መንትዮችን ማየት በአገራችንም ይሁን በተቀረው ዓለም ክፍል የተለመደ ነው፡፡ ይሁንና ከተለመደው በተለየ የቆዳ ቀለም እና አፈጣጠር ዓለምን የሚቀላቀሉ መንትዮች የበርካቶችን ትኩረት ያገኛሉ፣ መነጋገሪያም ይሆናሉ፡፡ ሳይንቲስቶችና የዘርፉ ባለሙያዎችም ይህን የተፈጥሮ ምስጢር ለመፍታት በርካታ ጥናቶችን ያደርጋሉ፤ እንቆቅልሹንም ለመፍታት ይጥራሉ፡፡ እነዚህ አስገራሚ ክስተቶች የሚታዩበትን የመንትዮች ዓለም የተለያዩ ክስተቶችን ከባለሞያዎች አስተያየትና የሳይንስ ሰዎች ትንታኔ ጋር አጣምሮ ተከታዩ ዳሰሳችን ቅኝቱን ያሳያችኋል፡፡
እ.ኤ.አ ሚያዚያ 2005 ላይ ጥንዶቹ ብሪታኒያውያን ካይሊ ሆድሰን ከባለቤቷ ሬማ ጋር ወደ ሆስፒታል በምጥ ምክንያት ሲያመሩ ካይሊ በሰላም መገላገሏን እንጂ ስለወለደችው ልጅ የምታስብበት ብርታት አልነበራትም፡፡ ካይሊ የተገላገለችው መንታ ልጆችን መሆኑ ተገልፆላት እንድታቅፋቸው ሲሰጧት ግን ጉልበቷን አሰባስባ በግርምት ነበር የተቀበለቻቸው፡፡ እርሷ ብቻ ሳትሆን መላው ዓለም በዜናው ተገርሞ ነበር፡፡ የተወልዱት ሁለት ልጆች ሴት ህፃናት ሲሆኑ አንደኛዋ ጥቁር መልክ ያላት፣ ሁለተኛዋ ደግሞ ነጭ ነበረች፡፡
የህፃናቱ ወላጆች ራሳቸው ከነጭና ጥቁር ወላጆች የተገኙ በመሆናቸው መልካቸው የክልስ እና በጥቁር እና ነጭ የሚመደብ የነበረ ቢሆንም የሚወልዷቸው ህፃናት እንዲህ ሙሉ ለሙሉ የተለያየ የቆዳ ቀለም ይኖራቸዋል ብለው አስበው አያውቁም፡፡ በወቅቱ ጋርዲያን ለተሰኘው የእንግሊዝ ጋዜጣ ሀሳቧን ያካፈለችው ካይሊ ‹‹የልጆቼን ቀለም ስመለከት በጣም ነበር የደነገጥኩት፡፡ ነገር ግን በጣም የሚያማምሩ ሴት ህፃናትን ማግኘቴ ሁሉንም ወዲያው አስረስቶኛል፤ ደስተኛም ሆኛለሁ›› ብላ ነበር፡፡
ክስተቱን አስመልክቶ ባለሙያዎች ሳይንሳዊ ትንታኔን ሰጥተውበት ነበር፡፡ አንዲት ሴት የተቀላቀለ ዝርያ ካላት በእንቁላሎቹ ጥቁርም ሆነ ነጭ የቆዳ ቀለምን የሚያስገኙ ጂኖችን ቀላቅላ ትይዛለች፡፡ በተመሳሳይ ከነጭና ጥቁር ወላጆች የተወለደ ወንድ እንዲሁ በዘር ፈሳሹ ውስጥ ሁለቱንም የያዙ ጂኖች ይኖሩታል፡፡ የዘር ፈሳሹ ውስጥ የያዛቸው ጂኖች በሙሉ ነጭ ቢሆኑ እና ተመሳሳይ ጂኖች ያሉት እንቁላል ጋር ቢገናኙ አለዚያም ጥቁር ቀለምን ኮድ የሚያደርግ ስፐርም ከተመሳሳይ እንቁላል ጋር ቢገናኝ ቀለማቸው ሙሉ በሙሉ የተለየ የጥቁር እና ነጭ ልጆች በመንታነት ይወለዳሉ፡፡ ይህ የመፈጠር ዕድል ከሚሊዮን አንድ ጊዜ ያህል ነው፡፡ በእነ ካይሊ የተከሰተውም ይህ ነበር፡፡
