-138 ሔክታር መሬት ተረክቧል
በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን አካል በሆነችው ዱከም ከተማ በሚገኘው የቻይና ኩባንያዎች ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ በጫማ ማምረት ላይ የተሰማራው ሁጂያን ግሩፕ የተባለው ኩባንያ፣ የራሱን የኢንዱስትሪ ዞን በለቡ አካባቢ ሊገነባ ነው፡፡
ኩባንያው የኢንዱስትሪ ዞን ፈቃድ በማውጣት ግንባታውን በ2007 ዓ.ም. ለመጀመር ማቀዱንና ለዚህም ተግባር 2.2 ቢሊዮን ዶላር መመደቡን፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ለመረዳት ተችሏል፡፡
ሁጂያን ግሩፕ ለመገንባት ያቀደው የኢንዱስትሪ ዞን የኢትዮጵያ መንግሥት እያዘጋጀ ከሚገኘው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ የተሠራ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ከተሰማራበት የጫማ ምርት በተጨማሪ በሚገነባው የኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ በጨርቃ ጨርቅና ልብስ ስፌት፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ፣ በኬሚካልና በፋርማሲዩቲካል የመሰማራት ዕቅድ አለው፡፡
በኩባንያው ዕቅድ መሠረት በኢንዱስትሪ ዞኑ ውስጥ 45 ኩባንያዎች እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ ይሰማራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሚገነባው ኢንዱስትሪ ዞን ውስጥ ሁሉም ኩባንያዎች ሥራ ሲጀምሩ በዓመት እስከ 250 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ የማስገኘት ዕቅድ አለው፡፡
ለዚሁ ተግባር እንዲረዳው መንግሥት 53 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያቀርብለት ኩባንያው ይፈልጋል፡፡ በተጨማሪም 15,555 ሜትር ኪዩብ ውኃ በቀን ኢንዱስትሪ ዞኑ እንደሚፈልግ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት ኩባንያው የሚፈልገውን ለቡ አካባቢ የሚገኝ 138 ሔክታር መሬት አቅርቦ ርክክብ መካሄዱን ለመረዳት ተችሏል፡፡ የኢንዱስትሪ ዞኑ ግንባታ የሚካሄደው በምዕራፎች ሲሆን፣ በመጀመርያው ምዕራፍ ማለትም በ2008 ዓ.ም. ሦስት የቆዳ ፋብሪካዎች ሥራ የሚጀምሩ መሆኑና በዚህም ሦስት ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በ2009 ዓ.ም. የፋብሪካዎቹ ቁጥር ወደ ስድስት እንደሚያድግና የተቀጣሪ ሠራተኞች ቁጥርም ስምንት ሺሕ እንደሚሆን፣ በኢንዱስትሪ ዞኑ የሚካተቱ 45 ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምሩ ደግሞ ለ30 ሺሕ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ዕቅዱ ያስረዳል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚገኘው አንድ የኢንዱስትሪ ዞን ነው፡፡ ይህ የኢንዱስትሪ ዞን ኢስተርን የኢንዱስትሪ ዞን የሚባል ሲሆን፣ በቻይና ኩባንያዎች የተመሠረተ ነው፡፡ ሁጂያን ግሩፕ የተባለው ኩባንያም በዚህ የኢንዱስትሪ ዞን በጫማ ማምረት ላይ የተሰማራ ነው፡፡ ኩባንያው አሁን ባለው ፋብሪካ 500 ሠራተኞችን መቅጠሩና ከዚህ ውስጥም 250 ሠራተኞች ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በየቀኑም አንድ ሺሕ ጥንድ ጫማዎችን በማምረት ላይ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር የኢንዱስትሪ ዞኖችን ማልማት በኢትዮጵያ መንግሥት እንደ ስትራቴጂ ተይዟል፡፡
ከተማ የሚያክሉ የኢኮኖሚ ዞን የሚል ስያሜ የተሰጣቸው የኢንዱስትሪ ዞኖች የማልማቱ ሥራ በቦሌ ለሚ አካባቢ የተጀመረ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በዚህ የኢንዱስትሪ ዞን ልማት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ላይ ያመነው የዓለም ባንክም 250 ሚሊዮን ዶላር ብድር በቅርቡ ፈቅዶ የኢትዮጵያ ፓርላማ ብድሩን አፅድቆታል፡፡ የኢኮኖሚ ዞን የተባሉትን ግዙፍ የኢንዱስትሪ ማዕከሎችን የመገንባቱ ሥራ በድሬዳዋና በኮምቦልቻ ከተሞች የመቀጠል ዕቅድ ተይዟል፡፡ የቻይና ኩባንያዎችም በድሬዳዋ የኢኮኖሚ ዞን የመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡
Source: Ethiopian Reporter