Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Health: የማህፀን በር ካንሰር

$
0
0

በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 65 ላይ ታትሞ የወጣ

የሴት ማህፀን ከስነ ተዋልዶ አካሎች ውስጥ አንዱ ሲሆን የተለያዩ ክፍሎችን የያዘና በፊት ለፊት በኩል ከሽንት ፊኛ በስተኋላ በኩል ደግሞ በትልቁ አንጀት የመጨረሻው ክፍል የሚወሰን አካል ነው፡፡ የሴት ማህፀንን ስንመለከት በመሰረቱ በሁለት ተከፍሎ እናየዋለን፡፡
- ዋናው የማህፀን አካል (Body of The Uterus)
- የማህፀን በር (Cervix)
Cervical Cancer
ይህ ዋናው የማህፀን አካል ሴት ልጅ ወላድ በሆነችበት የዕድሜ ክልል ውስጥ ከማህፀን በር ጋር ሲነፃጸር ሁለት እጥፍ ርዝመት አለው፡፡ የማህፀን በርም ዋናው የማህፀንን ክፍል ከውጪኛው ስነ ተዋልዶ ክፍል ጋር የሚያገናኝ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ መሰረታዊ ተግባራት አሉት፡፡
- በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ የወንድ ዘር ወደ ማህፀን እንዲገባ መንገድ ይከፍታል
- የወር አበባ የሚወጣበት መስመር ነው
- በእርግዝና ጊዜ ልጅ ከማህጸን አካል የሚወጣበት መንገድ ነው

በመሰረቱ ይህ የማህፀን በር ከነ አካቴው የተዘጋ ሲሆን በእነዚህ በሶስቱ ሁኔታዎች ክፍት ሆኖ ይገኛል፡፡ ይሄንንም ተንትነን ስንመለከተው፤

- በእንቁላል መመረት(Ovulation)ወቅት፡- የሴት ዕንቁላል ከእንቁላል ማቀፊያው ወጥቶ ወደ ማህፀን ቱቦ በሚጓዝበት ወቅት፣ ይህም የሚሆነው በየ28 ቀን ዑደት ባላት ሴት በ14ኛው ቀን ሲሆን ይህም የግብረ ስጋ ግንኙነት ይኖር እንደሆነ ለእርግዝና ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ነው፡፡
- በወር አበባ ወቅት፡- የወር አበባ ከማህፀን በሚወጣበት ጊዜ እንደየአስፈላጊነቱ ከ3-7 ቀናት ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡
- ምጥ በሚጀምርበት ወቅት፡- የማህፀን አካል እየተኮማተረ ቀስ በቀስ የማህፀን በር ይከፈታል፣ ይህም የፅንሱን ጭንቅላትና አንዳንድ ጊዜም የፅንሱን መቀመጫ ሊያሳልፍ በሚችል መልኩ አጠቃላይ ክፍት ይሆንና ከወሊድ በኋላ ተመልሶ ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞው ቦታ ይመለሳል፡፡
ስለ ማህፀን በር ጠቅላላ ግንዛቤ ይሄንን ያህል ከተመለከትን በብዛት ሴቶች የሚጠቁበትንና ከሴቶች የስነ ተዋልዶ አካላት ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ በብዛት የሚይዘውን የማህፀን በር ካንሰር እንዳስሳለን፡፡ ይህ የማህፀን በር ካንሰር በብዛት የሚታየው ከ35-55 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች ላይ ቢሆንም ማንኛውም የግብረ ስጋ ግንኙነት የጀመረችን ሴት ሊያጠቃ የሚችል ህመም ነው፡፡ ከግብረ ስጋ ግንኙነትም ጋር በብዛት ሊዛመድ የቻለበት ዋናው ምክንያት ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ የተባለው በግብረ ስጋ ግንኙነት ጊዜ የሚተላለፈው የቫይረስ አይነት ለዚህ ችግር ዋናው መንስኤ በመሆኑ ነው፡፡ በማህፀን በር ካንሰር የመጠቃት ሁኔታ ከላይ እንደተጠቀሰው በብዛት የሚታይ ሁኔታ ቢሆንም ለዚህ ሁኔታ ያጋልጣሉ ተብለው የሚታመኑ በርካታ ሁኔታዎች አሉ፡፡
- በአነስተኛ ዕድሜ የግብረ ስጋ ግንኙነት መጀመር ዕድሜ ባነሰ ቁጥር የማህፀን በር በካንሰር የመጠቃት እድሉም አብሮ እየጨመረ ይሄዳል፡፡
- የግብረ ስጋ ግንኙነት አጋሮች ቁጥር በጨመረ ቁጥር
- የሰውነትን የመከላከያ ብቃት የሚቀንሱ የተለያዩ ሁኔታዎች በሚኖሩበት ወቅት
- በአባላዘር በሽታ መጠቃት እንዲሁም የኤች.አይ፣ቪ ቫይረስ በሰውነት ውስጥ መኖር
- የእርግዝና ቁጥር በጨመረ ቁጥር
- የወሊድ መቆጣጠሪያ መድሃኒት ለረጅም ጊዜ መውሰድ
- እንዲሁም ሲጋራ ማጨስ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡
ይህ የማህፀን በር ካንሰርን እንደማንኛውም የካንሰር አይነት አደገኛ የሚያሰኘው አጀማመሩ ከዛው ከቦታው ይሁን እንጂ ጊዜ እያገኘ በመጣ ቁትር ወደ አካባቢው ወዳለ የማህፀን፣ የፊኛና፣ የአንጀት ክፍሎች ብሎም ወደ ተለያዩ የሰውነት ክፍሎች በመሰራጨት አንደኛ ደረጃ ሊያደርስ በመቻሉ ነው፡፡

