መኢአድ እና አንድነት የሚፈጥሩት የዉህዱ ፓርቲ ሊቀመንበር ለመሆን፣ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው ከቀረቡት መካከል አቶ በላይ ፍቃዱ በረዳ ይገኙበታል። አገር ቤት የሚገኙ የአንድነት አባላትና መሪዎች ዘንድ አድናቆትና ከበሬታ እንዳላቸው የሚነገርላቸው አቶ በላይ፣ ለነባሩ የአንድነት ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው እንደተገኙ የሚጠቁሙ መረጃዎች አሉ።
አቶ ዳንኤል ተፈራ የአንድነት ሥራ አስፈጻሚ አባል፣ የቀድሞ የአንድነት የሕዝብ ግንኙነት አሁን ደግሞ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ፣ አቶ ግርማ ሰይፉ የፓርላማ አባል እና የቀድሞ የአንድነት ም/ፕሬዘዳንት፣ በይፋ ጠቅላላ ጉባኤው አቶ በላይን እንዲመርጥ ጥሪ በማቅረብ ድጋፋቸዉን የሰጡ ሲሆን፣ አብዛኛዉ የአንድነት ሥራ አስፈጻሚ አባላት፣ በይፋ መግለጫ ባያወጡም ፣ የአቶ በላይን መመረጥ እንደሚደገፉ የሚገልጹ ምልክቶች እየታዩ ነው።
በአገር ቤት አቶ በላይ ካለው ጠንካራ ድጋፍ በተጨማሪ፣ በዉጭ አገር የሚገኙትም የአንድነት ድጋፍ ማህበራት ፣ በዉህዱ ፓርቲ ዉስጥ አዲስ አመራር መምጣቱ የበለጠ ለትግሉ ጥቅም እንደሚኖረው በመግለጽ፣ ለአቶ በላይ ድጋፋቸውን እየሰጡ ነው። በዉጭ አገር ካሉ የድጋፍ ድርጅቶች መካከል ጠንካራዎቹና ዋናዎቹ ከሚባሉት መካከል የዲሲ ሜትሮ እና የቦስት ድጋፍ ማህብራት ባወጡት መግለጫዎች፣ አቶ በላይን ኢንዶርስ አድርገዋል።
አቶ በላይ በአንድነት አባላትና ለፓርቲው ቅርብ በሆነ ወገኖች ዘንድ፣ ብዙ የሚታወቁ ቢሆንም ፣ ከበስተጀርባ ሆነው መስራት የሚወዱ፣ ለወንበር የማይሽቀዳደሙ እንደመሆናቸው፣ ብዙም በአብዛኛው ኢትዮጵያ ዘንድ የሚታወቁ ላይሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት ብዙዎች አለቸው። በመሆኑም፣ «አቶ በላይ ፍቃዱ በረዳ ማን ናቸው ?» ለሚለው ጥያቄ ኢትዮጵያዉያን አንዳንድ ምላሾች ይኖራቸው ዘንድ የሚከተለውን አቀናብረናል።
አቶ በላይ ፍቃዱ በረዳ
- ከሰላሳ አራት አመታት በፊት በኦሮሚያ ክልል፣ ጂማ ከተማ ተወለዱ።
- የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጂማ ካጠናቀቁ በኋላ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባችለር ዲግሪ በኢኮኖሚስ፣ ማስተርስ ዲግሪ በኢኮኖሚክ ፖሊሲ አናሊስዝ አግኙተዋል።
- በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ተቀጥረው የሰሩ ሲሆን፣ ቢ.ዲ.ኤፍ ኮንሳልቲንግ የሚባል ኩባንያ በማቋቋም፣ ከሰባት በላይ ፒ.ኤች.ዲ ያላቸውና ሌሎች አነስተኛ ዲግሪ ያላቸው በርካታ ባለሞያዎችን ቀጥረው ያሰሩ የነበሩ ምሁር ናቸው።
- አቶ በላይ ባለቤታቸውም በማስተርስ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን፣ በጋራ አንዲት ሴት ልጅ አላቸው።
- በተለያዩ የበጎ አድራጎት እንቅስቅሴዎች ላይ መሰማራት የሚወዱት አቶ በላይ፣ በርካታ ችግረኛ የሆኑ ተማሪዎችን እየከፈሉ አስተምረዋል።
- ወደ ፖለቲካዉ የመጡት በምርጫ ዘጠና ሰባት ወቅት ሲሆን፣ ያኔ ቅንጅትን ከመሰረቱት አራት ፓርቲዎች መካከል የነበረው የቀስተ ደመና አባል በመሆን፣ የወጣቶች ክፍል ሃላፊ ሆነውም ሰርተዋል።
- በ2000 ዓ.ም የአንድነት ፓርቲ ሲመሰረትም፣ ከመስራች አባላት መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ በ2002 የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤት አባል ሆነው ተመርጠው አገልግለዋል።
- አንድነት በፕላን እና በእቅድ ይመላለስ ዘንድ፣ ከሌሎች ጋር በመሆን የአምስቱ አመት እቅድ ፕላን በማዘጋጀትና በማሰራጨት፣ ፓርቲው አቅጣጫ እንዲኖረው ከማድረግ አንጻር ብዙ ሰርተዋል።
- የአንድነት ፓርቲ የራሱ ጋዜጣ ሊኖረው ይገባል በሚል፣ ፍኖት ጋዜጣ ታትማ እንድትወጣ፣ ቁልፍ ሚና ከተጫወቱት ሰዎች መካከል ነበሩ። ጋዜጣዋ በአገዛዙ እንዳትታተም እስክትደረግበት ጊዜ ጀምሮ የኢዲቶሪያል ቦርዱ ሃላፊ ሆነውም ሰርተዋል።
- በአንድነት ፓርቲ ዉስጥ፣ አገር ቤት እና ከአገር ዉጭ የነበሩ ምሁራን አክቲቪስቶችን ያሳተፍ የነበረዉን እና ለአባላት ትልቅ ስልጣና የሚያገኙበትን መድረክ ከፍቶ የነበረው፣ የአንድነት ዉይይት ፎረምን በማዘጋጀትን በመምራት አገልግለዋል።
- የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያገኘ ካደረጉት እንቅስቃሴዎች መካከል የሚጠቀሰው የሚሊየነሞች እንቅስቃሴ፣ ሐሳብ አመንጭና አስተባባሪ ሆነው የሰሩ ሰው ናቸው።
- ከስድሰት ወራት አንድነት እንዲመሩ የተመረጡት ኢንጂነርግ ግዛቸው ሽፈራው፣ በእወቀታቸውና አመራር ብስለትና ብቃታቸው በመተማመን፣ የአንድነት ፓርቲ ም/ሊቀመንበር ሆነው እንዲያገለግሉ በጠየቋቸው መሰረት፣ የፓርቲው ምክትል ሊቀምነበር ሆኔ እያገለገሉ ናቸው።
- የአንድነት ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት ኪራይን፣ ለአንድ አመት ከራሳቸው ወጭ በመክፈል የፓርቲው ሥራ እንዳይጨናገፍ ትልቅ አስተዋጾ በማድረግ፣ ከአዲስ አበባ ዉጭ ያሉ አራት ሌሎች የአንድነት ጽ/ቤቶችን ወጭ በመሸፈን፣ በገንዘባቸው ድርጅቱን እና ትግሉ ረድተዋል።