ከመላው ኢዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የተሰጠ መግለጫ
ለረዥም ጊዜ በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ጥያቄዎቻቸውን ሲያቀርቡ በነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ህውሓት/ኢህአዴግ የወሰደውን የኃይል እርምጃ አጥብቀን እናወግዛለን ፡፡ እንደ መኢአድ እምነት ለጥያቄዎቻቸው ተገቢውን መልስ መስጠት ሲገባ በግልባጩ መላው የኢትዮጵያን ሕዝብ ያሳዘነና ያስቆጣ የኃይል እርምጃ መወሰዱ የህውሓት/ኢህአዴግን ማንነት በተግባር ያሳየ ድርጊት ነው፡፡
ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም የእስልምና እምነት ተከታዮች በአንዋር መስጊድ በፀሎት ሥነ-ሥርዓታቸው ላይ ለጥያቄዎቻቸው መልስ እንዲሰጣቸው በመጠየቃቸው ጥያቄዎቻቸውን ወደጐን በመተው የኃይል እርምጃ በመወሰዱ ችግሩ ይፈታል ብለን አናምንም፡፡ ሆኖም በእለቱ በእምነቱ ተከታዮች ላይ እና በአካባቢው በነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የፀጥታ ሃይሎች የወሰድትን የሀይል እርምጃ አጥብቀን እናወግዛለን፡፡ አሁንም ቢሆን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥያቄዎቻቸው በሰላማዊና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት መፈታት አለበት ብለን እናምናለን፡፡ የህውሓት/ኢህአዴግ አባገነን ሥርዓት በእምነት ተቋማት ላይ እጁን አስረዝሞ የሚያደርገውን የአፈና ተግባር ማቆም አለበት፡፡
መኢአድ ለእስልምና እምነት ተከታዩችም የሚያስተላለፈው መልዕክት ከአሁን ቀደም በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎቻችሁን እንዳቀረባችሁት ሁሉ መፍትሔ እስክታገኙ ድረስ በሰላማዊ መንገድ መቀጠል እንዳለባችሁ ያሳስባል፡፡ በመጨረሻም መኢአድ የሚያምነው ችግሩ ስር ነቀል መፍትሔ የሚያገኘው የህውሓት/ኢህአዴግ አባገነን ሥርዓት በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲተካ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የሙስሊሙ ማህበረሰብ መኢአድ የሚያደርገውን ሰላማዊ ትግል በመቀላቀልና በመደገፍ የበኩላችሁን አስተዋፅኦ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናስተላልፉለን፣፣
አንዲት ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሐምሌ 17 ቀን 2006 ዓ.ም