Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

‹‹ይድረስ ላንቺ›› ተፃፈ ከስድስተኛ ተከሳሽ –በዘላለም ክብረት

$
0
0

‹‹ይድረስ ላንቺ››
ተፃፈ ከስድስተኛ ተከሳሽ
በዘላለም ክብረት

ወዳጄ ልቤ ከቶ እንደምንድን ነሽ? እውን እኔና አንቺ በአለም ስንኖር ሌላ የመገናኛ ዘዴ አጥተን ወደ snail mail እንመላለሳለን ብለሽ አስበሽ ታውቂያለሽ? ለማንኛውም እንዲህ ሆነ፡፡ ጥጋበኛ ሰው ያስቀናኝ ጀምሮልሻል፣ ጥጋበኛ እንዲህ የሚለው ትዝ አለኝ፡፡

‹‹ ….ደብዳቤ ቢጽፉት እንደ ቃል አይሆንም፣
እንገናኝ እና ልንገርሽ ሁሉንም….››
zelalem
የደላው! ቢያሻው በደብዳቤ፣ ሲፈልግ በአካል እያማረጠ እኮ ነው፡፡ ለእኔ አሁን ባለሁበት ሁኔታ ሁለቱም ቅንጦት ነው (ወይ ደብዳቤው አይደርስሽም ወይም አንቺን ማየቴ ሊገደብ ይችላል)፡፡ ቆይ ትንሽ የጎን ወሬ ላዋራሽና ምክንያቱን እነግርሻለሁ፡፡ ‹‹አንቺ›› ተብለሽ በዚህ ደብዳቤ ስለተጠቀስሽው ‹‹አንቺ››ና ይሄን ደብዳቤ ለሚያነቡ ወዳጆች የዕምነት ክህደት ቃሌን በትንሹ ላስፍር፡፡

እመቤት ሲልቪያ ፓንክረስት የኢትዮጵያ ፍቅረኛ (Ethiopian by choice) ዱቼ ሞሶሎኒ እትዮጵያን በወረረ ጊዜ፤ ወራሪው ሃይል በመላው ኢትዮጵያ ‹‹ የኢትዮጵያን ስም እያነሱ መፃፍ ክልክል ነው›› የሚል ያልተፃፈ አዋጅ አውጆ እንደነበር ይነግሩናል፡፡ በዚህም ምክንያት ፀሀፍቱና አዝማሪያኑ ስውር መጠሪያ መጠቀም ስላስፈለጋቸው እስከ ዛሬ ድረስ ተወዳጁ ሕዝባዊ ዘፈን አንቺ ልጅ አንቺ ልጅ እንደ ስውር የፍቅር ዘፈን ተበርክቷል፡፡ በዘፈኑ ‹‹አንቺ ልጅ ›› የተባለችውም ኢትዮጵያ ናት፡፡ እኔስ በዚህ ዘመን ‹ይድረስ ለባለ ታሪኩ›፣ ‹ይድረስ ለባለ ንብረቱ›… እንደሱ የሀዘን ደብዳቤ ርእስ ‹ይድረስ ለኢትዮጵያ › በማለት ፋንታ ‹ይድረስ ለአንቺ› ለማለት ስውር መጠሪያ ተጠቅሜያለሁ? ፤ በፍፁም! ጌቶች እንደሚሉት ሕገ መንግስቱ የመናገር ነፃነቴን ሙሉ ለሙሉ አስከብሮልኛልናi
ቧልቱ ይቆየንና በዚህ ደብዳቤ ርዕስ ዙሪያ ያለማንም አስገዳጅነት የእምነት ክህደት ቃሌን ላስፍር አንቺ የተባለችው ኢትዮጵያ አይደለችም፡፡ ‹አንቺ› የኔዋ ሀቢቢ ግን ባለሽበት ይድረስሽ፡፡ ውዴ እንግዲህ በዚህ ደብዳቤ ያለፈውን እያነሳሁ እነግርሻለሁ፡፡ወይ ትስቂያለሽ (ሳቅሽ እንዴት ያምራል?) ወይ ደግሞ ታዝኛለሽ (እኔን!)

