Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በዓሉ ግርማን ለመግደል ሴራ ያስፈልግ ነበር ወይ?

$
0
0

( ከተስፋዬ ተሰማ)

በቅርቡ በኢትዮ ሚዲያ የታዋቂው ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ አሳዛኝ ህልፈት/አሟሟት በተመለከተ “በዓሉ ግርማን የበሉት ጅቦች አልጮህ አሉ” በሚል ርእስ አንድ ጽሑፍ ቀርቦ ነበር። ይሄ ጽሁፍ የቀረበው በማን፣ በየትኛው የስነፅሁፍ ወይም የጋዜጠኝነት መስፈርት ተመዝኖ እንደሆነ ባይታወቅም “ድንቅ ጽሁፍ” የሚል ክብር ተሰጥቶታል። ይህን ጽሁፍ የፃፈው አበራ ለማ ይባላል። ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ በተገደለበት ዘመን በአንድ መስሪያ ቤት ህዝብ ግንኙነት ውስጥ ይሰራ የነበረ ነው።

አበራ ያቀረበውን ጽሁፍ ሳነበው ታዋቂው የህግ ባለሙያ አቶ አለማየሁ ዘመድኩን (አሌክስ) እየደጋገመ የሚነግረኝ ቀልድ ለበስ ቁምነገር ትዝ አለኝ፤ አሌክስ ለፍትህ የቆመ እውነተኛ ሰው ብቻ ሳይሆን ትልልቅ ቁምነገሮችን ለዛ ባለው ቀልድ የመግለጽ ችሎታም ያለው ሰው ነው። አሌክስና እኔ ብዙ ጊዜ ሻይ እየጠጣን ስለሃገራችንና ስለዓለም ሁኔታ የምናወራቸው የጋራ ወዳጆች አሉን። ሁለቱም ጋዜጠኞች ናቸው። አንደኛው ብዙ ነገር የሚያውቅ፣ በምክንያት የሚያምን፣ሃሳቡን በጥሩ ሁኔታ የሚገልጽ ነው። ሌላው ደግሞ ስሜታዊና አሰልቺ ነው። አሌክስ የሁለቱን ሰዎች ልዩነት ለዛ ባለው ቀልድ ለመግለጽ እንዲህ ይለኛል፤ «ስማ ምናለበት ጋዜጠኝነት እንደወታደርነት አስር አለቃ፣ ጄኔራል..የሚባል የማዕረግ ስም ቢኖረው?.አሁን እነዚህ ሰዎች ሁለቱም ጋዜጠኛ ይባላሉ?» ይለኛል፤
bealu girma 1
ጋዜጠኛ አበራ የፃፈው ፅሁፍ 16 ገጽ ያለው፣ በአራት ዋና ዋና ክፍል ተከፍሎ የሚታይ ነው። ፅሁፉን በአጭሩ፣ በጨዋነትና በቅንነት ስንፈትሸው ሶስት መልክቶችን በአንድነት የያዘ ይመስላል። በስነፅሁፍ አንድ ፀሐፊ በፅሁፉ ሊነግረን ከሚፈልገው መልክት ውጭ ሌሎች ተጨማሪና ዋና መልክቶች ሲኖሩት ፅሁፉ(intentional fallacy) አለው ይባላል። የአበራ ለማ ጽሁፍ የመጀመሪያ መልእክቱ ታዋቂው ደራሲና ጋዜጠኛ በዓሉ ግርማ የተገደለው የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ ኰ/ል መንግስቱ ሃ/ማርያም፣ በወቅቱ የነበሩ ከፍተኛ የደርግ ባለስልጣናት፣ ማንነታቸውን ግልጽ ያላደረገልን በዓሉን የሚጠሉ ሰዎች፣ ጥቅም የሚፈለጉ የበዓሉ ጓደኞች፣ የስራ ባልደረቦችና (በጊዜው የማስታወቂያ ሚ/ር መስሪያ ቤት ባለስልጣኖች የነበሩ) ሰዎች በመተባበር በተለየ ሴራ ነው። እኔ ይህን ሴራ ደርሼበታለሁ ነው።

ሁለተኛው መልእክቱ ደግሞ የበዓሉ አሟሟት ግልጽ እንዲሆን የደርግ ባለስልጣናት (በሱ አጠራር ትልልቆቹ ጅቦችና ጓደኞቹ፤ የስራ ባልደረቦቹ አሁንም በሱ አጠራር ትንንሾቹ ጅቦች በዓሉ እንዴት እንደተገደለ፣ ለምን እንደተገደለ፣ ማን እንደገደለውና ማን እንዳስገደለው ለኢትዮጵያ ህዝብና ለበዓሉ ቤተሰቦች ምስጢሩን የመናገር ታሪካዊ ግዴታ አለባቸው፤ እኛም እየጠበቅናቸው ነው የሚል ትእዛዝ አዘል ጥያቄና የአንድ ወገን ክስ ነው። የመጨረሻው ምናልባትም የዚህ ጽሁፍ ዋናው መልክት ጋዜጠኛ አበራ በተለያዩ ምክንያቶች ከቀድሞ የማስታወቂያ ሚ/ር አለቆቹና ከተወሰኑት ደራሲያን ጋር ያለውን ግጭት በቂም ደረጃ ይዞ፣ አሊያም ባለው የፖለቲካ አቋም በኢህአዴግ ውስጥ ያለውን ታማኝነት ለማሳየት እነሙልጌታ ሉሌን መስዋእት አድርጐ በኢህዴግ ለመሰዋት የበዓሉን ስም አስታኰ ስማቸውን ለማጥፋት የፃፈው ጽሁፍ ይመስላል።

በእርግጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ኢትዮጵያውያን ያለምንም ምክንያትና ያለበቂ ምክንያት የፍትህን አደባባይ እየታሰሩ፣ እየተገረፉና እየተገደሉ እንዲሁም አገዳደላቸው ምስጢር እንደሆነ ቀሮቷል። እንዳለመታደል ሆኖ ይህ አሳዝኝ ድርጊት አሁንም በኛ ዘመን ቀጥሏል። በደረግ ዘመን የአምባገነኖቹና ነፍስገዳዩቹ ሰለባ ከሆኑት ንፁሃን ዜጎች ውስጥ አንዳንዶቹ ለሃገራቸው ብዙ የደከሙና ሽልማት የሚገባቸው ነበሩ።በህይወት ቢኖሩ ለሃገራቸው ብዙ የሚጠቅሙ ነበሩ። በጣም የምንወደውና የምናደንቀው ታዋቂው ጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማም ያለበቂ ምክንያት በግፍ ከተገደሉት የሀገራችን ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው። የደራሲ በዓሉ ግርማ ጉዳይ የቤተሰቦቹ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳይ ነው። በዓሉ ግርማን የሚያክል በኢትዮጵያ ጋዜጠኛነትና ስነጽሁፍ ታላቅ ቦታ የነበረው ሰው እንደዋዛ ወጥቶ መቅረቱ ወይም ያለበቂ ምክንያት መገደሉ የሁላችንም ሃዘንና የልብ ስብራት ነው። የዚህን ታላቅ ሰው የአገዳደል ምስጢር ማወቅና ለማወቅ ጥረት ማድረግ መቀጠል ያለበት በመሆኑ ሁሉም ወገን ሃላፊነት እንዳለበት እሙን ነው።

በዓሉ ግርማ ከሞተ ከ30 አመት በኋላ የተፃፈው የጋዜጠኛ አበራ ለማ ጽሁፍ አሳዛኙን የበዓሉ ግርማን አሟሟት ምስጢር የሚፈታ ሳይሆን ነገሩን የበለጠ የሚያወሳስበውና አንባቢውን ግራ የሚያጋባ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።በአሉ ግርማ የተገደለው በሴራ ነው ብሎ ቃላቶችን እየቆራረጠና እየቀጠለ ሊያሳየን የሚፈልገው ነገር ምክንያታዊ ያለሆነና እውነትነት የሌለው ሁላችንም ከምናውቀው ወፍ በረር አሉባልታና ወሬ ያለፈ አዲስ ነገር የለውም። አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል እንደሚባለው አንድ ሰው ሲናገር/ሲጽፍ የተናጋሪው ወይም የፃሀፊውን ማንነት ከፅሁፉ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። አበራ ለማ ይህን ጽሁፍ ሲፅፍ የበዓሉ ግርማ አሳዛኝ የአሟሟት ምስጢር አሳዝኖትና አሳስቦት መሆኑን እንድንጠራጠር የሚያደርጉ ጭብጦች ግን አሉ።

