የቅርብ ጊዜው አርሰን ቬንገር ተለውጠዋል? ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሰውየው በዝውውር ገበያው የእርሳቸው የማይመስሉ እና ለደጋፊዎች ደስታ የፈጠሩ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡ ሳይታወቅባቸው የዝውውር ፖሊሲ ለውጥ አደረጉ? ተብሎ እስኪጠየቅ በዕድሜያቸው የበሰሉ ተጨዋቾችን መግዛት ጀምረዋል፡፡ ባለፈው ክረምት ለሉዊስ ሱአሬዝ ዝውውር 40 ሚሊዮን ፓውንድ ይዘው ሊቨርፑልን ቀረቡ የሚለው ዜና ሲሰማ ብዙዎች ባለማመን አይኖቻቸውን ቢጎለጉሉም ከሳምንት በኋላ ሜሱት ኦዚልን ከፍ ባለ ሂሳብ አስፈርመው ማምረራቸውን አሳይተዋል፡፡
በያዝነው ክረምት ቬንገር ዝውውሮችን እንደተለመደው ለማዘግየት በዓለም ዋንጫው በቂ ሰበብ ነበራቸው፡፡ ነገር ግን በቀኝ ፉልባክ ቦታ ማቲዩ ዴቡሺን ሊያገኙ መቃረባቸው ተነግሮ ሳያበቃ የአሌክሲስ ሳንቼዝን ግዢ በይፋ አጠናቅቀው ደጋፊዎቻቸውን ጮቤ አስረግጠዋል፡፡
አሁን ቬንገር ትልቅ ተጨዋች ሊገዙ ጠየቁ ሲባል ማንም አያሾፍም፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት በዚህ ወቅት የአርሰናል ደጋፊ የሆነ ሰው ክለቡ ኦዚልን በ42 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚገዛ፣ የኤፍ.ኤ.ካፕ ሻምፒዮን እንደሚሆን እና አሌክሲስ ሳንቼዝን እንደሚያስፈርም ቢነገረው የተቀለደበት ያህል ሊበሳጭ ይችል ነበር፡፡ ይሁን እንኒ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ ደጋፊዎቹ በአርሰናልንም ሆነ በቬንገር ላይ ዝውውሮችን አስመልክቶ ያላቸው አቋም ተለውጧል፡፡ ቡድናቸው ለከርሞ ክፍተቶቹን ደፍኖ ለዋንጫ እንደሚፎካከር መጠበቅ ጀምረዋል፡፡ ታዲያ ወደ ኤምሬትስ የሚመጡት ቀጣይ ተጨዋቾች እነማን ናቸው?
ቬንገር በጀርመን ተጨዋቾች ፍቅር የተለከፉ ይመስላሉ፡፡ ከወዲሁ ፔር ሜርቴሳከር፣ ሉካስ ፓዶልስኪ፣ ሜሱት ኦዚል፣ ሰርጂ ናብሪ እና ጌዲዮን ዘላለምን በቡድናቸው ቢይዙም ተጨማሪ ጀርመናዊ እፈለጉ ይገኛሉ፡፡ የፈረንሳዊው አይኖች ያረፉባቸው ሁለት አማካዮች ደግሞ ሳሚ ኬዲራ እና ላርስ ቤንደር ናቸው፡፡ የዴቡሺ ዝውውር መቼ በይፋ እንደሚጠናቀቅ ባይታወቅም አሁን የሚዲያው ትኩረት ያለው በኬዲራ ጉዳይ ላይ ነው፡፡
ኬዲራ ሆልዲንግ አማካይ ነው፡፡ የዝውውር ዋጋው ከ20-30 ሚሊዮን ፓውንድ የሚገመተው ተጨዋች በአርሰናል ማቲው ፍላሚኒ እና ሜኬል አርቴታን ተክቶ የተሰላፊነቱን ቦታ እንደሚይዝ ይጠበቃል፡፡ ምርጡ የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የጨዋታ ፍጥነት እና ፍሰት ላይ የኬዲራ እጅ አለበት፡፡ በዓለም ዋንጫው ግማሽ ፍፃሜ ብራዚልን ሲያዋርዱ የአዘጋጅ ሀገሯን ጥቂት የማጥቃት ሙከራ ለብቻው አጥፍቶ ጭራሽ በማጥቃቱ ሂደት ላይ ሲሳተፍ ታይቷል፡፡
