በቶኩማ አሸናፊ
አቅጣጫንና ግብን አለማወቅ ልዩነትን፡ መከፋፈልን ፡
አለመተማመንንይፈጥራል:: እርስዎስ የትነው ያሉት ?
እንደ አንድ ዜጋ በሃገራችን ጉዳይ ላይ በሚነሱ ማንኛውም ጥያቄዎች ላይ ነገሮችን በችላ ባይነት ለማለፍ ብዙ ጊዜ አልሞክርም ። ያም በመሆኑ ያቅሜን ያህል የማበረክተው ድርሻ ካለ ቀዳዳዋን ለመጠቀም እሞክራለሁ። በተለይ በአሁኑ ጊዜ በሃገራችን ጉዳይ ላይ በርካታ “ምሁራን” በየቀኑ የመያወጡአቸውን የተለያዩ ጽሁፎች አነብና ፡ በየቀኑ የሃገሬ ልጆች በየፓልቶኮቹ የሚያደርጉትን ውይይት ክርክር ስድብ እሰማና ማታ ጋደም ብዬ ሳብሰለስለው አንዱም ነገር ውስጤ ሳይቀር ሲሰማኝ በመብሰልሰል ብቻ እኖራለሁ።
ዛሬ በሃገራችን ያለውን ችግር የምንገዘብበት የግንዛበቤ መነጽራችን እጅግ የተለያየ ከመሆኑም በላይ ለመፍትሄውም ዝብርቅርነት ዋነኛውን አስተዋጽኦ አድርጎኦል ብዬ ስለምገምት እነሆ ወገኞቼ በተለይም በሃገራችን ጉዳይ ላይ ያገባናል የሚሉ ሁሉ ቀጥዬ በማቀርበው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በሚኖረን አቅዋም ልዩነቶቻችን ሊጠቡ ወይም ሊሰፉ ልንግባባ ወይም ላንግባባ በጋራ ለሃገር እንድንቆም ወይም ያለመፍትሄ ስንረጋገም እድሜያችንን እንድንፈጅ እንገደዳለን ብዬ አምናለሁ።
በወያኔ/ ኢህአዴግ ላይ በሚኖር አመለካከት ላይ ያለ ልዩነት/ተቃዋሚዎች
የአመለካከት አንድ ስብስቦች
ወያኔ/ኢሃዴግ ፋሸስታዊ መንግስት ነው
ወያኔ/ኢሃዴግ ኢትዮጰያን በኮሎኒ የያዘ መንግስት ነው
ወያኔ አፓርታይድ መንግስት ነው
ወያኔ የሽፍቶች ቡድን እንጂ መንግስት አይደለም
ወያኔ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ መንግስት ነው አላማውም ኢትዮጵያን ማፈራረስ ነው።
በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የአንድ ዘር የትግሬን በላይነት የሚጠብቅ መንግስት ነው
ወያኔ ሁሉም ነው
*የአመለካከት ሁለትንም ያጠቃልላል
ከላይ ለሚጠቀሱት የወያኔ/ኢሃዴግ መገለጫዎች የሚቀርቡት መፍትሄዎች
ኢትዮጵያውያን ድርጂቶች እንደግንቦት 7 አርበኞች ግንባር ተደራጅተው ታጥቀው ጦር መስርተው በሃገር ውስጥ ቤዝ ፈጥረው ትጥቅ ትግል መጀመር አለባቸው።
ስር ነቀል ለውጥ እንጅ ጥገናዊ ለውጥ አያስፈልግም
ኢትዮጰያዊ አጅንዳ ባይኖራውቸም ወያኔን እስካስወገዱ ድረስ ከሌሎች ሃይሎች ጋር ለምሳሌ እንደኦነግ እንደኦብነግ ከዚያም ከሻቢያም ጋር ህብረት ፈጥሮ ትጥቅ ትግል መካሄድ አለበት
ሁለገብ ትግል መጠናከር አለበት። ሰላማዊ ትግሉ በሃገር ቤት ትጥቅ ትግሉ ከውጭ መፋፋም አለበት።