ይህን መሰል አስገራሚ የመንትዮች ታሪኮች አልፎ አልፎ መሰማታቸው አልቀረም፡፡ ቀደም ሲል የነበረው አይነት ታሪክ ያላቸው ሰዎችም ጥቂት አይደሉም፡፡ እዚያው እንግሊዝ ውስጥ ከሰባት ዓመት በፊት መንትዮችን የወለዱ ቅልቅል ዝርያ የነበራቸው ወላጆች ለሁለተኛ ጊዜ ሲወልዱም አንድ ጥቁርና አንድ ነጭ ህፃናትን አግኝተዋል፡፡ በድምሩም የሁለት ጥቁር እና ሁለት ነጭ ልጆች ወላጆች ሆነዋል፡፡ ዲን ዱራንት የልጆቹ አባት ሲሆን ኦሊሳን ስፑነር ደግሞ እናቲቱ ነች፡፡ ጊዜው እ.ኤ.አ ሐምሌ 2008 ላይ ነበር፡፡ ‹‹በአምላክ ጥበብ ተደንቀናል ብሏል›› አባትየው ዲን ዱራንት፡፡ ከጀርመናዊ አባት እና ጋናዊት እናት እ.ኤ.አ 2008 እንዲሁ አንድ ነጭ እና አንድ ጥቁር ተወልደዋል፡፡ በዚህ መሰል አስገራሚ ታሪክ የታጀበው የመንትዮች ዓለም ላይ ሳይንስ የራሱን ትንተና ይሰጣል፡፡
አስገራሚው የመንትዮች ዓለም
መንትያ የሚለውን ቃል ባለሞያዎቹ ሲፈቱት በአንድ እርግዝና የተወለዱ ከአንድ በላይ ልጆች ይሉታል፡፡ ጥንቅር ይዘው በመልክም ሳይመሳሰሉ የሚወለዱ መንትዮች ‹‹ፍራተርናል›› የሚባሉት ሲሆን ሁሉም ነገራቸው አንድ አይነት ሆነው የሚወለዱት ደግሞ ‹‹አይደንቲካል›› ይሰኛሉ፡፡ ፍራተርናል የሚባሉት መንትያዎች የሚፈጠሩት የሴቷ ሁለት እንቁላሎች በሁለት ስፐርም ህዋሳት በተናጥል ሲሰበሩ እና ሲዋሃዱ ነው፡፡ በዚህ መልክ የሚፈጠሩ መንትዮች የዘረ መል ጥንቅራቸው የመመሳሰል ዕድሉ ዝቅተኛ ሲሆን በተለይ ዕድሜያቸው ከ35 በላይ በሆናቸው እናቶች ይህ አይነት መንትዮችን የመውለድ አጋጣሚያቸው ከፍ ያለ መሆኑን ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡
ሁሉ ነገራቸው አንድ አይነት ሆነው የሚፀነሱ እና የሚወለዱ መንትዮች የሚፀነሱት አንድ እንቁላል አንድ ውሁድ ሲፈጥርና ይኸው ውህድ ወደ ሁለት ተከፍሎ ሁለት ፅንስ ሲሆን ነው፡፡ የሚወለዱት መንትያ ህፃናት ‹‹አይደንቲካል ትዊንስ›› የሚባሉት ይሆናሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ10 ሚሊዮን የሚበልጡ በዚህ መሰሉ አፈጣጠር የመጡ መንትዮች እንዳሉ አንዳንድ ግምቶች ያሳያሉ፡፡ በየዓመቱ ከሚወለዱ 1 ሺ ህፃናት መካከል 3 የሚደርሱት አንድ አይነት መንትዮች ይሆናሉ፡፡ ታዲያ መንትዮች ሲወለዱ ሁል ጊዜም ተመሳስለው አሊያም አንድ አይነት ሆነው ይወለዳሉ ማለት አይደለም፡፡ ከተለመደው ወጣ ያለ አፈጣጠር ያላቸው በቁጥርም በአይነትም የሚደንቁ ውልደቶች በየጊዜው ይሰማሉ፡፡ ከሁለት እስከ አስራ ሁለት ህፃናትን አንድ ጊዜ መውለድ፣ አፈጣጠራቸው አንዱ ከአንድ የተጣበቀ አሊያም የዘረመል ጥንቅሩን ካደገ በኋላ እንደገና ከእናቱ አሊያም ከፅንሱ የሚወስድበትን ሁኔታ ሳይንቲስቶች ተመልክተው ትንታኔ ይሰጡባቸዋል፡፡
