ሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ
ግንቦት ፳፻፭ (May 2013)
የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች ይኸውም ለሥልጣን ያቆበቆቡ እሾም ባዮች ፣ ለጥቅማቸው የቆሙ ግለሰቦች እና ሆድ አደሮች የሀገራችው ፣ የሕዝባቸው፣ የቤተ ክርስቲያኗ ገዳማውያን እና መናንያን ሐዘንና ሰቆቃ ሳይገዳቸው እኔ ከሞትኩኝ ስርዶ አይብቀል እንዳለችው አህያ የግል ቀቢጸ ተስፋቸውን (ego) ላማሟላት ብቻ ቤተ ክርስቲያኗን ለወያኔ አሳልፈው ለመስጠት መሰናዶአችውን ጨርሰውና ወገባቸውን ጠበቅ እድርገው ተነስተውልህ June 2, 2013ን በትልቅ ጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ (በነገራችን ላይ ስለ June 2, 2013 ለማታውቁ ወይንም ላልሰማችሁ ለማሰማት ይረዳ ዘንድ….. June 2, 2013 የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ወደ ኢትዮጵያ ሲኖዶስ ትቀላቀል ወይንስ አትቀላቀል የሚለው ውሳኔ ይሰጥ ዘንድ የቤተ ክርስቲያኗ የአስተዳደር ቦርድ ስብሰባ የጠራበት ዕለት ነው፤ ስብሰባውም ከቅዳሴ አገልግሎት በኋላ ይከናወናል)።
በኢትዮጵያ ገዳማት እና አድባራት በመነኮሳት እና በመናንያን ወገኖቻችን ላይ የህወሃት/ኢህአዲግ መንግስት የሚፈጽመውን የዘር ማጥፋት እና ማፅዳት፣ የገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ መፍረስ፣ መዘረፍ እና መታረስ ሳይገዳቸው፤ በኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን ላይ በተለያዩ ቦታዎችና ግዜያት ለምሳሌ ያህል ከቡዙ በጥቂቱ በሐረር፣ በእርሲ አርባጉጉ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በአፋር፣ በጋንቤላ፣ በደቡብ ህዝቦች ከልል፣ በጂማ፣ በአሶሳ፣ በጎንደር፣ በአዲስ አበባ በ1997 ከተካሔደው ምርጫ በኋላ፣ በአዋሳ፣ በበደኖ፣ በአርባጉጉ፣ በአርሲ አሳሳ፣ በቤኒሻንጉል ህዝባችን ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ የተናጠል ግድያ፣ አማራው ወልዶ ከሳመበት አርሶ ከቃመበት ቀዬው/ሠፈሩ የዘር ሐረጉ እየተመዘዘ ሲባረር፣ እስራት፣ መከራ፣ ስቃይ፣ ግርፋት፣ እርዛት እና ረሐብ ሲቆላው እያዩ እና እየሰሙ የወገናቸው እና የህዝባቸው ሥቃይ፣ መከራ፣ ሰቆቃ እና ዋይታን ወደጐን በማለት በሌላው ላይ የሚደርሰው ግፍ የማይሰማቸው ካህናት እና መዘምራን የደንቆር ለቅሶ መልሶ ቀልሶ ይሉ ዘንድ አባት ያስፈልገናል በሚል የሐሰት ቅጥፈታቸው፣ የግል ፍላጐታቸውን ለማሟላት እና በወያኔ የተሰጣቸውን የቤት ሥራ ለመስራት ሲሉ ብቻ ቤተ ክርስቲያኗን፣ አንተን እና አንቺን አሳልፈው ሊሸጡህ/ሊሰጡህ የተዘጋጁ ሥለሆነ አንተም ጠንቅቀህ እውነታውን ተረድተህ እና ነቅተህ ቤተ ክርስቲያኗን ልትጠብቅ ይገባሃል።