ሰላማዊ ትግሉ ከግንቦት ምርጫ አሁንም ከ2002 ምርጫ ስላበቃለት ትጥቅ ትግሉ ብቻ ነው መፍትሄ የሚሆነው።
ትጥቅ ትግሉ በሃገር ቤት የራሱን የህቡእ ማደራጀት ስራ ሰርቶ ህዝባዊ አመጽ ማስነሳት አለበት።
ወያኔ በማንኛውም አይነት የትጥቅ ትግል ከተሸነፈ በሁዋላ የሽግግር መንግስት ተመስርቶ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ይነጋገርበታል።- ሰላማዊ ትግሉ እያስመዝገበ ያለው ውጤት ወያኔን ከስልጣን የሚያወርድ ብቃት ያለው አይደለም። – በሰላማዊ ትግሉ መጉዋዝ ወያኔን እድሜውን ማራዘም ነው ። እንዲዬወም አንዳንዶቹ በብሄረ ሰብ የተደራጁ ድርጅቶች እራሳቸው የወያኔ ተቀጥላዎች ስለሆኑ ሰላማዊ ትግሉ እነሱንም ማቀፉ ትግሉን ይጎዳዋል።
* በአመለካከት አንድ በአካሄድ ልዩነቶች አሉ። ከዚህ ውሰጥ ዋነኛው ለምሳሌ በኢህአፓና ግንቦት ሰባት መካከል ወያኔን ለማስወገድ የትግል አጋሮችን ወይም ህብረትን በሚመለከት
የአመለካከት ሁለት ስብስቦች
ወያኔ/ኢሃዴግ በብሄረ ሰብ መብት ስም ህዝብን በጎሳና በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ክልል ከፋፍሎአል። ስለዚህም ዘረኝነትን አስፋፍቶአል
ወያኔ ኢህአዴግ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሰጠና እየሰጠም ያለ መንግስት ነው ለምሳሌ የአሰብ ጉዳይ የሱዳን ዳር ድንበር ጉዳይ ላይ በወሰዳቸው እርምጃዎች ይገለጻል።
መንግስቱ ኢሃዴግ ይባል እንጂ የጥቂት አምባገነኖች ቡድን መንግስት ነው
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ያዳከመ መንግስት ነው
ዲሞክራሲን ፍትህን የመናገር የመጻፍ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብትን የግለሰብ ነዻነትን እያፈነ ያለ አምባገነን መንግስት ነው
ኢሃዴግ ዋናው ችግሩ እርሱ ያረቀቀውንና ህዝብ ያጸደቀውን ህገ መንግስት የጣሰ የሚጥስ አምባገነን መንግስት በመሆኑ ህገ መንግስቱ ከተከበረ ሊለወጥ የሚችል መንግስት ነው
ለተጠቀሱት መገለጫዎች የሚቀርቡ መፍትሄዎች
- በወያኔ የተለያዩ ጥፋቶች ቢኖሩም ጥፋቶቹን ለማስተካከል በህዝብ ውሳኔ ላይ የቆመ መንግስት ያስፈልጋል ።ስለዚህ ይህንን መንግስት ለማምጣት የሚያስችሉ የሰላማዊ ትግል ስልቶች ሁሉ መፈተሽ አለባቸው።
- ወያኔ ኢሃዴግ እነዚህ ባህርያት ቢኖሩትም ለሰላማዊ ትግል በሩን ፈጽሞ ያልዘጋ መንግስት በመሆኑ ትጥቅ ሊመዘዝበት አይገባም ። ወያኔ ኢሃዴግን የማስወገድ ሳይሆን የማሳተፍ ፖለቲካ እንደድርጅት ህልውናው ሊኖር ይገባል ኢሃዴግን የሚያጠፋ ፖለቲካ ሳይሆን በምርጫ የሚያስወግድ ፖለቲካ መሆን አለበት
- በሃገር ውሰጥ ሰላማዊ ትግል የማይታገዝ የትጥቅ ትግል ሕዘባዊ መሰረት የሌለውና ኢትዮፕያንም የበለጠ አደጋ ውስጥ የሚከት አካሄድ ነው።
_ የፈጀውን ጊዜ ቢፈጅም ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ በጠመንጃ ስልጣን መያዝን ማስወገድ አለበት ። በጠመንጃ የሚመጣ ስልጣን በህዝብ ንብረትና ህይወት ላይ ከሚያስከትለው ውድመት ባሻገር ዘለቄታ ለውጥ አያመጣም።
አመጽ አይመረጥም ። ይሁን እንጂ ህዝባዊ አመጽ ሊነሳ ይችላል ። ለዚህ ተጠያቂው ወያኔ ኢሃዴግ ነው የሚሆነው
ሰላማዊ ትግሉ የሚያስፈልገው ወያኔ ኢሃደግንም ጭምር የሚያሳትፍ የፖለቲካ ስርአት ለመዘርጋት መሆን አለበት
ብሄራዊ መግባባትን መሰረት ያደረገ ብሄራዊ እርቅ ሊፈጠር ይገባል
ዋና ዋና ጥያቄዎች በህዝበ ውሳኔ መፈታት አለባቸው።ስለዚህም ተጠናክሮ ለመውጣት በሰላማዊ ትግል የሚጉዋዙ ድርጅቶች ተባብረው መውጣት አለባቸው።
ኢሃዴግ የመለሳቸው አንዳንድ ጥያቄዎች ለምሳሌ የብሄረሰብ ጥያቄዎች በዘረኝነት ሽፋን መታለፍ የሌለበትና አግባብ ያለው መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል።
*በአመለካከት ሁለት ባካሄድ ልዩነቶች አሉ፡ ለምሳሌ በመድረክ በመኢአድና በኢዴፓ ህብረብሄራዊነትና በብሄር መደራጀትን አስመልክቶ
የአመለካካት ሶስት ስብስቦች/ የወያኔ ኢሃዴግ ደጋፊዎች
ኢህአዴግ ካለፉት መንግስታት የሚሻል መንግስት ነው
ኢህአዴግ የኢትዮጰያን መሰረታዊ ችግር የብሄረሰብ እኩልነትን ያረጋገጠና ዲሞክራሲን ያሰፈነ ወይም መሰረት የጣለ ድርጅት ነው።
ኢህአዴግ ወያኔ ሳይሆን እንደስሙ ኢህአዴግ የሆነ መንግስት ነው
ኢህአዴግ አንድም የሃገርን ጥቅም አሳልፎ የሰጠበት ሁኔታ የለም።
ኢሃዴግ ልማታዊ መንግስት ነው።
በኢህአዴግ አመራር ዲሞክራሲያዊ መብቶች ተከብረዋል። ጥቃቅን ቺግሮች ግን አሉ
በሃገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ጎረቤት አገሮች ጋር ሰላምን አስፍኖአል።
ለተጠቀሱት ባህርያቱ የሚሰጡ መፍትሄዎች
-ኢህአዴግ ካለፉት መንግስታት የሚሻልና ብዙ ለውጥም ያመጣ መንግስት ስለሆነ የምንታገለው መንግስት ሳይሆን የምንንከባከበው መንግስት ሊሆን ይገባል። ስህተቶቹን እንዲያርም ማድረግ ነው ከተቃዋሚ የሚፈለገው።
- ተቃዋሚው መቃወም ብቻ እንጂ በሀገራዊ ጉዳዮች ጭምር ተሳትፎ የለውም/
-ተቃዋሚ የተሻለ ራእይ ይዞ አልቀረበም። የረባ ተቃዋሚም የለም።
-ተቃዋሚው የድሮ መንግስታት ርዝራዦች እንጂ ስርአቱ የፈጠረው ብሶት የወለደው አይደለም። ስለዚህ የዲሞክራሲ ገደቡም ሆነ ተጽእኖው የተደረገው በአጥፊው ላይ ነው። ይህም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
