አርሰን ቬንገር ያለፈውን ወር በብራዚል የዓለም ዋንጫ አሳልፈዋል፡፡ በእርግጥ አብዛኛውን ጊዜ ያጠፉት በባህር ዳርቻዎች እየተዝናኑ ይመስላል፡፡ አንድ ሌላ ነገር ላይም ትኩረታቸውን አድርገው ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት ባዘዋወሩት አሌክሲስ ሳንቼዝ ላይ አይናቸውን ተክለው ነበር፡፡ ቺሊያዊው በብራዚል ያሳየውን ብቃት ተመርኩዘው 32 ሚሊዮን ፓውንድ ለዝውውሩ ሲያወጡም አልተጠራጠሩም፡፡ ከዚህ ሌላ በዓለም ዋንጫው ያስደሰታቸው እና ያስከፋቸው ምንድነው፡፡ ቃለ ምልልሱን እነሆ፡፡ (ቃለ ምልልሱ የተከናወነው ከዓለም ዋንጫው የፍፃሜ ግጥሚያ በፊት ነው)
ጥያቄ፡- በዓለም ዋንጫው እንግሊዝ ያጋጠማት ምንድነው?
መልስ፡- በብራዚል የእንግሊዝ ትልቁ ችግር በአንድ ጨዋታ ጠንካራ ወይም የበላይ በነበሩት ወቅት ጎል ማስቆጠር አለመቻላቸው እና ደከም ባሉበት ሰዓት ጎሎችን ማስተናገዳቸው ይመስለኛል፡፡ በግጥሚያ ወቅት ደከም ባልክበት እና በተጋጣሚህ የበላይነት በተወሰደብህ ጊዜ ጎል እንዲቆጠርብህ መፍቀድ የለብህም፡፡ መደንገጥ ከጀመርክ ተጋጣሚህ ዋጋህን ይሰጥሃል፡፡ በእኔ እምነት የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ጫና ውስጥ በገባ ቁጥር ጎል የሚያስተናግድ መስል ነበር፡፡ በተጨማሪም በጨዋታው ወሳኝ የሚባል ክፍሎች ላይ ቡድኑ ጥራት እንደሌለው ዓለም ዋንጫው አሳይቶናል ብዬ አስባለሁ፡፡ በእርግጥ እምቅ ችሎታው አላቸው፡፡ ሆኖም ብስለት እና በማጥቃት እና መከላከል መካከል ሚዛናዊነት የሚጎድለው ቡድን ነበር፡፡
ጥያቄ፡- የፈረንሳዮች ችግር ምን ነበር?
መልስ፡- ቡድኑ የተሰናበተው ምናልባትም የዓለም ሻምፒዮን ሊሆን ከሚችለው ጀርመን ጋር ተጫውቶ በመሸነፉ ነው፡፡ (ጀርመን ሻምፒዮን ሆኗል)፡፡ በጀርመን ግጥሚያ ቡድኑ የበታች የነበረሲሆን የሚገባውን ያህልም ችሎታቸውን ከፍ አድርጎ አልቀረበም፡፡ ዘንድሮ ከቡድኑ ብዙም ስላልተጠበቀ ተጨዋቾቹ በዓለም ዋንጫው እስከ ሩብ ፍፃሜው በመጓዛቸው ብቻ ደስተኛ የሆኑ ይመስል ነበር፡፡ ተጨዋቾቹ ችሎታው ቢኖራቸውም በጀርመኑ ግጥሚያ ግን ሙሉ በሙሉ አውጥተው ሊጠቀሙበት አልቻሉም፡፡ ጨዋታውን ማሸነፍ ይችሉ ነበር፡፡ በዚህ ዓለም ዋንጫ የሚፀፅተው ነገር በሩብ ፍፃሜው የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ሙሉ ብቃቱን አለማውጣቱ ነው፡፡
ጥያቄ፡- በውድድሩ የመጨረሻ ጨዋታዎች እንደ ፍራንክ ሪቤሪ አይነት ተጨዋቾች ምን ያህል ወሳኝ ናቸው?
