድር ከስልጣኑ እንዲወርድ ማድረግ አልያም የመንግስት ስልጣን ባንይዝም የህዝብ ጥያቄና አጀንዳ የፖለቲካ ስራችን ማእከል በማድረግ ተገዶም ቢሆን መሻሻል እንዲያደርግ በመታገል ለውጥ እናመጣለን ብለን ነው የምናምነው›› ይላል። ብርሃኑ በርሄ የተወላዋይ ሃይሎች አስተሳሰብ እዚህ ሲጋለጥ፤ እኛ አረናዎች የምንታገለው አምባገነኑ የህወሃት ስርአት እናስወግዳለን ስንል በአይዶሎጂ በሁሉም አንድ አይነት ፖሊሲዎች በሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት አጠባበቅ ባለን መሰረታዊ ልዩነት ህወሓት ኢህአደግን በምርጫ በማስወገድ የስርአት ለውጥ ለማምጣት ነው። ብርሃኑ በርሄ ግን የህወሓት መሪዎች በሚፈልጉት አቅጣጫ እየተራመደ ‹‹እኛ ስህተት ካለን በውስጣችን ሁናችሁ አስተካክሉን ለጠባቦችና ትምክህተኞች አሳልፋችሁ አትስጡን›› የሚሉት አቋም የሚያራምድና ሁለተኛ ልደቱ ሁኖ በስመ ተቃውሞ እየሸወደን ይገኛል። 

ብርሃኑ: ‹‹አፈናው እጅግ መጠናከሩና የፋይናንስ አቅማችን ውስኑነት የሚፈጥሩት ጫና ካልሆነ በስተቀር ከህዝብ ድጋፍና ፖሊሲያችን ከማስተዋወቅ አንፃር በመጪው ምርጫ ሰፊ ሽፋን ሊኖረን ይችላል›› ይላል። ሙሽራ ሳይዙ ሚዜን ይቀጥራሉ እንደሚባለው የብርሃኑ መጪው ምርጫ ለማሸነፍ ወይስ ለመሸፈን? የህወሓት ተግባራት በማጋለጥ የራስህን ሃሳብ በግልፅ ለህዝብ በማሳመንና የህዝብን ማዕበል በመፍጠር ነው ማሸነፍ የሚቻለው። ብርሃኑ በርሄና ጓደኞችህ ግን በዘንድሮ አመት በ8 ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባ ተጠርቶ በ6 ከተሞች ሲከሽፍ በቀሩት ከተሞች ጥቂት ከተሞች ነው ያገኘነው። የተሰራጩ የቅስቀሳ ፅሁፎችም የህዝቡ ችግር ነቅሰው የሚያወጡ ሳይሆኑ ለህወሓት መሪዎች ተገዢነትና የተለሳለሱ እንደውም የሚያሞካሹም ጭምር ነበሩ። በነዚህ እንቅስቃሴዎች ጥቂት አመራሮች እንደ አብርሃ ደስታና እኔ የመሳሰልን በጋዜጣ በፌስቡክ በሬድዮ የምናደርጋቸው ቅስቀሳዎችም በብርሃኑ በርሄና በአቶ ገብሩ አስራት ተቀባይነት አልነበራቸውም። ለዚሁ እንደ ማረጋገጫ ብርሃኑ በርሄ እኔ በነበርኩበት ለ5 ስራ አስፈፃሚ አባላት ሰብስቦ በሚዲያ የምትፅፉትና በሬድዮ የምትናገሩት ለህወሐት መሪዎችና ካድሬዎች የሚያናድድ መሆን የለበትም፡፡: ተናደው በኛ ላይ እርምጃ ሊወስዱብን ነው ብሎ በተለይ በኔና አብርሃ ደስታ በማነጣጠር ነው ሽብር የፈጠረብን። አቶ ገብሩ አስራትም ከ8 ወር በፊት አዲስ አበባ ላይ በተደረገው የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በጥያቄ መልክ ያነሳው ‹‹አብርሃ ደስታና ሌሎች የሚፅፉትና የሚናገሩት ከፖሊሳችንና ከመስመራችን ጋር አብሮ ይሄዳል ወይ እነዚሀ ሰዎች ቢቆጠቡ?›› ብሎ ተናግረዋል። በዛን ወቅት አብርሃ ደስታ ተናዶ ‹‹ይህ አባባል የግለሰቡን ነፃነት ይነጥቃል›› ብሎ መልስ ሰጥቶታል። 

በሌላ በኩልም የፋይናንስ እጥረት ካልወሰነን ብዙ ስራ እንሰራለን የሚለው የነበረው ገንዘብ መቸ አነሰና እድሜ ለደጋፊዎቻችንና‼ ግን ያ ገንዘብ በጥቂት የቡድን አመራሮች በብርሃኑና ሶስት ስላሴዎች ቁልፍ በመሆኑ የፋይናንስ ስርአታችን በጣም የተበላሸ ከመሆኑ በላይ ለሙስና የተጋለጠ ሁኖ ይገኛል። 

አረና በምርጫ ሰፊ ሽፋን እንዲኖረው ከተፈለገ ብርሃኑ በርሄም ሊቀ መንበር ሁኖ ከተደበቀ፤ እነ ገብሩ አስራትም አዲስ አበባ ምሽግ ከሰሩ፤ አባሉና ህዝቡ ማን ያንቀሳቅሰዋል? ብርሃኑ በርሄና የአረና ህዝብ ግኑኝነት ኃላፊ ተብየው አምዶም ገ/ስላሴ’ኮ ሌላው ቀርቶ ሚዲያዎች ስለ አብረሃ ደስታ መረጃ እንድትሰጧቸው ፈልገው በተደጋጋሚ ስትጠየቁ ፍቃደኞች አይደላችሁም፡፡ ለምሳሌ እንደ ማስረጃ ኢሳትን መጥቀስ ይቻላል። በምርጫ ብዙ ቦታዎች መሸፈን ይቻላል የምትለው የትኛው አባል ይዘህ ነው ምትሸፍነው? ከአለቆችህ በተሰጠህ ትእዛዝ’ኮ አባሉን በትነኸዋል። በየትኛው አቋምህ ጠባብ ፀረ-አንድነትና ውህደት የሆነ ጠባብ የህወሓት አስተሳሰብ ወርሰህ ሰፊ የኢትዮጵያን መሬት ምትሸፍነው? አሁንም ዜጎችን ባትሸውዱ‼

ብርሃኑ በርሄ፡ ‹‹በፓርቲው ችግር የለም ነገር ግን የሰዎች አቋም ባህሪም ጭምር በእንቅስቃሴው ፈተና ውስጥ ስለሚገቡ አንዱ ጠንከሮ ሲወጣ ሌላው አዳናቃፊ የሚሆንበት አጋጣሚ ይስተዋላል፤ እንቅስቃሴው ሲበረታና እንቅስቃሴውን ለማኮላሸት የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ሲበዙና ሲከብዱ ተስፋ መቁረጥም የሚጠበቅ ነው፤ ሌላው ደግሞ እንቅስቃሴው የሚወልዳቸው ፈተናዎች ከብደውት ወይ ብዥታ አድሮበት የመቀዛቀዝና ግራ የመጋባት ባህሪ ይስተዋላል›› ይላል። 