በዓሉ ግርማ ያለበቂ ምክንያት መሞቱ ያሳዝነኛል፣ የሚል ሰው ሌሎች ንጹሃን ሰዎችን ያለበቂ ማስረጃ “የበዓሉ ገዳዮች” እያሉ መወንጀልም አግባብ አይደለም። ከወንጀሎች ሁሉ ወንጀል- ወንጀለኛ ያልሆነን ሰው “ወንጀለኛ” ማለት ነው! የበዓሉን ስም እየጠቀሱ “የበዓሉ ጠበቃ ነኝ” በማለት የበዓሉን ጉዳይ አስታኮ የግል ቂም መወጣጫና የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ ለማድረግ መሞከር – በዓሉን እንደገና የመግደል ያክል ነው። በዚህ ቅኝት የተፃፉ ፅሁፎች በህዝቡ ውስጥ ሲሰራጩ የበዓሉን የአሟሟት ምስጢር የበለጠ ውሉን እያጠፋውና እያወሳሰበው ይመጣል የሚል ስጋት አለኝ። በዓሉ ግርማን በተመለከተ እስከአሁን ያልተመለሱ ጥያቄዎች ስላሉ እነሱ እስኪመለሱና የበዓሉ ግርማ መጨረሻ እስኪታወቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚችለውን ማድረግ አለበት። ይሄ ጥረት እንዲሳካ ከተፈለገ ከምንም አይነት ፖለቲካ ጋር ንክኪ የሌላቸው፣ ነፃና ገለልተኛ ሰዎች በተለይም የሀገራችንን ታሪካዊና ወቅታዊ ሁኔታ በትክክል የሚረዱ፣ ከቂምና ጥላቻ ነፃ የሆኑ ወጣት ምሁራኖች ማሳተፍ ያስፈልጋል። እዚህ ላይ ሁላችንም ልንረዳው የሚገባ አንድ ቁም ነገር ያለ ይመስለኛል።

እንደ አንድ መጠነኛ የስነጽሁፍ ግንዛቤ ያለው ተራ ዜጋ የጋዜጠኛ አበራን ያለፈ ታሪክ፣ የግለሰቡን ባህርይ፣ ድሮ የነበረውንና አሁን እያራመደ ያለውን የፖለቲካ አቋምና እንቅስቃሴ፣ ይህን ጽሁፍ ለምን አላማና ማን ልኮት ፃፈው የሚለውን የሰውዬው የግል ታሪክ ላይ ብዙ ጊዜ ሳላጠፋ የጽሁፉን ይዘት ብቻ ሚዛን ላይ አስቀምጬ ለማየት ሞከርኩ። ይኸው ጽሁፍ እንኳን እውነተኛውን የበዓሉ ግርማን አሟሟት ሊነግረን እራሱ በውሸት ስማቸውን ሊያጠፋቸው የፈለጋቸውንም ሰዎች ሰሩት የሚለውን የውሸት ወንጀል ሴራም በግልጽ የሚያሳይ አይደለም። ፅሀፊው ይህን ትልቅ አጀንዳ ያለውን ጽሁፍ ሲጽፍ በቂ ዝግጅት አላደረገም፣ አለኝ የሚለውን እውነት የሚያጠናክርለትም የተለየ ማስረጃ የለውም። የአበራ ጽሁፍ በልብወለድም ይሁን በኢልብወለድ መሰረታዊ የጽሁፍ ሚዛን ሲመዘን ደረጃውን ያልጠበቀ ተራ የፕሮፖጋንዳ ጽሁፍ ነው። ጽሁፉ በእውነተኛ መረጃ ድርቅ የተመታ በመሆኑ እንደ አጭር ልብወለድ መለካቱ የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። የሚያሳዝነው ነገር ፅሁፍ እንደ ልብወለድ ቢወሰድ እንኳ ደካማ ከሚባሉት የልቦለድ ፅሁፎች የሚመደብ ነው፡:

ይሄ በዓሉን ለመግደል የተጠነሰሰ ሴራ የሚባለው ነገር ግልጽ ሆኖ ያልተቀመጠ እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው። ለመሆኑ በአሉ ግርማን ለመግደል ይሄ ሁሉ ባለስልጣን የሚሳተፍበት ሴራ አስፈላጊ ነበር ወይ? ሴራው ቢኖርስ ይሄን ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣናት የተሳተፉበትን ሴራ ተራው ጋዜጠኛ አበራ ለማ ለማውቅ እድሉና አጋጣሚው ነበረው ወይ? አበራ የሌሎች ሰዎችን ማስረጃ በመውሰድ እሱ ከሚያውቀው ነገር ጋር በማገናኘት መረጃ ትንተና ነው የሰጠው ቢባል እንኳ ለመሆኑ አበራ እንደምንጭ የተጠቀመበት መረጃ ምን ያክል እውነተኛ ነው? ይህን ያገኘውን መረጃ አበራ በትክክል ለመተርጎማና ለመትንተን ችሎታውና ፍላጎቱ አለው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ብዙ የሚጠየቁ ጥያቄዎች፣ ብዙ ያልተመለሱ ነገሮች አሉት።

በኔ ግምት አንድ ቅን ዜጋ ይህን ጽሁፍ ሲያነብ መጀመሪያ አበራን የሚጠይቀው ጥያቄ “ለመሆኑ በደርግ ዘመን አንድ ደራሲ ለመግደል ይህ ያክል የተቀነባበረ ሴራ አስፈላጊ ነበር እንዴ?.” የሚል ነው። ጋዜጠኛ አበራ የደርግ ስርአትን ጠንቅቀው የሚያውቁ ንጹሃን ዜጎችን ያለምንም ምክንያት ያለምንም ሴራና አድማ በቀላሉ የመግደል ዘመቻው ውስጥ ተሳታፊ ስለነበሩ ጥያቄውን በቀላሉ ይመልሱታል። በነገራችን ላይ ጋዜጠኛ አበራ የቀይ ሽብር ነፍሰ ገዳዮች ጉዳይ የያዙት ልዩ አቃቤ ህግ ግርማ ዋቅጅራ ክስ ውስጥ እነማህደር የተባሉትን ወጣቶች በማስገደል ስማቸው በ27ኛ ተርታ ተመዝግቦአል። ከኢህአፓ መስራች አንዱ የሆኑትም ክፍሉ ታደሰ ደግሞ በመጽሃፋቸው ላይ አበራ ለማ ማስታወቂያ ሚ/ር አካባቢ በ07 ቀበሌ ቀንደኛ ነፍሰ ገዳይ እንደነበሩ ጠቅሰዋቸዋል። በአዲስ አበባ ከተማ የብዙ ወጣቶችን ደም የጠጣው የእርገጤ መድበው የቅርብ ጓደኛ እንደነበሩም የሚያውቋቸው ሁሉ ስለሚናገሩ በደርግ ጊዜ እንኳን እነኰ/ል መንግስቱ እነ አበራ እንኳን የሰዎችን ነፍስ በቀላሉ ማጥፋት የሚችሉበት ዘመን ስለነበረ የጋዜጠኛ/ደራሲ በዓሉ ግርማም ህይወት እንዲሁ በቀላሉ መቀጠፉን ለማሰብ አስቸጋሪ አይደለም።

ሌላው ይህን ጽሁፍ ተራ ውሸት የሚያደርገውና አጠቃላይ የጽሁፉን ይዘት የሚያናጋው በዓሉ ግርማ የተገደለው በተቀነባበረ ሴራ ነው ብሎ ሊነግረን የሚፈልገው ሃሳብ በግልጽ የተቀመጠ አለመሆኑ ነው፤ “ሴራውን” በጥንቃቄ ስንመረምረው ሁለት አይነት ይመስላል፤ በሴራው ውስጥ ማን ከማን ጋር ተባብሮ እንዳቀነባበረው በግልጽ አላስቀመጠውም። በጥንቃቄ ስላልዋሸ ሴራዎቹ የተለያዩና እርስ በርስ የሚቃረኑ ሆነውበታል። አንደኛው ሴራ መንግስቱ የተሳተፉበት ሆኖ ምንጩ ከላይ ይመስላል፤ አበራ በአጽሁፉ ገጽ 7 ላይ « ሊቀመንበር መንግስቱ በዘመነ ስልጣናቸው እነበዓሉ ግርማን ለማሰውገድ እነሙልጌታ ሉሌን ተጠቅመው» በዛው ገጽ ላይ በዓሉ ግርማ ለማጥፋት ከነኰ/ል መንግስቱ ጋር ከመሰጠሩ ጓደኞቹ ጋር ሙልጌታ ሉሌ አንዱ እንደሆነ በዚህ መጽሀፍ ገጽ 59 ላይ ይስተዋላል» ይለናል።