መልስ፡- በጣም ወሳኝ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ትክክለኛ ውሳኔዎችን የሚያሳልፉ ተጨዋቾች ያስፈልጋሉ፡፡ ሁሉም ነገር በመልካም እየተጓዘ ከሆነ የምትፈልገው የቡድንህ አቋም ትኩረት እንዳያጣ ማድረግ ነው፡፡ ሆኖም ነገሮች በመጥፎ መልኩ እየሄዱ ከሆነ ኳሱን ይዞ ልዩነት ሊፈጥር የሚችል ተጨዋች ያስፈልግሃል፡፡ አንድ ጥያቄ ልጠይቅ፡፡ አርጀንቲና ያለ ሊዮኔል ሜሲ በፍፃሜው መጫወት ትችል ነበር? ሆላንድ ያለ አሪዬን ሮበን በግማሽ ፍፃሜ መጫወት ትችል ነበር? መልሱ በፍፁም የሚል ይሆናል፡፡ ብራዚል ያለኔይማር ከምድቡ ታልፍ ነበር? በጭራሽ፡፡
ስለዚህ ታላላቅ ተጨዋቾች ወሳኝ ናቸው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ከምንም ተነስተው በራሳቸው ልዩ ነገር ይፈጥራሉ፡፡ በተጨማሪም ከትልቅ ጨዋታ በፊት በመልበሻ ክፍል ተቀምጠህ ዙሪያህን ስትቃኝ ሜሲ እና ኔይማርን የመሳሰሉ ከዋክብትን ስትመለከት በግጥሚያው አንድ የተለየ ነገር የሚፈጥር ተጨዋች በቡድንህ ውስጥ እንዳለ ትረዳለህ፡፡ ይህ ደግሞ የቡድኑን የማሸነፍ እምነት ከፍ ያደርጋል፡፡ ከፍተኛ ጫና ባለባቸው ግጥሚያዎች የእነዚህ አይነት ተጨዋቾች መኖር በራሱ ልዩ ጥቅም አለው፡፡
ጥያቄ፡- ፖል ፖግባ ያለው እምቅ ችሎታ ምን ያህል ነው?
መልስ፡- ፖግባ ወርልድ ክላስ የሚሆን ተጨዋች ነው፡፡ እያንዳንዱ ተጨዋች የሚያልማቸው ችሎታዎችን በሙሉ ይዟል ብዬ አስባለሁ፡፡ ጉልበት፣ ግርማ ሞገስ እና ቴክኒክ ችሎታዎችን አጣምሮ ይዟል፡፡ የማይታመን በድንገት አፈትልኮ የመሮጥ ችሎታ እና የከፍተኛ ፍጥነት ባለቤትም ነው፡፡ ወደ ሜዳ ሲወጣ አይኖች ሁሉ እርሱ ላይ ያርፋሉ፡፡ በፈረንሳይ ጨዋታዎች ላይ በከፍተኛ ፍጥነት ሲጫወት መመልከት ያስደንቃል፡፡ በብሔራዊ ቡድኑ ፈጣኑ ተጨዋች እርሱ ነው፡፡ ስለዚህ በከፍተኛ ደረጃ መጫወት እንደሚችል ታስባለህ፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጥያቄ ፖግባ ወደ ተራራው ጫፍ ለመውጣት በአዕምሮው በኩል ዝግጁ ነው ወይ? የሚል እንደሆነ እገምታለሁ፡፡ በቀጣዮቹ ዓመታት ለዚህ ጥያቄ መልስ እንደሚሰጠን እርግጥ ነው፡፡ በእምቅ ችሎታው ግን የወደፊቱ የዓለም ምርጥ አማካይ እርሱ ነው፡፡
ጥያቄ፡- ኮሎምቢያ ሩብ ፍፃሜ ትደርሳለች ብለው አስበው ነበር?
