ከረ/ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ አ.አ.ዩ
በኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ በሱማልያ፣ በጅቡቲና የመን የሚዘወተረው አነቃቂው ጫት ምሥራቅ አፍሪካን አልፎ አውሮፓን ሲያስጨንቃት ኖሯል፡፡ ዛሬ ግን የጫት አድባር በአውሮፓ አልቆመለትም፡፡ ከአውሮፓሀገሮች እስከ ዛሬ ድረስ ጫትን በህገ-ወጥነት ሳትፈርጅ የቆየችው እንግሊዝ ሰሞኑን የመጨረሻውን ውሳኔ አስተላልፋለች፡፡ ጫትን የቃመም ሆነ የነገደ የሚቀጣና ይህ አደገኛ ዕጽ የተከለከለ መሆኑን ይፋ አድርጋለች፡፡
የጫት ተጠቃሚዎች ጫትን እንደሚያሞካሹት ‹‹ጫትን ስንቅም ንቁ፣ ደስተኛና ተናጋሪ ያደርጋናል›› ቢሉም ከእንግዲህ በኋላ በሀገረ እንግሊዝ ጫትን መቃምም ሆነ ማዘዋወር የተከለከለ ሁኗል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለይ ለእንግሊዝ ገበያ በቀጥታ ከኬንያ የሚያቀርቡ የጫት ገበሬዎች በውሳኔው ተደናግጠዋል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ናሲር አደም የተባለው የካርዲፍ የሶማሌ ማህበረሰብ መሪ አብዛኛዎቹ የሶማልያ ማህበረሰብ አባላት ጫት በመታገዱ ደስተኞች ናቸው፡፡ ጫትን በብዛት መቃም በሰዎች የአእምሮ ህመምና የቤተሰብ መፍረስን ያስከትል እንደነበር ጨምሮ አስረድቷል፡፡
ናሲር እንዳለው በቀድሞ ጊዜ አዛውንቶች ነበሩ የሚቅሙት፣ በአሁኑ ዘመን ግን ወጣቶች ተለቀውበታል፡፡ የእንግሊዝ የሶማሌ ማህበረሰብ ጫት እንደታገድ ሲታገል ቆይቷል፤ ፖሊስ፣ የጤናና የፓርላማ ባለስልጣናት ሕብረተሰቡን በማዘጋጀት በኩል ምን አድርገዋል? ሲልም ጠይቋል፡፡
በተፃራሪው የጫት ኤክስፖርት ነጋዴው ማቲዎስ ጊቶንጋ ‹‹ጫትን ማገድ ሰብአዊነት አይደለም፡፡ የእንግሊዝ መንግሥት ዕገዳውን ቢያንስ እንኳ እኛ እስከምንዘጋጅ ድረስ ለአንድ ዓመት ሊያነሳ ይገባል›› ሲል አምርሮ ተናግሯል፡፡ ሌላኛው ሴት ቤሲያ ካቱሬ ደግሞ ‹‹ተስፋዬን አጥቻለሁ፡፡ ልጆቼን እንዴት እንደምመግብና የትምህርት ቤት ክፍያ እንደምከፍል አላውቅም›› ብላለች እገዳውን ተከትሎ፡፡
የእንግሊዝ የዕጾች ጉዳይ ክትትል ኃላፊ ቺፍ ኮንስታብል አንዲ ቢሊስ ደግሞ ፖሊስ ከጤና ሙያተኞችና ከማህበረሰቡ አባላት ጋር ስለ ዕገዳው ተቀናጅቶ እየሠራ ነው ሲል አስታውቋል፡፡ በነገራችን ላይ በብርስቶል ከተማ ከዚህ ቀደም ጫት የሚሸጡ 30 የንግድ ተቋማት በዕገዳው ምክንያት ሥራቸውን እንደሚያቆሙ ገልፀዋል፡፡
በሀገረ- እንግሊዝ ጫት መታገዱን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ያሰነዘራሉ፡፡ አንዳንዶቹ ጫት አንደ አደገኛ ዕፅ ተወስዶ መታገዱ ትክክል አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ዳኒ ኩሽሊክ የተባለ የፀረ- ዕፅ ዝውውር ፋውንዴሽን ኃላፊ ሲናገር ‹‹አልኮል መጠጥ በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋለ ጫት መታገዱ ትክክል አይደለም!›› ብሏል፡፡ አይይዞም የተወሰኑ ህዳጣን የሕብረተሰብ ክፍሎችን ማለትም ሶማሌውያንና የመናውያንን ጫት ጋር በተያያዘ መወንጀል አይገባም ሲል ተችቷል፡፡
