(በግርማ ደገፋ ገዳ)
ድምጻዊ አበበ ከፈኒ (ጄኔቭ) የሚገኝ እና ኤርሚያስ አስፋው ናዝሬት የሚኖር፤ የእነዚህን ሁለት የናዝሬት ድምጻውያንን ሙዚቃ ስሰማ አንድ ትዝ የሚለኝ ሁኔታ አለ። እ.ኤ.አ. 1998 በናዝሬት (አዳማ) ከተማ፣ ፋሲል ሆቴል ውስጥ በከተማዋ የሚገኙ ድምጻውያንን ለውድድር በአንድ መድረክ ላይ አቀረብናቸው። ሃሳቡ የዳንኤል ክፍሌና የመስፍን አስገዶም ነበር። ዳንኤል በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ምክንያት አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ከርቸሌ ከርሞ የመጣ ጋዜጠኛ ነው።
በእለቱ በናዝሬት ከተማ ይደረግ የነበረውን የመኪና ውድድር ኮካኮላ ፋብሪካ ስፖንሰር አድርጎ ስለነበር፣ እኛንም ስፖንሰር እንዲያደርገን አድርገን፤ ከአዳማ የመምሕራን ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ የሙዚቃ አስተማሪ የነበሩት መምህር ጉልቴ በመሃል ዳኝነት ውድድሩን ዳኙልን። ለመምህር ጉልቴ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ድረስ ሄጄ የትብብር ጥየቃ ደብዳቤያችንን የሰጠዋቸውም እኔ ነበርኩ። ወደ ዝግጅቱ ለመግባት አቅም ያለው እየከፈለና በነጻ እንዲታደም በደብዳቤ የጋበዝነውና አክብሮን የመጣው ብዙ በመሆኑ፤ መቀመጫ ጠፍቶ ዝግጅቱ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ለመቆም የተገደደ እድምተኛ ነበረን።
“የሆዴን አውጥቼ ልንገርሽ” የሚባለውን ምርጥ የጥላሁን ገሰሰን ዘፈን የተጫወተውና በውድድሩ አንደኛ የወጣው፤ ኤርሚያስ አስፋው ነበር። አበበ ከፈኒና ሰለሞን ዘሥላሴ ሁለተኛና ሶስተኛ ወጡ። ያን ጊዜ አበበ ባገኘው ውጤት አልተደሰተም ነበር። ይሁንና ከትንሽ ጊዜያት በኋላ አውሮፓ የሚወጣበት አጋጣሚ ተፈጠረና ለማሳተም ያዘጋጀውን ካሴት ናዝሬት ለሚገኙ ሙዚቃ ቤቶች አድሎ በዚያው ድምጹ ጠፍቶ ቀረ።
ዛሬ፤ አበበ ተቀማጭነቱን አውሮፓ አድርጎ ከአውሮፓውያን ሙዚቀኞች ጋር ልዩ ልዩ ዝግጅቶቹን ለፈረንጅም ይሁን ለአፍሪካውያን ከማሳየቱም ባሻገር ሲዲም ለገበየ ካቀረበ ሰነባበተ። “ናዝሬት አዳማዬ” የተባለ የናዝሬት ልጆችን ልብ የሰበረ ዘፈን ተጫውቷል። “ያርግልህ በሉኝ” በጥሩ ሙዚቃው የሚጠቀስ ነው። በቅርብ ጊዜ የአሊ ቢራን “ሂያዲኒ” የተሰኘ የኦሮምኛ ዘፈን ተጫውቷል፤ ዩቱብ እና የሙዚቃ ነገር ይመለከተናል ያሉ ዌብ ሳይቶችም አስተናግደውለታል። በቅርብ ቀን የሚወጣ የነጥላሁን ዘውገ የኮመዲ ቪሲዲ ላይም የራሱ የሆነ ድርሻ እንዳለው ከተለጠፈው ፖስተር ላይ እያየን ሲሆን፤ በኮመዲው ላይ ድርሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ቪሲዲው ገበያ ሲወጣ የምናውቀው ይሆናል። የዚህ ቪሲዲ አሳታሚና አከፋፋይ ዘውገ አርት ፕሮሞሽን ነው።
ኤርሚያስ አስፋውም ጥሩ ዘፈኖች የተሰባሰቡበት ሲዲ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ገደማ ለገበያ አውሏል። በተለይ “ልረሳሽ አልቻልኩ” በጣም ጥሩ ዘፈኑ ነች። ዩቱብ ላይም ትገኛለች። የግጥም ደራሲውም ዳንኤል ክፍሌ ነው። ኤርሚያስ አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ባላውቅም ጥሩ የሙዚቃ ሰው በመሆኑ በዚያው የቀጠለ ይመስለኛል።
በእለቱ አንጋፋ ጋዜጠኛ የነበሩትን አቶ ያለው በለውን በክብር እንግድነት ጋብዘን ስለጋዜጠኝነት ለታዳሚው የሚሉትን ብለዋል። ድራማ፣ አስቂኝ ጭውውቶችና ግጥሞች ቀርበዋል። የፋሲል ሆቴል ባለቤት ልጅ የነበረው ወጣቱ ፋሲል ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ እጅግ ሰነባበተ። ብዙ የረዳን እሱ ነበር።
ዛሬ እንደዚህ ዓይነት ነገር ናዝሬት (አዳማ) ላይ አለ ወይ? አበበ ከፈኒ ለሥራ ጉዳይ ወደ ናዝሬት መመላለሱ አልቀረም፤ ስለዚህ ከኔ የተሻለ የሚያውቀው ይኖራል።
http://www.youtube.com/watch?v=2zu28SQFyfQ “የሆዴን አውጥቼ ልንገርሽ”
http://www.youtube.com/watch?v=aGkfV63IEdI “ናዝሬት አዳማዬ”
http://www.youtube.com/watch?v=QGH-0PmvD2k “ያርግልህ በሉኝ”
http://www.youtube.com/watch?v=t6ivqTKyLtI “ሂያዲኒ”
http://www.youtube.com/watch?v=04CGqQliWaY “ልረሳሽ አልቻልኩ”
↧
ድምጻዊ አበበ ከፈኒና ኤርሚያስ አስፋውን ሳስታውሳቸው
↧