እሁድ ሐምሌ 20/2006
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ (በሆነው)
ምስጋና ለዓለም ችግሮች ሁሉ መፍትሄ ላወረደና በእርሱ መንገድ ላይ ጥረት የማድረግን ክብር ላጎናፀፈን የዓለማት ፈጣሪ አላህ (ሱ.ወ) ይሁን! ክብርና ሰላም የሰው ልጆችን ከጨለማዎች ወደ ብርሃን ለማውጣት በአላህ በታጩትና የነብያቶች ቁንጮ እና መደምደሚያ በሆኑት ነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)፣ በባልደረቦቻቸውና በተከታዮቻቸው ላይ ይሁን!
ውድ የነብያት ወራሽ የሆናችሁ ዑለሞች፣ ውድ አላህ ጀነትን በእግራችሁ ስር ያደረገላችሁ እናትና አባቶች፣ ውድ ለእንክብካቤያችሁ አደራ የተባልንባችሁ እህቶች፣ ውድ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) እንድናከብራችሁ ያዘዙን ታላቆቻችን፣ ውድ እንድናዝንላችሁ ያዘዙን ታናናሾቻችን፣ ውድ አላህ (ሱ.ወ) ከስጋ ወንድምነት በላይ ወንድምና እህት እንድናደርጋችሁ ያዘዘን ወንድሞቻችን እህቶቻችን፣ ‹‹ከስሜታችን እና ስጋችን በላይ ለመሆን እና ነፍስያችንን ድል ለማድረግ ስላበቃን ለምናከብረው እና የደስታ ቀናችን ለሆነው ለ1435ኛው የዒድ አል-ፈጥር አደረሳችሁ›› እንላለን!
ይህን መልዕክት ስናስተላልፍ ሰላማዊ የመብት ጥያቄ አንስተን ነጭ ሶፍት በማውለብለባችን ዱላ በመምዘዝና ጥይት በማርከፍከፍ ደማችንን ያፈሰሱና ያስፈሰሱ፣ ያሰሩና ያሳሰሩ፣ የደበደቡና ያስደበደቡ፣ የሃይማኖታችንን እና የእህቶቻችንን ክብር የነኩና ያስነኩ የመንግስትና የህገ ወጡ መጅሊስ አካላት ‹‹እንኳን አደረሳችሁ!›› በማለት የሚያስተላልፉት የስላቅ መልዕክት የሚፈጥርባችሁን ህመም በመጋራት ነው።
የ1435ኛው ዓመተ ሂጅራ የዒድ አል-ፈጥር በዓል በአላህ መንገድ ላይ ፀንተን በመታገል ላይ እያለን መድረሱ ልዩና አስደሳች ዒድ ያደርገዋል። በመሆኑም የዘንድሮው ዒድ በታላቅ ደስታና አላህ (ሱ.ወ) ለዋለልን ለዚህ ታላቅ ውለታ ምስጋና በማቅረብ የምናሳልፈው ዒድ ይሆናል።
የተከበራችሁ ምእመናን!