ይህንን ደብዳቤ የመፃፍ መብት
እነሆ ላንቺ ስለሆነው ሁሉ ላጫውትሽ ስጀምር፤ በመነሻው ያሰብኩት ነገር ይሄን ደብዳቤ የመፃፍ ሕጋዊ መብት አለኝን? የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህም መነሻዬ አሁን ያለሁበት ሁኔታ ነው፡፡ በመጀመሪያ “ሕገ-መንግስታዊ ስርአቱንና ሕገ-መንግስቱን በሀይል ፣በዛቻና በአድማ ለመናድ በመምከር/ በመናድ” ወንጀል ተጠርጥሬ የታሰርኩ ቢሆንም፤ በታሰርኩ በ23ኛው ቀን ወንጀል ወንጀልን፤ ጥርጣሬ ሌላ ጥርጣሬን እየወለደ የተለያዩ የሽብር ተግባራትን ለመፈፀም ለማሴርና ለማነሳሳት ወንጀል ተጨማሪ ጥርጣሬ በፓሊስ ዘንድ በማሳደሬ የክፋት ልኬ ከፍ ያለ ሲሆን፤ በመጨረሻም ሕገ-መንግስቱን እንደ እያሪኮ ግንብ ለመናድ በመሞከር፤ ሕብረተሰቡን ደግሞ ከሚተነፍሱት የሰላም አየር ለማቆራረጥ ከማሰብ የተለያዩ የሽብር ተግባራትን ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ ተይዟል በሚል ወንጀሎች ተከስሼ በማረፊያ ቤት እገኛለሁ፡፡ ይሄን ሁሉ የምነግርሽ ‹ለ አንቺ› አዲስ ነገር ነው በማለት አይደለም፡፡ ይልቁንስ ያለሁበት የእስር ሁኔታ ደብዳቤ ካንቺ ጋር እንዳልፃፃፍ ይከለክለኛልን? የሚለውን ለማስረዳት በማሰብ ነው፡፡

መቼም አሁን ያለሁበት ሁኔታ ተገቢ ነው ብዬ ባላምንም ‹ ዋስ ጠበቃዬ ነውና› ስለመብቴ ስናገር ያን የፈረደበት ህግ መጥቀሴ አልቀረም፡፡ ታዲያስ በእስር ላይ ያለ ሰው ከወዳጁና በሕይወቱ ጋር ደብዳቤ ሊፃፃፍ ምን ገደብ አለበት? ይላል ስል፤ ስለፌደራል ታራሚዎች አያያዝ የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/1999 በአንቀፅ 18 ላይ “ታራሚዎች (ተጠርጣሪዎች) ከማረሚያ ቤቱ (ከማረፊያ ቤቱ) ውጭ ካሉ ሰዎች ጋር መፃፃፍ ይፈቀድላቸዋል፡፡ ሆኖም ለጥበቃ ስራ ተቃራኒ የሆነ ተግባር እንዳይፈፀም በፅሁፎቹ ላይ ቁጥጥር ይደረጋል” በማለት የኔና አንቺ ደብዳቤ መፃፃፍ በሕግ የተፈቀደ ነገር እንደሆነ ደንግጎልናል፡፡ አሜን! (እንዲያው ይሄ ልጅ አሁንስ ተስፋዬ.. ማነው ? ሕጉ አይደለምን… የሚል የጅል ዘፈኑን አላቆምም እንዴ? ብለሽ እንደማታሾፊብኝ እምነቴ ነው) ጓድ ሌኒን በዛች የፒተርስበርግ እስር ቤት ውስጥ ደብዳቤ መፃፃፍ አትችልም ተብሎ ተከለከለ እርሱ ግን የ Russia Social Democratic Party ን ፕሮግራም መፅሀፍ ውስጥ በየመስመሮቹ መሀል በ Invisible Ink በመፃፍ ታሪክ ስራ፡፡ እነሆ እኔ ግን በትናንት ሌኒኒስቶች (ፋና)፤ በዛሬ አሳሪዎቻችን መልካም ፈቃድ ደብዳቤ የመፃፃፍ ሕጋዊ መብቴ ተከብሮልኝ ይሔው በነጩ ወረቀት ላይ እንደ ሕዳሴው ባቡር እፈነጭበታለሁ፡፡

እንዲህ ሆነልሽ
አበባዬ- አፄ ሀይለስላሴ ከማንኛውም ባለስልጣን በሕይወት ዘመናቸው የበለጠ የቀረቧቸው የነበሩት ከ1934-1948 ድረስ ለ14 ዓመታት በፅህፈት ሚንስትርነት ያገለገሏቸውን ፀሀፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዎርጊስ ወልደ ዮሀንስን እንደ ነበር ነግሬሻለሁ? ወዳጅነትና ፍቅር ያልፋልና ሀይለስላሴና ወልደ ጊዎርጊስ ተጣሉ፡፡ የአፄ ሀይለስላሴ መንግስት መፅሀፍ ፀሀፊ አቶ ዘውዴ ረታ የወልደጊዎርጊስን መጨረሻ ሲተርኩ፡፡

