Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የሁለት ሀገር ስደተኛው –ጋዜጠኛ። (ሥርጉተ ሥላሴ)

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 10.08.2014 (ሲዊዘርላንድ -ዙሪክ)

እንሆ – በዚህ ዘመን ታሪክን እንደ ከሰል አመድ ባደረገ ጽልመታዊ የወያኔ ሃርነት ትግራይ ዘመን – የአንድነቱ ልዑል የአሉላ ማሾ ከወደ ስሜን የብራና ኮከብ መሪን አሰቀድሞ ብቅ አለ። ይህ ደፋርና ንቁ፤ በራስ የመተማመን መንፈሱ ሙሉዑ የሆነ ዕንቡጥ ስሜቱን ለመግለጽ ያለውን ብቃቱን ብራና ቆሞ የሚመስከርለት ድንቅ ወጣት ጋዜጠኛ አብርሃማ ደስታ ነው። አብርሽ የሥርዬት መንገድ ነው።

የወያኔ ሃርነት ትግራይ በጎሳ የሚዘረዝራቸው በደሎችን ሁሉ እዬመነዘር በግልጽ፤ በተብራሩ፤ ስሜትን በሚፈትሹ፤ አጫጭር ዘገባዎቹ ዘመኑ የፈቀደለትን ታሪክ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ሲያኮመኩመን የቆዬ ትንታግ ነው። ጋዜጠኛና መምህር አብርሃም ደስታ „ ትግራይ የኢትዮጵያዊነት ባለ ጉልትነቷን እዬፈገፈገ እንድታጣ ከዘመተባት ጠላቷ ከአረሙ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማንፌስቶ ጋር ትፋታ ዘንድ ቆሞ ያሰተማረ – የሰበከ – የመከረ ትጉህ ወጣት ነው።

ታናሼ አብርሽ በፎሎቄማ የአጻጻፍ ለዛው የብዕር ፍቅረኞችን ሰጥ ብሎ እንደሚወርደው ኢትዮጵያዊ ወንዝ መንፈሳቸውን የገዛ፤ ማህል ላይ ወለል እያለ የሚያስቸግረውን ግራጫማ የዞግ ወረርሽኝ በሽታንም ሳይቀር በመግራት ህሊናን ሚዛን ላይ ያሰቀመጠ –  ዬእርቅም ድልድይም ነው። በቀልና እኛ - በበደል ዓይን፤ በቀልና እኛ በፍትህ ጆሮ፤ በቀልና እኛ በመገፋት የዕንባ ምጥ እያቆላመጠ በሥነ – ጥበብ ማራኪያዊ ውበት እንድንፈታተሽ ከህሊና መንበር ጋር ፊት ለፊት ያገናኘ ብቁ የጥበብ ሰው ነው። እንደ እኔ ብዙ ነፍሳትን ከጥፋት ውሃ በሁሉም አቅጣጫ ታድጓል ባይም ነኝ።

አብርሽ በራሱ ውስጥ ስሜቱን – ፍላጎቱን – ራዕዩን አቅርቦ እያባበለ – እያሟገተ ቀልብን ይዞ መልእክቱን በማስተዋል እንከታተለው ዘንድ በብቃቱ ፍቅርና ሰፊ ተደማጭነት ያገኘ ትጉህ የብዕር ገበሬ ነው። አብርሽ ጨርሶ ሚዲያ ዳስሷቸው ያማያውቀውን የገበሬ መንደሮችን ሳይቀር ከትግራይ ወጣ ብሎም የዳሰሰ ወርቅ ወጣት ነው። ለምሳሌ በዘመነ ታሪካቸው ብዕርና ብራና ጎብኝቷቸው የማያውቁትን በጎንደር እንደ „ጮንጮቅ“ ያሉትን እጅግ ትንሽ የገበሬ መንደር ሳይቀር የደረሰውን ህዝባዊ በደል በማጋለጥ ሃቅን አደባባይ አቅርቦ ዬወያኔ ሃርነት ትግራይ የነፃነት ጠላትንትነት፤ የርትህ ዘረፋን፤ የሰላማዊ ሰዎችን ሰላም ቀማኛነትን ቁልጭ ባለ ንጹህ አግባቢ ቋንቋና በውባውብ የቃላት ቅንብሮቹ ዘዬ ዕውነትን ለባለታሪኩ ለፍተሻ ያቀረበ ባተሌ የሰከነ ጋዜጠኛ ነው።