መልስ፡- በፍፁም፡፡ ውድድሩ ከመጀመሪያ በፊት አልጠበቅኩም ነበር፡፡ ነገር ግን በዓለም ዋንጫው ትሩ ስራን ሰርተዋል፡፡ ሃሜስ ሮድርጉዌዝን አውቀዋለሁ፡፡ የሚጫወተው በፈረንሳይ ሊግ 1 ለሞናኮ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ በዓለም ዋንጫው ባሳየው ብቃት በእጅጉ ተደንቄያለሁ፡፡ ያለው ጥራት ይገርማል፡፡ ፓስ ሲያደርግ ለው ብልህነት፣ ቅልጥፍናውና በቀላሉ አቅጣጫውን የመቀየር ችሎታው እንዲሁም ከባዱን ነገር ያለ ችግር መስራቱ ልዩ ያደርጉታል፡፡ በውድድሩ ያደረጋቸው ተከላካይ ሰንጣቂ ፓሶቹ የሚደነቁ ነበሩ፡፡ ሁልጊዜም ኳስ እግሩ ስር ሆና ማየትን ትፈልጋለህ፡፡ አንድን ተጨዋች ሁልጊዜም ኳስን ተቆጣጥሮ ማየት ስትፈልግ ደግሞ የተለየ ችሎታ ባለቤት እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡ እርሱም የዚህ ችሎታ ባለቤት ነው፡፡
ጥያቄ፡- ሞናኮ ለሮድሪጉዌዝ አይመጥነውም?
መልስ፡- በትክክል፡፡ ምክንያቱም እንደ ሪያል ማድሪድ እና ባርሴሎና ያሉ ክለቦች ተጨዋቾን እየፈለጉት እርሱን በፈረንሳይ ማቆየት ይከብዳል፡፡ ሮድርጉዌዝን ሲጫወት ተመልክተው ለማስፈረም የሚፈልጉ ሌሎች ክለቦችም ይኖራሉ፡፡ ዘንድሮ ሞናኮን ይለቃል? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ በዚህ ክረምት ከፈረንሳይ ይወጣል ብዬ አላስብም፡፡ በዚህ ክረምት ከፈረንሳይ ይወጣል ብዬ አላስብም፡፡ ምክንያቱም ከሞናኮ ጋር በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በቻምፒዮንስ ሊግ መድረክ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ ሞናኮ በፈረንሳይ ከትልልቆቹ ክለቦች አንዱ ነው፡፡ ከሚቀጥለው የውድድር ዘመን በኋላ ግን ወደ ሌላ ትልቅ የአውሮፓ ክለብ ለመዛወር ፍላጎት ማሳየቱ አይቀርም፡፡
ጥያቄ፡- በብራዚሉ ጨዋታ ተገቢው ጥበቃ ተደርጎለታል?
መልስ፡- በዓለም ዋንጫው የደቡብ አሜሪካ ቡድኖች ገና በጊዜ እርስ በርስ መጫወታቸው አሳዝኖኛል፡፡ በምድብ ጨዋታዎቹ በውድድሩ የበላይነት ያሳዩት የላቲን አሜሪካ ቡድኖች ነበሩ፡፡ ቀጥሎ ማለፍ ዙሩ ግን በአንድ ቀን ብራዚል ከቺሊ እና ኮሎምቢያ ከኡራጓይ ጋር ተገናኙ፡፡ ሁለት የደቡብ አሜሪካ ቡድኖች ከውድድሩ በአንድ ጊዜ ይሰናበታሉ ማለት ነው፡፡ በእርግጥ በእነዚህ ግጥሚያዎች ተጫዋቾቹ ያላቸውን ከፍተኛ የማሸነፍ ፍላጎት መመልከት ይቻላል፡፡ በሩብ ፍፃሜው ብራዚል ከኮሎምቢያ ያደረጉት ጨዋታ ልዩ ነበር፡፡ ነገር ግን የማሸነፍ ፍላጎቱ ከሚገባው አልፎ ነበር፡፡ በጨዋታው ብራዚላዊያኑ ሃሜስን ለማቆም የተጠቀሙበት መንገድ ትንሽ ከልክ ያለፈ ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን በዓለም ዋንጫው የተመለከትናቸው ጨዋታዎች ጥሩ ነበሩ፡፡
ጥያቄ፡- አምስት የአፍሪካ ቡድኖች በውድድሩ ተሳትፈዋል፡፡ አንዳቸውም ግን ወደ ሩብ ፍፃሜው አልገቡም? ለምን?