የማህፀን በር ካንሰር በሚኖርበት ወቅት ሊታዩ የሚችሉ ስሜቶች

የማህፀን በር ካንሰር በሚኖርበት ወቅት በተለይ በሽታው በጀመረበት ጊዜያት ውስጥ ምንም አይነት ምልክት ላይታይ እንዲሁም የህመም ስሜት ላይሰማ ቢችልም ሁኔታዎች በቀጠሉ ቁጥር የሚታዩ ስሜቶች፤
- የወር አበባ በማይጠበቅበት ወቅት ከማህፀን ደም የመፍሰስ ሁኔታ በብዛት የሚታይ ስሜት ነው፡፡ ይህንንም ስንል ወትሮ ከሚታየው የማህፀን ፈሳሽ ጋር ደም የተቀላቀለ ፈሳሽ ማየት በውስጥ ሱሪ ላይ ትንሽ/ብዛት ያለው ደም ማየት፣ ማህፀንን በሚታጠቡበት ጊዜ ደም ማስተዋል፣ ከግብረ ስጋ ግንኙነት በኋላ ደም የመፍሰስ ሁኔታ ሊታይ ይችላል፡፡
- ወትሮው የሚታየው የማህፀን ፈሳሽ ብዛት መጨመር፣ ቀለሙን መቀየር እንዲሁም መጥፎ ሽታ መከተል ሊታይ ይችላል፡፡
- ሁኔታዎች እየተባባሱ በሄዱ ቁጥር በማህፀን አካባቢ ህመም መሰማት፡፡ ይህም በአብዛኛው በአንድ ወገን ብቻ የሆነ የህመም ስሜት ሆንና ወደ ወገብና ወደ እግር የመሰራጨት ባህሪ ይኖረዋል፡፡
- እንዲሁም ውሃ ሽንትና አይነ ምድርን መቆጣጠር የማይቻልበት ሁኔታ እንዲሁም በማህፀን በኩል አይነ ምድር ማየት ፊስቱላ መፈጠሩንና ሁኔታው መባባሱን ሊያመላክት ይችላል፡፡
- አጠቃላይ የሰውነት ድካም ስሜት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የሰውነት ክብደት እጅግ በጣም መቀነስ እንዲሁም ደም ማነስ በብዛት የሚታዩ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

የማህፀን በር ካንሰርን ለመከላከል አልያም በጊዜ ለማወቅ የሚረዱን መፍትሄዎች

የማህፀን በር ካንሰር ቀስ እያለና ጊዜውን እየወሰደ የሚባባስ ችግር እንደመሆኑ መጠን አንድ ሰው ምንም አይነት ስሜት የለውም ማለት ጨርሶ ምንም አይነት አደጋ ላይ አይደለም ማለት አይደለም፡፡ ለዚህም ከዚህ በታች ሁኔታውን ለመከላከል ወይም በጊዜ ለማወቅ የሚረዱንን መንገዶች እንመለከታለን፡፡

- ከላይ የተጠቀሱትን ለማህፀን በር ካንሰር ያጋልጣሉ የተባሉትን ነጥቦች ከግንዛቤ በማስገባት አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ
- በአሁኑ ወቅት ባደጉ ሀገሮች ውስጥ የማህፀን በር ካንሰር መንስኤ የሆነውን ቫይረስ የሚከላከል ክትባት በዓለማችን ዝግጁ ሆኖ ቢገኝም ይህ ክትባት ባደጉ ሀገሮች ውስጥ ብቻ በመገኘቱና እንዲሁም ዋጋው ከፍተኛ እንደመሆኑ ሀገራችን ላለው ሁኔታ እንደ መከላከያ ዘዴ ልንጠቅሰው አንችልም፡፡
- ማንኛውም ዕድሜው ከ18-40 ዓመት የሆናት ሴት ቢያንስ በየ3 ዓመቱ የማህፀን ሐኪም ጋር በመሄድ አጠቃላይ የማህፀን ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
- ማንኛውም ከ18-65 የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለች ሴት ወይም የግብረ ስጋ ግንኙነት ከ18 ዓመቷ በፊት የጀመረች ሴት ለመጀመሪያው 3 ዓመታት በየዓመቱ የሚደረግ የፖፕ ስሚር ምርመራ ማድረግ፣ ለሶስት ተከታታይ ዓመታትም ምንም አይነት ምልክት ያልታየ እንደሆነ ከዛ በኋላ በየ3 ዓመቱ ይህንን ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ አብዛኛው ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶች ላይ ይህ ምርመራ ወሳኝነቱ እየቀነሰ ይሄዳል፡፡
ከላይ እንደተጠቀሰው ይህ የማህፀን በር ካንሰር ምንም አይነት ስሜት ላይኖረው እንደመቻሉ መጠን በየ1-3 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የፓናስሚር የተባለው ምርመራ ከመጣ በኋላ የማህፀን በር ካንሰር ሳቢያ የሚከተለውን የሞት ቁጥር 50 በመቶ ቀንሶ እናየዋለን፡፡
ይህ ምርመራ በመሰረቱ ትንሽ እንጨትና እንዲሁም አነስተኛ ብሩሽ በመተቀም ከማህፀን በር ላይ ናሙና የሚወስድበት የምርመራ አይነት ሲሆን በምርመራው ወቅት ህመም አለ እንኳን ብንል በጣም አነስተኛ የህመም ስሜት የሚያስከትል የምርመራ አይነት ነው፡፡ ይህ ከማህፀን በር የተወሰደው ናሙና በማይክሮስኮፕ ከተመረመረ በኋላ አንዳች አይነት ጥርጣሬን የሚያስከትል ሁኔታ የተፈጠረ እንደሆነ በትንሽ መሳሪያ ተጠቅሞ እንደየአስፈላጊነቱ የታየ ናሙና ወስዶ በደንብ ማጤን ተገቢ ነው፡፡
በአብዛኛው ሴቶች ፓፕስሚር ምርመራ ከማድረጋቸው በፊት ለ24 ሰዓታት ማህፀናቸው ባይታጠቡ እንዲሁም በማህፀን የሚገባ ምንም አይነት መድሃኒት ባይጠቀሙ ይመረጣል፡፡

ይህ ችግር በሚከሰትበት ወቅት ምን ማድረግ ተገቢ ነው?
አንድ ሴት የማህፀን በር ካንሰር አላት ካልን የሚቀጥለው እርምጃ የሚሆነው የካንሰሩ ደረጃ ምን ላይ ነው የሚለውን ማወቅ ይሆናል፡፡ ይሄም የተለያዩ ምርመራዎችን በማድረግ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ በመቀጠል ሐኪምዎን አማክረው እንደየአስፈላጊነቱና እንደየደረጃው ተገቢውን መፍትሄ ማግኘት ያስፈልጋል፡፡
ለዚህም ከላይ እንደተጠቀሰው በየጊዜውና እንደየአስፈላጊነቱ ምርመራ ማድረግ ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ ማንኛውም አይነት ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎችና ስሜቶች በሚከሰትበት ወቅት በቶሎ የህክምና ባለሙያ ማማከር ግድ ይላል፡፡ ለዚህም ሴቶች ሁሌ ለጤናችን ትኩረት እናድርግ እላለሁ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>