‹‹ ፀሃያማው ሚያዚያ 17/1948 ቀን ለ ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሀንስ እንደ ሌሎቹ ቀናት ብሩህ ሁና ነበር የነጋችው፡፡ ብሩህ ሁና እንደምታመሽም አልተጠራጠሩም ነበር፡፡ ምን ያደርጋል! ያች ክፉ ሰኞ የወልደጊዎርጊስ ከፍተኛ ስልጣን መጨረሻ ሆነች፡፡ በእኩለ ቀን ገደማ ቤተ መንግስት ተጠርተው ከፅህፈት ሚንስተርነታቸው ተነስተው የአሪሲ ጠቅላይግዛት ደረሳቸው››
(መፅሀፉ አጠገቤ ስለሌለ ቃል በቃል አልጠቀስኩም)

ወልደጊዮርጊስ ተሽረው ከቤተ-መንግስት እንዲርቁ የተደረገበት ምክንያት የሀይለስላሴን ወንበር በሰዒረ መንግስት ለመገልበጥ አስበዋል በሚል ምክንያት ነበር፡፡ወልደጊዎርጊስን እዚህ ጋር ማንሳቴ የሚያዚያ 17 ስለት እኔም ጋር በመድረሷ ነው፡፡ ውዴ! የእኔዋን ሚያዚያ 17/2006 ዓ.ም ውሎ እንደ ዘውዴ ረታ ስተርክልሽ ይሔን መሳይ ይሆናል፡፡

‹‹ ፀሃያማዋ ዓርብ ሜያዚያ 17/2006 ዓ.ም አጀማመር እንደ ወትሮው አልነበረም፡፡የጠዋት ትምህርት ክፍለ ጊዜ እንዳይረፍድብኝ እየተቻኮልኩ ወደማስተምርበት (የመጨረሻ ክላስ ነበር) አምቦ ዩንቨርሲቲ ስሄድ፤ ተማሪዎች አዲስ የተዘጋጀውን የአዲስ አበባ ከተማ መሪ እቅድ ‹ሕገ-መንግስታዊ አይደለም በሚል መነሻ የተለያዩ መፈክሮችን እያሰሙ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው ነበር፡፡ ሰልፉ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተካሂዶ እንደተጠናቀቀ በሰልፍ ምክንያት የቀረውን የመጨረሻ ክላስ ሚያዚያ 18/2006 ዓ.ም ለማካሄድ ተማሪዎቼ ጋር ቀጠሮ ይዤ ብለይም ‹ሰው ያቅዳል ፣ እግዜር ይስቃል› እንደሚባለው ሆነና በዛች ሚያዚያ 17/2006 ዓ.ም ማምሻ ላይ እንደ ወልደጊዎርጊስ ወልደ ዮሃንስ ‹የመንግስትን ዙፋን በሕዝባዊ አመፅ ልትነጥቅ አሲረሀል› በሚል ክስ በቁጥጥር ስር እንደዋልኩ የደህንነት ግሪሳዎች (8 ወይም 9 የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አባላት ) አበሰሩኝ፡፡

ነገሩ ብዙም አልገረመኝም፡፡ ትንሽ ያበሳጨኝ አቶ ዘላለም ለጥያቄ ስለምንፈልጎት አዲስ አበባ የፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማእከላዊ) ነገ ጠዋት 3 ሰዓት እንዲገኙ ብለው በስልክ ቢጠሩኝ ‹እሺ ነገ ሶስት ሰአት ላይ ክላስ አለኝ ከክላስ ወደ 9 ሰዓት አካባቢ አመጣለሁ › ብዬ የምቀርበውን ሰው ይሔን ሁሉ ሀይል ከሁለት መኪና ጋር በመመደብ ላከበረኝ መንግስቴ ‹ጉዳት› ባሰብኩ ግዜ ነው፡፡ ላክባሪዬ ውለታ መላሽ ያርገኝ i

ዓለሜ- ደብዳቤዬን እያነበብሽው እንደሆነ ተስፋ አለኝ፡፡ በቁጥጥር ስር ውሏል የምትለው ሀረግ ድሮም ትንሽ ፈገግ ታደርገኝ ነበር፤ አሁን ደሞ እኔን በቁጥጥር ስር ለማዋል ከአዲስ አበባ የመጣው የደህንነት ቡድን መሪ የመሰለኝ እድሜው ትንሽ ገፋ ያለ ሰው አንድ ሶስቴ ስልክ እየደወለ (ለማን ይሆን) ‹በቁጥጥር ስር አውለነዋል› እያለ መልክት ሲያስተላልፍ ስሰማ ፈገግ ማለቴ አልቀረም፡፡ ሀሳቤ ልቤ ፣ ይሄውልሽ ከስራ ቦታዬ ‹ሀገር ሰላም› ሕዝባዊ አመፅ ለመቀስቀስ አስበሃል በሚል ጥርጣሬ በቁጥጥር ስር የዋልኩት እንዲህ እንደገለፅኩት ነበር፡፡ ከሚያዚያ 17/2006 -ሀምሌ 11/2006 ዓ.ም ያሉት 84 ቀናት የተደጋገሙና ሕይወት አልባ በመሆናቸው እንዲሁ ከማሰለችሽ 5 ሁነቶችን ልፃፍልሽና ዘና በይ፡፡ ከሁነቶቹ በፊት ግን ስለ 84 ቀናቱ አጭር መግለጫ ልስጥሽ፡፡