መልስ፡- ምክንያቱ የቡድኖቹ የጥራት ችግር ብቻ አይመስለኝም፡፡ ከዓለም ዋንጫው መጀመር በፊት እና ውድድሩ እየተካሄደ እያለ ከሜዳ ውጭ የተፈጠሩት ነገሮች ለቡድኖቹ ደካማነት አስተዋፅኦ አድርገዋል፡፡ በሁለቱ ትልልቅ የእግርኳስ ሀገሮች ካሜሮንና ናይጄሪያ ያሉ ደጋፊዎችን ያስከፋው ብሔራዊ ቡድኖቹ ሩብ ፍፃሜ መድረስ አለመቻላቸው አይመስለኝም፡፡ ሁለቱም ቡድኖች ከሀገራቸው ዜጎች ጋር ወንድማማችነት አለማሳየታቸው ነው፡፡ ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ሁለቱም ቡድኖች ዓለም ያወቋቸው ችግሮች ነበሩባቸው፡፡ በውድድሩ በሜዳ ላይ የተሻለ ነገር ማሳየት ያልቻሉትና ረጅም ርቀት ያልተጓዙበት ምክንያት ይህ ይመስለናል፡፡ እግርኳስ አንድ ሆነህም ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ የዓለም ዋንጫ አንድ መሆን ካልቻልክ ምንም ዕድል አይኖርህም፡፡ ይህን ካልኩ አይቀር ለአልጄሪያ ተገቢውን ክብር መስጠት ይገባኛል፡፡ አንዳንድ ጊዜ በጣም ምርጥ ስለነበሩ በጥሎ ማለፍ ጨዋታው ጀርምን ሳይቀር ደካማ ቡድን አስመስለውት ነበር፡፡ ከአፍሪካ ሀገራት በዓለም ዋንጫው የተሻለ የነበረው የአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ነው፡፡
ጥያቄ፡- ከአልጄሪያ ቡድን የወደዱለት ምኑን ነው?
መልስ፡-በመጀመሪያው ግጥሚያ ውድድሩ የከበዳቸው ይመስሉ ነበር፡፡ በሁለተኛው ጨዋታ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ሲጋጠሙ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተቀይረው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ለቡድኑ ትኩረት መስጠት ትጀምራለህ፡፡ በምርጥ ብቃታቸው መቀጠልም ችለዋል፡፡ ራሳቸውን ሜዳ ላይ ይገልፁ ነበር፡፡ ይህን ነገራቸውን ወድጄላቸዋለሁ፡፡ በፈረንሳይ የተወለዱ እና ለአልጄሪያ የተጫወቱ ብዙ ተጨዋቾችም ነበሩ፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች ለሀገራቸው ተመልሰው በመጫወታቸው እና ያላቸውን ሁሉ በመስጠታቸው ደስ ብሎኛል፡፡ ወድጄዋለሁ፡፡
ጥያቄ፡- የቤልጂየም ብሔራዊ ቡድን እንደተጠበቀው ነበር?
መልስ፡- የዓለም ዋንጫው ከመጀመሩ በፊት ቤልጅየም ገና ከምድቧ በጊዜ ትሰናበታለች፡፡ አልያም እስከ ውድድሩ ፍፃሜ ትጓዛለች ብዬ አስቤ ነበር፡፡ ለምን? ምክንያቱም ቡድኑ በባልተሰጥኦ ተጨዋቾች የተሞላ ነው፡፡ ሆኖም የቅርብ ጊዜ ታሪክ የላቸውም፡፡ በሽግግር ወቅትም ነበሩ፡፡ በመጨረሻም በሩብ ፍፃሜው ከውድድሩ ወጥተዋል፡፡ ነገር ግን ለወደፊት ስኬት የሚሆናቸውን መሰረት የጣሉ ይመስለኛል፡፡ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ምን እንደተፈጠረ በደንብ ካጠኑ በኋላ ይበልጥ ጠንካራ ሆነው እንደሚመለሱ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በ2016 የአውሮፓ ዋንጫ ለውድድሩ ሻምፒዮንነት ከሚገመቱ ቡድኖች አንዱ ይሆናሉ፡፡
ጥያቄ፡- ኤዴን ሀዛርድስ የችሎታውን ያህል ተጫውቷል?