ባለፉት ሶስት ዓመታት በእያንዳንዱ ሰላማዊ የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴያችን የአላህን የቅርብ እርዳታና እገዛ፣ እንዲሁም እዝነት በግልጽ እና በተጨባጭ አይተናል። ሂደቱንም ወደ ታላቅ እና መልካም ደረጃ ሊያደርሰው እንዳጨው እርግጠኛ እንድንሆን ያደረጉንን በርካታ ክስተቶችንም አስተውለናል። ህዝባችንን አላህ (ሱ.ወ) እንደመረጠው፣ እንደወደደውና በእዝነት አይኑ እንዳየው የሚያረጋግጡ ምልክቶችንም ተመልክተናል።
እኛ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች አዲስ ምዕራፍ የከፈትንበትን ሕጋዊና ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ካነሳን ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ሆኖናል። ከዚህ እልህ አስጨራሽ ጊዜ በኋላም ከታላቁ ረመዷን ባህሪ እና ትክክለኛ ትርጉም ጋር የሚጣጣም የፅናት ወኔ ተላብሶ ድል እያስመዘገበ መቀጠል ችሏል። በርካታ ታሪካዊ ድሎች ሙስሊሞች በተቅዋ (ፈሪሃ-አላህ) ለመሆን በሚታነፁበትና ወደ አላህ ይበልጥ በሚቀርቡበት በዚሁ ታላቁ ወርሃ ረመዷን መመዝገባቸው ይታወቃል።
ህዝባችንም ሕጋዊና ሰላማዊውን የመብት ጥያቄ ካነሳበት ጊዜ አንስቶ በነበሩት ሦስቱ ረመዷኖች ከስሜቱ በላይ በመሆንና ለኢስላም መስዋዕትነትን ለመክፈል በመዘጋጀት፣ ነፍሱን ድል በማድረግ እና የመንግስትን ክፉ ምኞት በማኮላሸት ታላላቅ ድሎችንና ታሪኮችን አስመዝግቧል። ሦስቱ ረመዷኖች ታሪካዊ፣ እጅግ ጣፋጭና አስደሳች፣ እንዲሁም በምድራዊም በሰማያዊም ሂሳብ ትልቅ ድሎችና ታሪኮች የተመዘገቡባቸው ናቸው። መንግስት ንፁህና ሰላማዊ በሆነው ውድ ህዝባችን ላይ የፈፀማቸው ኢ-ሕገመንግስታዊ እና ሰብዓዊነት የጎደላቸው ተደጋጋሚ እርምጃዎች ለሙስሊሙ ጥንካሬን፣ ብስለትን እና አንድነትን ሲያጎናፅፉት በሌላ በኩል መንግስት ምን ያህል ኢስላምንና ሙስሊሙን፣ በአጠቃላይም ሃይማኖትን ለማጥቃት ታጥቆ እንደተነሳ እንዲገነዘብ አድርገውታል። ይህም መንግስት ሽፋን ያደረገው ጥቁር መጋረጃ ተገፍፎ እርቃኑን እንዲቀርና ማንነቱ እንዲጋለጥ አስችሏል።
የተከበራችሁ ውድ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችንና ወንድሞቻችን!
መንግስት ላይ ከተጣሉ ኃላፊነቶች ውስጥ ዋናው እና መሠረታዊው በአንድ ሀገርና ባንዲራ ስር በተጠለሉ የተለያዩ እምነት ተከታይ ወንድሞች መካከል መልካም ግንኙነት እና ትብብር እንዲኖር ማድረግ መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በግልፅ በአደባባይ እንዳየው ተቃራኒ በሆነ እና ፍፁም ኃላፊነትና ሰብዓዊነት በጎደለው መልኩ በአንዳንድ የተለየ ዓላማ ባነገቡ ሚኒስትሮች መሪነት መንግስት ያለውን ኃይልና ስልት በመጠቀም በሁለቱ ታሪካዊና ጥንታዊ ሃይማኖቶች መካከል ግጭትና አለመግባባት ለመፍጠር ተንቀሳቅሷል። ሆኖም ይህ እጅግ አሳዛኝና ኃላፊነት የጎደለው ፀያፍ ተግባር ጨዋና አስተዋይ በሆኑት የሁለቱ እምነት ተከታዮች ጠንካራና ተከታታይ ጥረቶች ሊከሽፍና መልካም ውጤቶችንም ሊያስመዘግብ ችሏል።