የመጀመሪያዎቹን 75 ቀናት በፌደራል ወንጀል ምርመራ ዘርፍ (ማዕከላዊ) ጥብቅ ጥበቃ ክፍል (Siberia) ውስጥ 5 ቁጥር የተባለ 4 ሜትር በ5 ሜትር የሆነችና 5 ፍራሾችን በምትይዝ ክፍል ውስጥ ከረምኩ፡፡ ክፍሉ የተፈጥሮ ብርሀን በምንም አይነት መንገድ (ቀንን ጨምሮ) የማይገባበት ሲሆን፣ ለ24 ሰዓታት የመብራት ብርሀን ይበራበታል፣ መብራት ሲጠፋ በጄኔሬተር ሀይል ይተካል፡፡ ጄኔሬተሩ ነዳጅ ሲጨርስ ደግሞ ቀንም ሆነ ማታ ጨለማ ነው ባትሪ፣ ሻማ፣ ማንኛውንም አይነት ሰዓት መያዝ አይቻልም፡፡ ጠዋት 12 ላይ ለ10 ደቂቃ ፤ ማታ ከ10 ሰዓት አስከ 12 ሰዓት ለ 10 ደቂቃ ሽንት ቤት ለመጠቀም የክፍላችን በር የሚከፈት ሲሆን፤ በቀን ውስጥ ከ15 – 20 ደቂቃ ለሚሆን ጊዜ ደግሞ ከክፍላችን በየተራ ወጥተን ነፋስ/ፀሀይ እናየለን፡፡ ከዛ ውጭ በቀን ውስጥ ከ23 ለሚበልጠው ሰዓት የክፍሉ በር ዝግ ሲሆን ጮክ ብሎ ማውራትና መዝፈንም ቅጣት ያስከትላል፡፡

ወዳጄ በነዚህ 75 ቀናት ስንት ‹አሸባሪ› ወዳጆችን አፈራሁ መሰለሽ፡፡ መንግስቴ የ 15 እና የ14 ዓመት ልጆችን በአሸባሪነት ጠርጥሮ እንደሚያስርም ለመረዳት ችያለሁ፡፡ አብረውኝ በእስር የነበሩት ወዳጆቼ ጥርጣሬ አጅግ የተለየ ነው፡፡ ከአል-ሸባብ አስከ ኦብነግ እስከ ኦነግ እስከ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ሕዝቦች ነፃ እውጭ ግንባር እስከ አቂዳ(አዲስ የሽብር ቡድን)… ስቃይን መማር ጥሩ ነውና ሁለት ለሚሆኑ ቀናት ብቻዬን በመታሰሬም solitary confinement ን experience ለማድረግ ‹ታድያለሁ›፡፡ በርግጥ ብቻዬን ታስሬ ነበር ከምል ካንቺ ሀሳብ ጋር ታሰርኩ ብል ይቀለኛል፡፡

አምስቱን ሁነቶች ዘንግቼ ስለ ስቃዬ ተንዛዛሁብሽ ይሆን? ለዚህ ተግባሬ በእስረኛ ቋንቋ ‹ተፀፅቻለሁ›፡፡ በቃ ወደ ጉዳዮቹ፡፡ ከዚህ በታች የምገልፃቸው ሁነቶች የ84 ቀናቱ የእስር ወቅት (የምርመራ) ጊዜ ምን እንደሚመስል እንደነበር ያስረዱሻል ብዬ አስባለሁ፡፡ (ሁሉም በእውነት እኔ ላይ የደረሱ ጉዳዮች ናቸው)፡

1. ተማሪዎቼን እንዳላበላሻቸው በማሰብ በቁጥጥር ስር ስላዋለኝ አመሰግናለሁ
ሚያዝያ 17/2006 ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ከምኖርበት አምቦ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ከደህንነቶች ጋር በቤት አውቶሞቢል እየተጓዝኩ ነው፡፡ አንድ ልጅ እግር ደህንነት ጠየቀኝ
‹‹ዘላለም የህግ መምሕር ነህ አይደል..››
እኔ፡ አዎ
ደህንነቱ፡ “ስንት ጠበቆች ዳኞች ማፍራት ሲጠበቅብህ አንተ ‹ልማቱን ካላደናቀፍኩ› ማለትህ እጅግ ያሳዝናል፡፡ ለማንኛውም እንኳን ተማሪዎቹን ሳታበላሻቸው በጊዜ በቁጥጥር ስር ዋልክ፡፡ ኧረ ለመሆኑ ከውጭ ስንት ሽህ ደላዮችን አግኝተሻል? Any way በልማታችን ቀልድ የለም” አለኝ፡፡ (እኔም ባስተማርኩባቸው 4 አመታት ስንት ተማሪዎችን ‹እንዳበላሸሁ › እያሰብኩና ልማታችን በወለደው የአስፋልት መንገድ ፏ ብዬ ከምሽቱ 3፡50 ላይ ማዕከላዊ ከቸች፡፡