በእርግጥ ኬድራ በባህርዩ በይበልጥ ከሳጥን ሳጥን የሚመላለስ የሚባል አይነት አይደክሜ ተጨዋች ነው፡፡ ይሁን እንጂ ተመሳሳይ ሚና ከሚወስዱ ሌሎች አማካዮች አንፃር ሳሚ መቼ ወደ ፊት መሮጥ እና መቼ ማፈግፈግ እንዳለበት ጠንቅቆ ማወቁ የተለየ ያደርገዋል፡፡ አማካዩ ጨዋታን በማንበብ እና ሜዳ ላይ የተሻለውን ውሳኔ በማሳለፍ የተመሰገነ ነው፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በከፍተኛ ጉዳት ብዙ ጨዋታ ሳያደርግ ቀርቶ ለዓለም ዋንጫው የመድረሱ ነገር በራሱ አስጊ የነበረ ቢሆንም የማታ ማታ የጀርመንን ቡድን እስከ ፍፃሜ ማሽኬድ ችሏል፡፡
የሳንቼዝን መፈረም ተከትሎ ወደ ሚዲያ የቀረቡት የአርሰናል ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኢቫን ጋዚዲስ የሰጡት ‹‹በቀጣይም ትልልቅ ተጨዋቾች ልናመጣ እየሰራን ነው›› የሚል መግለጫ የኬዲራን የዝውውር ወሬ ይበልጥ አቀጣጥሎታል፡፡
አርሰናል ኬዲራን ካገኘ ለከርሞ እውነተኛ የዋንጫ ተፎካካሪ እንደሚሆን እርግጠኛ ሆነው የሚናገሩት እግርኳስ ተንታኞች አሉ፡፡ ተጨዋቾቹ ከባለቤት ክለቡ ሪያል ማድሪድ የቀረለበትን የውል ማራዘሚያ እንደማይፈርም ካስታወቀ በኋላ መዳረሻ አዲስ ቦታው ኤምሬትስ ሊሆን እንደሚችል የበዛ ግምት አግኝቷል፡፡ ከስፔን እየተሰሙ ያሉት ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ቬንገር ለተጨዋቹ ግዢ ከወዲሁ 23 ሚሊዮን ፓውንድ ለማድሪዱ ክለብ አቅርበዋል፡፡ ኬዲራ በኮንትራቱ ላይ አንድ ዓመት ብቻ እንደሚቀረው እና እስካሁን ሁለት ጊዜ ውሉን እንዲያራዝም ተጠይቆ አሻፈረኝ ማለቱ ማድሪድ ከመሸጥ የተሻለ አማራጭ እንዳይታየው ሊያደርገው ይችላል፡፡
ጀርመናዊው እንደታሰበው ወደ አርሰናል ካመራ ከቡድኑ ተጨዋቾች ጋር ሜዳ ላይ ሊፈጥር የሚችለው ጥምረት ያጓጓል፡፡ ኬዲራ እና አሮን ራምሴይ ከፊት ለፊታቸው ኦዚል፣ ሳንቲ ካዞርላ እና ሳንቼዝን አድርገው የሚያሳዩት ብቃት በእጅጉ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን ዝውውሩን ለመጨረስ የሪያል ማድሪድ ስምምነት ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ ተጨዋቹ የሚጠይቀው ሳምንታዊ 150 ሺ ፓውንድ ደመወዝ በአርሰናል የፋይናንስ ባለሙያዎች ዘንድ አልተለመደም፡፡
ባለፈው ክረምት ኦዚል እስኪመጣ ድረስ የአርሰናል ትልቅ ደመወዝ ለፓዶልስኪ የሚሰጠው ሳምንታዊ 100 ሺ ፓውንድ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሳንቼዝን በሳምንት ከ120 ሺ ፓውንድ በላይ ሊከፍሉ ያመጡት አሰልጣኝ ለኬዲራ የጠየቀውን ያህልም ባይሆን ጥሩ ክፍያ ያዘጋጁለታል ተብሎ ይታመናል፡፡ አርሰናል በደመወዝ መጠን ችግር ምርጥ ተጨዋቾችን አለመግዛት ብቻ ሳይሆን የተሻሉ ከዋክብትን ሲያጣ እንደኖረ ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ጠንቅቀው ይገነዘባሉ፡፡
