ከሔርሜላ አበበ
በምዕራብ ካናዳ ኑሯቸውን ያደረጉ ኢትዮጵያውያን በካልጋሪ ከተማ ያደርጉት የእግር ኳስ ፈስቲቫል እሁድ ኦገስት 31 ምሽት ተጠናቀቀ:: በዚሁ ውድድር ላይ ከተለያዩ ከተሞች የመጡ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉ ሲሆን ኤድመንተን ቫንኮቨር ዊኒፔግና ካልጋሪ ከባድ ፉክክር አሳይተው በቫንኮቨር አሸናፊነት ውድድሩ ተጠናቋል::
የመዝጊያውም ምሽት ዝንኛ በሆኑት ውድ አርቲስቶቻችን ብርሃኑ ተዘራ እና አብዱ ኪያር ካልጋሪ ውስጥ ታይቶ በማያቅ መልኩ እጅግ ብዙ ህዝብ በተገኘበት ልዩ በሆነ በሃገርና በወገን ፍቅር የሞላ ድግስ ተጠናቋል::
የሃገርና የወገን ፍቅር የሚለውን አባባል የመረጥኩበት ምክንያት እጅግ ብዙ ኤርትራዊያኖች ከኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ጋር በያንዳንዱ ቡድን ዉስጥ አብረው የተሰለፉ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ነው:: ካናዳ በተለይ ምዕራብ ካናዳ ኳስ ሜዳ ላይ የታየው ሌላ የፍቅር መንፈስ ነጮች ኢትዮጵያ የሚል ማሊያ ለብሰው በኳስ የወንድማማችነትን ፍቅር ለጉድ ስላሳዩንም ነው::
የምሽቱን መድረክ አብዱ ኪያር ገብቶ ከፈተው ከዛም ብርሃኑ ቀጠለው:: ሁለቱ ምርጥ አርቲስቶች ለዲጄውም ጊዜ ሳይሰጡት ለሶስት ሰአታት ያህል እያፈራረቁ ድንቅ ስራዎቻቸውን በተከታታይ እያቀረቡ ትንሹን ትልቁን ሴቱን ወንዱን ኢትዮጵያዊውን ኤርትራዊውን ፍጹም ፍቅር ወደ ሆነ መንፈስ ወስዱት:: ጥበብ እንደዚህ ለህዝብ ሲቀርብ እና ጥበበኛው በስሜት እያንዳንዷን ደቂቃ ነፍስ ሲዘራባት ማየት እጅግ ያስደስታል:: የአገሪቱ ህግ ሆኖ ከሌሊቱ ስምንት ተኩል ሙዚቃው እንዲቆም ተደርጎ እንጂ እነሱም እኛም ከባድና ጥልቅ የፍቅር ድባብ ውስጥ ነበርን::
ዛሬ ጥበብን በጥቅምና በሆድ ለመቀየር በሚሞከርበት ዘመን ፣ የጥበብ ሰው ጥበቡን ትቶ ካድሬ መሆን በሚፈልግበት በዚህ ዘመን ፣ ስለአገር መዝፈን በጣም በከበደበት ዘመን ፣ ብርሃኑ ተዘራን እና አብዱ ኪያርን ስለፍቅር ስለ አገር እና ስለ አንድነት ሲዘፍኑ ማግኝት በጣም ደስ ይላል በተለይ በስደት ሲሆኑ ደግሞ እጥፍ ድርብ ደስ ይላል::
በናቴም አንድ ነኝ ባባቴም አንድ ነኝ
ከኢትዮጵያ ሃገሬ የለም የሚለየኝ
በናቴም ሃበሻ ባባቴም ሃበሻ
አንድ ናት ኢትዮጵያ እስከመጨረሻ
እያለ ብርሃኑ ተዘራ ሲዘፍን አዳራሹ እንዴት በጩኸት ይናጋ እንደነበር መመስከር ግድ ይላል:: ብርሃኑ ተዘራ ፈጣሪ ጥበቡን ከ እድሜ ጋር ይስጥልን እንላለን::
አቤት ብታያቸው አቤት ብታያቸው
እህልና ውሃ ማርና ወተታቸው
አርቴፊሻል ሆኗል እንዳለ ኑሯቸው
ዘመናዊው ባርነት ስላስገደዳቸው
ዜግነት ቀየሩ ካዱኝ አትበያቸው
በወረቀት የሰው በደም ያንቺ ናቸው
እያለ አብዱ ኪያር ሲዘፍን የነበረው ሺህ የሚጠጋ ህዝብ እንዴት አብሮት በፍቅር መንፈስ ይዘል እንደነበር ባይኔ ሳይ ልቤም እየተላወሰ ነበር:: አብዱ ኪያር የምታምነው ጌታ እድሜውን ከጥበብ ጋር አብዝቶ ይስጥልን ብለናል:: እውነትም እኔ እራሴ በወረቀት የሰው(የካናዳ) በደም የኢትዮጵያ እኮ ነኝ::
ከራሳቸው ዘፈን ውጭ ጉራግኛ ትግርኛ ኦሮምኛ ብቻ ምን ቀረ ሁለቱ ምርጥና ድንቅ አርቲስቶች እያንዳንዷን ዘፈን ሲሰሩ ኦሪጅናል ሲዲው የሚጫወት እስኪመስል ድረስ ኩልል እያለ በጥበብ ስራዎቻቸው እጅግ በጣም ያስደስቱ ነበር:: እያንዳንዱ ሰው ፊት ላይ የደስታና የፍቅር መንፈስ ሲነበብም ነበር በተለይ ቫንኮቨሮች ዋንጫውን ስለወሰዱት ደስታቸው ላቅ ያለ ነበር::
የምዕራብ ካናዳ እግር ኳስ መዝጊያ ምሽትን በሚያስደስት ሁኔታ አሳልፈናል ኮሚቴዎችም እጅግ ድንቅ ምርጫ አርጋችኋል አዳራሹ ሙዚቃው ስነስርአቱ እጅግ ደስ ያሰኝ ነበር በርቱልን:: ከብዙ ከተማ የመጣውን ስፖርተኛና የስፖርት ቤተሰብ ካልጋሪ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እጅግ ባማረ ፍጹም ጨዋነት በተሞላበትና ፍቅር በሞላበት መልኩ በአስደሳች መስተንግዶ ተንከባክባችሁናል እናመሰግናለን::