ተጣብቀው የሚወለዱ መንትዮች
የሁለቱ ወላጆች ዘር ማስተላለፊያ የሆኑት እንቁላልና ስፐርም ተቀላቅለው ውህድን ፈጥረው ወደ ሁለት ፅንስነት (መንትያነት) ለመለወጥ በአማካይ ፅንሱ ከተፈጠረ ጀምሮ 8 ቀናትን ይፈልጋሉ፡፡ ይህ 99 ከመቶ የሚሆኑት ላይ በመደበኛነት የሚፈጠር ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ፅንሱ ለሁለት ለመክፈል ከ8 ቀናት በላይ ከወሰደ ግን ፅንሶቹ ተጣብቀው የማደግና የመወለድ አጋጣሚ ዕጣቸው ይሆናል፡፡ የተጣበቁ ፅንሶች አካላትን ይጋራሉ፣ ተያያዥ ችግሮች ሞቶ እስከመወለድ በሚደርስ አደጋ የመከሰት ዕድሉ ከፍ ያለ መሆኑንም ስፔሻሊስቶቹ ይናገራሉ፡፡ ይህን መሰል እርግዝና ከ50,000 ሴቶች በአንዷ ላይ እንደሚከሰት ግምታቸውን የሚያስቀምጡ ባለሞያዎች እነዚህ ተጣብቀው የሚወለዱ ህፃናት እንደ ጭንቅላት፣ ልብ እና ጉብት የመሰሉ አካላትን የሚጋራ ሲሆን እነርሱን መለያየቱ ከባድ ፈተና ይሆናል ባይ ናቸው፡፡ ‹‹የሁለቱንም ህፃናት ነፍስ ማትረፍም ትልቅ ጥበብ ብቻ ሳይሆን እድለኛ መሆንንም ይጠይቃል›› ይላሉ ታዋቂው የአሜሪካ ተቋም ማዮ ክሊኒክ ባለሙያ ዶ/ር ሉሲ ጋርፊልድ፡፡ ‹‹ስኬታማ መንትዮችን የመነጣጠል ቀዶ ጥገና ሲካሄድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የሚቀባበሉትም ለዚህ ነው››
ሌሎች አስገራሚ አፈጣጠሮች ኪመሪዚም፣ ፓራሲቲዝም…
ሌላው በመንትያነት በሚያድጉ ፅንሶች መሀል ከሚከሰቱ ለየት ያሉ አፈጣጠሮች የሚመደበው ከአካላቶቻቸው መካከል አንድ ወይም ሌላውን አብሮት ካለው መንትያ ፅንስ አሊያም ከእናትየው ወስደው በመቀላቀል ለየት ያለ ህብር ያለው የቆዳ ቀለም የሚያበጁ፣ ፆታቸው ወንድ ወይም ሴት መሆኑን ቁርጥ አድርጎ ለመለየት የሚያስቸግር ብልት ያላቸው እና መሰል አፈጣጠርን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በሳይንሱ አጠራር ይህ ክስተት ኪመሪዝም ተብሎ ይጠራል፡፡