የኬዲራ ነገር ካልተሳካ ሌላኛው የቦታው ዒላማ ቤንደር ነው፡፡ ቬንገር ባለፈው ክረምትም ለዚህ ተጨዋች ዝውውር ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ በጉዳት ምክንያት የዓለም ዋንጫውን ያመለጠው አማካይ ወደ አርሰናል ከመጣ የውድድር ዘመኑን በትኩስ ጉልበት መወጣት ይችላል፡፡ ከሳምንት በፊት ሲሰሙ የነበሩ ዘገባዎች ተጨዋቹ የቬንገር ዋነኛ የክረምት እቅድ መሆኑን ሲያሳዩ አርሰናል የባየር ሌቨርኩዘኑን ተጨዋች ለማግኘት እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በእርግጥ የጀርመኑ ክለብ ተጨዋቾን የመሸጥ ፍላጎት የለውም፡፡ በዚያም በቅርቡ ረጅም ኮንትራት ያራዘመውን አማካይ ማቆየት ይሻሉ፡፡ ነገር ግን የኬዲራ የደመወዝ ጥያቄ ፈተና የሆነባቸው ቬንገር ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ቤንደር ሊያደርጉ እያሰቡ መሆናቸው ተነግሯል፡፡ ከደመወዝ ጥያቄው በተጨማሪ ቼልሲ ዘግይቶ የዝውውሩን ሂደት ለመቀላቀል እና ኬዲራን ለመውሰድ መዘጋጀቱ መታወቁ አርሰናልን ወደ ቤንደር ገፍቶታል፡፡
የብራዚላዊው ሉዊስ ጉስታቮ ስም በድጋሚ ከአርሰናል ጋር ተያይዟል፡፡ ባለፈው ክረምት ቬንገር ተጨዋቹን ሊያመጡት ሙከራ ሲያደርጉ ቢቆዩም የኋላ ኋላ በቡንደስሊጋው መቆየትን መርጦ ከባየርን ሙኒክ ወደ ዎልፍስበርግ አምርቷል፡፡ ጉስታቮ በአይነቱ እውነተኛ የተከላካይ አማካይ የሚባል አይነት ሲሆን ከአራቱ ተከላካዮች ፊት ለፊት ሆኖ ሽፋን በመስጠቱ በኩል አርሰናል ለዓመታት ያጣውን ብርታት ይጨምርለታል፡፡ ተጨዋቹ ለቦታው ሚና እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው የሚባሉትን የባላጋራን የማጥቃት ጨዋታ የመስበር እና የማጨናገፍ እንዲሁም ኳስን ተረጋግቶ እግር ስር ማቆየት ይችልበታል፡፡
ዎልፍስበርግ ገና ባለፈው ክረምት የገዛውን ተጨዋች ለመልቀቅ ቢቸገርም የሰሜን ለንደኑ ክለብ በውል ማፍረሻው ላይ የተቀመጠውን 26 ሚሊዮን ፓውንድ ከፍሎ ሊጠቀልለው ይችላል፡፡ ጉስታቮ ገና የ26 ዓመት ወጣት እንደመሆኑ በቦታው ለረጅም ጊዜ መጫወት ይችላል፡፡
ቬንገር እንደ ሃሳባቸው ትልቅ ደረጃ የሚሰጠው አይነት የተከላካይ አማካይ ካሰፈረው በክንፍ በኩል የሚጠቀሟቸው እና ከአጥቂ በስተጀርባ የሚያሰልፏቸው አማካዮች በይበልጥ በነፃነት ባላጋራቸውን ማጥቃት ይችላሉ፡፡ ሳንቼዝ እና ቲዮ ዋልኮት ከተቃራኒ መስመሮች እየተነሱ ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ሳጥኑ በመግባት ኦሊቪዬ ዢሩን ሊያግዙት ዕድል ያገኛሉ፡፡ ይህም ማለት አርሰናል ተመራጭ የ4-2-3-1 ፎርሜሽኑን ይዞ በእንቅስቃሴ መካከል ወደ 4-4-2- የሚለወጥበት ዕድል ይፈጥርለታል፡፡