ሁለተኛው ሴራ የደርግ ባለስልጣኖች በዓሉን ለማስገደል ኰ/ል መንግስቱን ለማሳመን ያደረጉት ይመስላል። የዚህ ሴራ ምንጩ ከስር ይመስላል። በአላማም ሆነ በአቀናባሪዎቹ ማንነት ከአንደኛው ሴራ የተለየ ነው።ሁለተኛው ሴራ በአበራ ፅሁፍ ላይ እንደዚህ ተቀምጣል። « ኦሮማይ ብዙ በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ስለሚነካካ ብዙ ሰዎችን አስቆጥቷል….እንደተለመደው ሊያጠፉት የሚፈልጉ ሰዎች ተሰባሰቡና መከሩ፤ ሁሉም በየተራ መንግስቱ ጋር እየሄዱ አሉታዊ የሆኑ ነገሮችን እንዲነግሩት ተደርጐ በዓሉን የማጥፋቱ ሴራ ተቀነባበረ» ይሄ ሴራ መንግስቱን ብቻ ሳይሆን ጓደኞቹንም ለማሳመን ጥረት ተደርጓል፣ “የቅርብ ጓደኞቹን አሳመኑና” ይህ ሴራ የደርግ ባለስልጣናት መንግስቱን ለማሳመን በራሳቸው በመንግስቱ ላይ የተጠነሰሰ ሴራ ነው። ለበዓሉ ቅርብ የሆኑና ጓደኞቹን ጭምር አሳመኑና ሁሉም በየተራ መንግስቱ ጋር እየሄዱ ስለበዓሉ አሉታዊ የሆኑ ነገሮችን እንዲነግሩት ተደርጐ በዓሉን የማጥፋቱ ሴራ ተቀነባበረ፤ ኦሮማይ ማለት አለቀለት፣ አበቃለት ማለት እኮ ነው እያሉ መንግስቱን ጠመዘዙት፣ መንጌ ይህን አይወድም» እዚህ ላይ የሴራው ጠንሳሾች የደርግ ባለስልጣኖች ናቸው፤ አላማው መንግስቱን መጠምዘዝ ነው፤ በዚህ ሃሳብ መንግስቱ ስሜታዊ እንጂ ሴረኛ አይደሉም።
ስለ በአሉ ግርማ አሟሟት ከነገርከን ከነዚህ እርስ በርስ ከሚቃረኑ ሁለት ሴራዎች የትኛውን አምነን እንቀበልህ? የመጀመሪያውን ማለትም በመንግስቱና በጋዜጠኛ ሙልጌታ ሉሌ መካክል የተደረገውን? ወይስ በመጽሀፉ በተናደዱት የደርግ ባለስጣናት መካከል የተደረገውን ሁለተኛውን ሴራ? ለወደፊቱ እንዲህ አይነት ከባድ ውሸት ስትዋሽ ሰዎች ሊነቁብኝ ይችላሉ ብለህ መጠንቀቅ ጥሩ ነው። ለግዜው የመጀመሪያውን ሴራ ትክክል ነው ብለን እንውሰደው፤ ምክንያቱም ከመጀመሪያው ሴራ ተነስተህ የራስህ የሆነ ሌላ ሰዎችን የሚወነጅል ተከታታይ ታሪክ በጽሁፉ ውስጥ ስለጨመርክ።
ኰ/ል መንግስቱና ታዋቂው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ በአሉን ለማጥፋት በመንግስቱ አማካይነት ሴራ ተጠነሰሰ። መንግሥቱ በአሉን ማጥፋት ሲያቅታቸው ለሙልጌታ በአሉን እንድገድል ከረዳኸኝ የበአሉን ስልጣን እሰጥሃለሁ አሉት፤ ሙልጌታ የበአሉን ቦታ ይመኝ ስለነበር በሴራው ውስጥ (ለመንግስቱ ምን እንድሚረዳቸው ግልጽ አይደለም) ተሳተፈ፤ በኋላ መንግስቱ በአሉን ካስወገዱ በኋላ ለሙልጌታ የገቡትን ቃል ሳይፈጽሙ ቀሩ፤ በዚህ ምክንያት ሙልጌታ ሉሌ ቂም ይዞ ነበር፤ ኢህዴግ ሲገባ “አጥፍቶ መጥፋት” የሚል መጽሃፍ ፃፈባቸው፤ በዚህ ምክንያት በአሉን ለመግደል ያሴሩት ሰዎች ተጣሉ የሚል ለማመን የሚያስቸግር ቅዠት የሚመስል መላምት ቃላት በመቀጣጠልና በመቆራረጥ ሊፈጥር ይፈልጋል።
ለመሆኑ ኰ/ል መንግስቱ በአሉ ግርማን ለምን መግደል አስፈለጋቸው? በመጽሃፉ ውስጥ ስለ እርሳቸው ጥሩ ነገር ነው የጻፈው። እሺ መግደል ፈለጉ የሚለውን እንመን። በአሉን ለመግደል ኰ/ል መንግስቱ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሴራ ማድረግ ለምን ያስፈልጋቸዋል? ሴራ ማድረግ ቢያስፈልጋቸው በሴራው ውስጥ እነሙሉጌታ ሉሌ ምን ይጠቅሟቸዋል? የሚሾሙት ራሳችው፣ የሚሽሩት ራሳቸው፣ የሚገድሉት ራሳቸው ሆነው ለመሆኑ መንግስቱ ሃ/ማርያም በአሉን ለማጥፋትና ሙልጌታ ሉሌን ለመሾም ምን ሴራና ምስጢር ያስፈልጋቸዋል? ይሄ አላግባብ የመንግስቱን መረን አልባ ስልጣን ማኰራመትና በአሉንና ጋዜጠኛ ሙልጌታን ስልጣን መለጠጥ ይመስለኛል። አበራ ይህን የመንግስቱንና ሙልጌታን ሴራ አገኘሁት የሚለው በአንድ ምንጭ ዙሪያ ጥምጥም ሄዶ ነው። ከቀድሞ አንድ የደርግ ባለስልጣናት ጋር ቃለመጠይቅ አድርጋለች የሚላት በእሱ አጠራር “መርማሪ ፀሐፊ” ገነት አየለ ናት። ጓድ ቁጥር 53 የሚል ኮድ ተሰጥቶታል። ስለዚህ ሰው ኋላ እመለስበታለሁ፡፤

ለጊዜው ይሄ ጓድ ቁጥር 53 እውነተኛ ሰው ነው (ፈለቀ ገድለጊዮርጊስ ነው) የተናገረውም እሱ ነው ብለን ብንቀበለው ይሄን ሃሳብ እንደተለመደው እርስ በርሱ ይጋጭል። መንግስቱ ሃ/ማርያም 17 ዓመት ሙሉ ብቻቸውን የፈለጉትን እየገደሉ፣ የፈለጉትን እየሾሙ፣ ያሻቸውን እያደረጉ የኖሩ ፈላጭ ቆራጭ መሪ ከነስማቸው “ቆራጡ መሪ” አንድ በአሉን ለማስወገድ ያውም ሌሎቹ የደርግ ባለስልጣናት ፍላጐት ተጨምሮበት ሴራ ውስጥ ገቡ በሴራው ምንም ጥቅም የሌላቸውን ግለሰቦች ሴራ ውስጥ አስገቡ ነው የሚለን። ይህን ሴራ አለ ብሎ ማሰቡ በተለይ ደግሞ ከዚህ ሴራ ተነስቶ በመንግስቱና ጋዜጠኛ ሙልጌታ መካከል ከበአሉ ሞት በኋላ መካካድና ጭቅጭቅ ተፈጠረ ብሎ ሌላ ሴራ ከአየር ላይ ዘግኖ ማምጣቱ ሞኝነት ነው፤ ይህን ሃሳብ ሰው ያምንልኛል ብሎ ማሰቡ እብደት ነው።

በመቶ ሺህ የሚቆጠር ሰራዊት የሚያዙ፣ የጥይትን እርሳስ እንደመፃፊያ እርሳስ የሚጠቀሙ ታላላቅ የጦር ጄኔራሎችን በአንድ ቁራጭ ወረቀት አዘው በአንድ ጀንበር የሚያስፈጁት ኰ/ል መንግስቱ ሃ/ማርያም በአሉ ግርማን ለማስገደል ከነሙልጌታ ሉሌ ጋር በማሴር ጊዜ ሲያጠፉ ነበር የሚል ታሪክ ጽፎ ማቅረብ የአንባቢውን ጊዜ ማጥፋት ይመስለኛል። በነገራችን ላይ “መርማሪዋ” ጋዜጠኛ ለሁለተኛ ጊዜ ባሳተመችው መጽሃፍ ላይ መንግስቱን ስለሙልጌታ ሉሌ አንስታባቸው ነበር፤ « እኔ ከርሱ ጋር ምንም ግንኙነት የለኝም፤ ከሱም ጋር ምሳ የበለሁበት ጊዜ የለም፤ ሾምነው ምን እንደሚፈልግ አላውቅም» ነው ያሉት።እና ገነት በመጀመሪያው መጽሃፍ ስለ ሁለቱ ሰዎች የነገረችንን በሁለተኛውም መጽሃፍ ኰ/ል መንግስቱ ያፈርሱታል። በርግጥ ታዋቂው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ “አጥፍቶ መጥፋት” የሚል መፅሀፍ ጽፎ መንግስቱን በስልጣን ዘመን ያጠፉትን ጥፋት በዛ ልዩ የጽሁፍ ችሎታው በማስቀመጡ ደስተኛ እንዳልነበሩ ይታወቃል። ይሄን ቅሬታ ወስዶ ከበአሉ ሞት ጋር በማገናኘት ሴራ መፍጠር የአበራን ሴረኛነት ነው የሚያሳየን።