አንድ ወገን የሆኑት የሁለት እምነት ተከታዮች እርስ በእርስ ተጋጭተው በደማቸው የመንግስትን የስልጣን እድሜ እንዲያረዝሙት ቢታጩም ለዓለም ምሳሌ የሚሆኑና የመከባበር እና የመፈቃቀር መገለጫ የሆኑ ተግባራትን በማከናወን የመንግስትን ሰይጣናዊ ምኞት መና አስቀርተውታል። ክርስትያኑ ማህበረሰብ ሙስሊሙንና ኢስላምን ለማጠልሸት መንግስት የከፈተውን ዘመቻ ንቆ በመተው እና ሀሰትነቱን በመረዳት መንግስት እርምጃ ሊወስድባቸውና ደማቸውን ሊያፈስ ያሳድዳቸው የነበሩ ሙስሊሞችን ቤቱንና ቤተ-ክርስትያኑን ከፍቶ ሸሽጓል፤ አስጠግቷልም። በዚሁ ረመዷን በሌሊት መንግስት የተከበረ ገላቸውን አራቁቶ በሌሊት የላካቸውን ጥብቅ እህቶቻችንን ልብስ በማልበስና ለቆሰሉ አካሎቻቸው እርዳታ በመስጠት ሰብዓዊነት በተሞላበት ሁኔታ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል። በዚህም መላው የክርስትያን ማህበረሰብ ሙስሊሙ የማይረሳውን ታሪካዊ ውለታ የዋለ ሲሆን የመከባበርና የመቻቸል ተምሳሌት የሆነ ተግባርም ፈፅሟል። ለዚህም የክርስትያን ወገኖቻችን ምላሽ መንግስት ሊፈጥረው ያሰበውን ብዥታ ሙስሊሙ ለመቅረፍና ቅንና ንፁህ አመለካከቱን ለማሳወቅ ያደረገው በሳል ጥረት፣ እንዲሁም ሙስሊሙ ያነሳው የመብት ጥያቄ ሁለቱም በጋራ ሊቆሙለት የሚገባ ሕጋዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ሕገ-መንግስታዊና ሰላማዊ መሆኑ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን መገመት አያዳግትም። መንግስት ህዝቡን አክብሮ የህዝብን ጥያቄና ሃሳብ ለመስማት እንደማይችልና ለመስማትም ዝግጁ እንዳልሆነ ለዓመታት በተግባሩ ቢያረጋግጥልንም አሁንም በሃይማኖቶች መካከል ግጭት እንዲፈጠር መጣር ሀገሪቱን ለውድቀት፣ ህዝቡንም ለእልቂት የሚዳርግ የክፋት መንገድ ነውና መንግስት ልቦና ገዝቶ ከዚህ ዓይነቱ ተግባር እንዲቆጠብ አጥብቀን እንጠይቃለን።
የተከበራችሁ ምእመናን!
በባርነትና በውርደት ለመኖር ፈቃደኛ ያልሆነ ማንኛውም የተከበረ ህዝብ ሊያሳካው የተንቀሳቀሰለትን ክብር የሚመጥን መስዋዕትነት መክፈሉ ግዴታ መሆኑ ተረድታችሁ መስዋዕትነት እየከፈላችሁለት ያለው መንገድ ትክክለኛው የእውነት መስመር መሆኑን ልናበስራችሁ እንወዳለን። ዛሬ ጥቂት መስዋእትነት ከፍለን ይህንን ግፍ ማስቆም ካልቻልን ነገ መጪውን ትውልድ ለህሊና ለሚዘገንን ስቃይና መከራ እንዳርገዋለን። መስዋእትነት ባደረ ቁጥር በእጥፍ የሚከፈል እንጂ እየቀነሰ የሚመጣ አይደለም። ዛሬ መስዋእትነት ላለመክፈል ብናፈገፍግ ነገ በእጥፍ የምንከፍለው በመሆኑ አሳድረነው በሚፈጠረው ተጨማሪ ጥፋትና አደጋ በታሪክም በአላህም ፊት ከመጠየቅ ዛሬ መስዋእትነትን ለመክፈል የመረጥነው መንገድ ከተጠያቂነት የሚያድን ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑ ለማረጋገጥ እንወዳለን።
በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥ ያስመዘገብናቸውም ሆነ በቀጣይ የምናስመዘግባቸው ስኬቶችና ድሎች ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በመንግስት በተወሰደባቸው ኢ-ሕገመንግስታዊ እርምጃዎች መገኖቻችን በከፈሏቸው የተለያዩ መስዋዕትነቶች የተገኙና የሚገኙ ናቸው። እያንዳንዱ ሰው ላይ የደረሰው ጉዳት እና የደም ጠብታ ስኬት እና ድላችን ላይ የራሱን ተጨማሪ አስተዋፅኦ አበርክቶ አልፏል። ወደ ስኬትም እንድንቃረብ እገዛ አድርጓል።
በከንቱ ተከፍሎ የቀረ መስዋትነት የለም፤ አይኖርምም። በመንግስት የተወሰዱ እና የሚወሰዱ እርምጃዎች ወኔያችንን እና ጥያቄያችንን ከፍ ያደርጉታል እንጂ ፈፅሞ በሞራላችንም በአቋማችንም ላይ ለውጥ አያመጡም። የእስከዛሬው የህዝባችን ምላሽም ለዚህ በቂ ምስክር ነው!