በአረና ውስጥ ዋናው ችግር ፈጣሪዎች አንተና አለቆችህ ናችሁ፤ በ2002 እኮ አንተና እነ ገብሩ አስራት እንቅስቃሴያችን ከመቀሌና አከባቢዋ መራቅ የለብንም፤ ለሪስክ (አደጋ) እንጋለጣለን አላችሁን፤ እኛ ገፍተን እኮ ነው ትግራይን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተንቀሳቅሰን 138 ጠንካራ አባላት ለውድድር ያቀረብነው፤ እነ አረጋዊ ገ/ዮሃንስ’ኮ እንደ ሰንጋ በሬ የታረደው በበረሃ ሲቀሰቅስ ነው፤ ትግሉ የከበደህ’ኮ አንተ ነህ፤ ከባድ ነው በምትለው አከባቢ’ኮ ተደብቀሃል፤ ሌላው እንተወውና ዘንድሮ በተደረገ እልህ አስጨራሽ ህዝባዊ ስብሰባዎች’ኮ በብዙ ቦታዎች ተደብቀሃል፤ የአኒማል ፋርም የአመራር ስልትህ በመከተል ችግር እየፈጠርክ ያለኸው’ኮ አንተ ነህ፤ ታድያ በየትኛው ሞራልህና ብቃትህ ነው አንተ “ተስፋ ቆርጠው የሚሸሹ አሉ” ማለት የምትችለው? ቁጥር አንድ ተስፋ አስቆራጭ አንተ መሆንህ እነዚህ በየግዜው ከፓርቲው የለቀቁ በሺ የሚቆጠሩና አሁን በፓርቲው ውስጥ ያሉም እየገለፁት የሚገኝ። ብርሃኑ ማን መሆንህ የትግራይ ህዝብ በተለይ የመቀሌ ህዝብ ያውቅሃል፤ የአድዋ፣ የአላማጣ፣ የአዲጉዶም፣ የውቅሮ፣ የማይጨውና ሌሎች አከባቢዎች’ኮ አቋምህ ከህወሓት ምንም ልዩነት እንደሌለህ ነግሮሃል።

ብርሃኑ በርሄ፡ ‹‹የአረና ከፍተኛ አመራር እነ አስራት አብርሃም ቡድናዊነት አለ ብለው ከፓርቲው መሸሻቸው በኔ እምነት ሃላፊነትን አለመወጣት ነው›› ይላል። እነ አስራት አብርሃም በፓርቲው ውስጥ የነበሩ ችግሮች አለመታገላቸው ከብርሃኑ እስማማለሁ። ነገር ግን ያሁኑ ወጣቶች ከዚያ ያረጀና ያፋጀ ፀረ-ዲሞክራሲ ትውልድ በቋንቋም በባህልና አስተሳሰብ አይግባቡም። እነ አስራት ብዙ ታግለዋል፤ በውስጣችን የነበሩ ችግሮችም ለመታገል ሞክረዋል፤ አንተ ስብሰባ ረግጠህ እስከምትወጣ፤ ምክንያት እየፈጠርክ ከስብሰባ ወጥተህ በግል ስራህ ትውል እንደነበርክ እናቃለን፤ ባንተና በ3ት ስላሴዎች ባህሪ ምክንያት እስካሁን እነ አስራትን ጨምሮ 18 ማ/ኮሚቴ፣ ስራ አስፈፃሚና ቁጥጥር ኮሚሽን ከፓርቲው አግልለዋል፤ ችግሩም አሳታፊነት የለም፣ አባታዊነት ነግሰዋል፣ የፋይናንስ ስርአታችን ግልፅነት የለም ወዘተ.በማለት ነው። እንድያው አንዳንዶቹ “የአረና አመራር በስም ካልሆነ ከህወሓት በምንም አይለይም” ብለው ላንተ የነገሩህ የአረና መስራች አባላት የነበሩ እጅግ ብዙ ናቸው። 

እነ አስራት አብርሃም በነበሩበት እኮ ቡድናዊነት እጅጉን የጠነከረ ነበር፤ ያ ቡድናዊነት በስራ አስፈፃሚ ውስጥ ከላይ እንደገለፅኩት አራታችሁ በድብቅ የጨረሳችሁት ጉዳይ ወደ ስራ አስፈፃሚና ማ/ኮሚቴ የሚቀርበው ለይስሙላ ነበር፤ ማ/ኮሚቴ ለስሙ የተቀመጠ እንጂ አምስት አመት ሙሉ የሰራውና የሚያውቀው አልነበረም፤ ያ ቡድናዊነት አሁንም ተባብሰዋል።
ብርሃኑ በርሄ፡- ‹‹እነ አስራት በለቀቁት ማግስት በተካሄደው 3ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ቡድናዊነት እንዳለ አስመስለው ሲናገሩ የነበሩ ግለሰዎችም አላሳመኑም ብቻ ሳይሆን ለስሙም አላነሱም፤ ስለዚህ እነ አስራትም ሆነ አስገደ የሚያማርሩት ቡድናዊነት አረና ውስጥ አልነበረም›› ይላል፡፡ ሀሰት ተደጋግሞ ሲነገር ሃቅ ይሆናል የሚል የነ ሂትለር፣ መንግስቱና ህወሓት ብሂል ይዘህ የትም አትደርስም። ከ3ኛ ጉባኤ በፊት በ3ት የስራ አስፈፃሚና በ2ት ማ/ኮሚቴ መደበኛ አመታዊ ስብሰባ ተነስተዋል፤ የፋይናንስ ስርአታችን በም/ሊቀመንበርና በ3ት ስላሴዎች በሚስጥርና በቡድናዊነት መሆን የለበትም፤ ወደ ስብሰባ የሚቀርብ አጀንዳ በህገ ደንብ መሰረት ሳይሆን በጥቂት ስራ አስፈፃሚ በቡድናዊነት መሆን የለበትም፤ የዲፕሎማሲ ስራዎች ለወጣት አመራሮች እድሉን አለመስጠት ወዘተ የሚሉ ወሳኝ ጥያቄዎች ተነስተዋል። የዚህ ቡድናዊነት እንደ ማስረጃ ደግሞ በ3ኛ ጉባኤ ታይቷል፤ የጉባኤው ተሳታፊዎች አባላት መሆናቸውና አለመሆናቸው ማይታወቁ፤ በጉባኤው ጠንካራ ነባር አባላት ወደ አመራር እንዳይመጡ አስቀድሞ በህዝብ ግኑኝነትና የድርጅት ጉዳይ ሃላፊዎች የማያውቁት ባወቁ ጊዜም የተቃወሙት አቶ ብርሃኑና 3ት ስላሴዎች ያወጡት ካሪክለም የውሸት ስልጠና የሰጥቷቸው ለጉባኤ የቀረቡ መሆናቸው ሁሉም አባል ያውቃል። ሌላው ቀርቶ በጉባኤ ብርሃኑና 3ት ስላሴዎች በየ6ት ሰአት በድብቅ እየተሰበሰቡ ይወስኑት እንደነበር ፤ከዚያም አልፈው የፕሮዚዴሙ ለቀመንበር አብርሃ ደስታም ወደ ቡድኑ በማስገባት በማስፈራራት ጉባኤው በድፈን ድፈን እንዲታለፍ ተደርጓል። በተለይ ደግሞ በውህደት ጉዳይ፣በፌደራሊዝም፣ በመሬት ጉዳይ፣ ህገ-ደንብን ማሻሻል በተመለከተ ጊዜ ስሌለለን የሚመረጠው ማ/ኮሚቴ አይቶ እንዲወስን አድርግ ብለው ጉባኤተኛ እንዲታፈን እንዳደረጉ አብርሃ ደስታና ስልጣኑ ሕሸ የሚመሰክሩት ነው። በተለይ ገብሩ አስራትና አረጋሽ አዳነ የፕሮዚዴም አባላት ስለነበሩ አብርሃ ደስታን ያስፈራሩት ነበር። ብርሃኑ በርሄ በአረና ቡድናዊነት አልነበረም፣ አሁን ደግሞ ቡድናዊነት የሚል ሃሜት ወደ አባታዊነት ተሸጋገረ። 

