Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: ሃይፖጎናዲዝም (Hypogonadism) –ወንድነትን ችግር ውስጥ የከተተ ሌላኛው ክስተት

$
0
0

ወንዶችም የወንዶች ጉዳይ የሚመለከታቸው ሴቶችም ስለ ወንድ ማወቅ የፈለጋችሁ ሁላችሁም እንዴት ናችሁ? ክረምቱ ብርዱ እንዴት ይዟችኋል፡፡ መቼም በዚህ ክረምት የሴቶች ጉዳይ ለወንዶች ጉዳይ የሚሰጠው ጥቅም በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህም ነው በክረምት ሁሉም ብርዱንም ቅዝቃዜውንም ችሎ በማለፍ ጉዳዩን በደንብ መያዝና ማጠናከር ያለበት፡፡ የበረታው ደግሞ ጉዳዩን ከክረምቱ አልፎ ለበጋም እንዲተርፈው ያደርጋል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ የያዘው ጉዳይ ሁሉ እስከ ህይወት ፍፃሜ ሆኖለት ይሳካለታል፡፡ እዚህ ላይ ጉዳዩ እያልን ያነሳነው ዕጣ ክፍላችን ሆኖ የሚያገናኘንንና የሚያጣምረንን ለማለት ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ወንዶች ጉዳዮቻችን ላይ ብዙ እርቀት እንዳንጓዝ የሚያደርጉን ችግሮች ይፈጠራሉ፡፡ በተለይም ወንድነታችንን ፈተና ውስጥ ከሚከቱ ህመሞች ውስጥ የተወሰኑትን ከዚህ በፊት እያነሳን ተማምረናል፡፡ ለዛሬም የወንዶች ጉዳይን ችግር ውስጥ ሊከቱ ከሚችሉ ህመሞች ውስጥ ሃይፖጎናዲዝም ስለተባለው ህመም እያወጋን ወንዶችም የበለጠ እየተማርን ችግሮቻችንንም እያወቅን መፍትሄ በማግኘትም ለሴቶች ጉዳይ ሁሌ ዝግጁ ሆነን እንድንጓዝ እላለሁ መልካም ንባብ፡፡

erectile dysfunction
ሃይፖጎናዲዝም ምንድነው?
በወንዶች ላይ የሚከሰተው አይፖጎናዲዝም የምንለው ክስተት ሰውነታችን በቂ የሆነ የቴስቴስትሮን ሆርሞን ሳይዝ ሲቀር ወይም ይህንን ሆርሞን በበቂ ሁኔታ ማምረት ሲሳነው የሚፈጠር ሁኔታ ነው፡፡ የቴስቴስትሮን ሆርሞን በወንዶች ላይ ብቻ የሚገኝ የሆርሞን አይነት ሲሆን በሁለት የዘር ፍሬዎች(Testies) አማካይነት የሚመረት ነው፡፡ ይህ የቴስቴስትሮን ሆርሞን ለወንድ ልጅ የመገለጫው ያህል በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ለወንድ ልጅ በጡንቻ መዳበርም ሆነ በኋላ በጎልማሳነት የዕድሜ ክልል ውስጥ በቂ የሆነ አካላዊ የዕድገት ለውጥም በተጨማሪም ከእነዚህ ዕድገት ጋር ተያዞ ለሚመጣው አዕምሯዊ ዕድገትም እንዲሁም የውስጥ የሙሉህነት ዝግጁነትና ለስሜት መዳበር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ በዚህ የእድገት ለውጥ ውስጥ እንደ ውጫዊ ለውጦች ልናያቸው ከምንችላቸው መካከል ለወንድ ልጅ የወሲብ አካላት መፈጠርና አስፈላጊውን የተራክቦ ስራ የመስራት ብቃት እንዲኖረው በተጨማሪም የወንድ ልጅ መለያ ባህሪያትን በጉርምስና የእድሜ ወቅት እንዲታዩና ወንድ ልጅ ለወሲብ ብቁ እንደሆነና እንደደረሰ የሚጠቁመን ይህ ሆርሞን ነው፡፡ የዚህ ሆርሞን ምርት ጤናማ በሆነ መልኩ እንዳይቀጥል ወይም መጀመሪያውኑ እንከን እንዲገጥመው ከሚያደርጉ ህመሞች አይፓጎናዲዝም አንዱና ዋናው ነው፡፡ ወንዶች ከዚህ የአይፖጎናዲዝም ችግር ጋር አብረው ሊወለዱ ይችላሉ፡፡ ወይም ደግሞ በኋላ ላይ በህይወታቸው ውስጥ በሚፈጠር አደጋ ወይም የተለያዩ ኢንፌክሽኖች የተነሳ ሊከሰትባቸው ይችላል፡፡