የተከበራችሁ ምእመናን!
በሙስሊሙ ላይ ሴራውን ከመጠንሰስ ጀምሮ እስከ መተግበሩ የተሳተፉ እና በንዋይና በስልጣን ፍቅር ታውረው ከተቃራኒ ወገን ጋር የተሰለፉ ጥቂት ሙስሊሞችን ሙስሊሙ ማህበረሰብ እና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፋረዳቸው ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ያለንን ተስፋ ልንገልፅላችሁ እንወዳለን። በተቋማችን መጅሊስ ውስጥ የተኮለኮሉት አመራሮች እና የመንግስት አካላት ባጠቃላይ ጸረ-ሃይማኖት የሆነ አቋም በመያዛቸው እና ለመብትና ነፃነት ደንታ የሌላቸው ከመሆናቸውም በተጨማሪ ባላቸው አቅም ሁሉ ለመጅሊስ እንዲዋትቱ ያደረጋቸው በየአመቱ በሃጅ ጉዞ ምክንያት ከሙስሊሙ የሚመዘብሩት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመሆኑ መላው ሙስሊም ማህበረሰብ ለችግሩ መፍትሔ እንዲፈልግለትና አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ለመጠቆም እንወዳለን።
የተከበራችሁ ሙስሊሞች!
በማንኛውም ጉዳይ ላይ አንድነታችንን ጠብቀን በጋራ የምንጓዝ ከሆነ ማንም መብታችንን ሊገፍ እና ሊያጠቃን እንደማይችል ግልፅ እንደመሆኑ እና በቁርአን እና በሃዲስ በጥብቅ የታዘዝንበት በመሆኑ አንድነታችንን አጠንክረን መያዝ እንዳለብን አበክረን ለማሳሰብ እንወዳለን። በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ በሃገር ውስጥም ሆነ በዲያስፖራው ሙስሊም ማህበረሰብ መካከል የሚታየው አንድነት ተስፋ ሰጪ በመሆኑ ኡለሞች (የሃይማኖት ሊቃወንት)፣ ዳዒዎች (ሰባኪያን)፣ ምሁራን እና መላው ሙስሊም ማህበረሰብ በመረባረብ መሰረት ማሲያዝ እና ወደሚፈለገው ደረጃ ከፍ ማድረግ ጊዜ የማይሰጡት ሃላፊነታቸው ሊሆን ይገባል።
ሃይማኖትም ሆነ ሌላ ሽፋን በመላበስ ሙስሊሙን ለመከፋፈል የሚደረጉ ጥረቶችን ሙሉ በሙሉ በፅኑ እናወግዛለን። አንድነትን በምኞት ብቻ እውን ማድረግ የሚቻል ባለመሆኑ፣ እንዲሁም ብዙ ጥረት እና ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ አንድነታችንን ከሚያናጉ ነገሮች መራቅ እና አንድነታችንን ሊያጠነክሩ የሚችሉ ተግባራትን ደግሞ በቆራጥነት መፈጸም እንደሚገባን አደራ ለማለት እንወዳለን።
የተከበራችሁ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አባላት!