ህዝበ ክርስቲያኑን እኛ እናውቅልሀለን፣ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ቆመናል፣ አባት ያስፈልግሃል እኛም አባትህ ነን የምንልህን ስማ ካላችሁ ምነው ታዲያ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ተባረው ወደ ጐጃም ሲጋዙ የተጫኑበት አይሱዙ ተገልብጦ አባይ በረሃ ላይ ከ 60ዎቹ 59ኙ ያለቀባሪና ያለአንሺ አስክሬናቸው የአውሬና የአሞራ ሲሳይ ሲሆን በደብረ ሰላም ቤተ ክርስቲያን ፀሎት አልተደረገላቸው፣ የዝቋላ ገዳማት ሲጋዩ፣ የዋልድባ መናንያን ከገዳማቸው ሲባረሩ ምነዋ የኛዋ ደብረ ሰላም በፀሎት አላሰበቻቸውም??? ባለፈው ቦስተን ላይ በደረሰው የሽብርተኞች ጥቃት ለሞቱት ፀሎት ሲደረግላቸው የኛን ግን ረሳናቸው!! ነው ወይንስ የዋልድባ አሳዳጆች የኛን ካህናትም ወዮላችሁ አሏችሁ፤ ካሏችሁ መቼስ ምን ይደረጋል
ፈሪ ለእናቱ ያገለግላል፣
ምጣድ ስትጥድ እንሰቅስቅ ይላል፣ ይባል የለ፤ ለማንኛውም የምንኖረው በ21ኛው ክፍለ ዘመን ስለሆነ በሃገራችን እና በቤተ ክርስቲያንናችን ላይ የሚደርሰውን ጥፋት፣ ውድመት እና ዘረፋ በስማ በለው ሳይሆን በቀጥታ በየእለቱ መከራውን ቀማሽ ከሆነው ህዝባችን ስለምንሰማው ልትሸነግሉን ባትሞክሩ መልካም ነው፤ ይልቁንስ ለእውነት ስለእውነት ቆማችሁ ሃገራችንን እና ቤተ ክርስቲያንናችንን በጋራ ብንታደጋት ለወደፊቱ ይበጀናል ይበጃችኋል።
አንዳንድ ካህናት በቤተ ክርስቲያኗ ዓውደ ምህረት ስብከታቸው ላይ ወደ ኢትዮጵያ ሲኖዶስ (ሀገር ቤት ያለው በአባይ ፀሐይ እና የፌድራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ሺፈራው ተ/ማርያም የሚመራውን ሲኖዶስ (በነገራችን ላይ ዶ/ር ሺፈራው ተ/ማርያም የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ናቸው) ከፓትሪያርክ ምርጫ በፊት ሲኖዶሱን ሲመሩት እንደነበረ የሚዘነጉት አይመስለንም) እንግባ እያሉ የሚያደነቁሩን ከቤተ ክርሲቲያን ውጪ ደግሞ የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎችን ሲኖዶሱ/የኮሌጁ አስተዳደር ከመኖሪያና መማሪያ ግቢ ባባረራቸው ወቅት ተማሪዎቹ የሚበሉት የሚጠጡት የላቸውምና እባካችሁን ለእነርሱ እንድረስላቸው እያሉ የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎችን የገንዘብ መለመኛ ያደርጓቸዋል። ነገሩ ለበጎ ቢሆነ ባልከፋ ነበረ ነገር ግን በአደባባይ ትክክለኛው ሲኖዶስ ኢትዮጵያ ነው ያለው፣ ሲኖዶስ አይሰደደም እያሉ የሚሰብኩ ነገር ግን ለገንዘብ መለመኛ ሲሆን ሲኖዶሱን ከሰውና ወቅሰው ከስንቶቻችሁ ገንዘብ አንደሰበሰቡ ቤት ይቁጠረው ገንዘቡም ይድረስ አይድረስ ለሰብሳቢው ካህን ትልቅ የጥያቄ ምልክት ? እያኖርኩኝ፤ ከቤተ ክርስቲያኗ አውደ ምህረት ውጪ ሲሆን ግን የተማሪዎቹ መባረር ስህተት ነው፣ ሲኖዶሱም የሚሠራው ሥራ ትክክል አይደለም፣ ጥፋት እየተፈፀመ ነው ብለው ካመኑ፤ ሲኖዶሱንም እያወገዙ ገንዘብ ከለመኑ ታዲያ ምነው ሲኖዶስ አንድ ነው፣ አይሰደድም፣ እሱም ኢትዮጵያ ያለው ነው፣ ትክክልም እየሠራ ነው፣ እሱን ልንከተል ይገባናል አያሉ አውደ ምህረት ላይ ለምን ይሰብካሉ (ባንድ ራስ ሁለት ምላስ ይሏል ይህ ነው)።