በፊት አጥቂ ቦታ ወጣቱ ጆኤል ካምቤል፣ ሉካስ ፓዶልስኪ እና ዋልኮት እየተቀያየሩ ዢሩን ሊቀይሩት እና ሊያሳርፉት ይችላሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ ተያያዥ ተፅዕኖው በተጨማሪ ቬንገር የሚያመጡት የተከላካይ አማካይ ቡድኑ በፉልባኮቹ በኩል ሊፈጠርበት የሚችለውን ቀዳዳ ይሸፍንላቸዋል፡፡ በአሰልጣኙም ጭምር ወደፊት እየሄዱ እንዲያጠቁ የሚታዘዙት ፉልባኮች በተለይ ከፊት ለፊታቸው ያሉት የክንፍ ተጨዋቾች እየተመለሱ ካልረዷቸው የሚፈጠረው አደጋ በተከላካይ አማካዩ ብርታት ይቀንሳል፡፡
የሳንቼዝ ዝውውር የቡድኑን የአጥቂ ጥያቄ እንደማይመልስ አሁንም የሚከራከሩ በርካታ ደጋፊዎች አሉ፡፡ በእርግጥ ሳንቼዝ እና ዋልኮት ከመስመር እየተነሱ እያንዳንዳቸው ከ15-20 ጎሎች ሊያገቡ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ቬንገር ለአጨዋወት ምርጫቸው የግድ የሚያስፈልጋቸውን የዢሩ ሚና ችላ ማለት አይችሉም፡፡ ፓዶልስኪ እና ዋልኮት በብቸኛ የፊት አጥቂነት ለመጫወት ብዙ ጉድለት እንዳለባቸው አሳይተዋል፡፡ ስለዚህ ከፕሪሚየር ሊጉ ግዙፍ እና ጠንካራ የመሀል ተከላካይ መካከል በጨዋታው ፍልሚያ የሚጠበቀው ዢሩ ሲዳከም እና ሲጎዳ እየታየ ተመሳሳይ ተተኪ ይፈልጋል፡፡
ሎይክ ሬሚ እንዳለፉት የውድድር ዘመናት ሁሉ ስሙ ከአርሰናል ጋር ቢነሳም ዝውውሩ አላለቀም፡፡ ሁኔታው ቬንገር ልጁን ወደ ኤምሬትስ ለማምጣት እያቅማሙ አስመስሏቸዋል፡፡ የኪውፒአሩ አጥቂ አርሰናል የሚፈልጋቸው ነገሮች ሁሉ አሉት፡፡ ጎሎች ያገባል፤ ኳስ ጥሩ አድርጎ ያቀብላል፤ በፍጥነት ይሮታል እንዲሁም ተከላካዮችን በቀላሉ አልፎ ይሄዳል፡፡ ዢሩ እነዚህ ችሎታዎች የሉትም ማለት አስቸጋሪ ቢሆንም ሁልጊዜም የመጀመሪያ ኳስ ሲነካ እና በፍጥነት ሊሮጥ ሲሞክር ድክመቱ ጎልቶ ይወጣል፡፡
ሬሚ በእነዚህ መለኪያዎች አይታማም፡፡ ምናልባትም ጎል በማስቆጠር ችሎታው ከዢሩ ይሻላል፡፡ ባለፈው ሳምንት አርሰናል ይህንን አጥቂ በይፋ ያስፈርማል ተብሎ ቢጠበቅም አሁን ሌሎች ተቀናቃኞች ገበያውን ተቀላቅለውታል፡፡ ቀደም ብሎ ከሬሚ ጋር በግል ስምምነት ላይ ደርሷል ተብሎ የተነገረለት ቶተንሃም ተጨዋቹን ወደኋይት ሀርትሌን ለመውሰድ ይበልጥ የቆረጠ መስሏል፡፡ የሉዊስ ሱአሬዝን ጎሎች ከሌሎች ተጨዋቾች በድምር ለማግኘት የወሰነ የሚመስለው ሊቨርፑልም ለ27 ዓመቱ ፈረንሳዊ ፍላጎት አሳይቷል፡፡
ከሳምንት በፊት የቶተንሃም ተጨዋች ለመሆን ተቃርቦ የነበረው እና ለቻምፒዮንስ ሊጉ ተሳትፎ ሲል የአርሰናልን የመጨረሻ ዕድል ሊሞክር ሁኔታዎችን ያዘገየው ሬሚ ምናልባት ወደ አንፊልድ ሊያመራ ይችላል፡፡ አርሰናል በውሰት ኒውካስል የቆየውን ተጨዋች ካላስፈረም ምናልባትም የ22 ዓመቱ ኮስታሪካዊ ካምቤል የተሻለ የመጫወት ዕድል ያገኛል፡፡ የሚና እና የውጤታማነት ጥያቄ ካልተነሳ በስተቀር ቬንገር በጠቅላላው ካምቤልን ጨምሮ ስድስት በአጥቂነት መጫወት የሚችሉ ተጨዋቾች ይኖሩታል፡፡ ዢሩ፣ ፖዶልስኪ፣ ሳንቼዝ፣ ዋልኮት፣ ሳኖጎ እና ካምቤል ምናልባት ቬንገር በሬሚ ዝውውር ላይ እንዲቀዛቀዙ አድርገዋቸው ይሆን? ቢያንስ ግን የተከላካ አማካይ እና በረኛ ከዝውውር እቅዳቸው አይቀንሱም፡፡