2. አላማችሁ ምንድን ነው?
እመቤቴ – መንግስት ሕዝባዊ አመፅ ለመቀስቀስ አሲራችኋል፤ ለዚህም በቂ ማስረጃ አለኝ በማለት ያሰረን ቢሆንም መንግስት ሀሳቡ እውነት ይሆንለት ዘንድ የእኛን ‹አዎ አሲረናል› የሚል መልስ በማባበልና በሀይል ለማግኘት ከመሞከር ውጭ ሌላ ያቀረበው አንዳችም ማስረጃም ሆነ መረጃ(በጠ/ሚንስትሮች ቋንቋ) አልነበረም/የለምም፡፡ ለዚህም ይመስላል በማእከላዊ የቆየሁባቸው ቀናት ምርመራው በሙሉ ‹አላማችሁ ምንድን ነው?› በሚል ሕይወት አልባና አሰልቺ ጥያቄ የተሞላው፡፡ እኔም የዚህ ጥያቄ ሰለባ ሁኜ ከረምኩልሽ፡፡ እንዲህ ላጫውትሽ፣
መርማሪ ፖሊስ (በተደጋጋሚ) – እንደ ዞን 9 አላማችሁ ምንድን ነው?
እኔ፡ ዓላማችን ግልፅ ነው፡፡ ማንም ብሎጋችንን የተመለከተ ሰው በቀላሉ ሊረዳው ይችላል፡፡ባጭሩ የተለያዩ ተረኮችን የሚያስተናግድ እና ሕብረተሰባዊ ተዋጾን የሚያሳድግ ፕሮፋይል ነው፡፡
መርማሪ ፖሊስ፡ እሱ ሽፋን ነው፤ እውነተኛ ዓላማችሁን ተናገር?
እኔ፡ ከዚህ የተለየ አላማ የለንም!

መርማሪ ፖሊሱ እንድንመልስለት የሚፈልገው ‹ከበላይ አካል› ይዞ እንዲመጣ የታዘዘውን መልስ፤ “አላማችን እንደ ጭቃ ተረግጦ፤ እንደ ገል ተቀጥቅጦ የሚገኘውን ጭቁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተጫነበት ቀንበር ነፃ ማውጣት ነው፡፡ ለዚህም መሳካት ሕዝባዊ አመፅ ማደራጀትን እንደ ዋነኛ ዓላማ አድርገን ነው የተቋቋምነው፡፡”
ሲሆን ይህ ደግሞ ከአላማችን ጋር የማይገናኝ መንግስታዊ ፍላጎት በመሆኑ እንዲህ አይነት መልስ ከእኔ ማግኘት እንደማይችል የተረዳው መርማሪ በተደጋጋሚ አስብበት በማለት ይሰናበተኝ ነበር፡

3. ከመርማሪዎች ጋር የነበረኝ ቆይታ
የእኔ ፅጌሬዳ አላማችን እንደ ቡድን ባይጠይቁኝ ኑሮና የግል ዓላማዬን ቢጠይቁኝ አላማዬ ‹አንቺ› እንደሆንሽ ከመናገር ወደኋላ እንደማልል ታውቂያለሽ አይደል? የሆንሽ ‹አሸባሪ› ነገር፡፡ Any way ምርመራዬ ቀጥሎልኛል፡፡ ሁለት መርማሪዎች እየተፈራረቁ ገራሚ ገራሚ ጥያቄዎችን እየጠየቁኝ ነው፡፡ እነሆ ፡
መርማሪ ፖሊስ፡ ከአለም መሪዎች ማን ማንን አግኝተህ ታውቃለህ?
እኔ፡ ማንንም
መርማሪ ፖሊስ፡ እኛ እኮ ያለመረጃ አይደለም እየጠየቅን ያለነው፡፡ ጉድ ሳይመጣብህ ብትናገር ይሻላል፡፡
እኔ፡ እስኪ አስታውሱኝና ምን እንደተነጋገርን ልናገር፡፡ በርግጥ ባለፈው የኔልሰን ማንዴላ ማስታወሻ ፕሮግራም በ አፍሪካ ህብረት በተከበረበት ወቅት ጠ/ሚ ሀይለማርያም ደሳለኝ አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ሌላ የማስታውሰው የለም፡፡
መርማሪ ፖሊስ፡ ህም! እሺ ዘንድሮ ኦባማ ፊት ንግግር ለማድረግ ከተመረጡ 3 ኢትዮጵያውያን አንዱ አንተ አይደለህም? አሜሪካ በ አፍሪካ ጉዳይ ምን አግብቷት ነው፡፡ ወጣት አመራሮች ምናምን እያለች የምታሰለጥነው?
እኔ፡ ‹‹እንዴ ኦባማ ፊት ንግግር ነው ያልከኝ? ድንገት ከታሰርኩ በኋላ ተመርጬ (በማሾፍ ድምፀት) ከሆነ አላውቅም፡፡ወይ በስም መመሳሰል ሊሆን ይችላል፡፡ አሜሪካ በአፍሪካ ጉዳይ ምን አግብቷት ነው? ላልከኝ ግን ወጣቶችን Empower ማድረግ ችግር ያለው አይመስለኝም ፤ ደግሞ በረሀቡም በድርቁም ጊዜ ርዳታ የምታደርገው እኮ አሜሪካ ነች፡፡ ምን አግብቷት ነው የምትረዳው አይባልም መቼም?!››
መርማሪ ፖሊስ፡ አሁን ዘመኑ የልማት ነው፤የምን ረሀብ ነው የምታወራው? በል ተወው፡፡