ለመብት እንቅስቃሴው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ በርካታ ሰዎች ለእስር፣ ለማህበራዊ ቀውስ፣ ከስራ ለመፈናቀልና ለሌሎችም ችግሮች መዳረጋቸው ይታወቃል። እነዚህን ወገኖቻችንን መዘየር፣ አስፈላጊውን ትብብር እና እገዛ ማድረግ የአላህን ውዴታ የሚያስገኝ፣ አንድነታችንን የሚያጠናክርና የመብት ትግላችንን በድል ዙፋን ላይ ለማስቀመጥ የሚያግዝ በመሆኑ ሁላችንም በየአካባቢያችን የበኩላችንን አስተዋፅኦ እንድናበረክት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ከዚህም በተጨማሪ ሁሉም ሙስሊም ደስተኛ ሆኖ እንዲያሳልፍ ሁላችንም በዙሪያችን የሚገኙትን ሚስኪኖች፣ የቲሞች፣ ኡለሞች፣ ታማሚዎች እና የተለያዩ ችግሮች የደረሱባቸውን የማህበረሰቡን ክፍሎች መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ድጋፍ በማድረግ መርዳት ይኖርብናል።
የተከበራችሁ ሙስሊሞች!
አምባገነን መንግስታት ማንኛውንም ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ለማደናቀፍ በሚያደርጉት ጥረት በዋነኝነት ሊያሳኩ የሚፈልጉት ሁለት መሰረታዊ ስኬቶችን ነው። አንደኛው ለመብት ጥያቄው ፈፅሞ ምላሽ እንደማይሰጡ ለማሳመን በመሞከር የመብት ጠያቂውን ተስፋ ማሰቆረጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በሚወስዷቸው አምባገነናዊ እርምጃዎች ህዝቡ ተበሳጭቶ ሰላማዊነቱን ጥያቄ ውስጥ የሚከት የሃይል ምላሽ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ነው። ይህ የአምባገነኖች ፍላጎት እንዳይሳካ በማድረግ እስከፍፃሜው መንቀሳቀስ የቻለ ማንኛውም እንቅስቃሴ ጉዞውን በስኬት ያጠናቅቃል። የእኛ ሰላማዊ እና ህጋዊ የመብት እንቅስቃሴም የመንግስትን ምኞት እንዳይሳካ በማድረግ ተስፋ ሳይቆርጥ እና ስሜታዊነት ውስጥ ገብቶ ህግ ሳይጣስ በራሱ ድል መስመር መጓዝ ችሏል፤ ወደፊትም ይበልጥ በሰከነ እና በበሰለ ሁኔታ በመጓዝ በአላህ ፈቃድ ስኬትን ይጎናጸፋል።
የተከበራችሁ መብት ጠያቂዎች!
ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከመነሻው ያቀረባቸው ሶስቱ ህጋዊ የመብት ጥያቄዎች በማንኛውም የመብት ጥያቄ እንደሚመከረው ቀላል እና ከመንግስት ጋር ውይይት በማድረግ የተጀመሩ ናቸው። የመብት ጥያቄውም አመክንዮአዊ ሆኖና የመብት ጥያቄ ህግን እና ሳይንስን ተከትሎ ሲጓዝ በተቃራኒው የመንግስት ምላሽ ግን በተሳሳተ እርምጃ የታጀበ በመሆኑ መንግስት የራሱን አባላት እንኳን ማሳመን ሲሳነው ተስተውሏል። የመብት ጥያቄ እንቅስቃሴውም ሃያል እና ብቸኛ በሆነው ፈጣሪ ፈቃድ ዋነኛ ስኬት የሆነውን ህዝብን ከጎን የማሰለፉን አላማ ለማሳካት ችሏል።