በአረና አባታዊነትና አምባገነንነትን በሚመለከት በየካቲት 2005 መደበኛ ማ/ኮሚቴ ስብሰባ እኔ አንስቼው ተሰብሳቢው ጠንከር ብሎ ለብርሃኑ በርሄ ሂስ በመሰነዘሩ ብርሃኑ አባታዊ በሆነ ትእቢት በተሞላበት በንቀት መድረክ ረግጦ ወጥቶ በኋላ ተለምኖ ነበር የተመለሰው። ሌላ የአባታዊነት መገለጫ በአረና ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ የፋይናንስ አቅማችንና አሰራራችን ለሁሉም ስራ አስፈጻሚ ግልፅ ይሁን የሚል ጥያቄ ቀርቦ በአቶ አውዓሎም ወልዱ የፋይናንስ አቅማችን ሁሉ የስራ አስፈጻሚ አባል ሊያውቀው ግዴታ አይደለም የሚል ሃሳብ ሲሰነዝር ገብሩ አስራት ተቀብሎት አረጋሽም ጨምራበት በዛው አለፈ፤ ታዲያ ከዚህ በላይ አባታዊነት ምን አለ? ከፓርቲዎች የሚደረገው ግንኙነት በቡድንነት እንደሆነ ሲነገራቸው ያኮርፋሉ፤ ሁሉም ነገር እኛ እንጨርሰው በማለት አያሳትፉም ሌላ አባል ከሰራ እንደሚያበላሽ አድርገው ነው የሚያዩት፤ ሌላው ቀርቶ ግለ ሰዎች ገዢው ፓርቲን በማጋለጥ በሚዲያ የምንሰነዝረው ሃሳብ መጀመርያ ኢዲት እናድርገው ብለውናል ተቀባይነት ባያገኙም፤ ታዲያ የግለሰብ መብት መጣስ የለበትም የሚለው የአረና እምነት አይፃረርም?

በሌላ በኩል ወደ ውጭ የዲፕሎማሲያዊ ስራ ከወጣቶች እንላክ ስንል በነዚህ 4ቱ ሰዎች ተቀባይነት አላገኘም፤ ወጣቱ ምንም አይሰራም ያበላሻል’ጂ የሚል አመለካከት ነበር፤ በሃገር ውስጥም ስለ ውህደት የት ደረሰ ተብለው ሲጠየቁ ለሁሉም ነገር በሚስጥር ይዘውት ነበር፤ በመጨረሻ ከአንድነትና ሌሎች የአማራ ፓርቲዎች አንዋሃድም ሊውጡን ነው ብለውናል፤ እንደውም በዚህ በሃምሌ 19ና 20/2006 የማ/ኮሚቴ ስብሰባ በ3ት አቅጣጫ ጦርነት ተከፍቶብናል፤ 

1. በህወሓት 2. በበተቃዋሚ ፓርቲዎች 3. በውስጣችን ባሉ በጥባጮች በማለት እኛን ካባረሩ በኋላ ያወጡት መግለጫ ያሳያል። ይህንን ደግሞ ለምን ተነካን ብለው ያላቸው አባታዊነት አሳይተዋል። 

ብርሃኑ በርሄ ‹‹በአረና የመብት ጥያቄ አንስቶ የታፈነ አንድም የለም፤ ታፍነናል በማለት ለሃገር ውስጥና ለውጭ ሚዲያዎች ብቻ ሳይሆን ለማይመለከታቸው ፓርቲዎች ሳይቀር የዚህ አመት አስገራሚ ሊባል የሚችል ምርጥ ውሸት በመደርደር የፓርቲያችንና አመራሩ መልካም ስም ለማጥፋት የዘመቱ›› ይላል፡፡ ደግ ብርሃኑ ለማያውቀው ሰው ሲናገር ሃቅ መስሎ ሊሰማው ይችላል። ሃቁን ለመናገር ግን ካሁን በፊት ለመግለፅ እንደሞከርኩት በአረና ትግራይ ዲሞክራሲያውነት መስፈርት ብለን የምናምንበት ከግለሰው መብት እስከ ቡድንና የህዝቦች መብት መከበር ነው፤ በብርሃኑና ጓደኞቹ አመለካከት ግን የግለሰው መብት አያከብሩም ብቻ ሳይሆን በግልም ሆነ በቡድን ማንኛውም አይነት ጥያቄ ማስነሳት ወንጀል ነው፤ ለዚሁ ምስክር በተለያዩ ጊዝያት ጥያቄ በማንሳታቸው በመታፈኑ ከፓርቲው ራሳቸው ያገለሉ ግን ደግሞ በህወሓትነት የተፈረጁ ግን እስካሁን ከህወሓት ምንም ግንኙነት የሌላቸው አሉ፡፡