አንድ ፅንስ የዕድገት ዘመኑን ሲጀምር አንዳንድ ጊዜ በመንታነት ሊጀምር ይችላል፡፡ ነገር ግን ሌሎቹ ተስፋ ያላቸው የእንቁላል እና ስፐርም ውህዶች ሲሞቱ አንድ ብቻ ትግሉን አሸንፎ አንድ ፅንስ ሆኖ ልጅ ሆኖ ይወለዳል፡፡ እንዲያውም ተመራማሪዎች የሚገምቱት በአንድ ወሲብ ግንኙነት እስከ 8 የሚደርሱ ፅንሶች የመፈጠር ዕድል እንዳላቸው ነው፡፡ ነገር ግን ሙሉ ጊዜውን ጨርሶ ህይወት ዘርቶ የሚወለደው አንድ ብቻ ይሆናል ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ሌሎቹ የተደመሩ ፅንሶች ሲሞቱ አንድ በርትቶ ህይወት የሚሆንበትን ይህን አጋጣሚም ‹‹ቫኒሺንግ ትዊን ሲንድሮም›› ሲሉ ይጠሩታል፡፡
አንዱ ፅንስ ለሌላኛው እየመገበ ተጎድቶ የሚሞትበት፣ አንዱ መንትያ አስርዷት ሁለተኛውን አምጣ ጤነኛ ልጅ እናት የምትወልድበት እና ሌሎችም ከመንትያ ፅንስ እና ልጆች ጋር የተያያዙ ክስተቶች የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስቶችን እና ተመራማሪዎችን ትኩረት የሚይዙና ልዩ ምርምሮችም የሚካሄድባቸው አስገራሚ የተፈጥሮ ሁነቶች መሆናቸው በተመራማሪዎቹ ይገለፃል፡፡
ተጣብቀው የተወለዱት ኢትዮጵያውያን
አገራችን ውስጥ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የተመዘገበ ታሪክን የሆስፒታሉ ባለሙያዎች እ.ኤ.አ 2005 ላይ በኢትዮጵያ ሜዲካል ጆርናል ላይ አሳትመው አቅርበውት ነበር፡፡ ከ25 ዓመት እናት የተወለዱት መንትዮች ደረታቸው ላይ ተጣብቀው የተወለዱ ሲሆን ይህም አጥኚዎቹ እንዳሉት በአገሪቱ የገጠመው ለሁለተኛ ጊዜ ነበር፡፡ በቀዶ ጥገና መንትዮቹ ተለያይተዋል፡፡ ከጥቁር እና ነጭ መንትዮቹ አንስቶ ተጣብቀው እስከሚወለዱት እንዲሁም ምግብ ጥገኛ ሆነው እስከሚጠፋፉት ድረስ የመንትዮች ታሪክ አስገራሚ ነው፡፡ ይህ ተወልደውም ይቀጥላል…
የመንትዮች ቆጠራ
እ.ኤ.አ 2006 ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት በዓለም አቀፍ ደረጃ 125 ሚሊዮን የሚደርሱ መንትዮች በህይወት እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ ይህም ከአጠቃላዩ የዓለም ህዝብ 1.9 ከመቶ መያዛቸውን ያመለክታል፡፡ የመንትዮች እርግዝና ከመደበኛው እርግዝና ቢያንስ በ3 ሳምንት ቀድመው ልጆቹ እንዲወለዱ ያስገድዳል፡፡ ከጊዜያቸው ቀድመው መወለዳቸው የጤና እክልን የማስከተል ዕድል ስላለው ጥብቅ የህክምና ክትትልን ይሻሉ፡፡
ናይጄሪያ የመንትዮች መናኸሪያ