ከኰ/ል መንግስቱና ከጋዜጠኛ ሙልጌታ ሉሌ ሴራ ሳልወጣና ወደ ሌላ ሃሳብ ሳልሄድ የአበራ የፈጠራ ሴራ አንድ ነገር ልበል፤ ጓድ ቁጥር 53 ይኑር አይኑር የማይታወቀው የደርግ “ቱባ” ባለስልጣን የሰውን ፍላጐት የማንበብ ልዩ የነብይነት ፀጋውን ተጠቅሞ ይሁን እራሱ ጋዜጠኛ ሙልጌታ ሉሌ ነገሮት እንደሆነ ሳይገልጽልን ጋዜጠኛ ሙልጌታ ሉሌ ለምን የበአሉ ማስገደል ሴራ ውስጥ እንደገባ የሚያሳይ በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ አንባቢ እንዲያስብ ተደርጐ የተሳለ አንድ አረፍተ ነገር አለ። “የበአሉን ቦታ ይመኝ እንደነበረ አውቃለሁ” በአበራ ጽሁፍ ገጽ 6 ላይ በገነት መፅሃፍ ገጽ 59 ላይ ይገኛል።
የአበራ ለማ ዋና አጀንዳ ታዋቂወን ጋዜጠኛ ሙልጌታ ሉሌን የበአሉ ግርማ ሞት ላይ እጁ እንዳለ በማስመሰል ያለ የሌለ እውቀቱንና አረፈተ ነገር የመቀጣጠልና የመቆራረጥ ጥበቡን ይጠቀማል። እንዳለመታደል ሆኖ ዓ/ነገርን ቆራርጦና ቀጣጥሎ ሊነገረን የፈለገው ሙልጌታ ሴራ ውስጥ የነበረው የበአሉን ቦታ ፈልጐ ነው የሚለውን ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ውሸት የሚያደርግ እርስ በርሱ የሚቃረን ሌላ መረጃ አስቀምጧአል።

አበራ በጽሁፉ መጀመሪያ በዓሉ የሞተበትን ቀን የካቲት 24 1976 ዓ.ም ነው፤ በ3ኛው ገፅ የመጨረሻው አንቀጽ ላይ ኰ/ል መንግስቱ በዓሉ ግርማ በመጽሃፉ ምክንያት ከስራ እንደተባረረ ይነግሩናል። በአሉን ከስራ ያሰናበቱት ቀን ኰ/ል መንግስቱ እንዲህ አሉት “ባለህበት የሃላፊነት ቦታ የምትቆይበት ሁኔታ ሊኖር አይችልም” ብለው ጳጉሜ 5 ላይ ከስራ አሰናብተውታል። በሌላ አገላለጽ በዓሉ በመፅሃፉ ምክንያት ከመገደሉ ከ6ወር በፊት ከስራ ተባሮአል፤ የኔ ጥያቄ ሙልጌታ ሉሌ ከስራ ከተባረረ 6ወር ያለፈውን ጓደኛውን ቦታ ለመያዝ ጓደኛውን አስገደለው የሚል ነገር መናገር ለሰው ምን ትርጉም ይሰጣል?
አበራ የበአሉ አሟሟት ሴራ (የተነሳበትን ሃሳብ) ያጠናክርልኛል ብሎ በዋና የመረጃ ምንጭነት የሚጠቅሳቸው ሶስት ሴቶችን ነው። አንደኛ- የጋዜጠኛና ደራሲ በዓሉ ግርማ ባለቤት ወ/ሮ አልማዝን፣ የበዓሉን ሴት ልጅ ወ/ሮ መስከረም እንዲሁም ስለበዓሉ ጉዳይ ከወ/ሮ መስከረም ኢሜል ውጭ ሁለቱ ጽሁፎች አገር ሁሉ የሚያውቃቸውና 10 አመት ያለፋቸው ታሪኮች ናቸው። የወ/ሮ መስከረም ኢሜልም ስለበዓሉ አሟሟት ፍንጭ አይሰጥም። ጋዜጠኛ አበራ ለማ ከበዓሉ ግርማ ቤተሰቦች ጋር የተለየ ቅርበት ስላለው ያገኘው መረጃ አስመስሎ ያቀረበው የመጀመሪያው ማስረጃ የደራሲ በዓሉ ባለቤት ወ/ሮ አልማዝ በዓሉ ስለመጥፋቱ ደራሲ አስፋው ዳምጤ ያውቃል ብለው በኢህአዴግ ዘመን ለጠቅላይ አቃቤ ህግ ያቀረቡትና ውድቅ የተደረገው ክስ ነው። ሌላው ጋዜጠኛ አበራ ለማ “መርማሪ ፀሃፊ” እያለ የሚያደንቃት ገነት አየለ የመንግስቱ ሃ/ማርያም ትዝታዎች ብላ ያወጣችው መፅሃፍ ላይ ስለበዓሉ የተጠየቁ ጥያቄዎችንና መልሶችን መስረት አድርጐ ነው (በዚህ መፅሀፍ ገፅ59 ላይ የተጠቀሰው ቁጥር53 የሚባል የፈጠራ ሰው በውል ይኑር አይኑር ያለየለት የፈጠራ ሰው የሚመስል ሰው የተናገረው ነገር የሃሳቡ ማጠናከሪያ መሆኑ ነው)
ፀሀፊ ገነት አየለ የበዓሉ ግርማን አሟሟት በተመለከተ ሶስት የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣኖችን አግኝታ 5 ጥያቄዎችን ብቻ ጠይቃለች። አራቱ ጥያቄዎች « በዓሉ ማን ገደለው?» የሚል ተመሳሳይ ጥያቄ ሲሆን አንዱ ደግሞ በጋዜጠኛ አበራ አገላለጽ “መርማሪዋ ጋዜጠኛ” ኰሎኔል መንግስቱን “አፋጠጠቻቸው” የተባለለት “በዓሉ መፅሃፍ እንዲጽፍ አዘውታል?” የሚለው ነበር። አበራ የዚህን ጥያቄና እነኰ/ል መንግስቱ የሰጡትን መልስ መሰረት አድርጐ ነው በዋነኛነት ጽሁፉን የሚጽፈው። መርማሪ የተባለችው ጋዜጠኛ ሶስት የደርግ ባለስልጣኖችን አግኝታ የበዓሉን ግድያ ምስጢር እስከወዲያኛው የሚፈቱ መቶ ጥያቄዎችን መጠየቅ ሲገባት አንድ ጥያቄ ብቻ ሰንዝራ እድሉ እንዲያመልጥ ማድረጓ ያሳዝናል።

መቸም ገነት አየለ በተፈጠረላት አጋጣሚ የደርግ ባለስልጣናትን ስለበዓሉ ጉዳይ መጠየቋ የሚደነቅ ቢሆንም ነገር ግን መርማሪ ጋዜጠኛ (ኢንቬስቲጌቲቭ ጆርናሊስት) የሚለው ስም የሚበዛባትና ጨርሶ ያልነካቸው መሆኑ ሳልገልጽ አላልፍም። አንድ መርማሪ ፀሃፊ ስለሚጠይቀው ነገር በሚገባ የተዘጋጀ፣ የውስጥ መረጃ ያለው መሆን አለበት። መርማሪ ጋዜጠኛ የተባለችው ገነት ግን ምንም አይነት መረጃ እንደሌላት የሚያስታውቀው በአበራ ጽሁፍ ገፅ 3 እንዲሁም በገነት መጽሀፍ ገጽ212 ላይ ያነሳችውን ጥያቄ ስናይ ነው። « ስለዚህ እርስዎ ቀይ ኮከብን በተመለከተ በዓሉ ግርማን መፅሀፍ ፃፍ ብለውታል የሚባለው እውነት ነዋ?» ይላል። ከዚህ ይልቅ “ የበዓሉ መፅሀፍ ኦሮማይ ከመታተሙ በፊት አንብበው እንዲታተም ፈቅደውለት ነበር ወይ?” ተብሎ ጥያቄው ቢቀርብ ኖሮ እንቆቅልሹ ይፈታ ነበር። ለነገሩ ወ/ሮ ገነት ያችኑ ጥያቄ ጠይቃ ተጠያቂው አላስፈላጊ ነገር እንዲያወሩ እድል መስጠት እንጂ- ተከታታይ ጥያቄ (ፎሎው ኦፍ ኮዌስችን) አላቀረበችም። በመሆኑም ጋዜጠኛ አበራ የጋዜጠኛ ገነትን ተልካሻ ጥያቄ መሰረት አድርጐ እጅግ ደፋር ድምዳሜ ላይ መድረሱ አሳፋሪ ነው።