አብርሽ መምህር እንደመሆኑ መሰሉን ለመተካትም በትምህርቱ ዘርፍም አባታዊ ሃላፊነቱን የሚወጣው ወያኔ ሃርነት ትግራይ „ ከትግራይ ውጪ ያሉ ኢትዮጵውያን በጥቅሉ አማራ በሚል ሥያሜ ሰው ያልሆኑ፤ ሁለት ትላልቅ ጆሮ ያላቸው። አንዱን ጆሮውን ለብሰው፤ ሌላውን አንጥፈው የሚተኙ“ እያለ ትግራይን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ፤ ጥላቻን ኮልኩሎ በበቀል ብቅል አብቅሎ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የነበረውን መሬት ያያዘ የቁርሾ ብክል ደም በማምከን በኢትትዮጵያዊነት መንፈስ የኔ ፍሬዎችን ያጠበ፤ ያጸዳ፤ የወያኔ ቆሻሻውን ሁሉ የጠረገ ብልህ ወጣት ነው። መምህር አብርሃ ደስታ በተማሪዎች የኢትዮጵያዊነትን አቅም በመገንበት፤ ኢትዮጵያዊነትን ብድግ ያደረገ ለጋ ወጣት ነው። እንደ ሌሎቹ የጎሳ ጥመኞች አዛውንት መምህራን የመረጥከውን መውሰድ ትችላልህ በማለት ታሪክን ለባንዳ በረድ ያለጋለጠ ንቁ ወጣትም ነበር። ታሪክን ማህል ላይ ገትሮ ያለጠቆረ የሙያውን ሥነ – ምግባር ክብር ያስጠበቀ ታታሪ ወጣት ነው። ስለሆነም ይህ ጋዜጠኛ፤ ጸሐፊና መምህር ወጣት ድርብ ሃላፊነቱን የተወጣ – የቆረጠ የቀለም – ቀለማም አባትም ነው።

እጅግ የምትናፍቁኝ የሀገሬ ልጆች። „የሥላሴ አንድነትና ልዩነት“ ለተዋህዶ ልጆች የተሰጣቸው አባቶች ብቻ ነው የሚተረጉሙት – የሚያመሳጥሩት። „ካህን“ በመሆን ብቻ ይህ ታላቅ የዕምነት ዶግማ ሊደፈር ከቶውንም አይችልም፤ ስለ „ነገረ ማርያምም“ ቢሆን በተመሳሳይ ሁኔታ የተፈቀደላቸው ብቻ አንደበታው ተከፈቶ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በአማንያን ሥረ ህሊና ማብቀል ይችላሉ። ታናሼ ጋዜጠኛ አብረሃም ደስታም „ማንነትን“ የተነተነበት መንገዱም ሆነ የሂደቱ ረቂቅነት ፍጹም ልዩ ስለነበር „እኔ ማን ነኝ? ከዬት ተገኘሁ? እንዴትስ መጣሁ? ከማንስ ተፈጠረኩ? ግንደ – ዘሬ እንዴት ተፈጠረ? ቅርንጫፉና ግንዱ እንዴት ሀረግን ፈጠሩ?“ በማለት ልክ የተቋም ያህል ነበር ያስተማረው። ዬአብርሽ ጸጋ ከሩቅ፤ ወይንም ከወንዝ ወዲያ ማዶ ወይንም ህዋው ላይ አይደለም የሚነሳው – ከተጨባጩ ከጠረኑ ከራሱ ውስጥ ተነስቶ አካባቢውን ቃኝቶ ደረጃውን እዬጠበቀ ወደ ብሄራዊ፣ አህጉራዊና፣ ዓለማቀፋዊ ትንፋሹን ያመጠዋል – ያጣጥመዋል። መሬት ይዞ ስለሚነሳ ዘርቶ ሊያበቅል የሚፈልገው ነገር  እጥፍ ድርብ እንደ ተፈጥሮው ማብቀል ዬቻለ ትምህርተ – ገቢራን ነው። አብርሽ ለትግራይ ህዝብ የታሪኩ አባወራ እንደ ሥሙ የአብራሃሙ ቤት ነው። „መድህን“ ቢሉትም ይገባል። ታዳሚዎችም ሆነ አድናቂዎቹ ዕልፍ ነን።