እውነታውን አንነጋገር ከተባለ ምነው የአቡነ ጴጥሮስ ኃውልት ሲነሳ በዓውደ ምህረት ላይ አንድ ካህን አልተነፈሰም ያውም የአቡነ ጳውሎስ ኃውልት በሲኖዶስ ውሳኔ እንዲፈርስ ተወስኖ ሳለ፣ የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ከትምህርት ቤቱ ግቢ ሲባረሩ ያውም ምግብ ተከልከለው የእለት ጉሮሮአቸውን አንኳን ለምነው አንዳይዳፍኑ በፖሊስ እየተሳደዱ ባሉበት፣ የዋልድባ መናንያን ቋርፍ በልተው ከሚኖሩባት ገዳማችው እየተባረሩ ወደ ነበሩበት ገዳም ለመመለስ ሲጠይቁ ወደ እዚህ ከምትመለሱ አናታችሁ ማሕፀን ብትመለሱ ይሻላችሗል ሲባሉ፣ በሰደፍ ተደቅትው ሜዳ ላይ ሲጣሉ፣ እንደ ሕፃን በአለንጋ ሲገረፉ በልምጭ ሲለመጡ፣ ከወፍጮ ቤት ገቢ ያሰባሰቧትን 60, 000 (ስልሳ ሺህ ብር) በአደባባይ በመንግስት ታጣቂዎች በጠራራ ፀሐይ ሲዘረፉ፤ ዝቋላ፣ የአሰቦት ገዳም፣ ታሪካዊ መጽሐፍት አና ቅርሶች ያሉባችው ደብሮች እና ገዳማት ሲጋዩ፣ በምዕራብ ጎጃም ጣና በለስ አካባቢ ያሉ አብያተክርስቲያናት እንዲፈርሱ በወያኔ ሲወሰን ምነው አንድም ቀን በቤተ ክርስቲያኗ ዓውደ ምህረት ላይ አልሰበኩ መልሱን ለአንባቢያን እና ለሰባኪያኑ እተወዋለሁ። የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች በተባረሩ ሰሞን አዲስ የተሾሙት ፓትሪያርክ በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ (VOA http://amharic.voanews.com) ተጠይቀው ይህ ጉዳይ እኔን አየመለከተኝም ሲሉ የሲኖዶሱ ፀሐፊም ተመሳሳይ መልስ ለኢሳት (Ethiopian Satellite TV/Radio www.ethsat.com) ሲሰጡ እንዲያውም ይባስ ብለው በሌላ ቃለ መጠይቅ እኚሁ የሲኖዶሱ ፀሐፊ ተብዬው አቡነ ህዝቅኤል ስለ ዋልድባ ገዳማውያን እንግልት ጥያቄ ቀርቦላችላቸው “ማርያምን አልሰማሁም” ሲሉ መስማቱ አያሳዝንም። ታዲያ የቤተ ክርስቲያኗ የበላይ ተብዮዎች አያገባንም ካሉ ማ ሊጠየቅ ኖሯል በቅጥፈት እውነትን ለመሸሸግ መሞከሩ ከተጠያቂነት አያድንም፤ ነው ወይንስ የተሾሙት አባት ተብዮዎች ወንበር ለማሞቅ የተቀመጡ ጉዶች ናቸው?? ለነገሩማ ከአነጋገራቸው ለመረዳት እንደቻልነው ምንም ነገር ከመተንፈሳቸው በፊት ከመንግስት አካል ትዕዛዝ/መመሪያ መጠበቅ አለባቸው፣ እህህህ ከማለት ውጪ ምን ይባላል የሚሰብኩትን ወንጌል ሰባኪ ብቻ ሳይሆኑ ፈፃሚም ያድርጋቸው።
ታዲያ የደብረ ሰላሞቹም ካህናት እራሳቸውን አዋቂ ሌላውን አላዋቂ ለማስመሰል ስለ ዮዲት ጉዲት፣ ግራኝ መሀመድ አና ስለ ሌሎችም በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ስለደረሱት ጥፋቶች በተደጋጋሚ ሰበኩን፤ አዎ በጣም ብዙ ብዙ ጥፋቶች እና ውድመቶች በዮዲት ጉዲት እና በግራኝ መሀመድ ተፈጽመዋል ይህንን የካደ በደብራችን ማንም ሰው የለም ወይንም አላጋጠመንም ነገር ግን አሁንም ከዛ ባልተናነሰ መልኩ ቤተ ክርስቲያኗን እያጠፏት እና እያወደሟት ስለሆነ ከእነርሱ ጋራ አንተባበርም፣ ከእነርሱ ጋራ ቤተ ክርስቲያኗን አናጠፋም ነው እያልን ያለነው፤ ካህናቶቹ እያላችሁ ያላችሁት ግን ከአጥፊዎች ጋር ተባበሩ፣ ከአጥፊዎች ጋር እጥፉ ነው፣ ዮዲት ጉዲትም መጥታ ስለ አንድነት እየሰበከች ቤተ ክርስቲያንን ብታጠፋ ከእርሷ ጋር ተባበሩ እያለችሁ ነው፤ አሁንም ደግመን ደጋግመን የምንለው ከአጥፊዊች ጋር አንተባበርም ነው።