መልስ፡- በፍፁም፡፡ እኔ መጫወት ይችላል ብዬ ያሰብኩትን ያህል አልተጫወተም፡፡ በፕሪሚየር ሊግ የተለየ ተጫዋች ነው፡፡ በጨዋታ ላይ የተለየ ነገር መፍጠር የሚችል ምርጥ ተጨዋች ነው፡፡ በዙሪው ያለ ነገር ሀዛርድ ላይ ምንም ተፅዕኖ እንደማይፈጥርበት አስብ ነበር፡፡ በትልልቅ ጨዋታዎች ጥሩ ነገር መስራት ይችላል፡፡ ሆኖም በዓለም ዋንጫው ቤልጅየም በምትፈልገው ወቅት አልደረሰላትም፡፡ ምንም ነገር ማድረግ አልቻለም፡፡ ጉዳዩ ከችሎታው ጋር ሳይሆን ከአዕምሮው ጋር የተገናኘ ነው፡፡ ገና ወጣት ነው፡፡ የዓለም ዋንጫ ዕድሜያቸው ከ25-30 ላሉ ተጨዋቾች የሚመች ውድድር ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሜሲ ወደ ዓለም ዋንጫው ተጉዞ ምንም ሳይሰራ ተመለሰባቸውን ውድድሮች እናስታውሳለን፡፡ በክለቡ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚችል ቢሆንም በአርጀንቲና ግን ይቸገር ነበር፡፡ በዓለም ዋንጫው ተጫዋቾች የሚጋፈጡት ግዙፍ ጫና አለ፡፡ ይህን መቋቋም የሚችሉት በእንደህ አይነት ውድድሮች ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡
ጥያቄ፡- በብራዚል ላይ ከፍተኛ ጫና ነበር? 7-1 የተሸነፉት እንዴት እና ለምን ነው?
መልስ፡- ለሽንፈቱ አስተዋፅኦ ያበረከቱ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ግን ጨዋታውን ለማሸነፍ የሚያስችል በቂ ጥራት አልነበራቸውም፡፡ በኔይማር ላይ ከተገቢው በላይ ጥገኛ ነበሩ፡፡ ስሜታቸውን መቆጣጠር እንዳልቻሉም አምናለሁ፡፡ ጫናው እንዲቀንስላቸው በቂ ጥበቃም አልተደረገላቸውም፡፡ ቴሌቪዥን በምከታተልበት ወቅት ብራዚልን ማየት የቴሌቪዥን የሪያሊቲ ፕሮግራሞችን እንደመመልከት ነው፡፡ በቡድኑ ከካምፕ ውስጥ 25 ሰዓታት ሙሉ ተጨዋቾችን የሚከታተሉ ጋዜጠኞች ነበሩ፡፡ የተጫዋቾቹ እያንዳንዱ እንቅስቃሴም ለቴሌቪዥን ፍጆታ ይውል ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ተፅዕኖ አድርጎባቸዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ወደ ጨዋታው ከማምራትህ በፊት ትኩረትህን መሰብሰብ እና መዘጋጀት አለብህ፡፡ ነገር ግን በየቀኑ እንደ ብራዚል ተጨዋቾች ተጋላጭ ከሆንክ ለግጥሚያው የሚያስፈልግህን ጥንካሬ አታገኝም፡፡ ለማሸነፍ የነበራቸው ከልክ ያለፈ ስሜትም እንደልብ አላንቀሳቀሳቸውም የነበራቸው ከተገቢው በላይ የሆነ ስሜት እንዳለ ለማሳየት ከፍተኛ ደረጃ ለመጫወት የሚያስችል አይደለም፡፡ እነርሱም ይህን ነገር እንደሚገነዘቡት አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ለብሔራዊ ቡድኑ ስሜት እንዳለ ለማሳየት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ስለዚህ በሆነ ባልሆነው ወደ ማልቀሱ አመሩ፡፡ እናም ይህ ስሜት እንዲቆታጠርህ ትሆናለህ፡፡ በመጨረሻ ደግሞ እንደ ልብህ እንዳትጫወት ያደርግሃል፡፡ አንድ ተጨዋች ኳሱን ሲቆታጠር አጠገቡ ሌላ ብራዚላዊ ተጨዋች ተገኝቶ ኳን ለመቀበል ሲሞክር አልታየም፡፡ ምክንያቱም በከፍተኛ ጫና ውስጥ ነበሩ፡፡
ጥያቄ፡- በግጥሚያው (በጀርመን እና ብራዚል) በስታዲም ተገኝተው ነበር፡፡ ከታክቲክ አንፃር ጨዋታውን እንዴት ተመለከቱት?