መንግስት ተቋማችንን በመቆጣጠርና ትክክለኛውን አስተምህሮ የሚቃረን ርእዮተ አለም (Ideology) ወይም ቡድን (Sect) በማዘጋጀት፣ የዕውቀት ማሰራጫ ማዕከላት የሆኑትን መስጂዶች፣ መድረሳዎች፣ መርከዞች ወዘተ በመቀማት፣ እንዲሁም በዩኒቨርስቲ፣ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በተለያዩ የንግድ እና የሙያ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ለሃይማኖታቸው ተቆርቋሪ የሆኑ ሰዎችን በማስወገድ እና በማሽመድመድ ይዞት የተነሳውን ለሃይማኖት ደንታቢስ የሆነ ማህበረሰብ የመፍጠር አላማ ለማሳካት ቢንቀሳቀስም የሙስሊሙ የመብት ጥያቄ መነሳት መንግስት ህዝባዊ መሰረት እና ተቀባይነት እንዳይኖረው በማድረጉ ይህ ለሃገርም ለወገንም ጎጂ የነበረ ክፉ ውጥን ሳይሳካ ሊቀር ችሏል። ይህ ለሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን ለመላው ሃይማኖት ወዳድ ለሆነው ኢትዮጵያዊ ትልቅ ስኬት ነው።
መንግስት ሙስሊሙ ላይ የከፈተውን ዘመቻ በስኬት ቢያጠናቅቀው ለጥቃት በተመቸው ታሪካዊ እና ቀደምት በሆነው የክርስትና እምነት ላይ በሙሉ ሃይል ይከፍት የነበረውን ዘመቻ አና ጥቃት መገመት አያዳግትም። ከዚህም አንፃር ሙስሊሙ ማህበረሰብ ላነሳቸው ሶስት የመብት ጥያቄዎች መላው ሃይማኖት ወዳድ ኢትዮጵያዊ ምንም አይነት አስተዋፅኦ ቢያደርግ እና መስዋት ቢከፍል አግባብነት ያለው ነው ብለን እናምናለን።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ተራ የመንግስትን ፕሮፖጋንዳዎች እና ማጠልሸቶች ንቆ በመተው፣ ሃገሪቷን እየመሩ ከሚገኙ አካላት በላይ በሳል እና አስተዋይ በመሆን ህጋዊ፣ ህገ መንግስታዊ እና ሰላማዊ የሆነውን የሙስሊሙን የመብት ጥያቄ የሁሉም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ጥያቄ ነው ብላችሁ፣ ጥያቄያችንን ጥያቄያችሁ በማድረግ ከጎናችን የተሰለፋችሁ እና የበኩላችሁን አስተዋፅኦ ያበረከታችሁ ወገኖቻችንን እና ወንድሞቻችንን ሁሉ ከልብ እናመሰግናለን። የክርስትና እምነት ተከታይ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃገር ውስጥ እና የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የለውጥ ሃዋርያት (Activists) እና የተለያዩ ሚዲያዎች ይህ ምስጋና ይበልጥ የሚገባችሁ እና ቀዳሚዎች መሆናችሁ አያጠራጥርም!
ከዚህ ጋር በማያያዝ ሙስሊሙ ላይ የሚታየው መብቱን የማስከበር ጠንካራ ፍላጎት እና መነቃቃት ለሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን በሃገራችን ፍትህ፣ ነፃነት፣ እድገት እና ብልፅግና እንዲሰፍኑ ለማድረግ እጅግ ጠቃሚና ወሳኝ በመሆኑ በሃገር ደረጃ ሊጠቅሙ የሚችሉ ህልሞችን በመሰነቅ እና አርቆ በማሰብ ዛሬ መሰረት መጣል፣ እንዲሁም ነገሮችን ፈር በማስያዝ ህዝባችን ሃይማኖቱን ጠብቆ እና ተከባብሮ ስልጣኔን እውን የሚያደርግባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸች እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ለሚያሳስበው ቅን ዜጋ ሁሉ ለመጠቆም እንወዳለን።