ይሁዳ ጌታን አሳልፎ በመስጠቱ ያገኘው ፀፀትና ሐዘን እንጂ ፍሰሐ እና ደስታ አልነበረም እናንተስ እኛን አሳልፎ በመስጠት የምታገኙት ደስታ ምን ይሆን??? መልሱን ለእናንተው እተወዋለሁ። ለማንኛውም ለሹመቱ ጉጉት ያሎት ጠቀም ያለ ገንዘብም ያዘጋጁ በቅርቡ ሐራ ተዋህዶ አንደዘገበችው ከሆነ ለደብር እልቅና በአነስተኛ ግምት እስከ ብር 80,000 (ሰማኒያ ሺህ) ፣ ለፀሐፊነት አስከ ብር 30,000 (ሰላሳ ሺህ) ብር ጉቦ መስጠት ይጠበቃል (ለዝርዝሩ ይህን ሊንክ ይክፈቱ http://www.zehabesha.com/amharic/archives/3506)፤ አሁን አሁን ደግሞ ሰውን አሳልፎ በመስጠት ብቻ ጵጵስና የሚገኝበት ዘመን ላይ አይደለንምና!!! ያውም ካገኙ፤ በቅርቡ ከቤተ ክህነት እንዳፈተለከው ወሬ ከሆነ ሦስተኛ መመዘኛም ተመዟል (መቼም የትግራይ ህዝብ ፈርዶበት በስሙ ይነገዳል) ከትግሬ በቀር ሌላው ቤተ ክህነትን አይረግጥም እየተባለ ነው፤ ታዲያ የኛዎቹ ጉዶች ሌላውን መመዘኛ ብታልፉ ይሄኛው ሳይጥላችሁ አይቀርም (አበስኩ ገበርኩ) ።
አንድነት አንድነት እያሉ የሐሰት ነጋሪታቸውን የሚጐስሙና የውሸት ጥሩንባቸውን የሚነፉ ግለሰቦች ስለ እውነተኛው አንድነት ቢለፉና ቢደክሙ ምንኛ መልካም ነበረ፤ በቅርቡ በአዳባባይና በሚዲያ ወጥተው አማራና ኦርቶዶክሱን አከርካሪውን ሰብረነዋል እያሉን አንዴትስ ነው ከአከርካሪ ሰባሪዎች ጋር አንድ የምንሆነው፤ ይልቁንም የእነርሱ የገደል ማሚቶ ሆኖ የሐሰት ጩኸታችውን ከማስተጋባት ቤተ ክርስቲያናችንን በህብረት ብንሰራ ምንኛ በተሻለ ነበር ይልቁንም በአስራ አንደኛው ሠዓት ላይ የራሳቸውንም ሆነ የቤተ ክርስቲያኗን ሠላምና አንድነት ከሚነሱ አርፈው ቢቀመጡ እንመክራቸዋለን። ለመሆኑ እስቲ አንድነት አንድነት የሚሉትን አንድ ጥያቄ ልጠይቃቸው፤ ባለፈው በዳላስ ቴክሳስ የነበረውን የአንድነት ጉባኤ የበተነው ማነው፣ ጉባኤው ሳያልቅ ከኢትዮጵያ መግለጫ ያወጣው ማነው፣ በሰላም ጉባኤው ላይ የተካፈሉትን ቄሶች መስቀል ነው ያለውስ የህወኃት መስራች የየትኛው አካል ይሆን???? እኛማ የኢትዮጵያን አንድነት እና የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት አጥብቀን እንሻለን እናንተ የምትድግፏቸው ግን ወገኖቻችንን አሳደዷቸው የኢትዮጵያ አንድነት እና የቤተ ክርስቲያን አንድነት ስላሉ ገደሏቸው፣ ተከብሮና ተፈርቶ የኖረውን ገዳም አትንኩብን ባሉ ገረፏቸው፣ ቀጠቀጧቸው፣ የቤተ ክርስቲያኗን ሀብት እና ቅርስ ዘርፈው ሸጡ፣ ገዳማትን አቃጠሉ፤ ታዲያ አንድነቷን ያሳጣ ሰላሟን የነሳ የትኛው አካል ይሆን???? ጉድ ሳይሰሙ መስከረም አይጠባ ይባል የለ……
እሁድ May 19, 2013 አቡነ ዘካሪያስ በራችስተር ሚኒሶታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ንግስ እና የአዲስ ቤተ ክርስቲያን ግዢ ምርቃት ላይ ተገኝተው በነበረበት ወቅት በተደረገው ስብከት ላይ ባካበቢያችን ሦስት ቤተ ክርስቲያናት ብቻ እንዳሉ እና ሶስቱም በኢትዮጵያ ሲኖዶስ ስር እንዳሉ አድርጐ የተሰበከውን ስብከት አንቀበለውም። አቡነ ዘካሪያስ የጐጃም ክፍለ ሃገር ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት ወቅት እናቶችና አባቶች ከልጆቻቸው ጉሮሮ ነጥቀው ለቤተ ክርስቲያን የሰጧትን ምፅዋት ዘርፈው ወደ አሜሪካን በአቡነ ጳውሎስ የተላኩ ናቸው። ይህንንም ከጎጃም አካቦቢ የመጣነው ጠንቅቀን እናውቀዋለን፣ እርሳቸውም ቢሆኑ ሳይክዱ በኤሚሪካን ድምፅ ራዲዬ ቀርበው በማመን ከልጆቻቸው ለምነው እንደሚከፍሉ ለአቶ አዲሱ አበበ በቃለ መጠይቁ ወቅት የእምነት/ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል። አቡነ ዘካሪያስን፤ አባታችን አባታችን ለሚሉት አንድ ጥያቄ እናስቀምጥላቸው፤ እንደተባለው እና እንዳመኑት የወሰዱትን ከ 1.5 ሚሊየን ብር በላይ ከምን ከተቱት፤ ቤት ሰርተውበት እያከራዩት ይሆን ወይንስ???? እርሳቸውን ብትጠይቁልን?? ሌላው እኚሁ አቡነ ዘካሪያስ በራችስተር ሚኒሶታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በዓለ ንግስ በኋላ በዕለቱ በበዓለ ንግሱ ላይ የነበሩትን ካህናት እና መዘምራንን ሰብስበው በርቱ የምትሰሩትን መልካም ሥራ እየተከታተልን ነው በማለት ተጨማሪ የቤት ሥራ ሰጥተዋቸዋል፣ ያቺ June 2 ደርሳ ማን ከኢትዮጵያዊያን ማን ከወያኔ እና ከቤተ ክርስቲያን ዘራፊዎች ጋር አንደሚወግን እንተዛዘባለን።
እነሆ ሀገር ወዳድ የሆንከው ኢትዮጵያዊ በሙሉ ይህችን ቤተ ክርስቲያን ከጥፋት ትታደጋት ዘንድ ጥሪያችንን ስናቀርብ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የወያኔን በስመ አባይ ቦንድ ሽያጭን (እዚህ ላይ ወገኔ እንድትገነዘብ የምንፈልገው ሀገር ብትለማ የሚጠላ ማንም እንደሌለ ልብ ይሏል፤ ይሁን እንጂ የሚሰበሰበው ገንዘብ የሚውለው ያንተኑ ወገን ለማፈናቀያ እና ለማሰቃያ እንጂ ለሀገር ልማት ቢውልማ ማን ይጠላ ነበረ!!!) በደቡብ አፍሪካ፣ ሒውስተን ቴክሳስ፣ ሳንዲያጎ ካሊፎርኒያ፣ በኖርዌይ ስታቫንጋር አሳፍረህ እንደመለስክ ዛሬም ይህንኑ እንድትደግም አንቢ ቤተ ክርስቲያኔን ለወያኔ መፈንጫ ገንዘቤን ወገኔን ለማፈኛ አሳልፌ አልሰጥም የምትል ሁላ June 2, 2013 በደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን (4401 Minnehaha Ave S. Minneapolis MN) ተገኝተሽ/ህ ድምፅሽን\ህን እንድታሰሚ\ማ።
በመጨረሻም ከአንድ ድረ ገጽ ያገኘነውን ቀንጨብ አድርገን እናካፍላችሁ እና ፅሑፋችንን ለዛሬው በዚሁ እንግታ “ወያኔ መራሹ ዘረኛ መንግስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ለማጥፋት ኢላማውን ካነጣጠረ እነሆ 21 ዓመታትን አስቆጠረ። ወያኔ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት በግልፅ የግድ ወታደር ማዝመት አይጠበቅበትም ለምን ቢባል ገና በደደቢት እያለ ያሰለጠናቸውን ልዩ ሃይል መነኩሴ በማስመሰል አሰልጥኖ በመላክ ተልዕኮውን እያሳካ ይገኛል” (ከጥላ መጽሔት http://www.ethiomedia.com/abc_text/tila_sixth_edition_2013.pdf)
For general knowledge please read the below article
http://www.ethiofreedom.com/tplf-is-appying-the-nazi-model-to-exterminate-the-amhara-people/
ሠላም ሠንብቱ የከርሞ ሰው ይበለን
ውበት ኢትዮጵያዊነት – ከሚኒያፖሊስ