Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የአፍሪካ ነገር – የኢትዮጵያ ነገር

$
0
0

መስፍን ወልደ ማርያም

የካቲት 2006

Prof. Mesfin

መስፍን ወልደ ማርያም

በሃያኛው ምዕተ-ዓመት ላይ የታወቀ የፈረንሳይ ፈላስፋ ነበረ፤ እሱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት ጊዜ ከእሱ ጋር በዩኒቨርሲቲ ሁለት አፍሪካውያን አብረውት ይማሩ እንደነበሩ ይናገራል፤ እነዚህ አፍሪካውያን የፈረንሳይኛ ቋንቋን ልክ አንደፈረንሳዮች እየተናገሩ፣ እንደፈረንሳዮች እያሰቡ ከፈረንሳዮቹ ተማሪዎች ጋር እኩል በትምህርት እየጎለበቱ ነበር፤ በኋላ እነዚህ አፍሪካውያን ወደአገራቸው ተመልሰው ሥልጣን ላይ ሲወጡ ሰፊ አገራቸው ለሁለቱ የተማሩ አፍሪካውያን የማይበቃ ሆነባቸው፤ ስለዚህም አንደኛው የአገር መሪ ሆነና ሌላውን ገደለው፤ የፈረንሳዩ ፈላስፋን ያሳዘነው ትዝብት ነው።

በአለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ የታየው የሥልጣን ሽኩቻ ለብዙ የአፍሪካ አገሮች የእድገት ማነቆ ሆኖ ቆየ፤ ከአውሮፓውያን ቄሣራዊ ኃይሎች ቅኝ አገዛዝ ነጻ ሲወጡ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለባቸው አገሮች ዛሬ ቆመው ቀርተዋል፤ በሰሜን አፍሪካ አልጂርያና ቱኒስያ እንደፈረንሳይ የሚቆጠሩ ናቸው ይባል ነበር፤ እነዚህ ትልልቅ አገሮች ለሁለት ለሁለት ሰዎች የማይበቁ ሆነው የመከራ አገሮች ሆነዋል፤ ከፈረንሳይ ጋር በአደረጉት መራራ ትግል ሕዝቦቹ የከፈሉትን መስዋእትነትና ትግላቸው አሳድሮባቸው የነበረውን የላቀ ተስፋ መሪዎቹ ዋጋ አልሰጡትም፤ (ተመስገን ደሳለኝ በፋክት ቁጥር 33 ‹‹የሕወሓት ሰማዕታት አጭር ማስታወሻ፣) በዚህም ምክንያት እነሱ ለአንድ ወንበር ሲፎካከሩና ተወዳዳሪዎቻቸውን አስረውም ሆነ ገድለው ወንበሩን ለብቻቸው ሲይዙት ቆይተዋል።

በአንድ በኩል ከወንበሩ በሚመነጨው ኃይልና ሀብት መከታን የሚያገኙ መስሏቸው በነበራቸው ተስፋ፣ በሌላ በኩል በምዕራባውያን ኃይሎች ላይ ተማምነው ሕዝባቸውን በመናቃቸው በአረብ አገሮች መሪዎች ላይ በቅርቡ በተከሰተው ወረርሺኝ ብዙዎች ከወንበራቸው ተደፍተዋል፤ የሁሉም አወዳደቅ የከፋ ውርደትን የለበሰ ቢሆንም አንደጋዳፊ ያለ አልነበረም፤ እኛስ ብንሆን በዓለም በሙሉ የተከበሩትን ንጉሠ ነገሥት እንዴት አዋርድናቸው! ያወረዷቸውስ ሰዎች በተራቸው እንዴት ተዋረዱ! ያዋረዱ ሁሉ ይዋረዳሉ፤ ሕዝብን ያዋረዱ ይዋረዳሉ፤ አገርን ያዋረዱ ይዋረዳሉ፤ የሰው ልጅን ያወረዱ ሁሉ ይዋረዳሉ።