እኔ አብርሽን እጅግ አውደዋለሁ። እሱ በሚጽፋቸው ጹሑፎች ሥር የአስተያዬት ግድፈቶች ከሥር ተጽፈው ሳይ እጅግ ልቤ ይቆስል ነበረ። ይህ ልጅ – ይህ ወጣት – ይህ ቀንበጥ – ይህ ጀግና በወያኔ ሃርነት ትግራይ ሆነ በሰሉ የወያኔ ደጋፊዎቹ  የከረፋ የበደል ክምር ተጠያቂ ሊሆን ከቶውንም ፈጽሞ አይቻልም።

ወገኖቼ ይህን ቢፈቅድ እኮ ጋዜጠኛ አብርሃም ደስታ ለዶተሬትነቱ ሰፊ ዕድል ማግኘት ይችል ነበር። ተነጥፎ ተጎዝጉዞለት። ሀገር ውስጥ እኖራላሁ ቢልም እስከ ሚ/ር ደረጃ የሚያደርስ ዕድሉ ሰፊ ነበር። የመጀመሪያውን የወያኔ ሃርነት ትግራይ መስፈርት የሚያሟላ ጉልህ ወጣት ነበር። ግን አላስፈለገውም። መኖር የፈለገው በእውነተኛው ዓለም በጋህዱ ዓለም ነበር። ገሃዱ ዓለም የሚፈልገው ደግሞ እንደ ተፈጥሮው የሆነ ነፃነትን ነው።

የመኖር – የመተንፈስ፤  የመናገር፤ የመጻፍ፤ የመደራጀት፤ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፤ የህግ የበላይነት፤ በድምጽ የሚመራ ሀገር፤ በደል – አድሎ – ስጋት – ረሃብ የሌለበት የእኩልነት ዜግነት ዓለም ነው። ይህን ከወያኔ ሃርነት ትግራይ የ40 አመት ትግል ጠብቆ ማዬት አልቻለም። ስለዚህ ከበደሉ ማሳ እራሱን አውጥቶ እሱ ስለሚያልማት ኢትዮጵያ መናገር ጀመረ …. ማስተማር ጀመረ …. መስዋዕትነቱን ተርጉሙት በነፃነት ህገ – ህግጋት መገዛት ቻሉ! በማለት ወቀሳውን ካለይሉኝታ  ለአራዊቱ ወያኔ  ገለጸ …. ሰሚ አጣ … እንዲያውም ተጠቂም ሆነ።

እኔ በጣም ለረጅም ጊዜ አስተውለው የነበረው አብይ ጉዳይ „ጋዜጠኛ አብርሃ ደስታ“ ለማለት እንኳን ጋዳ ነበር። ሙያው የሚጠይቀውን ያሟላ ሆኖ እያለ። ዘገባዎቹ ትኩስ – ግልጽ – የተብራሩ – ከማህበረሰቡ የተነሱ – ፈጽሞ በግነት ያልተወረሩ – ብዙኃኑን ያደመጡ –  አጭር – ደፍረው ጦርነት ውስጥ የሚያገቡ – ቅራኔ የተጋሩ፤  ዬእውነትን ጅረትን ተከትው ዬሚጓዙ – የዘመኑን ባህሪ ያደመጡ ነበሩ። ይህ ሙያው የሚጠይቀው በጋዜጠኛ አብርሃም ደስታ በቀጥታ በተፈጥሮው ያገኘው ልዩ ብቃቱ ነበር። ለነገሩ በሥልጠና የሚገኝ ክህሎት ነበር — ግን እሱ ከላይኛው ተፈቀደለት።

ወደ ሥነ -ጹሑፍ ሥልጡነነቱ ስትሄዱ ደግሞ  የነጠረ አቅም ነበረው፤ ጹሑፎቹ  የወያኔን ሆድዕቃ አሳምረው ጎርጉረው ግን ሳይጠገቡ እንዳጓጉ ላጥ ይሉ ነበር። ልብን እንደ ቅል አንጠልጥለው። ዝንፈት ያልጎበኛቸውም ነበሩ።

