ኢየሩሳሌም አረአያ እንደዘገበችው፦
የቀድሞ የትግራይ ፕሬዝዳንትና የሕወሐት/ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር አባል የነበሩትና በ1993ዓ.ም ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር በፈጠሩት የፖለቲካ ልዩነት ከስልጣናቸው እንዲባረሩ ከተደረጉት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ገብሩ አስራት 516 ገፅ የሸፈነ መፅሐፍ ማዘጋጀታቸው ታውቋል።
«ሉአላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ» የሚል ርዕስ የተሰጠው ይኸው መፅሐፍ የድርጅቱን አጠቃላይ ጉዞ የሚፈትሽና ሕዝብ ዘንድ ያልደረሱ በርካታ መረጃዎችን ያካተተ እንደሆነ ተመልክቷል። መፅሐፉ ከሴፕቴምበር 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለገበያ እንደሚውል ሲታወቅ በዚሁ ዕለት በዋሽንግተን ዲሲ የምረቃ ስነስርአት እንደተዘጋጀ ማወቅ ተችሏል። አቶ ገብሩ በ1997ዓ.ም መስቀል አደባባይ በተጠራ የተቃውሞ ሰልፍ በይፋ ህዝብን ይቅርታ ከመጠየቃቸውም ባሻገር በስልጣን ላይ እያሉ ለተፈፀመ ጥፋት አብረው እንደሚጠየቁ መናገራቸው ይታወሳል። «ቤሳ ቤስቲን እንደሌለው አውቃለሁ» ሲሉ አቶ መለስ ዜናዊ በ1994ዓ.ም ስለአቶ ገብሩ አስራት ንፁህነት መናገራቸው አይዘነጋም።