ለጭቆናና ለክፋት ሰብአዊ መብቶችን እንደልብ እየጣሱ በጉልበተኛነት መታወቅ የራስን ታሪክ ራስን ዋቢ አድርጎ መጻፍ ነው፤ ያለፉት ባንዶች ተመችቷቸው ስለነበረ ወደፊትም የባንዶች ዕጣ-ፋንታ እንደበፊቱ ይሆናል ማለት ልበ-ደንዳናነት ብቻ ሳይሆን፣ በጥላሸት የጨለመ አእምሮ ብቻ ሳይሆን፣ በዛር ፈረስ ላይ ወጥቶ ወደገደል መጋለብ ነው፤ ከአሁን ወዲያ አገዛዙ ሲከሽፍ ሕዝቡ አብሮ ከከሸፈ በአገዛዙ ማመካኘት አይጠቅምም፤ ሕዝብ ኃላፊነትን መውሰድ አለበት፤ አገር በጥቂት ሰዎች አይገነባም፤ እያንዳንዱ ሰው የድርሻውን ኃላፊነት መቀበል አለበት፤ የእየአንዳንዱ ሰው አስተዋጽኦ አሰፈላጊ ነው።

የእያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት ከየት የመጣ ነው? አንደኛ አያት ቅም-አያቶቻችን ይችን አገር ለመገንባትና በነጻነት ለመጠበቅ በሕይወታቸው ሳይቀር የከፈሉት ከባድ መስዋዕት እየቆረቆረን ኃላፊነትን ይጭንብናል፤ በሞታቸው ያስተላለፉልንን ኩራትና ክብር ብናጣ የምናዋርደው እነሱን ብቻ ሳይሆን ራሳችንንም ነው፤ የኃላፊነታችን አንዱ ምንጭ ይህ ነው።

ሁለተኛው የኃላፊነታችን ምንጭ ልጆቻችን ወይም የሚቀጥለው ትውልድ ነው፤ እኛ ከአባቶቻችን የወረስነውን ኩራትና ክብር መጠበቅ አቅቶን ለልጆቻችን ውርደትን እንዳናወርስ ኃላፊነት አለብን፤ ሲሆን የወረስነውን ኩራትና ክብር አዳብረንና አጠንክረን ማቆየትና ለልጆቻችን ማውረስ፣ ቢያንስ ግን የተረከብነውን ማስረከብ ግዴታችን ይሆናል፤ አለዚያ መክሸፍ ይሆናል፤ ኢትዮጵያዊነት ማንነት አይደለም ከተባለ፣ ከኋላችን በሕይወት መስዋእትነት የተረከብነውን ክደናል፤ ከፊታችንም ለልጆቻችን የምናስረክበው የጋራ እሴት የለንም፤ በወጥመድ ውስጥ እንዳለች አይጥ መንፈራፈር ብቻ ነው።

በአገርና በአገዛዝ ሥርዓት መሀከል ያለውን ገደል ማየት የማይችሉ ሰዎች የወጣቱን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ሲያላሉት፣ የወያኔ ካድሬዎች እየተቀባበሉ ሲያራግቡት ውርደታችን የለበስነውን ክብራችንን እየገለጠ ገብቶ ራቁታችንን እያስቀረን ነው፤ ኢትዮጵያም እንደኮንጎ፣ ኢትዮጵያም እንደኒጄር፣ ኢትዮጵያም እንደመሀከለኛው አፍሪካ፣ ኢትዮጵያም እንደሩዋንዳ፣ ኢትዮጵያም እንደሱዳን፣ ኢትዮጵያም እንደሶማልያ ወደትርምስ እየዘቀጠች መሆኑን ምስክሮች ሆነን እያየን ነው፤ ምዕራባውያን ኃይሎች ለውርደታችን እንጂ ለክብራችን እንደማይጠቅሙ በኢራቅ፣በአፍጋኒሰታን፣ በፓኪስታን ለሆነው ሁሉ ምስክሮች ሆነን እያየን ነው።