መልስ፡- እውነቱን ለመናገር ከታክቲክ አንፃር አስደንጋጭ ነበር፡፡ ለእኔ አሰልጣኙ (ልዊስ ፊሊፔ ስኮላሪ) ላይ ጣቴን መቀሰሩ እንደሚቀልለኝ እርግጥ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ አሰልጣኝ ሆኜ በመቆየቴ እንዲህ አይነት ነገሮች እኔ ላይ ሲከሰቱ ተመልክቼያለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የቡድንህ በራስ መተማመን በድንገት በንኖ ሊጠፋ ይችላል፡፡ ሆኖም በእግርኳሱ የብራዚል የረጅም ጊዜ አድናቂ ነኝ፡፡ በመጨረሻ ግን ለጀርመን ብሔራዊ ቡድን ተገቢውን ክብር መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ስታዲየም ተቀምጬ ጀርመናዊያኑ እንዴት ጫናን መቋቋም እንደሚችሉ ተመልክቼያለሁ፡፡ በዓለም እግርኳስ እጅግ የደመቀ ታሪክ ያላትን ሀገር በሜዳዋ ቢገጥሙም ደጋግመው ለማጥቃት ሲሞክሩ ነበር፡፡
በእንዲህ አይነት ሰፊ የጎል ልዩነት ስትሸነፍ ስሜትህን ለመቆጣጠር ትቸገራለህ፡፡ ብራዚላዊያኑ ላይ የተፈጠረው ነገር ይበልጥ ያሳመመኝ ግን ምንም ምላሽ መስጠት አለመቻላቸው ነበር፡፡ ሙሉ ለሙሉ አቅም አጥተው ነበር፡፡ የ18 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 11 ታዳጊዎች ወደ ሜዳ ወስደህ ከጀርመን ጋር ብታጋጥማቸው እንኳን በስድስት ደቂቃዎች ውስጥ አራት ጎሎችን አያስተናግዱም፡፡ ለእኔ ብራዚሎች በሜዳ ላይ (በስሜት) እግራቸው ተሳስሮ ነበር፡፡
ጥያቄ፡- በሆላንድስ ጉዞ ተደንቀዋል?
መልስ፡- አዎ! ባለፈው ማርች ከፈረንሳይ ጋር ሲጫወቱ ተመልክቼያቸው ነበር፡፡ በዕለቱ በሁሉም ረገድ ተበልጠው ነበር፡፡ ወደ ዓለም ዋንጫው ከመጡ በኋላ ግን አስደናቂ ነበሩ፡፡ በዓለም ዋንጫው ልምድ የሌላቸውን ቡድን ሆነዋል፡፡ ለልዊስ ቫን ሃል እና በአሰልጣኞች ስታፍ ክብር መስጠት እንደሚኖርብን አምናለሁ፡፡ ያሳለፏቸው ውሳኔዎችን ግልፅ መሆን፣ ውሳኔዎችን የሚያሳልፉበት ጊዜ ትክክለኛነትን ወድጄላቸዋለሁ፡፡ በእኔ እምነት በዓለም ዋንጫው የወሰዷቸው እርምጃዎች ሁሉም ትክክል ነበሩ፡፡ ስለዚህ በእኔ አስተያየት ቫንሃል ብዙ ሙገዛ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ጥያቄ፡- በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ከቫን ሃል ማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ለመፎካከር አጓጉተዋል?
መልስ፡- በትክክል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ምርጥ አሰልጣኝ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ዩናይትድም በቀጣዩ የውድድር ዘመን ለዋንጫ እንደሚፎካከር እርግጠኛ ነኝ፡፡ ይህ ደግሞ ሊጉን አጓጊ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም ዩናይትድ አርሰናልን ቢረታ እንኳን በቀጣዩ ሳምንት በቼልሲ ሊሸነፍ ይችላል፡፡ ከዚያ ማንቸስተር ሲቲ እና ሊቨርፑል ፉክክሩ ውስጥ አሉ፡፡ ስለዚህ ፕሪሚየር ሊጉ አጓጊ ይሆናል፡፡
ጥያቄ፡- ቲም ክሩልን ለመቀየር ቫን ሃል ስለወሰዱት እርምጃ ምን ያስባሉ (በኮስታሪካው ጨዋታ የመለያ ፍፁም ቅጣት ምት ወቅት ማለት ነው)?