(‹ፈሪ ውሃ ውስጥ ያልበዋል› ሰምተሻል ውቤ? መንግስቴ ብቻውን እየሮጠም ፍርሃቱና ስጋቱ ብዛቱ፡፡ የሚቆጨኝ ነገር ከዓለም መሪዎች ማን ማንን አግኝተሃል? ‹ስባል› ከሲሪላንካ ፕሬዜዳንት ጋር ተገናኝቼ ወደ ደቡብ አሜሪካ ፔሩ በመጓዝ ማቹፒቹን ጎብኝቻለሁ ብዬ ብናገር ኑሮ፤ ክሳችን ላይ ‹ከሲሪላንካ መንግስት ባገኘው የገንዘብና የመሳሪያ ድጋፍ ወደ ፔሩ በመጓዝ ሕገ-መንግስት እንዴት እንደሚናድ በማቹፒቹ ኮረብታ ስልጠና ወስዶ ተመልሷል፡፡ ለዚህ እንደ ማስረጃ ይሆን ዘንድ ላፕቶፔ ውስጥ የተገኙት ከ300 በላይ የቼጉቬራ ምስሎችና Machu Pichu: The Mecca of Hippies” የሚል ባለ 22 ገጽ ‹ሰነድ› አብሮ ይያዝልኝ ነበር፡፡ ሲያበሳጭ

4. ‹አሸባሪው› ገብረሕይወት ባይከዳኝና ሀገሪቱን በሀራጅ የመሸጥ ጉዳይ
ፍቅር አደከምኩሽ አይደል?! ልጨርስ ስለሆነ ትንሽ ታገሺኝ፡ በዛውም ‹ፍቅር ታጋሽ ነው› የሚለውን Paulian ወንዴነት፤ ‹ፍቅር ታጋሽ ናት› በሚል ማስተካከያ እንድናርመው፡፡ የዚህ የምርመራ ነገር እኮ አላልቅልኝ አለ፡፡ በእስሬ ወቅት ሌላው በተደጋጋሚ እንዳስረዳ ስጨቀጨቅበት የነበረው ጉዳይ ‹ኒዮ-ሊብራልነቴና ልማትና ዲሞክራሲ ጎን ለጎን አብረው ይሄዳሉ ማለቴ ነበር፡፡
መርማሪ ፖሊሶቹ እየተቀያየሩ ስለኢህአዴግ የፖሊሲ ትክክለኛነት ‹ያስረዱኝ› ነበር፡፡ “አንተ ምን ጎደለብኝ ብለህ ነው ነጭ አምላኪ የሆንከው ? ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል ስናይ አንተና ጓደኞችህ አይናችሁ ለምን እንደሚቀላ እስኪ ንገረን ? ይህች አባቶቻችን ‹በደምና በጾም› ያቆዩልንን አገር አንተና ያንተ ትውልድ ግን ውበቷ እና ድንቅነቷ ላስጎመጃቸው ነጮች ለመሸጥ መደራደር ጀመራችሁ….” እያሉ ‹በባንዳነት› ሲከሱኝ ከረሙ፡፡ የሀገሪቱ ውበትና የነጮች በውበቷ መጎምጀት ነገር ሲነሳ ጊዜ ‹አንቺ› ትስቂ ዘንድ የሚከተለውን አንቀፅ አሻግሬ ታደሰ የተባሉ ፀሐፊ ከ 50 ዓመት በፊት ‹እኔና አንተ› ካሉት ጽሁፋቸው ላይ እጠቅስልሻለሁ