አሁን የተባረርን አባላትና አመራርም በፓርቲው ያሉ ነባራዊ ችግሮች ለማስተካከል ብለን በመድረክ፣ በፅሁፍ፣ በክስ መልክ ደረጃውን ጠብቆ ህገ ደንብን መሰረት በማድረግ ለ9 ወራት ጠይቀናል። ሌሎች በራሳቸው ይገልፁት ይሆናል። እኔ የሄድኩበት መንገድ ልግለፅ ፤ከ2003 እስከ 2005 በማ/ኮሚቴና ስራ አስፈፃሚ በፓርቲያችን መጥፎ ሁኔታ እንዳለ አንድ በአንድ ዘርዝሬ አቅርቤ ነበር። በተለይ ደግሞ በ2005 በአረና ውስጥ ስል አንድነትና ውህደት የላላ አቋም እንዳለ፤ አባታዊነትና አምባገነንነት ባህርያት እንዳለ፤ ከማ/ኮሚቴ እስከ ታች የተዘረጋ ቡድናዊነት ወዘተ. እንዳለ በአጠቃላይ ከላይ የገለፅኳቸው የፓርቲው ችግር እንዲስተካከሉ አንስቼ ነበር፤ በ3ኛ ጉባኤም በመድረክ አንስቼዋለሁ፤ ከጉባኤ በኋላም ከጥቅምት ወር 2006 ጀምሮ በማ/ኮሚቴ በተለይ በሊቀመንበሩ ስለ ሃገራዊ አንድነትና ውህደት የሚታዩ ችግሮች፤ ቡድናዊነት በማስፋፋት አባላቱ እንዲፈርሱ ሚደረገው መጥፎ ስራ፤ ከህወሓት ካድሬዎችና አመራሮች የጠበቀ ግንኙነት መኖር እስከ በህብረት ሲሚንቶ መንገድ ወዘተ. ብየ አጀንዳ በመያዝ መቀሌ ካሉ 5 ስራ አስፈፃሚዎች እንዲያወያዩን ጠይቄ ብርሃኑ አፍኖ ለ2 ወር ቆየ፤ እኔም ተስፋ ሳልቆርጥ ብርሃኑ ግብረገብነት የጎደለውና ህገ-ደንብን በመጣስ ህገ ወጥ ስራ እየሰራ ነው ይታይልኝ በማለት ለጠቅላላ ማ/ኮሚቴ አመለከትኩ፡፡ ለ32 ቀናት ታፈነ፡፡ ቀጥሎ 13 አጀንዳዎች የያዘ አቀረብኩ፡፡ አልተቀበሉትም፡፡ ቀጥሎ ሊቀመንበሩ ማኸል ያደረገ 4 ጊዜ ለቁ/ኮሚሽን ክስ አቀረብኩ፡፡ ቁጥጥር ኮሚሽንም ለ2 ወራት ዘጋው፡፡ በቃ አፈናው በረታ፡፡ መጨረሻ አስቸኳይ ጉባኤ ጠርቼ አሁንም ተዘጋሁ፡፡ መጨረሻ በአረና ስራ አስፈፃሚ የታፈነው ጥያቄ 15 ነጥቦች የያዘ 5 ገፅ ሰነድ ለአረና አባላትና ደጋፊዎች ብቻ አሰራጨሁ፡፡ ሁሉም በፅሁፍ ያቀረብኳቸው ጥያቄዎች የአረና ፅ/ቤት ፈርሞ ተቀብሎታል፡፡ በመዝገብ ቤቱ ይገኛል።
ለ9 ወራት ያመለከትኩት ጥያቄዎች ከአረና አመራር ውስጥ በግልም ይሁን በቡድን ያነጋገረኝ ሰው የለም፡፡ አንፃሩ ብርሃኑ በርሄና ጥቂት አጃቢዎቹ በጥላቻ አይን እያዩ በሃሜት ስሜን እያጠፉ ቆይተዋል። በእኔ እምነት አንድ ዲሞክራሲያዊ መሪ ይቅርና ከአባላቱ ለሚነሱ ጥያቄዎች ከማንም ሰው ለሚነሳ ጥያቄ በማዳመጥ መፍትሄ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ከዚያ አልፎ በቅርብ ርቀትና በርቀት እየተከታተለ ምን አይነት ሁኔታ እንዳለ በመከታተልና ኢንፎርሜሽን በማሰባሰብ ጥያቄዎቹ እሱ ላይ ከመድረሳቸው በፊት መፍትሄ ማስቀመጥ ይገባ ነበር፡፡ ብርሃኑ በርሄ፣ 3ቱ ጓደኞቹና አጃቢዎቹ ግን ለዚህ አይነት መልካም አመራር አልታደሉም፡፡ ይኸ ደግሞ ሆን ተብሎ አረናን ለማዳከምና እነሱን የሚፈታተን መሪ እንዳይወጣ አባላቱን በማመናመን እነሱ ደግሞ በዚህ ምሽግ እድሜ ልካቸው እንዲኖሩበት እኩይ ተግባር ነው። 

የተከበራችሁ ወገኖች የአረና ማ/ኮሚቴ ለ9 ወራት ሙሉ ሲያፍነኝ እኔ ግን ምንም ቂም ሳልይዝ አንድ ቀን ይፈታል ብየ ተስፋ በማድረግ ለአፋኙና አምባገነኑ የህወሓት ኢህአደግ ስርአት ለማጋለጥ ከአረና ማ/ኮሚቴ ሆነ ስ/አስፈፃሚ በላይ ግምባር ቀደም በመሆን በህወሓት ባንዳዎች እየተደበደብኩ በጎዳና ደሜን እየነዘረ እየታሰርኩ እልህ አስጨራሽ ትግል ሳደርግ ቆይቻለሁ፡፡ እነ ብርሃኑና አጃቢዎቹ ለመናገር የሚፈሩት እኔ፣ አብርሃ ደስታና መ/ር ታደሰ ቢተውልኝ ነበር፡፡ ህዝቡን ማሳመን የቻልነው ህዝቡም የነ ብርሃኑ ተወላዋይነትና የኛ ጥንካሬ ነግሮናል፡፡ በሌላ በኩል በሃገር ውስጥና በውጭ ሚዲያዎች አምባገነኑ ስርአት ስናጋልጥ ብርሃኑ በርሄ ሚዲያዎች መረጃ ፈልገው እንደ ሊቀመንበር ሲጠየቅ እምቢተኝነቱን ነው ያሳየው፡፡ አስፈላጊ ከሆነ ወደፊት እገልፀዋለሁ፡፡ ብርሃኑ በርሄ ግን አፉን ሞልቶ በአረና አፈና የለም ማለቱ ምን ያህል ሞራል አልባ መሆኑ ያሳያል። ብርሃኑ በርሄ እስካሁን ከአባይ ወልዱ የማይተናነስ አረናን እያፈነ ይገኛል፡፡ ጭራሹም ወደ ህወሓት ለመቀላቀል በበር መዝግያ ከፍቶ ለመግባት በፍጥነት የሚያጋልጠው ስለሆነ በምርጫ አማካኝነት በጓዳ በመግባት በፓርላማ የህወሓት አፈና ሟሟያ እንዲሆን አዘጋጅቶ የተቀመጠ ነው የሚመስለው።
ይህ ካልኩ በኋላ እኔና ሌሎች ጥያቄ ያነሱ ወገኖች ባለፈው ሀምሌ 19ና 20/2006 ዓ.ም የማ/ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ጥያቄያችን መልስ ያገኛል ብለን ነበር፡፡ በተለይ አቶ ገብሩ አስራት ከአሜሪካ በሮ መምጣቱ ችግሩ በሰላማዊና በበሰለ መንገድ ይፈተዋል ብለን ነበር፡፡ ውጤቱ ግን የባሰ አፍራሽና የገብሩ ማንነት በማያጠራጥር ያጋለጠው ሁኖ ነው የተገኘው፡፡ እንደውም አቶ ገብሩና ጓዶቹ በጓሮ ወደ ህወሓት ለመግባት ፈልገው ይሆናል? የሚል ሃሜት እየተናፈሰ ሰንብተዋል፡፡ ምክንያቱም ጠንካራ አባላት ማባረር ለህወሓት እንደ መጠናከር ለአረና እንደመፍረስ ማለት ነው የሚሉ ወገኖች ብዙ ናቸው። 