ጋዜጠኛ አበራ ለማ የፅሁፉ ዋና አጀንዳ አድርጐ የተነሳው ገነት አየለ አግኝታ ጠየቀችው ከሚባለው ከሶስቱ የደርግ ባለስልጣኖች አንዱ የሆነውና ስሙ ያልተጠቀሰው “ጓድ ቁጥር 53” የሚባለው ግለሰብ ነው። ይሄ ጓድ ቁጥር 53 በእውን በገሃዱ አለም ያለ ሰው ነው..ወይስ የገነት የፈጠራ ውጤት?..የሚል ጥያቄ ለማንሳት የግድ ጋዜጠኛ ገነት አየለን መሆን አያስፈልግም። ሰውየው እንደተባለው እውነተኛና ያለ ሰው ነው ከተባለ “የበዓሉ ግርማን አሟሟት አውቃለሁ፣ እነሙልጌታ ሉሌ አሉበት” እያለ የሰው ስም እያጠፋ በአንፃሩ የራሱን ስም መደበቁ በጭራሽ ተቀባይነት የለውም። ትክክልም አይደለም። ለበዓሉም፣ ለሚከሰስትም ሰዎች፣ ለደራሲ በዓሉ ቤተሰቦችና ለኢትዮጵያ ህዝብ ሲል አውቃለሁ የሚለውን አደባባይ ወጥቶ ይናገር። ( ለነገሩ ጓድ ቀጥር 53 ስለበዓሉ አሟሟት አውቃለሁ የሚለውን ነገር ለመናገር ድፍረት አግኝቶ ከወጣ በገነት አየለ መጽሀፍ ገጽ 59 ላይ የቀባጠረው ብዙ ነገር ስላለ ለሱ ጥያቄ መልስ ሊያዘጋጅ ይገባዋል) በህግም ቢሆን ገድሎአል ብሎ የከሰሰው ሰው እንጂ ገድለሃል የተባለው ሰው አለመግደሉን የሚያሳይ ማስረጃ ማምጣት አይጠበቅበትም። ስለዚህ በአሉን የበሉት ጅቦች ሳይሆን በአሉን የበሉትን ጅቦች አውቃለሁ የሚለው ሰው የግድ ወጥቶ መናገር አለበት።

የጋዜጠኛ አበራን ጽሁፍ በዓሉ ግርማን ለማስገደል በኰ/ል መንግስቱ ሃ/ማርያምና በሌሎች ታላላቅ የደርግ ባለስልጣኖች እንዲሁም የበዓሉ የቅርብ ጓደኞች፣ ጋዜጠኞችና የማስታወቂያ ሚ/ር ባለስልጣኖች መካከል የተደረገውን ሴራ ሊነግረን ይሞክራል። ከላይ በገለጽኩት መንገድ ህዝብ የሚያውቃቸውን መረጃዎችንና የመረጃ ምንጮችን መሰረት አድርጐ እንደ አዲስ ክስተት ሊነገረን ይሞክራል። ታዋቂው አልበርት አንስታይን “እብደት ማለት አንድን ተመሳሳይ ነገር እየደጋገሙ፣ እያደረጉ የተለየ ውጤት/ አዲስ ነገር መጠበቅ ነው” ይላል። በርግጥ ይሄ ምሳሌ የሚመለከተው በቅንነት – ስህተት ለሚሰሩ የዋሆች እንጂ ለጋዜጠኛ አበራ ለማ አይነቱ ሆን ብሎ ለሚያጠፋ ወይም የተለየ ተልእኮ ላለው ሰው አይደለም። አበራ አምነን እንድንቀበለው የሚፈለገው ሴራ በእውነት ላይ ያልተመሰረተ፣ ለአመታት ሲወሩ ከነበሩት ነገሮች የተለየ አዲስ ነገር የሌለው፣ የመረጃ ምንጮቹ ያልተቀየሩና በስነፅሁፍ ሚዛን ተራ የሚባል ነው። ይሄ ጽሁፍ ለበዓሉ ግርማ ታዝኖና ታስቦም የተፃፈ አይደለም። ብዙ ተራ ስድቦች የሚበዙበት ነው። ሆን ተብሎ በዓሉ ግርማን “አስገደሉ” የሚላቸውን ሰዎች ብቻ ሳይሆን የራሱን የበዓሉን ስም ጥላሸት ለመቀባትና ህዝቡን ለማሳሳት (ግራ ለማጋባት) በተፈጠሩ የውሸት ታሪኮች የታጨቀና የተንሻፈፉ መላምቶች የሚበዙበት፣ በጣም አደገኛ የክርክር ግድፈቶች ያሉት፣ አሰልቺ ቃላቶችና አረፍተ ነገሮች የሚበዙበት፣ ግማሽ እውነቶች በተደጋጋሚ የሚጠቀም ተራ የፕሮፖጋንዳ ፅሁፍ ነው።

በመግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት የጋዜጠኛ አበራ ጽሁፍ አራት ክፍሎች አሉት። የመጀመሪያው ገጽ በበአሉ ሞት እጁ አለበት የሚለውን ደራሲ አስፋው ዳምጤ ይከሳል። ከገጽ2 እስከ 5 ደግሞ “ታላላቅ” ጅቦች የሚላቸውን የደርግ ባለስልጣናት ይከሳል። ከገፅ 5 እስከ 9 ታዋቂውንና አዋቂውን ጋዜጠኛና የብእር አርበኛ የሙልጌታን ሉሌ ስም ያጠፋል። ከገጽ 10 በኋላ ደግሞ “የማስታወቂያና መርሀ ብሄር ሚ/ር ካነሳን ዘንዳ ወደኋላ ዘመን ተመልሰን የጓዳ ምስጢር ሰነድ መፈተሽ የግድ ሊለን ነው” ብሎ በደርግ ዘመን ብቻ ሳይሆን በአጼ ሃ/ስላሴ ዘመን ሁሉ የተከበረውን ታዋቂውን ጋዜጠኛ የገዳሙ አብርሃን ስም ጥላሸት ለመቀባት ይፈለጋል።

በርግጥ አበራ ለማ ይሄ ምኞቱ ብዙ የተሳካለት አይመስልም። አንድ ስለ ኢትዮጵያ መጠነኛ ግንዛቤ ያለው ሰው የአበራን ጽሁፍ ሲያነብ የነዚህን ሰዎች ጥፋት ሳይሆን የአበራ ለማን አጭበርባሪነት ውሸታምነት በተራ ምክንያት ሰዎችን ለማታለል የሚሞክር አላዋቂ ሰውነት ግልጽ አድርጐ ያሳያል። ይሄ ጽሁፍ እንኳን ወንጀለኛ ናቸው ያላቸውን ሰዎች ይቅርና እየታገልኩለት ነው የሚለውን የደራሲ በአሉ ግርማን ገጽታ የሚያበላሽ ሰላማዊውና ተወዳጁ በአሉ ግርማን ባለብዙ ጠላት የሚያደርግ ጽሁፍ ነው።

ስለ በአሉ ግርማ አሟሟት አጣራች የሚላትን ገነት አየለን ቃለምልልስ ዋቢ አድርጐ የሚነሳው የአበራ ለማ ጽሁፍ በአሉ ግርማን የደህንነት ሰራተኛ ያደርግዋል። አበራ ገነት ስለ በአሉ ቃለመጠይቅ ካደረገችላቸው ሰዎች አንዱ የቀድሞ የደህንነት ዋና ሰው ተስፋዬ ወ/ስላሴ ናቸው ይላል፤ በአበራ ጽሁፍ በአሉ ግርማ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር ችግር እንዳለበት ተስፋዬ ወ/ስላሴ ጠቁመውኛል ብሎ ተስፋዬ ወ/ስላሴ ስለበአሉ ለገነት ነግሮት የሚለውን ሀሳብ በራሱ በአበራ ፅሁፍ ገጽ 5 ላይ እንዲህ አስቀምጦታል፤

« በዓሉ መቼም በዚህ መጽሀፉ ብቻ ሳይሆን በሌላ በሌላም..ከእኛ ጋር በመስራቱም ሁሉ ብዙ ሰዎች ጠምደውታል…የስራ ባልደረቦቹም ቅርበት በመፍጠሩ ጥላቻ አላቸው» ይልና እንደአበራ አባባል ይህን ሃሳብ የተጠቀመበት በአሉ ከስራ ባልደረቦቹ ጋር ችግር አለበት ለማለት እንዲመቸው ነበር፤ ጽሁፉ ግን በአሉ ግርማ የደህንነት ሰው ነበር ነው የሚለን። በርግጥ አበራ ቃላት የመቆራረጥና የመቀጠል የሞኝ ዘዴውን በመጠቀም ከዚህብ አረፍተ ነገር “ ቅርበት በመፍጠሩ ጥላቻ አላቸው” የሚለውን በሚቀጥለው ገጽ ቆርጦ ወስዶ የበአሉን ጓደኞች ሊወነጅልበት ነበር። በአሉን ብዙ ጠላት አለው የደህንነት ሰው ነው ብቻ ሳይሆን የሚለው በመጽሃፉ የሚያውቃቸውን ሰዎች ገፅባህርይ አድርጐ መሳደብ የሚወድ ሰው ነው ይለናል፡፤