በዓለም ላይ ከሚወለዱ 90 ህፃናት አንዱ በመንትያነት የተወለደ እንደሚሆን የመንግስታቱ ድርጅት ፖፑሌሽ ቢሮ ይገምታል፡፡ በተለይ ከፍተኛውን የመንትዮች ቁጥር በማስመዝገብ የምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ናይጄሪያ ቀዳሚ ናት፡፡ ዮሩባ በምትባለው የናይጄሪያ ግዛት ከ1,000 ህፃናት መካከል 45 የሚወለዱት በመንትያነት ነው፡፡ አንዳንድ ተመራማሪዎች በናይጄሪያ ዩሩባ ግዛት መንትዮች የበረከቱበትን ምክንያት በግዛቲቱ ሰዎች ከሚበሉት አንድ ጣፋጭ ተክል ጋር አያይዘውታል፡፡ ዲዮስኮሪያ ሮቱንዳታ የተሰኘው ይህ ጣፋጭ በውስጡ ፋይቶ ኤስትሮጅን የሚባል ንጥረ ነገር ሴቶች ከእንቁላል ማምረቻቸው ሁለቱም ጎን እንቁላል እንዲያመርቱ እና ሁለት ፅንስ እንዲፈጠር አድርጓል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ናይጄሪያን ተከትላ ሊንሃ ለአፔድሮ የተሰኘችው የብራዚል አነስተኛ መንደር ትጠቀሳለች፡፡ በዚህች መንደር ከሚፈጠሩ እርግዝናዎች 10 ከመቶ የሚሆኑት መንትዮችን ይወልዳሉ፡፡
መንትዮችን መውለድ ስንት ሰዓት ይፈጃል?
መንትዮችን ማርገዝ ብቻ ሳይሆን መውለድም ታዲያ ቀላል አይሆንም፡፡ ምጥ የተለመደ የነፍሰጡሮች ፈተና መሆኑን የሚያውቁት ባለሙያዎች ግን በዚህ ሳያበቁ ‹‹መንትዮችን መውለድ ስንት ደቂቃ ይፈጃል?›› ሲሉ ጥናት አድርገው በአንድ የጥናት መፅሔት ላይ ውጤታቸውን አሳትመው ነበር፡፡ በተለይ በጀርመን የተካሄደው 15 ዓመታትን የፈጀ ጥናት 8,220 ወላጆች መንትያ ልጆች ሲወልዱ የፈጀባቸውን ሰዓት መዝግቦ ተንትኗል፡፡ በዚህ ጥናት እንደተመለከተው መንትዮችን የምትወልድ እናት በአማካይ ለ13 ደቂቃ አምጣለች፡፡
75 ከመቶ የሚሆኑት በ15 ደቂቃ ውስጥ ዱብ ሲያደርጉ 23 ከመቶዎቹ ከ15 ደቂቃ እስከ 1 ሰዓት ወስዶባቸዋል፡፡ 2 ከመቶዎቹ ደግሞ ከአንድ ሰዓት በላይ አምጠው መንትያዎቻቸውን ተገላግለዋል፡፡
መንትዮችን መፀነስ ብቻ ሳይሆን መውለድም ፈተና መሆኑን ያሳዩት ጥናቶች አንዲት ሴት መንትያ ልትወልድ የምትችልባቸውን እድሎች እና አጋጣሚዎች ከታሪካዊ ዳራዎችና ሳይንሳዊ ትንታኔዎች በመነሳት ግምት አስቀምጠዋል፡፡ እነዚህ መንታ በመውለድ እድል ውስጥ ይከታሉ ከተባሉት ምክንያቶች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
- የምዕራብ አፍሪካ በተለይ የዮሩባ ዘር ካለባት
- ዕድሜዋ ከ30-40 ከሆነ
- በአካል የበለጠ ቁመት እና ክብደት ካላት
- ከዚህ ቀድሞ በተደጋጋሚ አርግዛ የምታውቅ ከሆነ
- መፀነስ የሚያስችሉ ሕክምናዎችን የምትወስድ ከሆነ
እርስዎ ከላይ የተዘረዘሩት ምድብ ምክንያቶች ውስጥ ገብተው ይሆን? አምላክ የእርስዎ በረከት ይሁን ካለው ፀጋውን መቀበል እና መደሰት እንጂ ምን ያደርጋሉ?