በወጣው የዕገዳ ህግ ጫትን ለመቃም ይዞ የተገኘ 60 ፓውንድ ይቀጣል፡፡ የእንግሊዝ የሀገር ውስጥ ሚንስትር ቴሬዛ ሜይ እንዳሉት ጫት በእንግሊዝ ብቻ ሳይሆን በኔዘርላንድስ፣ በአብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሕብረት ሀገራት፣ በቡድን 8 ሀገራት ማለትም ካናዳና አሜሪካን ጨምሮ ጫትን አግደዋል፡፡ በአዲሱ ህግ መሰረት በእንግሊዝ ሀገር ጫትን ማዘዋወር ለ14 ዓመት እስራት እንደሚዳርግ ታውቋል፡፡
በሀገራችንም ሆነ በአካባቢው ሀገሮች በስፋት የሚመረተውና ኤክስፖርት የሚደረገውን ጫት ማገድ ለምን አስፈለገ? ብሎ መጠየቅ ተገቢነት አለው፡፡
በብዙዎች ዘንድ ካት፣ በሀገራችን ደግሞ ጫት፣ በኬንያ ሚራ የሚባለው ተክል እጅግ ስለ ተከሉ ሲንቆላጰስ ደግሞ ‹‹የአረቦች ሻይ›› በመባል ይታወቃል፡፡ ጫት በበለፀጉት ሀገራት ቢታገድም በሀገራችንና በአካባቢው መመረቱና ጥቅም ላይ መዋሉ ቀጥሏል፡፡ በአብዛኛዎቹ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከጫት ይልቅ አልኮል ጉዳት አለው ይባልለታል፡፡ ጫት እንደ ቡናና ሻይ ሁሉ ጉዳት የለውም የሚሉ ሞልተዋል፡፡
በእንግሊዝ የዕጽን አላግባብ መጠቀም አማካሪ ምክር ቤት ግምት ወደ ሀገረ- እንግሊዝ በዓመት 2,560 ቶን ጫት ይገባል፡፡ ከዚህ ውስጥ የእንግሊዝ መንግስት 2.5 ሚልዮን ፓውንድ ቀረጥ ያገኝበታል፡፡ ብዙ በእንግሊዝ የሚኖሩ ሱማልያውያን፣ ኢትዮጵያውያንና የመኖች በጫት ንግድ የሚተዳደሩ በመሆኑ እነዚህን ነጋዴዎች ስራ ፈት ያደረጋቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ዕገዳው በምሥራቅ አፍሪካ በጫት ምርት የተሠማሩ 500,000 የሚደርሱ ገበሬዎችን ይጎዳቸዋል፡፡
ጫት አእምሮን ይረብሻል፣ ያሰንፋል፣ ድብርት ያሳድራል፡፡ በተጨማሪም አፍን ማሽተት አልፎ ጥርስን ይጎዳል፡፡ ብዙዎቹ ቃሚዎች ጥርሳቸው የሻገተና የወላለቀ ከመሆኑም በላይ የአፍ ካንሰር ያመጣል ተብሎ በተመራማሪዎች ተነግሯል፡፡ ጫት ከአእምሮ ወታወክ (psychosis) በሽታ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው በሚል የተረጋገጠ ማስረጃ ግን አልቀረበም፡፡ በአንድ በየመን ሀገር በተደረገ ጥናትና ለዓለም ጤና ድርጅት የቀረበው ማስረጃ እንደሚያመለክተው 90 በመቶ የሚሆኑ ጎልማሳ ወንዶች ለሦስትና አራት ሰዓታት ጫት ይቅማሉ፡፡ ዶክተር ጓንኤይድ ከሰንዓ ዩኒቨርስቲ ሲናገሩ ‹‹ጫት ቃሚዎች መጀመሪያ ደስታ፣ ከዚያም በድብርት ስለሚያዙ ለአእምሮ መታወክ ተጠቂዎች ሊሆኑ ይችላሉ ብለዋል፡፡ በእንግሊዝ ሀገር የተደረገው ጥናት የሚያመለክተው ብዙ ወጣቶች ከትምህርት እንዲቀሩና ቤተሰቦቻቸው ደግሞ ሥራ ከመሥራት ይልቅ በጫት ደንዝዘው ቤት እንዲውሉ ማድረጉን በተጨባጭ ማስረጃ ያቀርባል፡፡ በተጨማሪም አል-ሻባብ የተሰኘው አሸባሪ ድርጅት በጫት ኤክስፖርት ገቢውን እንደሚያጠናክርም ይጠረጠራል፡፡ አል-ሽባብ ለሽብር ድርጊቱ ማጠናከሪያ ጫትን የሚጠቀም መሆኑ ከተረጋገጠ ጫት- አሸባሪው ዕጽ መባሉ አይቀሬ ይሆናል፡፡