“በአሉ ግርማ በ1972 ዓ.ም ባሳተመው “የቀይ ኮከብ ጥሪ” ታሪካዊ ልብ ወለድ መጽሃፍ ላይ ከዋናው ሚ/ር እስከ ተራ ሪፖርተሮች ያሉትን የማ/ሚ/ር ሰራተኞች በገፀ ባህርይነት እየተጠቀመባቸው ደህና አድርጐ ተሳልቆባቸዋል። ከነዚህ በገፀ ባህርይነት ከተሳለቀባቸው መካከል ገዳሙ አብርሃ ነው” ይለናል። በሱ ቤት ስለበአሉ ደህና ነገር ማውራቱ ነው፤ ለሌላ አንባቢ የሚሰጠው ትርጉም በ1972 የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ላይ ተሳለቀ፣ በ1974 መጽሃፉ ላይ ደግሞ ስለደርግ ባለስልጣናት ሲሳለቅ አደገኛ ወጥመድ ውስጥ ገባ የሚል ትርጉም ነው የሚሰጠው።
በአሉን በማስገደል ሴራ ላይ እጁ አለበት ብሎ በመጀመሪያው ገፅ ላይ ያቀረበው አስፋው ዳምጤን በተመለከተ ብዙ ውሸቶች የተንሻፈፉ መላ ምቶች፣ የአንድ ወገን እውነቶች ይበዙበታል። በነገራችን ላይ ስለአስፋው ዳምጤ ወንጀለኛነት አበራ የፃፈው አበራ የጋዜጠኞች ማህበር ሊቀመንበር ለመሆን ፈልጐ እሱና ማሞ ውድነህ ስለተቃወሙት ነው ይባላል፣ ለጊዜው እኔም እንደሱ አሉሽ..አሉሽን ትቼ ወደዋናው ይዘት ላይ ብቻ ላተኩር።

አበራ ስለአስፋው ዳምጤ ወንጀለኛነት የሚጠቅሰው ማስረጃ የበአሉ ግርማ ባለቤት በኢህዴግ ዘመን በአሉ በሞተበት ቀን አስፋው ደውሎለት ነበር፤ በአሉም ከቤት ወጥቶ የቀረው አስፋው ጋር ልሂድ ብሎ ነው፤ ብለው ለአቃቤ ህግ ያመለከቱትና ውድቅ የሆነ ክስ መሰረት አድርጐ ነው፤ ስለበአሉ አሟሟት የተለየ ሴራ አለ እስከተባለ ድረስ ያንኑ ነገር ነው ደግመን የምንጠይቀው ለመሆኑ በደርግ ዘመን ደርጐች በአሉን መግደል ከፈለጉ አስፋው ዳምጤን ከቤት ይዘህልን ውጣ ይሉታል ወይ? ይዘህ ውጣ ቢባል መልሱ ምን ነበር የሚሆነው? ግምቴ ስህተት ሊሆን ይችላል፤ ግን እንደኔ ግምት በዛ ዘመን ደርጐች በአሉን ከፈለጉት ራስህ ና ቢሉት በአሉ እንቢ አይልም፤እንኳን እሱ ባለቤቱም ይዘውት ይምጡ ቢሉዋቸው የተለየ መልስ ያላቸው አይመስለኝም፤ በተለይ አበራ በአሉን ይዘህ ና ብለው እነመንግስቱ ቢያዙት ገና እነሱ ጋር ሳይደርስ እራሱ ገድሎት ሬሳውን ይዞ የሚመጣ ነው የሚመስለኝ፤
አበራ የወ/ሮ አልማዝን ክስ መሰረት አድርጐ የራሱን ሴራ የሚያጠናክርበትና አስፋው ዳምጤን የሚከስበት ታሪክ ይፈጥራል፤ አንደኛ አስፋው ዳምጤ በአሉ ከሞተ በኋላ በዚያው ጠፋ፣ እባሉም ቤት ሄዶ አያውቅም፣ ስልክም ደውሎ አያውቅም ይሄ የሆነው ደግሞ የጥፋተኝነት ስሜት ስለሚሰማው ነው፤ ለማለት የመፅሃፍ ቅዱስ ጥቅስ ይጠቅሳል። ለዚህ የውሸት ክስ አሁንም አስፋው ዳምጤን በቅርብ ከሚያውቁ ሰው የሰማሁት ወ/ሮ አልማዝና ደራሲ አስፋው ዳምጤ በበአሉ ጉዳይ ተገናኝተው አውርተዋል፤ በመሃላቸው የተፈጠረ ቅሬታ አለ፤ እሱን ደግሞ አስፋው ዳምጤ እንደ አበራ ለማ ስላልሆኑ እውነቱን እንደ ጥላሁን ገሰሰ ሆድ ይፍጀው ብለው ዝም የሚሉ ይመስለኛል፤ ህዝብ ይወቀው ብለው የራሳቸውን እውነት ቢያወሩ ጥሩ ነው፤

ሌላው አበራ ለማ አስፋው ዳምጤን ወንጀለኛ ነው ብለን እንድናምን በገጽ 2 የመጀመሪያው አንቀጽ ላይ “በአሉ ግርማ እንደወጣ በቀረበት ሰሞን ከገንዘብ ሚ/ር ቋሚ ተጠሪነት ስራው ተባሮ…በድንገት የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖ በደርግ ተሾመ” ይልና ይሄ ሴራ አስፋው በአሉን አስገድሎ ተሾመ ነው መልክቱ፤ ይሄ ደግሞ ግማሽ ውነት ይባላል፤ አስፋው ዳምጤ ከደርግ ዝመን በፊት ከታወቀው ካምብሪጅ ዩኒቭርሲቲ የኢኮኖሚክስ ማስተርስ የነበረው በደርግ ጊዜ ልክ እንደ ጓደኛው እንደበአሉ ግርማ የገንዘብ ሚ/ር ቋሚ ተጠሪ (ሚኒስትር) የነበረ፣ ደርግ ጋር ስላልተጣጣመ ስራ የለቀቀ ሰው በአሉን አስገድሎ እዚህ ግባ የማትባል ድርጅት ም/ስራ አስኪያጅ ሆነ ነውየምትለን አቶ አበራ? ሰው ባታፍር እንኳ ፈጣሪን ፍራ::

አበራ በጽሁፉ ውስጥ ከገጽ 2-5 ገነት አየለ ከደርግ ባለስልጣናት ጋር ያደረገችውን ቃለመጠይቅና የነሱ መልስ ነው፤ ከላይ እንደጠቀስኩት ገነት አየለ በአሉን በተመለከተ በቂ ጥያቄ ስላልጠየቀች ከዛ ተነስቶ ምንም ማለት ባይቻልም በኔ አመለካከት አበራ በሚነግረን ሴራ መንግስቱና ሙልጌታ ሉሌ አሲረውም ይሁን ታናናሾቹ የደርግ ባለስልጣኖች ነገር እየሸረቡ እናዶዋቸው በአሉን ከገደሉ በህግ ባይቻል በታሪክ ተጠያቂ ናቸው፤ መንግስቱ ብ ዙ ሰው ገድለዋልና በአሉንም ገድለውታል ወይም እጃቸው አለበት ብሎ ካለጥፋታቸው መክሰስ አስፈላጊ አይመስለኝም፤፡

በአሉ ግርማ ተገደለ ተብሎ በደርግ ባለስልጣናት ዙሪያ እንደዘበት የሚወራው እውነት አሁን አበራ ወይም ገነት እንደምትነግረን አይነት አይደለም፤ ሌላ የተለየ ታሪክ ነው፤ እጃቸው አለበት የሚባሉትም ሰዎች ሌሎች ናቸው፤ የበአሉ ጉዳይ የቤተሰቡና የጓደኞቹ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ ስለሆነ ሁላችንንም ይመለከተናል፤ አሁን ሁሉም ነገር አልፎ ታሪክ ሆኗል፤ ግን እውነተኛው ታሪክ ለኛና ለልጆቻችን ግልጽ ቢሆን የዘወትር ምኞታችን ነው፤ ስለበአሉ አገዳደል ትክክለኛው መረጃ ያላችሁ ባለስልጣኖች፣ ግለሰቦች ይህን በመስራት ታሪካዊ ግዴታችሁን ልትወጡ ይገባል።
በነገራችን ላይ ጓድ ቁጥር 53 የገነት መፅሀፍ በገጽ 59 በአበራ ጽሁፍ ገጽ 6 ላይ የተጠቀሰ በነአበራ አገላለጽ የደርግ ባለስልጣን ነው ይባላል፤ አንባቢዎች ጊዜ ካላችሁ አንድ ገጽ ብቻ ስለሆነች አንብቧት፤ በጣም የሚገርመው ለማመን የሚያስቸግሩ ሃሳቦች አሉት፣ እና ከዚህ ሰው ንግግር ተነስቶ ሰውን ወንጀለኛ ማለት በጣም ያሳዝናል።ጓድ ቁጥር 53 በኔ እይታ የበአሉ ግርማና የሙልጌት ሉሌ አለቃ ሳይሆን የነፍስ አባት ይመስላል፤ እነሱ የማይነግሩት ነገር የለም በዛ ላይ አይምሮ የሚያነብ ተሰጥኦም አለው።