በሰብዕዊ መብት ተቆርቋሪነቱም ቢሆን ቁስሉ የተሰማው መንፈስ ነበር የሚታይበት። በሴቶች የእኩልነት ተሳትፎ ላይም አንጋፋ – ጎልማሳ – ወጣት – ጋዜጠኞች የሚዘሉትን ሥነ – ምግባር ያሟላ ነበር ማለት እችላለሁ። እጅግ አብዝቼ እምከታተለው ዘርፍ ነውና። በአብርሽ የዜና ትንተና የመረጃ አቅጣጫ ደግሞ ድንቅ ትርጉም ይታፈሳል። ዘገባዎቹ ሁሉ – ከቆዳ መልስ ነክቷቸው አያውቅም።  ወይንም ተቆርጦ እንደ አደረ ዝንጣፊ ጥንዙል አልነበሩም። ትኩስ ትኩሱን ለመንፈሳችን ይቀልብን ነበር። እንሆ አሁን ትግራይ አንደበቱ ተዘጋ …. ስለ አሉላ መንፈስ፣ ስለ አሉላ ጸሐይ – ትግራይ ምን ይል ይሆን? ጸጥ – ረጭ – ዝም —-  ያቺ የእኔ ጀግና ወ/ሮ አልጋነሽ ገብሩና መንገድ እንደወጡ ያዳመጥነው ዬፍሬዎቻስ – የነገ ተስፋዎቻችን ጉዳይ ማን ይንገርን – ዝግት ድርግም ያለ ጉድ …. ዳፍንት!

እኔ አንጀቴን የሚበላኝ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ጎጣዊ ማንፌስቶ ትሸታላቸሁ ብሎ የሚመጣን ኢትዮጵያዊ ዜጋን ለመቀበል ያለን አቅም ስስ መሆኑ ነው። ሁልጊዜ ጥርጣሬ። ሁልጊዜ ወቀሳ። ሁልጊዜ ዱላ። አብሶ ወጣቶች ባልበሉት ዕዳ ስለምን እንደሚወቀሱ ፈጽሞ አይገባኝም። እንዲገባኝም አልፈቅድለትም።

ማያያያዣ ነገር – አሁን የአንድነቱ አንደበቱን – ብቃቱን – አቅሙን ሳልጠግበው ለካቴና የበቃው አቶ ሃብታሙ አያሌው „ዬወያኔ ደጋፊ ዬነበር“ በሚል ከልብ ለመቀበል የነበረን ፈቃደኝነት ያረረ ነበር። አሁን ሲታሰር ጀግና እንለዋለን? ወያኔ አሁን ከሚያደርስባቸው ማናቸውም ስቃይ የኛውም የመንፈስ ረገጣ ሆነ ጥቅጠቃ ዘመን ይቅር የሚለው አይመስለኝም። አንድ ሰው በነፃነት ትግሉ እሰለፋለሁ ሲል በጣም ብዙ ነገሩን ነው የሚያጣው። የሚተርፈው የመንፈስ ጥሪት ለህሊና ማደሩ ብቻ እንጂ በግራ በቀኝ በሚወርደው ወጀብ ያለው ወጨፎ መመዘን ከቶ አይቻልም።

ለነፃነት ታጋዮቻችን ለመንፈሳቸው ጥበቃ ጥንቃቄ በሚመለከት ምድረበዳ ነው። ወያኔ እዬከፈለ። ውጭ ሀገር ላሉ ቱቦዎቹ ሳይቀር እንኳን ቀለብ እዬሰፈረ የእኛ ደግሞ በብላሽ ለማገልግልም ቆመጥ —- እም!

እርግጥ ተሰውረው – ተቀላቅለው አንድ ደረጃ ላይ የሚሾልኩ ይኖራሉ። ከዚህ ስጋት አንጻር ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አራሳቸው ከፈለጉ ወደ ውርዴታቸው ያዝግሙ። በእኛ በኩል ያለውን መልካም አቀባባልና ፍቅር ከመሰጠት መቆጠቡ ግን የማይጠቅም ነው። ባይሆን ደረጃውን ይጠብቅ ያግባባል — እንጂ ገና በሩ ሳይደርሱ …

አንጀቴን እዬበለኝ የምጽፈው አብርሽ የሁለት ሀገር ስደተኛ የነበረ መሆኑ ነው። እኛ የነጻነት ፈላጊ ቤተሰቦች በይደር ዬያዝናቸው ጉዳዮች ነበሩን። ወያኔ ከጎጥ ዶክተሬኑ በማምለጡ እርምጃውን እዬተከታተለ መተንፈሻውን መዝጋቱ በሁለት ወጀብ ሲንገላታ እነሆ በእጅ ወድቆ እንደፈለጉት ይዘለዘላል። የበለጠ – የቀደመ – የተሸላ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን „የኢትዮጵያዊነት ፋና“ በመሆኑም ጭምር ሁለመናውን ይደምስሱታል።