መልስ፡- በምድብ ጨዋታዎች ወቅት የሆላንድ ብሔራዊ ቡድን በርካታ ጎሎችን አስቆጥሮ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የጎል ድርቅ ተመትቷል፡፡ ይህ የተፈጠረበትን ምክንያት ሊነግሩኝ ይችላሉ?
መልስ፡- አዎ! የዓለም ዋንቻው እየገፋ በሄደ ቁጥር እና ጨዋታዎቹ እየከበዱ ሲመጡ ጎል የማስቆጠር ዕድልህ ይቀንሳል፡፡ የአርጀንቲና እና ሆላንድ ጨዋታ የተደረገው ብራዚል በጀርመን 7-1 ከተሸነፈች በኋላ ስለነበር ስነ ልቦናዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ብራዚልን የሚያህል ቡድን ሰባት ጎሎች ተቆጥረውበት እንዳልነበር ሲሆን ስትመለከት ‹‹ይህ ነገር እኛ ላይ ሊደርስ ይችላል›› በማለት ስለራስህ ማሰብ ትጀምራለህ፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ተጨዋች ጥንቃቄን ይመርጣል፡፡ እያንዳንዱ ቡድንም እንደ ብራዚል አይነት ቅጣት እንዳይደርስበት ለማረጋገጥ ይመክራል፡፡ ከብራዚል እና ጀርመን ጨዋታ በኋላ በሚቀጥለው ቀን የተፈጠረውን መታዘብ ይቻላል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ፊት የመጓዝ ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ ነገር ግን በአጠቃላይ እስከ ጥሎ ማለፍ ዙሩ ድረስ ሆላንድ ጥሩ ነበሩ፡፡
ጥያቄ፡- በዓለም ዋንጫው ምን ያህል ወሳኝ ነበር?
መልስ፡- ሜሲ ተነሳሽነት ያለው መስሏል፡፡ በደቡብ አፍሪካው የዓለም ዋንጫ ለመጫወት ፍላጎት ያለው አይመስልም ነበር፡፡ በዘንድሮው ውድድር ግን ራሱን ሙሉ ለሙሉ ለቡድኑ የሰጠ ይመስላል፡፡ ይህን አመለካከቱን ወድጄዋለሁ፡፡ ነገር ግን ከእርሱ የሚጠበቀው ከፍተኛ ደረጃ ላይ አልደረሰም፡፡ እኔ ከማውቀው ሜሲ ጋር ሲወዳደር ከተለመደው እርሱነቱ በሽርፍራፊ ሰከንዶች ወደኋላ ቀረት ብሏል፡፡ ይህ ነገር ባለፈው የውድድር ዘመን ካስተናገዳቸው ተደጋጋሚ ጉዳቶች ጋር የተገናኘ ይሁን አይሁን አላውቅም፡፡ እንደፈለገ በፍጥነት መጫወት ግን አልቻለም፡፡ ሆኖም እንደወትሮው ያልሆነው በአካል ብቃቱ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ብቃቱ አሁንም አብሮት አለ፡፡ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር እንዲህ ራሱን ሲገልፅ እና ስሜታዊ ሲሆን አይቼው አላውቅም፡፡
ጥያቄ፡- ጀርመን ለስምንተኛ ጊዜ ለፍፃሜ ደርሷል፡፡ እንዲህ ወጥ አቋም የሚያሳዩት ለምንድነው?
መልስ፡- የእግርኳስ ሀገር ነው፡፡ መሬት ላይ ባለ ነገር የሚያምኑ ናቸው፡፡ ችግር ሲያጋጥማቸውም መፍታት ይችላሉ፡፡ በኢኮኖሚውም ዘርፍ ተመሳሳይ ነው፡፡ በኢኮኖሚው መስክ በአውሮፓ በጥሩ ጎዳና ላይ እየተጓዘች ያለችው ጀርመን ናት፡፡ እግርኳሳቸውም የተደራጀ ነው፡፡ የቴክኒክ ችሎታቸውንም አሻሽለዋል፡፡ አሁን በዓለም ዋንጫው በቴክኒኩ ምርጡን ቡድን ይዘው ቀርበዋል፡፡ በወጣቶች ላይ ለሰሩት ስራ ምስጋና ይግባና ትክክለኛ ውሳኔ በማሳለፋቸው ፍሬውን እየተመዘገቡ ነው፡፡