ገና በጽሁፉ መጀመሪያ ጓድ ቁጥር 53 እንዲህ ይላል« መንግስቱ በአሉ ግርማን ቀይ ኮከብ መጽሀፍ እንዲጽፍ ይጠይቀዋል፤ ራሱ ፃፍ ማለቱን ማንም ሰው አያውቅም» ማንም ሰው ካላወቀ ጓድ ቁጥር 53 እንዴት አወቀ? « መንግስቱ ከሲዳሞ ጉብኝት ሲመለስ ኦሮማይን እያነበበ ነው የመጣው» ይለናል፤ መንግስቱ ደግሞ በአበራ ፅሁፍ ገጽ 3 ላይ “መጽሃፉን ማታ ማታ ነው ያነበብኩት 1 ሳምንት ፈጀበኝ” ይላሉ፤ ጓድ ቁጥር 53 “እንደተለመደው ሊያጠፉት የሚፈልጉ ሰዎች ተሰበሰቡና መከሩ፣ ለበአሉ ቅርብ የሆኑ ጓደኞቹ ጭምር አሳመኑ” እንደተለመደው ሊያጠፉት የሚፈልጉት እነማን ናቸው?

“ሙልጌታ ሉሌ ለደህንነት ይሰራል” ደህንነት የምስጢር ስራ ነው፤ “የበአሉን ቦታ ይመኝ እንደነበረ አውቃለሁ” ይህን ነገር ያወቀው በዛ የሰውን አይምሮ በማንበብ ችሎታው ተጠቅሞ ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል፤ የጓድ ቁጥር 53 ሌላ አስቂኝ ነገር ይነግረናል፤ መንግስቱ በአሉን ለመግደል ከሙልጌታ ጋር ሊያሴሩ ሲፈልጉ ሙልጌታን በቀጥታ ማግኘት ሲችሉ፤ሽመልስ ለጓድ ቁጥር 53 ፣ ጓድ ቁጥር 53 ለሙልጌታ ነገሩት ይለናል፤ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌን ጠርቶ ማሴርፈለገ በቀጥታ ደውሎ መጥራት ሲቻል ይሄ ሁሉ መዞር ለምን አስፈለገ? ገድ ቁጥር 53 ሌላ የሚቀባጥረው ነገር አለው ፤ ሙልጌታ ሉሌ መንግስቱ ጋር ሄዶ በአሉን ለመግደል በምስጢር ካሴሩ በኋላ ጓድ ቁጥር 53ን ፈልገው እኔና መንግስቱ በአሉን ለመግደል አሴርን ሊሉት ፈለጉ ጓድ ቁጥር 53 ምንም ነገር ሳይሰማ አእምሮው የማንበብ ችሎታውን በመጠቀም የሁለቱን ሰዎች ምስጢር ስለደረሰበት ለራሱ ለበአሉ ንገረው አልኩት ይለናል።

ጓድ ቁጥር 53 ምን ያህል ሞኝ ናቸው ሙልጌታን ያህል የአለምን የኢትዮጵያን ፖለቲካና ኢኮኖሚ ታሪክ ጠንቅቆ የሚያውቅ ምሁር በቀን አንድ መጽሃፍ የሚያነብ ፈላስፋ በ50 አመት የጋዜጠኛነት ሙያ ብዙ የኖረ ሰው ሰው ለመግደል ከመንግስቱ ጋር አሲሮ ለአለቃው/ለነፍስ አባቱ ሊነግረው ፈለገ፣ ነፍስ አባቱ ግን የነብይነት ችሎታውን ተጠቅሞ ይህንን ሴራ ቀድሞ አውቆ አልሰማ አለ፤ ጓድ ቁጥር 53 ፈለቀ ገ/ጊዮርጊስ ይሁን ከነብያቶቹ አንዱ መጥቶ እርሱን ለህዝብ መግልጽ ያለበት ይመስለኛል።

ጓድ ቁጥር 53 የራሱን ስም ደብቆ እየቀባጠረ የሰው ስም ካጠፋ በኋላ ስሙ የጠፋው ሰው ወጥቶ ይናገር እንኳን ሙልጌታ ሉሌ ሌላም ሞኝ ሰው የሚቀበለው አይደለም፤ ሙልጌታ ሉሌ ለውነት የቆመ፣ ከማያለቀው እውቀቱ ትውልዱን የሚያስተምር፣ የህዝብ አስተማሪ፣ የኢህዴግን መንግስት ገና ከመጀመሪያው በጽኑ የሚቃወምና የሚታገል የብዕር አርበኛ ነው። በአፄ ምኒልክ ዘመን ጋዜጠኛ የነበሩ ደስታ ምትኬን ጨምሮ እስከአሁኖቹ በዘመናችን ጋዜጠኞች እንደአርአያ የሚታይ ሰው ወያኔን የሚቃወምና የተጣመሙ የሃገራችን ታሪኮችን ጻፍክ ተብሎ ስሙን ማጥፋቱ ትክክል ነው ብዬ አላምንም። ሙልጌታ ሉሌ አሁንም ይጽፋል፣ አሁንም ትውልዱን ስለምንወዳት ኢትዮጵያ ያስተምራል፣ ስለ ዲሞክራሲ ይሰብካል፤ ስለ ጀግንነት ይናገራል። ትልቁን ሰው ማዋረድ ትንሹን ትልቅ አያደርገውም።

ጸጋዬ ገ/መድህንና ሙልጌታ ሉሌ በአንድ አካባቢ ያደጉ ብቻ ሳይሆን የአንድ ዘመን ሰዎች ናቸው። ከሙያቸው ጋር በተገናኘ አላስፈላጊ እስጥ አገባ አጋጥሟቸው ነበር። ሁለቱም ለተነሱባቸው ሰዎች የሰጧቸው ምላሾች ተመሳሳይና ሁል ጊዜ የሚጠቀሱ ናቸው። ጸጋዬ ገ/መድህን የሆኑ ሰዎች ተነስተውንብሃል በየጋዜጣው ስምህን ያጠፉታል፣ ለምን መልስ አትሰጥም ተብሎ ተጠየቀ። ጽጋዬም እነዚህ ሰዎች የትልቅ ሰው እግር ይዘው ሽቅብ መሳብ የሚሹ ናቸው፡ እኔ ደግሞ ለነኚህ ግልገሎች እግሬን አለሰጥም አለ፡፤ ሙልጌታ ሉሌም በጣም የምትወደውን የቅርብ ጓደኛህን በአሉ ግርንማን በማስገደል ሴራ ውስጥ አለህበት ብለው ሰዎች ስምህን ያጠፉታል፤ ለምን መልስ አትሰጣቸውም ተብሎ ሲጠየቅ እንዲህ ሲል መለሰ፣ በድሮ ጊዜ አንድ ሰው መኪና እየነዱ ሲሄዱ መንገድ ላይ ሰው ገጩ የገጩት ሰው ትንሽ ጠቆር ያለ በዛን ጊዜ አጠራር “ባርያ” ስለነበረ እኔ ከሱ ጋር አልነጋገርም፣ ጌታውን ጥሩልኝ አሉ። እኔም ስለዚህ ነገር መልስ ል፤እመስጠት ወይ ጓድ ቁጥር 53 ራሱን ገልጦ ይምጣ፣ ካልሆነም አበራን የላኩት ጌቶች ይታወቁና ለነሱ መልስ እሰጣለሁ አለ።
ጋዜጠኛ አበራ ከገጽ 10 ጀምሮ እስከ ጽሁፉ መጨረሻ ገጽ 16 ድረስ የፃፈው እሱ ጋዜጠና ሆኖ በሰራበት ዘመን በማ/ሚ/ር ውስጥ የነበሩ የጓዳ ምስጢሮችን የሚላቸውን ነው፤ “የማ/ሚ/ር መስሪያ ቤት ካነሳን ወደ ኋላ ተመልሰን የጓዳ ምስጢር ሰነድ መፈተሽ የግድ ነው” ይለናል፤ በዚህም መሰረት አበራ በዚህ መስሪያ ቤት ይሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞችን በራሱ አይን እያየ እራሱንና የሚወዳቸውን ሰዎች የሚያወድስበትን የድሮ አለቆቹን የሚሰድብበት ክፍል ነው፤ ይሄ ጽሁፍ ከበአሉ አሟሟት ጋር ምንም አይነት ቀጥተኛ ግንኙነት አልነበረውም። በአሉ በወቅቱ በስራው ደስተኛ አልነበረም። ከስራ ባልደረቦቹ ጋርም ጥሩ ግንኙነት አልነበረውም ይለናል። አበራና በአሉ አንድም ቀን ተገናኝተው ሻይ ጠጥተው እንደሚያውቁ አልነገረንም። በአሉም በስራዬ ችግር አለብኝ ብሎ ለአበራ አልነገረውም፤ የተገናኙት ከ2 ጊዜ አይበልጥም፤ እሱንም በአሉ የስራ መመሪያ ሊሰጠው ቢሮ ጠርቶት፤
በዚህ በመጨረሻው የአበራ የፕሮፖጋንዳ ጽሁፍ ውስጥ ውና የጥቃት ሰለባ የነበሩት ጋዜጠኛ ገዳሙ አብርሃ ናቸው። ብዙ በሙያው የለፋና ሰውዬውን የሚያውቁ ሰዎች እንደሚሉት የኢትዮጵያ ታሪክ በትክክለኛ ሰዎች ሲፃፍ ገዳሙ አብርሃ በጋዜጠኛነት ሙያ አንቱ ከተባሉት ተርታ ይመደባሉ። ወዳጄ አለማየሁ እንደሚለው ጋዜጠኛነት እንደወታደር ማእረግ ቢኖረው ባለ 4 ኮከብ ጄኔራል የሚባል ስልጣን ሊሰጣቸው የሚገባ በኢትዮጵያ ጋዜጠኛነት ሙያ ከፍተኛ አስተዋፆኦ ያደረጉ ያገር ባለውለታ እንደነበሩ ከታሪካቸው፣ ከሰሩት ስራ በቀላሉ ማወቅ ይቻላል።