ምልክቶቹ የችግሩ ምልክቶች እንደ የዕድሜ ልዩነቱ ብዙ አይነት ሆነው ይገኛሉ

ሊወለድ በደረሰ ልጅ ላይ
በእዚህ ወቅት ምንም አይነት የቴስቴስትሮን ምርት መኖሩን ለማረጋገጥ የሚያስችል ምልክት ላያሳይ ይችላል፡፡ እንደዚሁም የወንዱ የመራቢያ ብልቶችም ጉልተውና አድገው አይታዩም፡፡ ይህ ሊታይ ከሚችልባቸው ምክንያቶች ውስጥ፡-
- ልጁ በዘረመን(በጅን) ምርመራ ወንድ መሆኑ ቢታወቅም የሴት የመራቢያ አካላትን ይዞ መገኘት፣
- በጣም አሻሚ የሆነ የመራቢያ አካላትን ይዞ መገኘት (ወንድ ይሁን ሴት ለመለየት በሚያስቸግር ደረጃ)፣
- በደንብ ዕድገቱን ማሳየት ያልቻለ የወንድ መራቢያ አካል ሲኖር፣

ከ13-16 ዓመት ባሉ ወንዶች ላይ
ይህ ወቅት ወንዶች የመራቢያ አካላቸውን በደንብ ለይተው የሚያውቁበትና ፒውበርቲ የምንለው ጊዜያቸው ላይ መሆናቸውን የሚያሳዩ ሲሆን በዚህ የዕድሜ ወቅት አይፓጎናዲዝም ከተከሰተ ሊያሳይ ከሚችለው ምልክቶች መካከል፡-
- የሰውነት ጡንቻዎች ዕድገትና መዳበር እየቀነሰ መምጣት
- ጥልቀት ያለው የድምፅ አወጣጥ ችግር መኖር
- የሰውነት ላይ ፀጉሮች በጊዜያቸው አለመብቀል
- የመራቢያ አካላት ትክክለኛውን የዕድገት ለውጥ ሳያመጡ መቅረት
- እጅና እግር ከላይ ካለው የሰውነታችን ክፍል ጋር በማይመጣጠን መልኩ ማደግና መርዘም፣
- ጅኒኮማስቲያ ተብሎ በሚገለፀው ደረጃ የወንድ ልጅ ጡት ማደግና መተለቅ

የተሟላ ዕድገት ላይ በሚገኙ ወጣት ወንዶች ላይ
ይህ ወቅት በአጠቃላይ ከወጣትነት የእድሜ ክልል ጀምሮ ባሉት ላይ የሚታይ ሲሆን ከምልክቶቹም ውስጥ፡-
- የመራቢያ ችግር ወይም መሀንነት
- በወሲብ ወቅት ብልትን ለማቆም ወይም ለመወጠር መቸገር
- ጺምም ሆነ የሰውነት ፀጉሮች ዕድገት መቀነስ
- ሰውነት በጣም መወፈርና ዝርግፍ ያለ ቅርፅ መያዝ
- የዘር ፍሬዎች መጠናቸው ማነስና ጥንካሬያቸውን ማጣት
- የጡንቻ መዳበርና ክብደት ቀንሶ መገኘት
- የጡት ማጎጥጎጥና ትልቅ ሆኖ ማደግ
- የአጥንት ዕድገትና መዳበር ብሎም ክብደቱ መቀነስ