“ኢትዮጵያ እጅግ ያማረች፤ የተዋበች ፤የተደነቀች፤ላያት ሁሉ የምታማልል፤የምታዘናጋ…….ናት፡፡ ዓይኗ የብር አሎሎ መለሎ ከአጥቢያ ኮከብ የተፎካከረ….. ነው፤ አገራችን ኢትዮጵያ ፅጌረዳ መስላ የሰኔን ቡቃያ ትመስላለች፡፡ የመስከረም አበባ ሆና በሩቅ ትስባለች፤የመስህቧ ኃይል ማግኔት ምስጋን ይንሳው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ጥርሷ እንደ በረዶ ሆና ለፈገግታ ያህል ትንሽ ከንፈሯን ስትገልፀው እንኳንስ ለሰው ግብዙ መልዓክ ያብዳል፡፡ ኢትዮጵያ ፀጉሯ የሀር ነዶ ነው፤ኢትዮጵያ አጠረች ፤ረዘመች፤ወፈረች፤ብሎ ስለአካሏ መናገር አይቻልም፡፡ እንዲያው ዝም ይሻላል፡፡ በጠቅላላው ኢትዮጵያ ውበቷ ሰነፉን ይገድላል፡፡ ብርቱውን አነሁልሎ ያሳብዳል፡፡ እግዚአብሔር፤ኢትዮጵያን ሲፈጥር በብዙ ተራቋል፤ተጠቧል፤ ውበቷ በሩቅ ይስባል፤ አጥንትም ይሰብራል፤አዕምሮን ይሰውራል፡፡ ይገርማል!” ይላሉ፡፡

ምንም እንኳን ውበት እንደተመልካቹ ነው ቢባልም፤ መርማሪዎቹ በዚህ ዓይነት Vulgar Natioanlism ሰክረው እኔና የእኔ ትውልድ ሀገሪቱን ‹በውበቷ ለሰከሩ› ነጮች ልንሸጣት እንደተዋዋልን እየነገሩኝ ነው፡፡ ይገርማል! ዲሞክራሲን ከልማት እኩል ማስኬድ ነውር የለበትም፤ ተገቢም ነው ማለት እንደ አገር ሽያጭ ውል የሚቆጠርበት ብሎም ‹ሩቅ አስባ ሩቅ ለማደር እየተጋች ያለችን አገር› መንገድ ላይ በጠረባ ለመጣል የተደረገ ሙከራ ተደርጎ የሚወለድባትና ‹አሸባሪ› የምንሰኝባት፣ ‹ለፈገግታ ያህል ትንሽ ከንፈሯን ስትገልጠው እንኳን ሰውን ግብዙን መልዓክ የምታሳብደው ኢትዮጵያ!

ሊቁ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ‹ልማትን ሲተች› “እውቀት በሌለው ሕዝብ አገር መንገድና የምድር ባቡር ቢሰራ ሕዝቡ እንዲደኸይ ያፋጥናል እንጂ አይጠቅመውም፡፡ ጥቅሙ ከርሱ ጋር የሚገበያዩ አዋቂ ሕዝቦች ነው” በማለት ‹ልማት ብቻውን ዋጋ የለውም› ሲል ይበይናል፡፡ ገብረሕይወት የእኛው ትውልድ አባል ቢሆን ኖሮ “የኢኮኖሚ እድገቱን በመካድ፤ ሕዝቡ በአዕምሮ መናወጥ ምክንያት የዘረጋነውን የባቡር ሀዲድ ፈነቃቅሎ እንዲጥልና ሌሎች የሽብር ተግባራትን እንዲፈፀም በማነሳሳት ‹ወንጀል›” መመርመሩና መከሰሱ አይቀሬ ነበር፡፡
ውዴ! ያን ‹አሸባሪ› ሳቅሽን ሳስብ በፀረ-ሽብር ሕጉ መሠረት ጉዳይሽ ሊታይ ይችላል የሚል ስጋቴ የበዛ ነው፡