ገዳሙ ዛሬ በህይወት የሉም። አሁን አበራ ስለሚከሳቸው ክስ ከመቃብር ተነስተው መልስ አይሰጡትም። ለነገሩ በህይወት ቢኖሩም መልስ የሚሰጡት አይመስለኝም። አበራ ገዳሙን የለየላቸው ሻእቢያ ናቸው ይለናል፤ ገዳሙ ፀረ አንድነት አቋም ስለነበራቸው ሌሎች ኢትዮፕያዊ ጋዜጠኞችን ያሰቃዩ ነበር፣ ገዳሙ በበአሉ ስልጣን የሚቀኑ ሰው ነበሩ፣ ይለናል። እውነታው ግን ገዳሙ ጥርት ያሉ ኢትዮጵያዊ እንኳን ኤርትራን ከሚያስገነጥለው ሻእቢያ ይቅርና ከየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ምንም አይነት ንክኪ የሌላቸው ነፃ ጋዜጠኛ ገዳሙ ጋዜጠኛነትና ፖለቲካ ተለያይተው መታየት አለባቸው የሚል ትክክለኛ የጋዜጠኛነት አቋም ላይ የተመሰረቱ፣ በሌሎች ጋዜጠኞችም እንደ ሞዴል የሚታዩ ነበሩ።

አበራ የገዳሙን ስም ለማጥፋት ለምን ፈለገ? ብለን ከጠየቅን መልሱ አንድና አንድ ነው፤ በራሱ በአበራ ጽሁፍ ውስጥ በተለያየ ቦታ ይታያል ገጽ 10 ላይ “ገዳሙ አብርሃ የዚህን ጽሁፍ አቅራቢና የጐበዞቹን አገር ወዳድ ባልደረቦቹን ፎቶግራፍ በማስለጠፍ ወደ ኢትዮጵያ ራዲዮ ግቢ እንዳንገባ ያከናወኑት ህገወጥ ተግባር” እነዚህ ጋዜጠኞች በገዳሙ ትእዛዝ ከስራ እንደተባረሩ ሁላችንም እንስማማለን፤ ለምን ተባረሩ ለሚለው መልስ ግን ይለያየናል፤ አበራ እንደሚለው እነአበራ የተባረሩት አገር ወዳድ ስለሆኑ፣ ገዳሙ ደግሞ ሻእቢያ ስለሆኑ ነው፣ ገዳሙን የሚያውቁ ሰዎች የሚሉት ደግሞ ገዳሙ እነዚህን ሰዎች ያባረረው መኢሶን የሚባል በወቅቱ ከደርግ ጋር ይሰራ የነበረ ድርጅት አባል ነበሩ፣ የድርጅታቸውም አባል የአራት ኪሎ ወጣቶችን የጨረሰው ግርማ የሱ ተራ ደርሶ ደርግ ሲገድለው አንደኛው የነአበራ ጓድ የግርም፣አን መሞት በዜና አልናገርም አለ በዚያ ምክንያት ገዳሙ ስራህን ስላልሰራህ ብለው ከስራ አባረሩት፤ የሱ ፓርቲ አባላት በሰውየው መባረር ሲጮሁ ጀግናው ገዳሙ ፖለቲካና ጋዜጠኛነት አብሮ አይሄድም ብለው ሁሉንም አባረሯቸው፣ አበራ ሁልጊዜ እንደሚያደርገው ይህን ታላቅ ውነት ዘለለው።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ አንድ የተለመደ ነገር አለ፤ የአንድን ሰው ሃሳብ ሃሳቡን መቃወም ሲያቅትህ ሰውዬውን ሌላ ሳጥን ውስጥ ማስገባት፣ ገዳሙ የወሰዱትን እርምጃ ማስተባበል ስላልተቻለ ወይም የሰውዬውን ችሎታና ስራ ማጣጣል ሳይቻል ሲቀር ከሰውዬው ሃሳብ ይልቅ የሰውዬውን ማንነት መምታት ነው። በነገራችን ላይ በሃ/ስላሴና በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ 24% የመንግስት ሰራተኛና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የኤርትራ ተወላጆች ነበሩ። ጥቂቶቹ ኢትዮጵያዊ ናቸው ብለን ስናስብ እነሱ ኤርትራዊ ሆነው ቢያሳዝኑንም ብዙዎቹ የኤርትራ ተወላጆች ከማንም የበለጠ ኢትዮጵያዊነት የሚሰማቸው በኢትዮፕያ ብዙ የሰሩና ዋግ አየከፈሉ ናቸው። አልበርት አንሰታይን በአንድ ወቅት እንዲህ አለ፤ ጥሩ ከሰራሁ አሜሪካኖቹ አሜሪካዊ ነው ይሉኛል፣ እነሱ የማይፈለጉትን ካደርጁ አሜሪካኖቹ ጀርመናዊ ነው ይሉኛል፣ ጀርመኖቹ አይሁድ ነው ይሉኛል..እንደሚለው ታላቁን የኢትዮጵያ ጋዜጠኛ ገዳሙን ሻእቢያ ማለት ትክክል አይደለም።

አበራ ለማ በጅብ የጀመሩትን ታሪክ እኔ በውሻ ልጨርሰው፤ ጀግናው አሉላ አባነጋ በዶጋሊ ጦርነት ወራሪውን ጠላት ድል በማድረግና 500 የጣሊያን ወታደሮች በመግደላቸው ብዙ ጣሊያኖች ተናደው እንደነበረ ይታወቃል። ከነዛ መሀል አንዱ በጣም የተናደደ ጣሊያን ውሻውን አሉላ ብሎ ጠራት፤ ውሻ ከለታት አንድ ቀን ኢትዮጵያዊው የጣሊያን አሽከር ውሻዋን ጫካ ወስዶ ገደላት፣ ጣሊያኑ ውሻዋን ሲጠራት አትመጣም፤ ጣሊያኑ አሽከሩን ጠርቶ ውሻዋ የት ደረሰች?. ብሎ ሲጠይቀው ስሟ ከብዷት ሞተች አለው ይባላል።
እኔም የአበራ ለማ ፅሁፍ ድንቅ መባሉ አበራ በጽሁፉ ዋና ምንጭ የተጠቀመባት ገነት አየለ “መርማሪ ፀሐፊ” መባሏ፣ ለዚህ ሁሉ አላስፈላጊ ውዝግብ ምክንያት የሆነው የነገነት አየለ የፈጠራ ሰው ጓድ ቁጥር 53 “ቱባ የደርግ ባለስልጣን ” መባሉ ከሁሉ ደግሞ ራሱ አበራ ለማ ጋዜጠኛ መባሉ እንደውሻዋ የተሸከሙት ስም እንደከበዳቸው አሳይቶኛል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>