እነዚህ በአጠቃላይ አካላዊ ለውጦች ሆነው የምናያቸው ሲሆን በአይፖጎናዲዝም ችግር ሊፈጠሩ የሚችሉ የስሜትና የአዕምሮ ለውጦችም ይኖራሉ፡፡ በዚህ ችግር ምክንያት የቴስቴስትሮን ሆርሞን ምርት ስለሚቀንስ ወንዶች ልክ ሴቶች የማረጫ ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ከሚያሳዩት ምልክቶች ጋር ተመሳሳይ ምልክቶችን ሊያሳይ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፡-
- የድካምና የመጫጫን ስሜት መኖር
- ለወሲብ የመነሳሳት ችግር ወርዶ መገኘት
- በነገሮች ላይ ትኩረት የማጣት ችግር
- መነጫነጭና በትንሽ ነገር መረባበሽ
- ጭንቀት
- ራስን አለማረጋጋትና ወደ መጥፎ ቀውስ ውስጥ መክተት

ሃይፖጎናዲዝም የሚፈጠርበት ምክንያቶች
በወንዶች ላይ የሚከሰተው አይፖጎናዲዝም በቀጥታ የዘር ከረጢትን የሚጎዳ በመሆኑ በቂ የሆነ የቴስቴስትሮን ሆርሞን እንዳይመረት ያደርጋል፡፡ ከዚህም አንፃር የሚፈጠርበትን ምክንያቶች በሁለት ከፍለን እናያቸዋለን፡፡

የመጀመሪያው ሃይፖጎናዲዝም

በዚህ ወቅት ሃይፖጎናዲዝም የሚፈጠረው በቀጥታ በዘር ከረጢት ላይ በሚደርሱ ችግሮች የተነሳ ነው፡፡ ለምሳሌ ሊጠቀሱ ከሚችሉት፡-
- ክሊንፌልተርስ ሲንድረም ሲከሰት ይህ ክስተት ወንዶች ሊኖራቸው ከሚገባው አንድ ‹‹X›› እና አንድ ‹‹Y›› ክሮሞዞም በተጨማሪ ሁለትና ከሁለት በላይ ‹‹X›› ክሮሞዞም ሲገኝባቸው ነው፡፡ ይህም ከውልደት ጋር በተያያዘ የሚፈጠር ችግር ሲሆን ተጨማሪ ‹‹X›› ክሮሞዞም መኖራቸው በዘር ከረጢቱም ላይ ሆነ በቴስቴስትሮን ሆርሞን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡
- ከውልደት በኋላ ዘር ከረጢት ፍሬዎች ተለይተው በመውጣት ዕድገታቸውን ባለማካሄዳቸው የተነሳ
- በዘር ከረጢት ፍሬዎች ላይ በሚርሱ አደጋዎች የተነሳ
- ከፍተኛ የብረት ማዕድን በደም ውስጥ መገኘት(Hemochromatosis)ይህም በዘር ከረጢት ፍሬዎች ላይም ሆነ በፒውቲታሪ ዕጢ ላይ በሚያደርሰው ተፅዕኖ በቂ የቴስቴስትሮን ሆርሞን እንዳይመረት ያደርገዋል፡፡
- በዘር ከረጢት አካባቢ ለሚፈጠር የካንሰር ህመም የሚሰጡ የኬሚካልና የጨረር ህክምናዎች የተነሳ
- በምራቅና በፓሮቲይድ እጢዎች ላይ በሚደርሱ ችግሮች
- ከዕድሜ መግፋት ወይም ከእርጅና የተነሳ የመሳሰሉትን ያጠቃልላል፡፡

