(ፍኖተ ነፃነት) በዝቋላ ብረታ ብረት ማምረቻ ፋብሪካ ንብረት አስተዳደር ከፍተኛ ሙስና መኖሩን አስመልክቶ የደረሳቸውን ጥቆማ በመንተራስ የጸረ ሙስና ኮሚሽን አጣሪዎች በፋብሪካው ምርመራ ሲያደርጉ ቢቆዩም የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አሊ ሱሌይማን ለፓርላማው አቅርበውት በነበረው የአስር ወራት የኮሚሽኑ ሪፖርት በዝቋላ ብረታ ብረት የታየው ክፍተት ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል በሚል ምክር ማለፋቸው በፋብሪካው እየተፈጸመ የሚገኘውን ብክነት በቅርበት የሚያውቁ ሰዎችን አስገርሟል፡፡
የፍኖተ ነፃነት ምንጮች እንደጠቆሙት ከሆነ ግልጽ ጨረታ ባልተደረገበት ሁኔታ 2.5 ሚልዮን ዩሮ ወጥቶባቸው የተገዙ የማምረቻ ማሽኖች ያለ አገልግሎት ተቀምጠዋል፡፡ ጸረ ሙስና ኮሚሽን በሪፖርቱ ከፍተኛ የምርትና የስራ ሰዓት ብክነት እንዲሁም ተመሳሳይ ችግሮች እንደሚስተዋሉ ከመጠቆም አልፎ ለፋብሪካው መሰረታዊ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብለው የተገዙት ማሽኖች የሚፈለገውን አገልግት በመስጠት ላይ እንደማይገኙ ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል፡፡ለፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ጥበበ አየለ በፍኖተ ነፃነት ተደውሎላቸው በስልክ አለ ስለሚባለው ከፍተኛ ሙስና እና ተያያዥ ችግሮች በሰጡት ምላሽ ‹‹በመጀመሪያ ደረጃ ጸረ ሙስና ኮሚሽን የእኛን ፋብሪካ በሚመለከት በፓርላማ ሪፖርት ስለማቅረቡ የማውቀው ምንም ነገር የለም፡፡ ምርመራ ተደርጓል መባሉም ከኛ እውቅና ውጪ ነው፡፡ ማሽኖቹን የገዛናቸው ግልጽ የሆነ ጨረታ በማውጣት ሲሆን አስፈላጊነታቸውም በፋብሪካችን ባለሞያዎች ታምኖበታል በዚህ ላይ ማሽኖቹ ያለ አገልግሎት አልተቀመጡም አስፈላጊውን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ›› ብለዋል፡፡
ተመሳሳይ ጥያቄ የቀረበላቸው የፋብሪካው ኃላፊ አቶ በፍቃዱ ዘውዴ በበኩላቸው ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ የዝቋላ ብረታ ብረት ፋብሪካ በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን የተመሰረተው ከደቡብ አፍሪካው የብረታብረት አምራች ፋብሪካ (ISCOR)ብረት ለማምረት የሚያስችል ንጥረ ነገር ተገዝቶ በ1990
መገንባቱ አይዘነጋም፡፡
↧
ጸረ ሙስና የዝቋላ ብረታ ብረት ፋብሪካን አስተዳደር በምክር ማለፉ አነጋጋሪ ሆኗል
↧