ምንሊክ ሳልሳዊ
‹‹ኢህአዴግ ራሱ በአኖሌ ስም እየነገደ ለእሱ የሚቀርቡት አካላት ከእነ ቴዲ አፍሮና ሰማያዊ ፓርቲ ጋር አላትሞ መውቀሱ የሚያስገርምና ውይይት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳ ነው›› የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጥቁር ሰው አልበም በስልጠና ሰነዱ ላይ ለአክራሪነት ምሳሌ ተደርጎ የቀረበ ሲሆን ተማሪዎችም ቴዲ አፍሮ ለአገር አንድነት የቆመ መሆኑን በመግለጽ መከራከራቸውን ገልጸውልናል፡፡
በኢህአዴግ ጽ/ቤትና በትምህርት ሚኒስትር ትብብር ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተሰጠ ባለው ስልጠና ሰማያዊ ፓርቲና ቴዲ አፍሮ አጀንዳ መሆናቸውን ሰልጣኞች ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ ‹‹የልማታዊ ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ትግላችንና ፈተናዎቹ›› በሚለውና በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ ውጭ በየ ክልሉ እየሰለጠኑ ለሚገኙት ተማሪዎች እየተሰጠ ባለው ስልጠና ሰማያዊ ፓርቲና ቴዲ አፍሮ ለልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባታ ፈተናዎች ተብለው ቀርበዋል፡፡ አሰልጣኞቹ ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹መንግስት የእምነት ነጻነት ያክብር!›› እያለ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በአክራሪነት የፈረጀ ሲሆን ቴዲ አፍሮም ‹‹ጥቁር ሰው›› በሚል ለህዝብ ያደረሰው አልበም ተመሳሳይ ውንጀላ ቆርቦበታል ሲሉ ሰልጣኞቹ ገልጸዋል፡፡
ሰማያዊና ቴዲ አፍሮ በተለይ በውይይት ወቅት ከአሰልጣኞቹ ሰፋ ያለ ወቀሳና ውንጀላ እንደደረሰባቸው ሰልጣኞቹ ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎቹ በበኩላቸው ‹‹ሰማያዊ ፓርቲ እንደ አንድ ለህዝብ እንደቆመ ፓርቲ መንግስት በእምነት ጣልቃ እንዳይገባ መጠየቅና መታገል መብቱ ብቻ ሳይሆን ግዴታው ነው፡፡›› ብለው እንደተከራከሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ጥቁር ሰው አልበም በስልጠና ሰነዱ ላይ ለአክራሪነት ምሳሌ ተደርጎ የቀረበ ሲሆን ተማሪዎችም ቴዲ አፍሮ ለአገር አንድነት የቆመ መሆኑን በመግለጽ መከራከራቸውን ገልጸውልናል፡፡ ተማሪዎቹ አክለውም ‹‹ጥቁር ሰው የሚለው ተወዳጅ ዘፈን በገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ስር ከሚገኙት ውጭ በአብዛኛዎቹ ሚዲያዎች በስፋት ይለቀቃል፡፡በስልጠናው እያየነው እንዳለነው ግን ገዥው ፓርቲ ቴዲ አፍሮን ብቻ ሳይሆን ሚዲያዎቹንም በአክራሪነት እየከሰሰ መሆኑ አሳዛኝ ነው፡፡›› ሲሉ ለነገረ ኢትዮጵያ አስተያየታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሰነዱ ‹‹ጠባብና ትምክተኛ ተብለው የተፈረጁ ኃይሎች ተመጋጋቢ ናቸው›› ተብለው የቀረቡ ሲሆን ‹‹የትምክት አስተሳሰብ የተጠናወተው ሚዲያ ‹‹ጥቁር ሰው›› በሚል ዘፈን ሚኒሊክን ሲያሞካሽ በጠባብነት የተለከፈው ሚዲያ የአኖሌን ግፍ ህዝብን ለመለያየት ይጠቀምበታል›› ሲል ሁለቱንም በጅምላ ይወቅሳል፡፡ ይህን ስልጠና እየወሰዱ ያሉ ተማሪዎች ‹‹ኢህአዴግ ራሱ በአኖሌ ስም እየነገደ ለእሱ የሚቀርቡት አካላት ከእነ ቴዲ አፍሮና ሰማያዊ ፓርቲ ጋር አላትሞ መውቀሱ የሚያስገርምና ውይይት ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳ ነው›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ‹‹እራሱ ህዝብን በተለያዩ መንገዶች ህዝብን እየነጣጠለና የከፋፍለህ ግዛ ስርዓት አስፍኖ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑትን አካላት በማይገባቸው ክስ መክሰሱ የዪኒቨርሲቲ ተማሪዎች አላዋቂ አድርጎ መውሰዱንና ንቀቱን የሚያሳይ ነው፡፡›› ብለዋል፡፡ ሰልጣኝ ተማሪዎች የላኩልንን የሰነዱን አካል እንደሚከተለው አያይዘነዋል፡፡