Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

እኛና ገዥዎቻችን –በቢርደያ ይሃማክ

$
0
0

ጫርጫር ማረግ አምሮኛል፡፡ ‹እኛና ገዥዎቻችን› በሚል  ርዕስ ሥር ተከታታይ ጽሑፎችን ለማቅረብ ወስኛለሁ፤ ልጀምር ነው፤ ቀጠልኩ፡፡

ቀጥያለሁ—–

(ፀሐፊ፡- ቢርደያ ይሃማክ   e-mail: aklilhabte@gmail.com)

ሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2004 ዓ.ም. 5 ሰዓት አካባቢ ወደ ደንበል ለመሄድ ከጥቁር አንበሳ ሼል ስነሳ በየቀኑና በየቦታው እንደተለመደው ታክሲ አጣሁ፡፡ ሞልተው የሚያልፉ ታክሲዎችን በመሸኘትና የመለስ ዜናዊ ፎቶ የተለጠፈበትን ጥቁር ከነቲራ የለበሱ አንዳንድ ባልቴቶችን በማየት ብዙ ደቂቃዎችን በክብር ከሰዋው በኋላ በእግር ጉዞዬን ጀመርኩ፡፡ እነዚህን ባልቴቶች ሳይ የወጣቶች ሊግ፣ የሴቶች ሊግ እና የቀበሌ ሸማቾች ማህበር ትዝ አሉኝና ተናደድኩ፤ ለምን እንደተናደድኩ የገመተ አለ@ በጣም ጥሩ፤በደርግ ጊዜ የነበረው የአገልግሎት ሱቅ (የቀበሌ ሱቅ) ስኳር፣ አሻቦ፣ ቡና የሚሸጥበት ዋጋ ውጭ በገበያ ላይ ከነበረው ዋጋ ምን ያህል ይቀንስ እንደነበርና ከቀበሌ መግዛት በርግጥ ሰውን እንዴት ይገላግል እንደነበር ያየሁ ሰው ዛሬ የወያኔ ባላባቶችና ቁልፍ ነጋዴዎች ዋጋን እንቆጣጠራለን በማለት የሆነ ውዥንብር ፈጥረው ወይም የነሱ ብቻ በሆኑት ግዙፍ ጅምላ አከፋፋይ ድርጅቶቻቸው ምርትን ሆን ብለው ደብቀውና አከማችተው የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ካደረጉ በኋላ ጅንአድ፣ ሸማቾች ወዘተ በሚሏቸው ቱቦዎቻቸው በኩል ገበያ ላይ ካለው ዋጋ አንድ ብር ወይም ሁለት ብር ብቻ በመቀነስ በውድ እየቸበቸቡ ሲከብሩ አያለሁ፡፡ የሚገርመው የአንድ ብር ቅናሽም ተስፋ የሆነችበት ይህ ምስኪን ሕዝብ ከነሱ ለመግዛት ቀኑን ሙሉ በቀበሌዎችና በሸማቾች ደጃፍ ተሰልፎ ይውላል፡፡ በነፍስም በሥጋም የሞተው የሟቹ የለገሰ ዜናዊ የሞተ መንግሥት ለምን በህዝቤ እንደሚጫወት አይገባኝም፡፡ ለምንስ የህዝቤን ሰዓት ያቃጥላል@ ይኸ እኮ ነው ወገኖቼ የዛሬ ሸማቾች፣ ቀበሌ፣ሊግ ትዝ ሲሉኝ በቶሎ የሚያናድደኝ፡፡

ጥቁር አንበሳን ሆስፒታል በስተቀኝ እያየሁ ቁልቁል ስወርድ በስደተኞችና ዜግነት ጉዳይ መሥሪያ ቤት (ኢሚግሬሽን) ለመስተናገድ የሚተራመስ ሕዝብ ታየኝ፡፡ አቤት ብዛቱ! የሰማይ ኮከብ፣ የባህር አሸዋ ወይስ ምን@ ይኸ ሁሉ ሰው ነው@ ውጭ ለመሄድ የተሰለፈ ሰው! ‰ረረ በዚህ ከቀጠለ ወደፊት ወያኔ የሚገዛው ሕዝብ እንዳያጣ ያሰጋዋል-ሰው ሁሉ ሄዶ ያልቅበታላ!

ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ 21 ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያ በጎሣ ትሸንሸን በሚለው ከሰሜናዊው አባቴ ከኢሳያስ አፈወርቂ በቀሰምኩት አስተሳሰቤ ለምን ከክርስቶስ አሳንሳችሁ ታዩኛላችሁ በማለት ሲሰድበን፣ሲያዋርደንና ሲገድለን የኖረው የወያኔ አምበል ፈርኦን ለገሰ ዜናዊ በመሞቱ የተደናበሩት የሱ ደቀ-መዛሙርት ዛሬ በአደባባይ በሬዲዮና በቴሌቪዥን አንደሚነግሩን በአንድ ግለሰብ ብቻ ሲነዱ የባጁ፣ የኖሩ፣ ያረጁ የአንድ አውራጃ (የአድዋ) ሰፋ እናርግላቸው ካልንም የ3 አውራጃዎች (አሽአ-አክሱም፣ሽሬ፣ አድዋ) ዘመናዊ ነገሥታት የሥልጣኑን ቁልፍ ጨብጠው በፈጠሩት ውጥንቅጥ ኢህአዲግ የሚባለው ጭራቅ ድርጅት አባል የሆኑ ሰዎች በየቀበሌው ተደራጅተው፣ በተለያዩ የመንግሥትና የግል መሥሪያ ቤቶች ተቀጥረው እየጨፈሩ፣ እየሰከሩ አንዳንድ ጊዜም አንዳንዶቹ ምስኪኑን እያሰሩ ሲኖሩ፤ እየተራቡ የበይ ተመልካች የሆኑትና አገሬ ላይ በራብ ከምሞት፣ ቤተሰቦቼና ዘመዶቼ በራብ ሲሞቱ ከማይ፤ አረብ አገር ሄጄ ከፎቅ ተወርውሬ፣ በፖሊስ ተደብድቤ ወይም ትንሽ ካየሁትና ለውጥ ከሌለ ታንቄ ልሙት፤ ፈጣሪ ብሎልኝ ካልሞትኩም ለራሴና ለቤተሰቤ ትንሽ ገንዘብ አገኛለሁ በሚል በሕይወታቸው ፈርደው ወደውጭ ለመሄድ ሰልፍ የያዙትን ምስኪንና ቆነጃጅት ያገሬ ልጆች ከብዛታቸው የተነሳ ማየትና መቁጠር አቅቶኝ እግዚኢ-አቤት የፈጣሪ ያለህ፣ የመንግሥት ያለህ፣ ያገር ያለህ፣ የሕዝብ ያለህ እያልኩ ከግፊያው በመከራ ወጥቼ ቸርችል ጎዳና ገባሁ፡፡ በዐይኔ ይኸን እያየሁ አሁን ይህን ጊዜ የወያኔ ሬዲዮዎች (ቱልቱላው ፋና 98.1፣ የቀንደኛዋ ካድሬ ንፋው ዛሚ 90.ምናምን፣ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1) ስለ መለስ ተዐምራትና ገድል ያወሩ ይሆናል፡፡ ምን ዐይነት ዓለም! ይህን ጊዜ እኮ በጥበብ፣ በዕውቀት፣ በሥልጣኔ የተራቀቁት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲየን ቁንጮ ላይ ዶላር ጎዝጉዘው የሚደንሱት የአሽአ (አክሱም-ሽሬ-አድዋ) ቀሳውስት፣ ሊቃውንት፣ኤጲስ ቆጶሳት፣ ጳጳሳት – - በአስደናቂ ራዕይ እየተመሩ፣ ክንፎቻቸው እያበሩ ስለ ቅዱስ፣ ሰማዕት- በስመ ድንጋጤ ወአንቅጥቅጤ፣ ልክፍተ ቡዳ በአበበ ገላው ዘጎጃም ወጎንደር ዘነገደ ይሁዳ – ለገስ መለስ – ገድል በወርቅ ብዕር እየፃፉ ይሆናል፡፡ አዎ፣ ይሁን ያርገው ይገባል፡፡ የቅዱስ ለገስ አባ መለስ ገድል ተፅፎ በስማቸው ለሚቀረፀው ታቦት ማደሪያ- ማህደር በሚሆነው ደጀ-ሰላም ውስጥ ቅዳሴ ይቀደስበታል፡፡ ውዳሴ ይወደስበታል፡፡ ልጋሴ ይለገስበታል፡፡ ህዳሴ ይኸደስበታል፣ ይታደስበታል፡፡ አሃሃሃሀ—እውነቱን ለመናገር ርካሴ፣ ርኩሰት ይረከስበታል፡፡

