Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

‹‹የአንዳርጋቸው ጽጌን የሞት ቅጣት ሊያፀኑ የሚችሉት ፕሬዚዳንቱ ናቸው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

$
0
0

ባለፈው ዓርብ በጽሕፈት ቤታቸው ከጋዜጠኞች ጋር የተወያዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የሞት ቅጣት ሊፀና የሚችለው በፕሬዚዳንቱ ይሁኝታ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ላይ ያላት የመሪነት ሚና እንዳልቀነሰ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥታቸው የአገር ውስጥ የግል ዘርፉን ለማበረታታት እየሠራ እንደሆነና የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትን እያሰረ ያለው በፖለቲካ አቋማቸው የተነሳ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡ የደመወዝ ጭማሪውን መጠንም ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ዓርብ ሐምሌ 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ከ9፡00 ጀምሮ ከሁለት ሰዓት በላይ በፈጀው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ከጋዜጠኞች በርካታ ጥያቄዎችን ያስተናገዱ ሲሆን፣ ከእነዚህም አንዱ ሪፖርተር የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ በድጋሚ የማይታይ ከሆነ የሞት ፍርዱ ተፈጻሚ ይሆናል ወይ? ሲል የጠየቃቸው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሞት ፍርድ ተፈጻሚ የሚሆነው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ካፀደቁት በኋላ እንደሆነ አስታውሰው፣ ይኼን ጥያቄ መመለስ የሚችሉት ፕሬዚዳንቱ ብቻ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የነበራት ተሰሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ስለመቀነሱ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በደፈናው የኢትዮጵያ ተቀባይነት ቀንሷል ከማለት ይልቅ በየትኛው ዘርፍ እንደሆነ ተለይቶ ጥያቄው ቢቀርብ የተሻለ እንደሚሆን ካስረዱ በኋላ፣ በእሳቸው እምነት የኢትዮጵያ የመሪነት ሚና አሁንም እየቀጠለ ለመሆኑ ማሳያ የሚሏቸውን ጉዳዮች ጠቅሰዋል፡፡ የመጀመርያው ጉዳይ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ የአፍሪካውያንን ድምፅ ማሰማት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ተፅዕኖ አሁንም ጉልህ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እንደ ምሳሌም በዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር በሚመራው የአረንጓዴ ዕድገት ፎረም ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሯ አማካይነት የቦርድ አባል ሆና መመረጧን ጠቅሰዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2015 የሚጠናቀቀው የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ከተጠናቀቀ በኋላ ስለሚቀጥለው ሁኔታ አፍሪካ ያላትን ድምፅ ለማሰማት ከተወከሉት አገሮች መካከል አንዷ ኢትዮጵያ እንደሆነችም አመላክተዋል፡፡ የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) አፍሪካ ላይ በተለየ ሁኔታ ትኩረት አድርጎ መሥራቱን ለመቃወም የተደረገውን ትግል በስኬት ለመደምደም፣ በተለይ የኬንያ ፕሬዚዳንት ክስ በሥልጣን ላይ እስካሉ ድረስ እንዳይነሳ ለማድረግ የኢትዮጵያ መሪነት ሚና ጉልህ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡ ይኼን ስኬት የጠቀሱት ባለሥልጣናት ከተጠያቂነት ቢያመልጡ ደስተኛ ስለሆኑ ሳይሆን፣ የአገሮች ሉዓላዊነትና የሕዝቦች ምርጫ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ስለሆነ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እስርም የተለየ ፖለቲካ ስለሚያራምዱ የተወሰነ ውሳኔ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያንና አካባቢውን በሽብርተኝነት ለማናጋት በተቀናጀ ሁኔታ ከሚሠራው የሽብር መረብ ጋር ግንኙነት ፈጥረው በመገኘታቸው እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የጦማርያኑና የጋዜጠኞቹ ጉዳይም ከተመሳሳይ መረብ ጋር የተገናኘ እንደሆነ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥታቸው የዜጎችን ሰላማዊ ኑሮ ለማረጋገጥ የሽብርተኝነት መረቡን ለመበጣጠስ የጀመረውን ስኬታማ ሥራ አጠናከሮ እንደሚቀጥልም ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ሥር ተወሽቀው የሽብር ተግባር ላይ ተሳታፊ የነበሩ ጥቂት ግለሰቦች ታሰሩ ማለት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ታሰሩ ማለት እንዳልሆነም በመጠቆም፣ ለምርጫ 2007 ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እያደረጉት ያለው ዝግጅት ሊስተጓጎል እንደማይችልም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት አቶ አንዳርጋቸውና ግንቦት 7 ብቻቸውን ኢትዮጵያ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ከባድ እንደማይሆን ቢገባውም፣ እነዚህ የሽብር ቡድኖች የተደገፏቸውና የሚተማመኑባቸው አገሮች ጋር ከሠሩ ጉዳቱ ከባድና አካባቢያዊ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ግን አስረድተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በቁጥጥር ሥር መዋል በሽብርተኞቹ ላይ የሚያመጣው ተፅዕኖ ከባድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከአስመራ ወደ ደቡብ ሱዳን ለመዘርጋት የተሞከረው መረብ እየተበጣጠሰ ለመምጣቱ የአቶ አንዳርጋቸው መያዝ ማሳያ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ በቅርብ ጊዜያት የጋምቤላ ንቅናቄና የኦብነግ አባላት በቁጥር ሥር መዋላቸውም የሽብር ቡድኑ አባላት የሌላ አገር ዜግነት ቢኖራቸውም፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እስከነኩና ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባለው የሽብር ወንጀል እስከተካፈሉ ድረስ ዕርምጃ ከመውሰድ ኢትዮጵያን የሚያቆማት አካል እንደሌለም አስታውቀዋል፡፡ በተለያዩ ሙያዎች ውስጥና በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በመጠለል የሽብር ወንጀል ላይ ተካፋይ ከሆኑ በኋላ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የውጭ ኃይሎችን በተለይም ኤምባሲዎችን በመጠቀም የኢትዮጵያን መንግሥት ለመጠምዘዝ ሙከራዎች እየተደረጉ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት በማክበር ሕጋዊ ዕርምጃ ከመውሰድ የሚያግዳቸው ኃይል እንደሌለ አመልክተዋል፡፡

በተደጋጋሚ የፋይናንስ ችግር የለም በሚል መንግሥታቸው ቢገልጽም፣ በዚህ ችግር በተለይ የአገር ውስጥ የግሉ ዘርፍ እየተጠቃ ስለመሆኑ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት ለብድር ያስቀመጠውን ገንዘብ አሟጦ ጥቅም ላይ የሚያውል አካል ባልመጣበት ሁኔታ የገንዘብ ችግር አለ ማለት ተገቢ እንደማይመስላቸው ገልጸዋል፡፡ 70 በመቶ የባንክ ብድር ለማግኘት 30 በመቶ የፕሮጀክት ወጪ ማሳየት የሚጠይቅ ሕግ ያለ ሲሆን፣ የውጭ ባለሀብቶች ይህን 30 በመቶ ማሽንን በኮላተራልነት እያቀረቡ እያለ ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች መከልከሉ አግባብነት ያለው ስለመሆኑ የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የውጭ ባለሀብቶች ፋብሪካ በመንቀል ሲመጡ የቴክኖሎጂ ሽግግር ስለሚያመጣ የተፈቀደ ቢሆንም ይህን የማድረግ አቅም ያለው የአገር ውስጥ ባለሀብት እስከመጣ ድረስ መንግሥት ለአገር ውስጥ ባለሀብቱ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያጤነውም ቃል ገብተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ መንግሥታቸው ይፋ ባደረገው የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ጭማሪ መጠን ላይ የተጠየቁ ሲሆን፣ በሐምሌ ወር መጨረሻ እስኪገለጽ ድረስ የመንግሥት ሠራተኞች በትዕግሥት እንዲጠባበቁ ጠይቀው፣ ገና የደመወዝ ጭማሪው መጠን ሳይታወቅ በአንዳንድ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ አሳሳቢ መሆኑን ግን ተቀብለዋል፡፡ መንግሥት የደመወዝ ጭማሪ ያደረገው ባለፉት ሁለት ዓመታት በገንዘብና በፊሲካል ፖሊሲው እንዲሁም በአስተዳደራዊ ዕርምጃዎች አማካይነት የዋጋ ግሽበቱን ኢኮኖሚያዊ ጤንነት ጋር በተጣጣመ መልኩ በአንድ አኃዝ እንዲገደብ ካደረገ በኋላ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ የዋጋ ግሽበቱ የመንግሥት ሠራተኛውን ብቻ ሳይሆን በዝቅተኛ ደመወዝ ኑሯቸውን የሚገፉ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ እንደሚጎዳ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ የዋጋ ግሽበትን ጉዳት በሚፈለገው መጠን መቀነስ ባይቻልም አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ገቢያቸው እንዲጨምርና የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ለማድረግ መንግሥታቸው የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የደመወዝ ማስተካከያው የሚደረገው የመንግሥት ሠራተኞችን ኑሮ ለማሻሻል ቢሆንም፣ ስግብግብ ነጋዴዎች የሚያደርጉት የዋጋ ጭማሪ ችግር እንዳይፈጥር መንግሥት ቁጥጥር እንደሚያደርግና አደብ እንዲገዙ ለማድረግ ዕርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ነጋዴዎቹን የማሳመንና የማስረዳት ሥራ እየሠራ መሆኑን በመጠቆም፣ ከሕጋዊ ዕርምጃ ባለፈ ማግባባት መምረጡን አስረድተዋል፡፡ ሕጋዊ ዕርምጃ የሚወሰደው ስግብግብ ነጋዴዎች ካስገደዱ ብቻ እንደሚሆንም አመላክተዋል፡፡

 

Source: Ethiopian Reporter

ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሰጡት መግለጫ – ክፍል 1& &2  (ሐምሌ 11/2006 ዓ.ም)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>