ፎቶዎቹን ስብስብ አድርጌ ስመለከታች መልሼ በዚህ መንፈስ እንደማለገኘው ሳስበው መንፈሴ ይመረቅዛል – በመግል። ፈዞ በድኑን ብቻ ይሆናል ዬሚሰጡን። ቀጣዩ የእሱ የወደፊት ተስፋ ሁለት ያጣ ጎመን እንዳይሆን እንደማንንኛውም የብዕር አርበኛ ለዓለም ዓቀፉ የብዕር ሽልማት ይበቃ ዘንድ ተግቶ መሥራት ያስፈልጋል። የታሪኩ ጠበቂና ዘብ አደር ልሆንለት ይገባል። አብሶ ወጣት ኢትዮጵውያን አብርሽን እንደ ወጣት አብነታቸው፤ እንደ ወጣት ሙሴያቸው ሊያዩት እንደሚገባ በእናትነቴ ዝቅ ብዬ እጠይቃለሁ።

የተግባር ዲታው እውነተኛውና አንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበርም በክህሎት የተቀመመውን ተመክሮውን አበልጽጎ ለሙያ አጋሩ ያለውን አክብሮትና አድናቆት ሊገልጽ ዬሚችልበትን ስልት መፍጠር እንዳለበት አሳስባለሁ – በትህትና። በአንድ ወቅት የክፍለሃገር አዳራጃችሁ ነበርኩና – ህገ ደንባችሁ እንዲህ ለሙያው አርበኛ አክብሮቱን እንደማይነፍገውም አስባለሁ። በተጨማሪም ጋዜጠኛና መምህር ርዕዮት ዓለሙም ታሪካችሁ ናት። እሷንም አዘውትራችሁ ልታስቧት እንደሚገባ በትህትና እጠቁማለሁ።

በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ሥነ ጥበብ ቤተሰብ አባልንቴ ወጣት ከያንያን አብርሽን – ክታባቸው እንዲያደርጉት በትህትና አሳስባለሁ። እንደ ጋዜጠኝነቴም ደግሞ የሙያ አጋራቹ ከፊተኛው ረድፍ ላይ በመገኘት ለሙያው አህጉርና ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ወቅታዊ መረጃዎችን በመላክ – ተግባሩን በማስተዋወቅ እረገድ ተጓዳኝ ተግባራትን አቅሙ ያላችሁ ወገኖቼ ትከውኑ ዘንድ በአጽህኖት አሳስባለሁ።

ምን ቀረኝ? ለሰብዕዊ መብት አስከባሪ ድርጅቶችም መረጃዎችን በአጫጭር በእንግሊዘኛ ከተሰሩ ባለው መስመርና ግንኙነት የሎቢውን ተግባር በቀላሉ መከወን ይቻላል። አብሶ የፍርዱን ሂደት የቀጠሮ ቀናቱን ውሎዎች ሁሉንም በእንግሊዘኛ መሠራታቸው እጅግ ጠቃሚው መንገድ በመሆኑ አትኩሮት ቢሰጠው መልካም ነው።

ማህበራዊ ድህረ ገጾች፤ የመወያያ መድረኮች፤ ሚዲያዎች ለአጋራቸው – ለጀግናቸው የነበራቸው አቅርቦትና አክብሮት አብነት ነበር ማለት እችላለሁ። የአብርሽ ጹሑፎች ሆኑ ዘገባዎችን በሽሚያ ነበር የሚያወጡትና አዬር ላይ የተገባውን አክብሮት ይሰጡት የነበረው። ተመስገን። በዚህ ልጽናና።

በቀጣይም በአብርሽ የነጻነት ራህብተኛ ጹሑፎቹ ዙሪያ ውይይቶች – ትናንሽ ወርክ ሾፖችን በዬአካባቢው ፈጥሮ አጀንዳ ማደረግ የተገባ ይመስለኛል። አሁን ለምሳሌ „እኔና ሚኒሊክ“ የሚደንቅ ጹሑፍ እኮ ነው።  ስለሆነም የቆዩትንም  ከአርኬቡ እያወጡ ድጋሚ እንዲነበቡ ቤተኛ ማደረጉ መንፈሱ ከመንፈሳችን ጋር እንዲቆራኝ ይረዳል። አብሶ አሁን ፆም ስለሆነ በጸሎት መተጋጋዙም መልካም ነው። ፎቶውን በፌስ ቡኮች – በቲተር አካውንቶች ሁሉ መጠቀም ሌላው መንፈስ አራሽ መንገዶቻችን ሊሆኑ ይገባል። ጹሑፎቹ የማሰባሰብና ታሪካዊ ቋት ማበጀትም – ነገን ያሳድራል።