ብርሃኑ በርሄ፡- ‹‹በፓርቲ የምንወስደው ቅጣት ደረጃ በደረጃ ነው›› ይላል፡፡ በኔ ላይ የተወሰደ እርምጃ 1ኛ የከሰሰኝ ማነው? 2ኛ ያ ቁጥጥር ኮሚሽንስ አይቶታል ወይ? 3ኛ ያጠፋሁት ጥፋትስ አይነገረኝምን? 4ኛ የተጣለብኝ ውሳኔስ በወሰነልኝ ኣካል በስርአት በደብዳቤ ሊሰጠኝ አይገባምን?
ብርሃኑ በርሄ፡- ‹‹አስገደ 2005 ከባድ የስነ ምግባር ጉድለት በማሳየቱ በቁጥጥር ኮሚሽን ማስጠንቀቅያ ተሰጥቶት ነበር፤ አሁንም ሊያሻሻል ስላልቻለ ተባረዋል›› ይላል፡፡ ለመሆኑ የተፈፀመው የስነ ምግባር ጉድለት ምንድ ነው? የተሰጠኝ ማስጠንቀቅያስ ለማ/ኮሚቴ ወይ በጠቅላላ 3ኛ ጉባኤ መገለፅ አልነበረበትምን? ለመሆኑ ቁጥጥር ኮሚሽን ለአንድ ስራ አስፈፃሚ ማስጠንቀቅያ የመስጠት ወይ የመቅጣት ስልጣንስ አለዉን? ለመሆኑ አሁን ያባረሩኝ የመቀሌ ዞን መሰረታዊ ድርጅት የሚባሉ አዛውንትስ እነማን ናቸው? ማነው ጠፍጥፎ ያቋቋማቸው? መቀሌ’ኮ አባል የሚባል የለም፡፡ ስለዚህ የብርሃኑ ማጭበርበር ካልሆነ በስተቀር እኔ በአረና በነበርኩበት 6 አመታት በሁሉም ዞኖች ያሉ አባሎቻችን አንድም ቀን ሂስ አድርጎልኝ አያውቅም። በአንፃሩ ብርሃኑ ያባረራቸውና ያበሳጫቸው አባሎቻችን ለማግባባትና ለማበረታታት ተጠምጄ ነው የኖርኩት፡፡›› በነገራችን ላይ የአረና ስራ አስፈፃሚ እንዳባረረኝ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ተናግረዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይግባኝ ማለት ይችላል ብለዋል፤ በአንድ መሰረታዊ ድርጅት የተወሰነ ስህተት በስራ አስፈፃሚና ማ/ኮሚቴ ሊቀየር ይችላል፡፡ ነገር ግን ይግባኝ ከማለቴ በፊት ያየመጨረሻ ብይን ይሰጣል የሚባል የፓርቲው አካል በራሱ አባርሮኛል፡፡ በመሰረታዊ ድርጅት ይሁን በስራ አስፈፃሚ የተወሰነው የውሳኔ ደብዳቤ 4 ጊዜ ብለምናቸውም ሊሰጡኝ አልቻሉም፡፡ በአንዳንድ የፓርቲው ማ/ኮሚቴ አባላት ለምሳሌ እንደ ሃፍታይ ወልደሩፋኤል እንዲያሰጡኝ ብለምናቸውም ሊሰጡኝ አልቻሉም፡፡ ታዲያ በየትኛው የስንብት ደብዳቤ ለየትኛው አካል ነው ይግባኝ የምለው? የብርሃኑ የውሸት ሰደድ አድርጌ ነው የምመለከተው።
ብርሃኑ በርሄ: ‹‹በአረና የውስጥ ችግር የለም፡፡ ፓርቲው በፕሮግራም በእስትራተጂ አልተለያየም፡፡ እንደ አንድ አካል ሁነን ተስማምተን እንሰራለን፡፡ በአንድ ሁነን ሁሉም የፓርቲ እቅዶችን እያወጣን እንሰራለን፡፡ አንድ ሁለት ሰዎች ከራሳቸው ምክንያት ተነሳስተው ስማችን እያጠፉን ያሉት ውሸት ነው›› ይላል፡፡ በአረና እስካሁን የተደረጉ ስብሰባዎች፣ የአባላት ስልጠና ተብየዎች፣ የማ/ኮሚቴ ስብሰባዎች፤ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባዎችና ጉባኤዎች በህገ ደንቡ መሰረት የሚመለከታቸው አካለት አጀንዳ ይዘው ተወያይቶበትና ተግባብተው ሳይሆን ብርሃኑና 3ት ስላሴዎች በፈለጉትና ባቀዱት ብቻ እየተካሄዱ ቆይተዋል። ህገ ደንቡ ግን የማ/ኮሚቴ ስብሰባ ሲደረግ ስራ አስፈፃሚ አጀንዳ አዘጋጅቶ ከስብሰባ በፊት ለኩሉም ማ/ኮሚቴ ከ7 ቀናት በፊት ያሰራጫል።

እስካሁን ሲሰራ የነበረ ግን የሚቀርቡ አጀንዳዎች በብጣሽ ወረቀት በሊቀመናብርቱ ይቀርባል፡፡ ይህ ተግባር በ2004፣ በ2005 በ3ኛ ጉባኤ ህገ-ደንብ ተጥሰዋል እየተባለ በተደጋጋሚ ሲነሳ ንሯል፡፡ አቶ ገብሩ አስራት ግን በጣም ያበሳጨው ነበር፡፡ በአረና ትግራይ እስካሁን ድርጅታዊ አሰራር ተግባራዊ ተደርጎ አያውቅም፡፡ ኮሚቴአዊ አሰራር የሚያስፈልገው በኮሚቴ ተወስኖ አያውቅም፡፡ አሁንማ እቺ ፓርቲ የብርሃኑ በርሄ፣ 3ት ስላሴዎችና ጥቂት ባንዳዎች የግል ድርጅት ነው ቢባል ይቀላል። ሌላ ውህደትን በተመለከተ የህወሓት ሌጋሲ በመከተል አረና ክልላዊ ፓርቲ መሆኑ ቀርቶ ራሱ ሃገራዊ አውራ ፓርቲ ሊሆን ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ደግሞ የትምክህተኛ አማራ ፓርቲዎች መሰባሰብ ሊውጠን ነው የሚል ጠባብ አስተሳሰብ ራሱ ትልቅ የስተራተጂና የፕሮግራም ልዩነት ነው። በነገራችን ላይ አረና በቃል ካልሆነ በስተቀር የቅርብና የሩቅ እስትራተጂ በሰነድ የተነደፈ የለም። ሌላ በውስጥ መከፋፈል የለም የሚለው እነ ሰለሞን ገ/አረጋዊ፣ ብርሃኑ መለሰ (ብርሃኑ ሞርታር)፣ አስራት አብርሃም፣ ጉዕሽ ገ/ፃዲቅ፣ ስልጣኑ ሕሸ፣ ይልማ ይኩኖ ወዘተ. ፓርቲው ውስጥ ባለው ችግር አይደለምን የወጡት? አሁን ደግሞ ታደሰ ቢተውልኝ፣ ገብሩ ሳሙኤል፣ ሽሻይ አዘናውና እኔ ራሴ ያነሳነው መሰረታዊ ጥያቄዎች ማለት የህገ-ደንብ አለማክበር፣ የተጠያቂነትና ኮሚቴአዊ አሰራር ግድፈት ስንቃወም አንድነትን ያመላክታል። አረና ትግራይ በመጋቢት 20/2000 የትግላችን የሩቅ አላማ በሃገራችን ከሚገኙ ማናቸውም ሃገራዊና ክልላዊ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ከቅንጅት እስከ ውህደት በመጓዝ አንድነቷና ሉአላዊነቷ የተረጋገጠ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮፕያን ለመመስረት ነው ብለን በሃሳብ ከተስማማን በኋላ በዛ መሰረት ተጉዘን እስከ ግንባር ተጉዘናል፡፡