ማንኛውንም መብት ለማስከበር ጥያቄውን የሚመጥን መስዋእትነት መክፈል የግድ ነው። በመሆኑም መብቱ እንዲከበርለት የሚፈልግ ሁሉ መክፈል ያለበትን ለመክፈል ዝግጁ መሆን ይጠበቅበታል። በተለይ ሙስሊሙ ይዟቸው የተነሳቸው ዓይነት ሀይማኖታዊ ጥያቄዎች ሲሆኑና ጉዳዩ የሃይማኖት ሲሆን ደግሞ የእምነቱ ተከታዮች ሌላ የመብት ጥያቄ ይዘው ከተነሱ ፍትህ ናፋቂዎች በላይ መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀትና መክፈልም ይጠበቅባቸዋል።
አሳሳቢው ጥያቄ ‹‹ዛሬ እኛ ለሃይማኖታችን እና ለህዝባችን ፍትህ እና ነፃነት ስንል እና በታሪክም በፈጣሪም ፊት የተጣለብንን ኃላፊነት ለመወጣት መክፈል ያለብንን እንከፍላለን? ወይስ መጪው ትውልድ ሊሸከመው የማይችለውን መከራ እና ስቃይ እናሳድርለታለን?›› የሚለው ነው። አሁን ሙስሊሙ ማህበረሰብ እየከፈለ ያለው መስዋእትነት ለተተኪው ትውልድ የከፋ መከራና ስቃይን ላለማስረከብና በምትኩ ፍትህ እና ነፃነትን እውን በማድረግ መጪው ትውልድ ሀይማኖቱን በነፃነትና እና በእኩልነት እያራመደ ለሀገራችን እድገትና ስልጣኔ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማበርከት የሚችልበትን ምቹ አየር ለመፍጠር ነው።ለዚህም ነው ህዝባችን ከጥቁር መጋረጃ ጀርባ በመንግስት አካላት የሚፈጸሙ ጥቁር ሽብሮችን ሁሉ በፅናት ተቋቁሞ የመብት ጥያቄውን መቀጠል የቻለው!
መንግስት በየትኛውም ዘመን ከነበሩ አምባገነን መሪዎች እና የሃይማኖት ጠላቶች በላይ የሁለቱን ታሪካዊ ሀይማኖቶች አከርካሪ ለመስበር በመወሰን የሙስሊሙን ደም ማፍሰስ ጀምሯል። ሁሉንም ሰማያዊም ምድራዊ ህግጋት በመፃረር የሃይማኖታችን ምልክት የሆኑትን ሂጃብ፣ ኒቃብ፣ መስጂድና መድረሳዎችን አዋርዷል። የሃይማኖት መመሪያችን የሆነውን ቁርአን አቃጥሏል። ሊከበሩ የሚገባቸውን የሃይማኖት አባቶች እና ሰባኪያን እርቃናቸውን በመግረፍ፣ ፂማቸውን በመንጨት፣ አካላቸውን በማጉደል እና ፀያፍ ስድብ በመስደብ አዋርዷል። የተከበረውን የእህቶቻችንን ገላ አራቁቷል፤ ደፍሯል። እንክብካቤ የሚፈልገውን ስስ ገላቸውን ለጠላት በፈረጠሙ ጡንቻዎች እና ለጠላት በተዘጋጁ መሳሪያዎች አድምቷል፤ ደብድቧል። ነጭ መሃረም እያውለበለቡ ሃይማኖታዊ መብታቸውን በጠየቁ ሰዎች ላይ ጥይት በማርከፍከፍ የንፁሀን ሙስሊም ወገኖችችንን ደም አፍስሷል። እጁን በደም አጨማልቋል። መስጂዶቻችንን አርክሷል። ሂጃብ፣ ቁርዓን እና ኒቃብ በማቃጠል ለሃይማኖታችን ያለውን ስር የሰደደ ጥላቻና ንቀት አሳይቷል። ‹‹አላህ የለም! እስቲ መጥቶ ያድናቸው!›› በማለት ሃገር ከሚመራ አካል የማይጠበቅ ወራዳ ንግግር በመናገር የፈጣሪያችንን ክብር ነክቷል።
ይህ በድቅድቅ ጨለማ ህዝባችንን በአወልያ በመደብደብ ተጀምሮ በድቅድቅ ጨለማ ሴት እህቶቻችንን በማራቆት እና በማዋረድ ከሀምሌ እስከ ሀምሌ የዘለቀውን ‹‹ጥቁር ሽብር›› የመሩና የተባበሩ በመጅሊስ መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አካላት ሁሉ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፋረዳቸው መሆኑን እና በደረሰው ግፍና በፈሰሰው ደምም ተጠያቂዎች መሆናቸውን ደጋግመን ልናሳውቃቸው እንወዳለን። የፈፀማችሁትን ዘግናኝ እና አሰቃቂ ወንጀል እኛም ሆንን ታሪክ ፈፅሞ የማይረሳው፣ ሀያልና ሁሉንም ቻይ የሆነው ፈጣሪም