በማናቸውም ብሄራዊ ህዝባዊ ስበሰባዎች ሰላማዊ ሰልፎች፤  ጀግናችን አጀንዳችን፤ ጀግናችን ኮከባችን መሆኑን ከውስጣችን ሆነንበት እንታይበት ዘንድ ዝቅ ብዬ አሳስባለሁ። ለእኔ አብርሽ የአንድነቱ ልዑል ዬአሉላ አባነጋ የአደራ ማሾዬ ነው። በብዙ ጹሑፎቼ እሱን እንደ ማመሳካሪ እያደረኩኝ ሰርቼበታለሁ። አሁንም ከልቤ ውስጥ ትንሽ ሙዳያ አለች። በእሱ ውስጥ ታናሼ የሙያ አጋሬ፤ የሥነ ጥበብ ቤተኛዬ፤ እንዲሁም የነፃነት ፈላጊ ቤተሰቤ አበርሽ በክብር ለዘለአለም ይኖራል፡“ አራዊቶች የፈለገውን ነገር አስገድደው ያሰፈርሙት። የእሱ ነው ብለው ይጻፉ። ለእኛ የባንዳ መረጃ ምናችንም ነው። ይልቁንስ አብርሽን የሚገልጸው የሚያብራራው ዬሚያነበው “ የኢትዮጵያዊነት ህግ – አመክንዮ“ መሆኑ ብቻ ነው መስተውታችን ሆነ ሰነዳችን።

ማንም ሰው የአብርሽን ፍቅር ሊቀማን አይችልም። አይፈቀድም። የተከለከለ መንገድ ነው። የእሱ የተስፋ ማሳዎች ዕሸቶች ናቸው – ነገን ያበልጋሉ። እኔ አብዝቼ  እወደዋለሁ። የእሱ መፈጠረ ከብዙ ነገር ታድጎናል። ኢትዮጵያን ከበቀል ያዳና ትንሽዬ ወጣት የድህነት መንገድ ነው …..  አብርሃ ደስታ። አጋጣሚና ሁነኛ ጊዜ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ሰፊ ማሳን ማልማት በቻለ ነበር። ታዲያ ወ ያኔ አቅል ብሎ አልሰራለት። ፈሪ – ብዕርን መድፈር የተሳነው ልፍስፍስ።

የትግራይ ህዝብ ቢያውቀው አብርሽ እንደ መጥምቁ የኋንስ „መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስኃ ግብ“ እያለ እንደ መራው ሐዋራያዊ ተግባር ነው የፈጸመው እሱ እራሱ መልእክተ የኋንስ ነው። በሁሉም ዘርፍ ሲመዘን የአብርሽ ተልዕኮ የብዙኃኑ ፍቅርና ሰላም የተራቆተው ወያኔ ሃርነት ትግራይ እርቃነ – መንፈስ ጎጂ ጉዞ ስለመሆኑ፤ ነገን የማያሳድር ዛሬንም ያማያበርክት ስለመሆኑ ነበር እንደ ተሰጠው መክሊት ሲፈጽም የቆዬው።

ክወና – አብርሽ ሞገድ ነው – ሃቅን የታጠቀ፤ አብርሽ ነበልባል ነው – በራስ መተማመንን የዋጠ፤ አብርሽ ፍቅር ነው  የነፃነት መርህን ከልቡ የተቀበለ። አብርሽ አብነት ነው መከራን ለመቀበል የፈቀደ። ስለሆነም ስቃዩ ስቃያችን፤ መከራው መካራችን፤ ሰቆቃው ሰቆቃችን ነው። የኔ አባት ላደርክልን መልካም ነገር ሁሉ አመስግንሃለሁ። ውድድድ /////

 

የኔዎቹ እንሰነባበት – ፍቅርም – ናፍቆትም – ውስጥም ተሸለማችሁ። ቸር አገኛችሁ ዘንድም አምላኬን ጠዬኩኝ። ደህና ሰንብቱልኝ። ውድድድ

 

ጀግኖቻችን የመንፈስ ሀብሎቻችን ናቸው!

ኢትዮጵያዊነት ፈተናን አሸንፎ የተፈጠረ ሚስጥር!

 

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።

Comment


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>