ውህደትን በተመለከተ ግን ያ ሃገርን ያበላሸ የህወሓት ጠባብ አስተሳሰብ አገረሸባቸውና ብርሃኑ በርሄና 3ት ስላሴዎች የአንድነትና መኢአድ መሰባሰብ አማራን አጠናክረው የበላይነታቸው ለማረጋገጥ ስለሆነ ከአንድነትና ሌሎች የትምክህት ሃይሎች አናብርም ብለው የህወሓት የ1968 አቋም ይዘው ቁጭ ማለታቸው የእስትራተጂ ስህተት ከመሆኑ አልፎ ሃገርን የማስገንጠል አቅጣጫ የሚከተሉ ይመስላሉ። የአንድ ብሄር ፓርቲ የኢትዮጵያ አውራ ፓርቲ እንሆናለን ካላችሁ ከህወሓት በምን ትለያላችሁ? ለምን ፊትለፊት የህወሓት በር ከፍታችሁ ህወሓትን አትቀላቀሉም? ለምን በስመ ተቃውሞ በጓዳ መግባት አስፈለገ? ስለሆነ አሁንም ብርሃኑ በርሄ አታጭበርብር! ጠበቃ ስለሆንክ አልሸነፍም ብለህ እየተሟገትክ ከሆነም አሁን አይደለህም የተሸነፍከው ከተሸነፍክና ከተነቃብህ ቆይቷል። 

ፕሮግራማችን የግለሰው መብት የሚያስቀድም ነው፡፡ በነብርሃኑ ግን ጥያቄ ላነሳ ግለሰብ ይቅር በማ/ኮሚቴ በቡድንና በተናጠል የሚቀርቡ ጥያቄዎች ተቀባይነት የላቸውም፡፡ በአንፃሩ የአረና ፈላጭ ቆራጭነት የነገሰበት ሁኔታ ነው ያለው፤ ግለሰዎች ነፃ ሁነው ሃሳባቸውን መግለፅ አልቻሉም። 

ብርሃኑ በርሄ ‹‹የነዚህ ሰዎች አቀራረብ እነሱ ራሳቸው ለነበራቸው ሃላፊነት የሚያበቃ እውቀትም ሆነ ስነ ምግባር እንደሌላቸው ለአንባቢ ያስረገጡበት ሁኖ ነው የተሰማኝ›› ይላል። የአንድ ሰው እውቀት መመዘኛ የህወሓት ጠባብ አስተሳሰብ በማራመድ ሃገርን ለመገነጣጠል ማቀድ፣ ከህገ-ደንብ በላይ ሁነህ መገኘት፣ አባላትን በማባረር፣ ስርአትና ግብረገብ አልቦ ወዘተ. ከሆነ ብርሃኑ እውነት አዋቂ ነህ፡፡ አለበለዚያ የአንድ መሪ እውቀት ዲሞክራሲያውነት፣ ተጠያቂነት፣ ግልፅነት፣ የሰዎችን ሃሳብ ማዳመጥና በብቃት መመለስ፣ በሀገ-ደንብ መገዛት፣ መሪዎችን በማፍራት የድርጅቱን ራኢይ ብሩህ የሚያደርግ በአጠቃላይ ለህዝብና ሃገር ጥቅም መቆምና መስዋእት መሆን ከሆነ ብርሃኑ መሃይም ነው ማለት ይቀላል። እኛ’ኮ ህገ ደንባችን ይከበር፣ ለህዝብና ሀገር ጥቅምና ክብር መስዋእት እንሁን፣ ከጠባብ አስተሳሰብ ወጥተን ለተዋሃደች ኢትዮጵያ እንቁም፣ ለሆዳችን መገዛት ትተን የገባነው ቃል እንፈፅም፡፡ በአጠቃላይ ህገ ደንባችን ፕሮግራማችንና አላማችን ተንዷል ነው እያልን ያለነው። ይኸ አለማወቅና ሃላፊነትን አለመወጣት ከሆነ አንባቢ ይፍረደን፡፡ ብርሃኑ ግን ካሁን በፊትም አህያ ግብሯን አይቶ ቀንድ ከለከላት ብሎ በኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ከአህያ ጋር አመሳስሎናል፡፡ የአህያ አስተሳሰብ የታደለ ማን እንደሆነ ፍርዱ ለአንባቢ ትቼዋለሁ። 

ብርሃኑ በርሄ፡- ‹‹ … ሽሬን በጎጠኝነት ካነሱ ሽሬ የብቻቸው እንዳልሆነች መከራከሩ ብዙ ባያስፈልግም የሽሬ አረና አባላት እነዚህ አሁን በጎጠኝነት ተባረርን አሉ ያልከኝ ወደ ሽሬ እንዳትልኩልን እንዳሉ በማ/ኮሚቴው ስብሰባ ከፈጠሩት ችግር ተያይዞ ተነግሮአቸዋል….. አቶ አስገደ የጎጥ ፕሮጀክት ሽሬን ተንተርሶ በጎጥ መክሰስ መጀመራቸው የህወሓትን አርማ ደግመው ማንሳታቸው ካልሆነ አንዳች እውነታም ሆነ ምክንያት የለውም›› ይላል። መጀመርያ ከላይ የዋሸኸው በሽሬ ያሉ አባላት እነዚህ ሰዎች እንዳትልኩልን ብለውናል የምትለው በነሱ ፊት አትደግመውም፡፡ እጅጉን ሰነፍና ውሸታም ተከራካሪ ስለሆንክ፡፡ ሁለተኛ እኔ አስገደ በጎጠኝነት አልታማም፡፡ አረና ከተመሰረተ በሁሉም የትግራይ ዞኖችና ወረዳዎች እስከ ቀበሌ ድረስ ተንቀሳቅሼ ለዚህ ፓርቲ ብዙ አባልና ደጋፊ አፍርቼአለሁ፡፡ በትግራይ ያለው ሙሁሩ፣ ገበሬው፣ ነጋዴው ወዘተ. ያውቀኛል፡፡ አንተ ደግሞ በአንፃሩ መለያህ ጎጠኛነትህ ነው፡፡ እጅጉን የወረድክና ውሸታም መሆንህ ደግሞ ሽሻይ አዘናው የእህቱ ልጅ ማለትህ ሀቀኛ እንቅስቃሴ ወደ ዘረኝነት አቅጣጫ ለማስቀየር መሞከርህ ነው፡፡ የራያ ትውልድ መኖሬንም ብታውቅ ኑሮ ገብሩ ራያንም የወንድሙ ልጅ ትለው ነበር፡፡ ይህ ተግባርህ ደግሞ የጌታህ ህወሓት ጠባብ አስተሳሰብና የጎጥ አርማ እያነሳህ ያለኸው አንተ ራስህ ነህ፤ በተግባርም ለአረና ጎድትሃታል፡፡ ባዶዋን አስቀርሃታል፡፡ ከህወሓት እጅና ጓንት ሁነህ እየሰራህ ያለኸው አንተ ነህ፡፡ እስኪ አንድ ነገር ልጠይቅህ፡፡ እንኳን የአረና አባል ደጋፊ ነው ተብሎ የተጠረጠረ እንኳን መሳርያው እየተነጠቀ ባለበት ሁኔታ አንተ በምን መስፈርት ነው በምልሻነት ነፍጥ የታጠቅከው? እኔና ሌሎች ንፁሃን አባላትማ እንኳን መሳርያ ሊፈቀድልን ልጆቻችንና ዘርመንዘራችን የ3ኛ ዜጋ መብትም የለንም። 