ሁለተኛው ሃይፖጎናዲዝም
የዚህ አይነት ችግር ደግሞ የዘር ፍሬዎች ጤናማ ሆነው ነገር ግን በትክክል የማይሰሩበት ሁኔታ ሲኖር ነው፡፡ ይህም በፒውቲታሪ ዕጢ ላይ ወይም አይፖታለመስ በተባለው የጭንቅላታችን ክፍል ላይ በሚደርስ ችግር የሚፈጠር ነው፡፡ ከመነሻዎቹም መካከል፡-
- ካልማን ሲንድረም አይፖታለመስ ትክክለኛ ዕድገቱን ባለማካሄዱ የሚፈጠር ነው
- ከፒውቲታሪ ዕጢ ጤናማ አለመሆን የተነሳ
- ውስጣዊ አለርጂ ሊፈጥሩ ከሚችሉ ነገሮች የተነሳ
- አይፖታለመስንም ፒውቲታሪንም ከሚጎዱና የቴስቴስትሮን ሆርሞንን ከሚያዛቡ እንደ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ከመሳሰሉ ህመሞች የተነሳ
- ከተለያዩ የመድሃኒት ህክምናዎች የተነሳ
- ከሚገባ በላይ መወፈርና ክብደት መጨመር ይጠቀሳሉ፡፡
ሁለቱም አይነት ምክንያቶች በዘር የተመተላለፍ ወይም በህይወት ቆይታ ውስጥ በሚደርስ በተጠቀሱት ችግሮችም አይፖጎናዲዝምን ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡

ለህመሙ የበለጠ ተጋላጭ የሚያደርጉ ሁኔታዎች
- የዘር ፍሬን ለአደጋ ተጋላጭ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች
- በዘር ፍሬና በፒውቱታሪ ላይ በሚከሰት እብጠት
- የኬሚካልና የጨረር ህክምናዎችን በብዛት በመጠቀም
- የብረት ማዕድንን በደም ውስጥ እንዲበዛ ከማድረግ
- የዘር ፍሬን ሊያጠቁ ለሚችሉ የተለያዩ ኢንፌክሽኖች በመጋለጥ

ሃይፖጎናዲዝምና ምርመራዎቹ
ለአይፖጎናዲዝም የሚደረጉ ምርመራዎች እንደየምክንያቱና እንደሚጠረጠረው መነሻ የተለያዩ ምርመራዎች ሊደረጉለት ይችላሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል፡-
- የሆርሞን ምርመራ
- የዘር ፈሳሽ ምርመራ
- የፒውቲታሪና የሃይፖታለመስ ሁኔታን ማጥናት
- የዘረመል ወይም የጀኔቲክ ጥናት ምርመራ
- ከዘር ፍሬ ላይ በሚወሰዱ የህብረ ህዋስ ወይም የቲሹ ናሙና ምርመራ
- የደም ምርመራ፣ የመሳሰሉትን ይጨምራል፡፡

ህክምናዎቹ
ህክምናዎቹ እንደ የዕድሜ ልዩነቱና እንደሚፈጠረው ችግር ይለያያል፡፡ በአጠቃላይ ግን የተለያዩ የመድሃኒት እንደዚሁም የቴስቴስትሮን ሆርሞንን እስከመቀየር እና የዘር ፍሬ ዕድገትን በቀዶ ጥገና እስከማስተካከል ያሉትን ህክምናዎች ይጨምራል፡፡ ከህክምናው ባሻገርም በዘር ፍሬ አካባቢ ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን መቀነስ እንደዚሁም ጭንቀትና ጫና የበዛበትን ህይወት ማስተካከል ወሳኝና እንደ መከላከያ ጥንቃቄ በማድረግ ትኩረት ልንሰጥበት የሚገባ ነው፡፡ ወንዶች እንደ ወንድነታችን በችግሮቻችን ላይ መፍትሄ በመስጠት ለራሳችንም ለሴቶቻችንም ጥሩ ህይወት እየኖርን ጉዳዩን ጥሩ ጉዳይ ማድረግ እንችላለን፡፡ ሰላም ቆዩ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>