ከሃምሳ ዓመታት ያህል በፊት በማናቸውም ነገር የአፍሪካ መሪዎች ሆነን የጀመርነው ሰዎች ዛሬ በዚህ ትልቅ የአፍሪካ አህጉር ኔልሰን ማንዴላ ከሚባል ትልቅ ሰው በቀር ስሙ በዓለም የሚጠራ አለመኖሩ የውርደታችንን ጥልቀት ያመለክታል፤ በኔልሰን ማንዴላ ትልቅነት ላይ ብቻ ሳይሆን በኔልሰን ማንዴላ ህልውና ላይም ኢትዮጵያ ማኅተምዋን በጉታ ዲንቃ ሃይማኖት አማካይነት ማሳረፍዋን አልዘመርንበትም፤ በአብዲሳ አጋ የአውሮፓ አርበኝነት አልዘመርንበትም፤ በዘርዓይ ደረስ የአውሮፓ አርበኝነት አልዘመርንበትም፤ በአበበ አረጋይ አርበኝነት አልዘመርንበትም፤ በበላይ ዘለቀ ስቅለት እንጂ በአርበኝነቱ አልዘመርንለትም፤ ኢትዮጵያን የጠበቋትን ልጆቿን፣ ኢትዮጵያን ያስከበሯትን ልጆቿን ታሪክ ረግጦና ችላ ብሎ ለባንዶችና ለባንዶች ልጆች ውዳሴ ከርስ የሚዘምር ትውልድ ውርደትን ይለብሳል፤ በኀልዮም ሆነ በነቢብ፣ ወይም በገቢር፣ አውቆም ይሆን ሳያውቅ አገሩንና ወገኑን ያዋረደን ማንም አያከብረውም፤ በሆዳሞች የተገነባውና የሚገነባው ሁሉ ከርሰ-መቃብር ውስጥ ይፈራርሳል።

የዛሬ ሁለት መቶ ዓመታት ግድም አንድ የአንግሊዝ ፈላስፋ ሕዝብን ስለማዶልዶም የሚከተለውን ብሎ ነበር፤ ዛሬ ለኛ የሚናገር ይመስላል፡–

ለጥሩ ዓላማም ቢሆን እንደፈለገ የሚያገላብጣቸው የተገሩ ለዘብተኛ መሣሪያዎች እንዲሆኑለት የራሱን ሕዝብ የሚያቀጭጭ ሀገረ-መንግሥት በትንንሽ ሰዎች ምንም ትልቅ ነገር ማከናወን አንደማይቻል ይገነዘባል፤ መሣሪያው በቀላሉ እንዲሠራለት ሁሉንም ነገር መስዋእት በማድረግ መሣሪያውን ፍጹም አድርጎ ሲስል  ያወደመው የሕይወት ኃይል በመጨረሻ ላይ  ለምንም ነገር አይጠቅመውም፡፡  

በእንግሊዝኛው  … a state which dwarfs its men, in order that they may be more docile instruments in its hands even for beneficial purposes, will find that with small men no great thing can really be accomplished; and the perfection of the machinery to which it has sacrificed everything will in the end avail it nothing, for want of the vital power which, in order that the machine might work more smoothly, it has preferred to banish.

በሃያ አንደኛው ምዕተ ዓመትም ኢትዮጵያ በረጅም ታሪክዋ ሲከሽፍባት የቆየውን ሥልጣንን የመግራት ብቃት ማግኘት አቅቷት ትናንት ከተፈጠሩ አገሮች ተርታ ተሰልፋ ትገኛለች፤ ይህ ውርደት የማይሰማው ባለሥልጣን ነኝ-ባይ ከነሎሌዎቹ በውርደት ባሕር እየሰመጠ ነው፤ የሚሰምጠው ሎሌዎቹን ብቻ ይዞ አይደለም።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>