ብርሃኑ በርሄ፡- ‹‹አብርሃ ደስታ የአረና የህዝብ ግንኙነት ኮሚቴ አባል ስለነበረ ሃላፊነቱ በአግባቡ ተወጥተዋል ብቻ ሳይሆን ብቁ የፖለቲካ መሪ ሁኖ ሊወጣ ተስፋ የሚጣልበት መሆኑ ደጋግሜ ስለው የነበረ ነው›› ይላል። አብርሃ ደስታ ወደ አረና ከመቀላቀሉ በፊት 2 አመት አስቀድሞ ከኔ ጋር ነበር የተገናኘው፡፡ ከአብርሃ ደስታ በሳምንት ቢያንስ 2 ጊዜ እንገናኝ ነበር፡፡ በኋላ ግን በየቀኑ እስከ ሁለት ጊዜ እንገናኝ ነበር ስለ አብርሃ ደስታ ብዙ ጊዜ እነግርህ ነበር፡፡ ደስ ግን አይልህም ነበር፡፡ አባል ይሁን ፎርም ይሙላ ስልህ ይቆይ እናጥናው ነው ያልከኝ፡፡ ሰውየው በማህበራዊ ድረ-ገፅ እየታወቀ ሲመጣ አንተ ደስ አይልህም ነበር፡፡ ነገር ግን በኔ ተፅእኖ ወደ ፓርቲው ተቀላቀለ፡፡ እነ ስልጣኑም በጥሩ ሁኔታ ስለያዙት በአጭር ጊዜ ውስጥ በአባላት ታዋቂ ሆነ፤ በ3ኛ ጉባኤም ለፕረዚዴም ሲመረጥ አልተደሰትክም፡፡ በኋላም ለአረና ህዝብ ግኑኝነት ሲጠቆምም አቶ ገብሩ አስራት በፀረ-ዲሞክራሲ ያለጥቆማና ድምፅ አምዶም መሆን አለበት ብሎ ያለድምፅ አፀደቀለት፤ ለህዝብ ግንኙነት ምክትልም አብርሃ የተጠቆመ እያለ ባንተ ጥቆማ ፍፁም ግሩም ሆነ፤ ስለሆነ አብርሃ ደስታ ጥሩ መሪ እንዲሆን ፍላጎት አልነበራችሁም፡፡

አብርሃ ደስታ በማህበራዊ ድህረ ገፆችና ሚዲያዎች በሚያደርገው እንቅስቃሴ ትእግስት አድርግ እያልክ ተፅእኖ ታደርግለት ነበር፡፡ እሱ ግን እኔ የግለሰብ ነፃነቴ ካላከበርኩ እንዴት ነው የህዝብ ነፃነት ማከብረው ብሎ ተቃውሞሃል፤ አቶ ገብሩ አስራትም የአብርሃ ደስታ እንቅስቃሴ ከፓርቲያችን አቋም ይሄዳል ወይ ብሎ ሲጠይቅ አሁንም ተቃውሞታል፤ እኔጋ በነበረው ግንኙነትም እንደ ቡድን ትቆጥረው ነበር እሱ ግን አልተቀበለህም፤ በአጠቃላይ በአብርሃ ደስታ ያለህ አመለካከት የቅናት እንጂ የፍቅር አይደለም፡፡ ለዚሁ እንደ ማስረጃነት አብርሃ ደስታ በጠራራ ፀሃይ ሲታፈን እኛ በየፖሊስ ጣቢያ ስናፈላልግ አንተ ግን በጥብቅና ቢሮህ ሁነህ ራፖልህ ነበር የምትሰራውና ገንዘብ የምትለቅመው፤ ደብዳቤ ፅፈን ፈርምልን ስንልህም ደስተኛ አልነበርክም፡፡
አብርሃ ደስታ ሲታሰር መግለጫ ከመስጠት ተቆጥበሃል፤ እኔ በኢሳትና ሌሎች ሚዲያዎች ስለ አብርሃ ስፅፍ አንተና አምዶም በውጭ ሚዲያ ተጠይቃችሁ ፍቃደኞች አልሆናችሁም፡፡ ስለ አብርሃ መታሰርም ለአባላት አልተናገራችሁም፤ ብዙ አባላት ጠበቃ እናቁምለት ብለው ሲጠይቁም ይቅርና ጠበቃ ለማቆም ሂዳችሁ’ኳን ለማየት አልሞከራችሁም፡፡ መጨረሻም ጠበቃ ልታቁምለት የተገደዳችሁበት ምክንያት አንድ ወገን በራሱ ሊጣበቅለት ሲወስን እንዳትታሙ እንከፍላለን ብላችሁት፡፡ ታዲያ የቱ ጋ ነው አድናቆቱ? የት ነው ፍቅሩ? መልሱ ላንተ። 

ብርሃኑ በርሄ፡- ‹‹በአብርሃ ደስታ አሳብበው የራሳቸው ፍላጎት ማስተንፈሻ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች መኖራቸው እናውቃለን ግን ያላወቁት ሁነው ነው’ጂ አብርሃ ደስታ ባለፉት 9 ወራት ስራ አስፈጻሚ ሁኖ የአረና ባህሪና አመራር ያውቀዋል፡፡›› ይላል። በመሰረቱ በአብርሃ ደስታ ምናስተነፍሰው ነገር የለም፤ ያንተ ጨካኝነትና ከዳተኝነት አብጠርጥረን እናውቃለን፤ አብርሃ ደስታ በናንተ እጅጉን አዝኖ እንደ ነበረ ታውቃለህ፤ የህወሓት ካድሬዎች የሚያስቆጣ ነገር እንዳትናገሩ ስትለው አልነበርክም፤ አብርሃ በደንብ ሚያውቃችሁ በፀረ-ዲሞክራሲ አስተሳሰባችሁ፤ አባታዊነታችሁ፤ በአምባገነናዊነታችሁና ቡድናዊነታችሁ ነው፤ በናንተ በጣም ተስፋ ቆርጦ እንደነበር ይነግረኝ ነበር፤ እንደውም አስገደና አብርሃ ደስታ እኛን ከድተው አንድነትን የሚቀላቀሉ በግምባር ቀደምትነት እንደምንጠቀስ አጃቢዎችህ ያሙን ነበር፤ አሁን በውጭም በውስጥም ደጋፊ ስለበዛ ቀንተህ ነው። አብርሃ ደስታ’ኮ ባሳየው ጠንካራ ተቃውሞ አሸባሪ ተብሎ ነው የታሰረው፤ አንተ ግን አሸባሪ እንዳትባል ከህወሓት ተለማምጠህ ትኖራለህ። 