- የረባ ተቃዋሚ እስከሌለ ኢህአዴግ 40ም 50 አመትም ሊገዛ ይችላል።
ኢህአዴግ/ህወሃት መስዋትነትን ከፍሎ የመጣ ሃይል በመሆኑ ሌላውም ኢህአዴግን ለማስወገድ መስዋእትነት መክፈል አለበት ። ጫካ መግባት አለበት
ኢህአዴግን መቃወም ያለፈ ስርአትን መናፈቅ ነው።
እንግዲህ እነዚህ ከላይ የጠቀስኩዋቸው ሃሳቦች በሀገራችን ፖለቲካ ዙሪያ የሚያጠነጥኑና በተቃዋሚውም በኩል ሆነ በኢሃዴግና ደጋፊዎቹ የትግሉን አቅጣጫ የሚያመላክቱ አንዳንዶቹ በውስጣዊ ይዘታቸው የሚመሳሰሉና የጋራ ባህርይ ያላቸው አንዳንዶቹ ደግሞ ፈፅሞ የማይቀራረቡና አንዱ አንዱን ካላስወገደ ሊመለሱ የማይችሉ ተቃራኒ አመለካከቶች መሆናቸውን ማየት ቀላል ጉዳይ አይደለም።
ለጊዜው ሶስተኛውን አመለካከት እናቆየውና በተለይም በተቃዋሚው ክፍል ባሉ ሃይሎች ነጋ ጠባ የሚጮህለት የህብረት ጥያቄ በነዚህ የአመለካከት ልዩነቶች ላይ የጠራ አቁዋም እስከሌለ ድረስና በልዩነቶቹ ላይ የመስጠትና የመቀበል ፖለቲካ እስካልታከለበት ምንም አይነት የተጠናከረ ትግል ለማካሄድ እንደማይቻል ያለፉት አመታት ልምዶች ያስገነዝቡናል።
በተለይም ወያኔ /ኢሃዴግ በየጊዜው በሚወስዳቸው አስከፊ እርምጃዎች የአመለካከት መሸጋሸግ ሊኖር እንደሚችል ቢታመንም አሁን ባለንበት ሁኔታ እነዚህን አመለካክቶች ሊቀይሩ የሚችሉ መሰረታዊ ጉዳዮች አይታዩም
-አንዳንዶቹ አመለካከቶች ኢሃዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ የተነሱ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ በሂደት የተፈጠሩ መሆናቸው ለምሳሌ የማስወገድ ፖለቲካ ገኖ የወጣው ከምርጫ 97 በሁዋላ መሆኑ ከምርጫው በፊት የነበረውን አመለካከት የቀየሩ ባህርያትና የሃይል አሰላለፍን ያደበላለቁትን ምክንያቶች ለይቶ ማውጣት ያስከተለው ችግር።
- ስለ አንድ መንግስት ባሀርይና ማንነት ገላጭ የሚሆኑ ጉዳዮች በተወሰነ የፖለቲካ ሂደት ውሰጥ በሚፈጠር የአንድ ወቀት ክስተት ላይ በመመርኮዝ ይሁን ወይም ስልጣን ላይ ከወጣ በሁዋላ በየጊዜው በሚወስዳቸው የተሳሳቱ የፖለቲካ ውሳኔዎች ላይ መሆኑን በቂ ግንዛቤ የማግኘት ችግር
-ኢሃዴግ እንደ ማንኛውም መንግስት ለህልውናው ብሎም ቢሆን የሚተገብራቸው በጎ ተግባራትን የመቀበልና በጎ ባልሆኑት ላይ ህብረተሰቡን የማንቀሳቀስ ልምድ ያለመዳበር ችግርና ሌሎችም ብዙ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ።
እርስዎስ የትኛው አመለካከት ለሃገራችን ይበጃል ይላሉ?
ክጭፍን ደጋፊነት ወይም ነቃፊነት ለመውጣት ከቻልን አንድ እርምጃ ወደፊት እንራመዳለን።