የማይዘነጋው መሆኑን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን – ‹‹ኣላህንም በዳዮች ከሚሰሩት ዝንጉ አድርገህ አታስብ›› ይላልና ቅዱስ ቁርአናችን! ጥቁሩን ሽብር የጠነሰሱ፣ የተባበሩና የፈጸሙ ሁሉ ማንነታቸው ተጣርቶ በህዝብና በፍርድ ፊት መቅረብ እንዳለባቸው ጽኑ እምነት ያለን በመሆኑ ከአገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ ፍርድቤቶች ድረስ ጉዳዩን ለማስኬድ ወስነናል። በመሆኑም መላው ኢትዮጵያዊና ለሃይማኖት መብት ተቆርቋሪ የሆነው መላው ዓለምአቀፍ ማህበረሰብ ከጎናችን እንዲሰለፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በእርግጥ በጥቁር ሽብር ዘመቻው የተፈጸመው ኢ-ህገመንግስታዊ እና ኢሰብዓዊ ድርጊት ዘግናኝ እና አሳዛኝ ቢሆንም ውርደቱ ግፉን ለፈጸመው መንግስት እንጂ መስዋዕትነቱን ለከፈለው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ክብር እና ድልም ነው። እስከዛሬ በከፈልነው መስዋዕትነት ከፍተኛ ውጤት አግኝተናል። በመክፈላችንም ደስተኞች ነን። ምናልባትም ወደ ስኬት በቀረብን ቁጥር የምንከፍለውም እየጨመረ እንደሚመጣ እናውቃለን፤ ለዚህም ዝግጁ ነን! የሰው ልጅ ህይወቱ ጣዕም የሚኖረው ያለውን ሁሉ ሊሰዋለት የተዘጋጀ ዓላማ ሲኖረው ብቻ መሆኑን ህዝባችን የተገነዘበና ይህንኑ ህይወትም ማጣጣም የጀመረ በመሆኑ ፈጽሞ ከዚያ በታች ወደሆነ የውርደት ህይወት አይመለስም።
ህዝባችን በፊርማው ከጣለብን ከባድ ሃላፊነት በላይ ስሜታችንን የነካው እና ይህ ህዝብ ምንም ዓይነት መስዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባው መሆኑን እንዲሰማን ያደረገን ለሶስት ዓመታት ያለምንም ክፍተት እና ጉድለት የዘለቀው ስሜቱ፣ ፅናቱ እና ፍቅሩ፣ እንዲሁም ቃልኪዳኑን ማክበሩ ነው። ይህ የመብት እንቅስቃሴ የህዝባችን ፍቅር በደማችን ውስጥ እንዲሰርጽ፣ መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ እንድናከብርና ከባድ ሃላፊነት እንዲሰማን አድርጎናል። በዚሁ አጋጣሚ ያጎደልነውን አስተካክለንና ሞልተን ለውዱ ህዝባችን ማድረግ ያለብንን ለማድረግና መክፈል ያለብንን ለመክፈል ያለንን ጠንካራ ስሜት ልንገልጽም እንወዳለን። ብቸኛ፣ ሃያልና ታላቅ የሆነው ፈጣሪ ጽናት፣ ኢኽላስና ቃልኪዳን የማክበርና የመፈጸም ዕድልን እንዲያጎናጽፈን ትማጸኑልን ዘንድ እንጠይቃለን።
በመጨረሻም የመብት ጥያቄያችንም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ አጠቃላይ የፍትህና የነጻነት ጥያቄ የስኬት ዙፋን ላይ ማረፍ የሚችለው በጥቂት ጀግኖች ወይም ሰዎች ከፍተኛ ጥረት እና መስዋዕትነት ሳይሆን በመላው የማህበረሰቡ አባላት ጥቂት አስተዋጽኦ መሆኑን ተረድተን ጥቂት ነው ብለን የምንንቀው ሳይኖር ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እንድናበረክት አጽንኦት ሰጥተን እንጠይቃለን።
ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለም!