አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በደቡብ ክልል የወላይታ ዞን የፓርቲው አመራር የሆኑት ወ/ሪት ሀዲያ መሀመድ ዓሊ አንድነት ፓርቲ በወላይታ ለሚያደርገው ሕዝባዊ ስብሰባ በፓርቲው የተዘጋጀ ፍላየር ከፓርቲው አባሎች ጋር በመሆን ሲያሰራጩ በፖሊስ ተይዘው መታሰራቸው የሚታወስ ሲሆን ጥር 8 ቀን 2006 ዓ.ም በወላይታ ዞን ፍ/ቤት ቀርበው በ1000. 00 /አንድ ሺህ ብር/ ዋስትና መለቀቃቸውን ፍኖተ ነፃነት መዘገቧ ይታወሳል፡፡
በወላይታ ዞን ከ/ዐ/ህግ ይግባኝ ባይነት ጥር 8 ቀን የተሰጠው ውሳኔ ተከሳሿ ጥፋተኛ የተባሉበት ወንጀል በዓለም አቀፍ ሽብርተኞች አስተሳሰብ ሲቀሰቅሱ የነበሩትን እንዳለ በመውሰድ ከአስተሳሰብ ባለፈ መልኩ በተግባር በአገራችን ውስጥ ተቻችሎ የመኖር ሁኔታ የሚያቃውስና ወደ ጦርነት የሚያመራ ጽሑፍ በርካታ ገፆች ይዛ የተገኙትን ግለሰብ በጥፋታቸው ልክ መቅጣት ሲገባ በጣም ዝቅተኛና ተመጣጣኝ ያልሆነ ቅጣት በመሰጠቱ ቅር ብሎኛል በማለት የስር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ በማሻሻል ከጥፋታቸው ጋር የሚመጣጠን ቅጣት እንዲሰጣቸው በማለት በወላይታ ከተማ ለሚያስችለው መደበኛ ተዘዋዋሪ ችሎት እንዲቀርቡ አዟል፡፡
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የተቃዋሚ ፓርቲ አባሎችን በማስፈራራት፣ በመደብደብና በማሰር ሀሰተኛ ምስክር አዘጋጅቶ ክስ መመስረት ለማሸማቀቅ የሚደረገው ሙከራ አባላትን እያጠናከረ እንጂ እነሱ እንደሚያስቡት እንዳልሆነ ለፍኖተ ነፃነት የገለጹት የፓርቲው አባላት ወደፊትም ሰላማዊ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