ብርሃኑ በርሄ፡- ‹‹ክላሽ የለኝም ሽጉጥ ግን አለኝ ባለ ፍቃድ ነው፤ ሽጉጡ በትጥቅ ጊዜ እኔጋ የነበረ ነው፤ በትጥቅ ትግል ታጋይ በመሆን ትጥቁ የያዙ ፓርቲው ጋር ቢቀጥሉም ባይቀጥሉም አልተነጠቁም፤ ሊነጠቁም አይገባም፤ አቶ አስገደ ገ/ስላሴም ሽጉጥና ክላሽ ነበረው አሳበው ችግር እንዳይፈጥሩብኝ ትጥቄን አስረክቤያለሁ ብሎ በ2000 ነግሮኛል…››
አሁንም ብርሃኑ እየሸፈጥክ ነው፤ በኢትዮጵያ የፓርቲዎች ማቋቋምያ አዋጅ ማንም ፓርቲ ነፍጥና ሰውን የሚጎዳ መሳርያ አይታጠቅም፤ መንግስት ካቋቋማቸው ፖሊስ፣ መከላከያ ፣ ደህንነት ብቻ ይታጠቃሉ፤ የህወሓት አባልም ከነዛ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች ውጪ የሆኑ ትጥቃቸው ያራግፋሉ ይላል፤ በዚህ መሰረት ሁሉም ተቃዋሚ ሃይሎች ማንም ነፍጥ የታጠቀ የለም፤ ህወሓት እንደ ሆነ ራሱ ዳኛ ልጁ ቀመኛ ዳኛ የለውምና በትግራይ ክልል ብቻ በምልሻ ስም ካድሬ አመራሮች በአንድ ቀበሌ ከ72-90 ታጣቂዎች አሉ፡፡ እነዛ ሁሉ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ስጋት ናቸው፡፡ ይህ የሆነበት ህወሓት ፀረ-ህገ መንግስት ስለ ሆነ ብቻ ነው። ታዲያ ብርሃኑ የፓርቲ ሊቀመንበር ሁኖ ነፍጥ መታጠቁ የህወሓት ልጅ አይደለምን? ምልሻ ታጋይ የነበሩ አሁን የአረና አባላት የሆኑ ነፍጣቸው ተቀምተው በሁሉም መልኩ መብታቸው ተነጥቀው እየተሰቃዩ ነው፡፡ ይቅርና አባል ዘመድ አዝማድ እየተቆጠረ ተፍጓቸዋል። ታዲያ ብርሃኑ እንዴት አድርገህ ታታልለናለህ? እኔ በተደጋጋሚ ትጥቃችን እናስረክብ፤ ለራሳችን ነፃ አድርገን ለህወሓት ሲቪል ታጣቂዎች እንዲያስረክቡ እናድርግ ብየው እምቢ ብሎኛል።

አሁን ብርሃኑ ፍቃድ አለኝ ብሎናል፤ ፍቃድ የሚሰጠው በደህንነት ወይ በፀጥታና ፍትህ ነው። በመሆኑ ብርሃኑ ደህንነት ወይ ሚሊሻ ካልሆነ ፍፁም አይፈቀድለትም፤ ስለዚህ ብርሃኑ ደህንነት ወይ ሚሊሻ መሆኑ እያረጋገጠልን ነው። ደህንነትና ሚሊሻ ደግሞ የህወሓት ካድሬዎች ናቸው። ስለዚህ ብርሃኑ በርሄ የህወሓት አባል ነው፤ በኛ ላይ የተወሰደ እርምጃም አረናን ለማዳከም ተብሎ ነው።
ማሳሰቢያ:
1.የአረና አባላትና ደጋፊዎች በአረና ውስጥ ያለ ልዩነት በኔና በብርሃኑ የግል ንትርክ አድርገው የሚመለከቱ አባላት አሉ፤ ይኸ ፍፁም ስህተት ነው፤ የግል ቂምም የለኝም፤ ልዩነታችን በብርሃኑና በ3ት ስላሴዎችና በኛ ያለው ከላይ በተዘረዘሩ ችግሮች ምክንያት ነው፤ እነሱ ተሸፍነው ለመሄድ ሲሞክሩ እኛ ችግሩ መታገላችን ብቻ ነው ልዩነታችን፤

2.ውህደትን በተመለከተ እኛ ለመላው የኢትዮጵያ በእኩል የሚያስተናግድ፤ ህዝቡን ከዘር ፖለቲካ አውጥቶ በህዝቦች ጠንካራ መተማመን እንዲሰፍን፤ ክብሯና ሉአላዊነቷ የተረጋገጠች ኢትዮጵያን ለመገንባት ከማንኛውም ኢትዮፕያዊ ያለ ጥርጥርና ስጋት መወሃሃድ ስንፈልግ እነሱ ደግሞ ልክ የህወሓት አቋም እያራመዱ ስለሆነ ነው፤ በተለይ ብርሃኑ አባላት ሰብስቦ ከነ አንድነት ለውህደት ብየ አልደራደርም፤ አንድነትና ሌሎች ፓርቲዎች በመወሃሃድ የትግራይን ስነ ልቦናዊ ፍላጎት አያከብሩም ወዘተ. በማለቱ ነው፤

3. በዲያስፖራ የአረና ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ አመራርና አባላት እኛ ያነሳነው ጥያቄ ረጋ ብለው ምን እየተባለ እንደሆነ አስበውና አጣርተው አቋም እንደመውሰድ የነ ብርሃኑ የአንድ ወገን ሃሳብ ብቻ በማዳመጥ ጥያቄያችሁ በውስጥ እንደ መፍታት የትምክህተኛ አማራ መሳቂያ አደረጋችሁን ብላችሁ ፅሁፍን ማሰራጨታችሁ ከህወሓት ጠባብ አስተሳሰብ እጅጉን የወረደ ነበር፡፡ በእርግጥ ፅሁፉ የሁሉም ዲያስፖራ ደጋፊያችን እንደማይወክልና የጥቂት የነብርሃኑ አጃቢዎች አስተሳሰብ ብቻ ብለን ነው የምናምነው። እኛ ግን ከዚህ ሁሉ ጠባብ አስተሳሰብ ነፃ ነን።

4. በኔ እምነት ለህወሓት ተሸክመን መጥተን ሃገር አጠፋን፤ እንደገና ሁለተኛ ህወሓት የሚሸከም ትክሻ የለንም። አሁንም እኔ ለአምባገነኑ የህወሓት ስርአት በሰላማዊ መንገድ ከመታገል ወደኋላ አልልም፤ ለኢትዮጵያ አንድነት፤ ሉአላዊነት በአጠቃላይ የኢትጵያ ችግር ለመፍታት ቆርጦ ከተነሳ ሃይል በመሰለፍ ትግሌን እቀጥላለሁ፤ ለህወሓትና ለተበላሸው የአረና አመራር እኩል እታገለዋለሁ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ‼


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>