5. ናፍቆቴ ሆይ!
እንዲያው ለዚህ 84 ቀናት ውስጥ የሆንኩትን ሁሉ እንዳልፅፍልሽ እንዳትሰለችብኝ ፈራሁ፡፡ እያንዳንዱን ሁነት በ Diary መልክ ከትቤ እንዳልክልሽ በነዛ ቀናት ውስጥ ብዕርም ሆነ ነጭ ወረቀት ይዞ መገኘት ‹ከፍ ብሎ አንገትን፣ ዝቅ ብሎ ባትን› ባያስቆርጥም ዛቻና ዱላን ማስከተሉ አይቀርም ነበርና ልከትብ አልቻልኩም፡፡ እንዲሁ በደፈናው ግን አንዳንድ ጉዳዮችን ብዘረዝርልሽ፡
በነዛ ክፉ ቀናት ከምሽቱ 12 ሰዓት እንቅልፍ መተኛትን ለመድኩ፡፡ ይሔም ነገር መልካም እንደሆነ አየሁ፡፡ ምክንያቱም ሌሊት ከእንቅልፍ ተቀስቅሰው ራቁታቸውን ሲደበደቡ አድረው ከ 3 እና 4 ሰዓታት ቆይታ በኋላ በነፍስ ወደ መኝታ ክፍላችን የሚመጡ የእስር ጓደኞቼን (Cellmates) ስቃይና ሰቆቃ ላለመስማት፡፡
በ2004 ዓ.ም የፌዴራል ፖሊስ ‘Cyber crime Laboratory’ ተቋቁሟል መባሉን ሰምቼ ‹እንግዲህ cyber criminal ሁሉ የት ትገቢ? አለቀልሽ!› ብዬ ነበር፡፡ በጊዜ ቀጠሮ ጊዜ እንደተረዳሁት ደግሞ ‹ያለችን አንዲት ኮምፒውተር ናት የእነዚህ ልጆች ዳታ በአንድ ኮምፒውተር መርምረን መጨረስ ስላልቻልን የጊዜ ቀጠሮ ይሰጠን› ሲባል ነው፡፡ አረ እንዲያውም ‹እስኪ Anti-virus ካለህ ኮምፒውተሬ ላይ ጫንልኝ› ተብዩ ሁሉ ነበር፡፡ ‹ለሽብር ተግባራት› መመርመሪያ ያልሆነ ‘Cyber crime laboratory’ ለመች ሊሆን ነው?
አንድ ቀኑንና ወሩን በማላስታውሰው ቀን አንድ ጎልማሳ የታሰርንበትን ክፍል አስከፍተው ገቡና እያንዳንዳችን መጠየቅ ጀመሩ፡
- ‹አንተ ከየት ነው የመጣኸው?› (አንድ ተማሪ ወዳጄን)
- ‹ከሀሮማያ ዩኒቨርስቲ›
- ‹አሀ እናንተ ናችኋ…..›
****
- ‹አንተኛውስ ከየት ነው የመጣኸው?!›
- ‹ከወለጋ ዩኒቨርስቲ›
- ‹አሁን ኦሮሚያ ብትለማ ምን የሚያስከፋ ነገር አለው?!….›
*****
- ‹አንተስ ከየት ነው የመጣኸው› (እኔን ነው)
- ‹ከአምቦ ዩኒቨርስቲ›
- ‹ሕዝቡን እርስ በርስ አጋጭታችሁ ከተማዋን በደም ያጠባችኋት እናንተ….›
- ‹አረ እኔ ከግጭቱ በፊት ነው የታሰርኩት›
- ‹በእውነት ነው የምልክ እድለኛ ነህ፡፡ የኦሮሚያን ልማት ተቃወመ ተብለህ በታሪክ አለመስፈርህ በጣም እድለኛ አድርጎሀል፡፡›
(ለመሳቅ ሁላችንም የጎልማሳውን ከክፍል መውጣት እየተጠባበቅን እኮ ነው ውዴ) – ሁሉ ቧልት የሆነበት ሀገር!

በነዚህ ሁሉ የጉድ ቀናት ለምን እንደታሰርኩ ትክክለኛውን ምክንያት የሚነግረኝ አካል ፍለጋ ሁሌም አስብ ነበር፡፡ መታሰሬ ግን አያስገርመኝም፤ አያስከፋኝም! ደስታን በሔድኩበት ሁሉ እፈልጋለሁ፤ የእድል ነገር ሆኖ ደስታም ከእኔ አይርቅም፡፡ ፍቅሬ ለረጅም ዘመናት ‹የሰው የመኖር አላማ ማወቅ ነው› የሚለውን Aristotlian (አሪስቶትሊያን) አስተምህሮ በልቤ ይዤ እኖር ነበር፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ‹የመኖር ዓላማ መደሰት ነው› የሚለው አስተምህሮ በአርስቶትሉ ‹የማወቅ ዓላማ› ደባልቄ ይሔው እየተደሰትኩልሽና እያወቅሁልሽ እገኛለሁ፡፡ ‹አንች› የደስታዬ ምንጭ፡

‘‘Thanks to you….For you exist’
Clézio

ስለክሴና ስለተስፋዬ ሌላ ደብዳቤ እፅፍልሻለሁ፡፡
P.S አሳሪዬ ሆይ ልብ ይስጥህ!
ያንችው ዘላለም
ከብዙ ፍቅር ጋር!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>