እየተጓዝኩ ነው፡፡ በቸርችል ጎዳና ትንሽ ከወረድኩ በኋላ ዋናው ፖስታ ቤት አካባቢ ስደርስ ወደ ግራ በመታጠፍ ወደ አምባሳደር ሲኒማ ቤት ወረድኩ፡፡ በስተቀኝ የመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መሥሪያ ቤት አላሳልፈኝ አለ፡፡ በሕንፃው ላይ የተለጠፉትን የመለስ ፎቶዎችና አብረው የተፃፉትን ተዐምራት እንደምንም ተቋቁሜ ቀጠልኩ፡፡መስቀል አደባባይማ የኢትዮጵያውያን አደባባይ መሆኑ ቀርቶ የመለስ ዜናዊ አደባባይ ሆኗል፡፡ ወይ የባንዳ ዘመን! ጸረ-ኢትዮጵያ የሆነን ሰው ፎቶ በአደባባይ በመስቀል ኢትዮጵያዊያንን አንገት ማስደፋት ምን የሚሉት ኢትዮጵያዊነት ነው@ እህህህ!! ቀንደኛ የኢትዮጵያ ጠላት የሆነን ሰው ፎቶውን በመስቀል ከሞተ በኋላ ኢትዮጵያዊ ማድረግ የሚቻል መስሏቸው ይሆን@ ምስኪን አጎብዳጆች!

ከጥቁር አንበሳ እስከ ኦሎምፒያ ድረስ ያየሁትን ነገር ሳሰላስል አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሳይሆን የመለስ ቤተሰቦች ለሟቹ መታሰቢያ ባሰሩት ትልቅ መቃብር ቤት ውስጥ ያለሁ መስሎኝ ደገነጥኩ፡፡ መቃብር ቦታ ሰይጣን አይጠፋም፣ መቃብር ቦታ ይከብዳል እየተባልኩ ያሳለፍኩት አስተዳደጌ ትዝ ብሎኝ በድንጋጤ ላማትብ ስል አበሩስ ሕንፃ 1ኛ ፎቅ ወዳለው ጉዳዬ ለመውጣት የደረጃውን የመጀመሪያ መካን መርገጥ እንደጀመርኩ ተገነዘብኩ፡፡

በደርግ መንግሥት የመጨረሻ ዘመን አካባቢ የሚዘወተረው ወቅታዊ ዜና የሚከተለውን መልዕክት የያዘ ነበር- ‹‹ ገንጣዩ ሻዕብያ እና በአምሳሉ የፈጠረው ውላጁ ወያኔ በሀገራችን ታሪካዊ ጠላቶች መሣሪያና ገንዘብ ሰክረው፤ ኤርትራን ከእናት አገሯ ኢትዮጵያ ለመገንጠል፣ የሃገራችንን ታሪክና ቅርስ ለማጥፋት፣ የባህር በራችንን ለመዝጋት፣ ዳር ድንበራችንን ለመቆራረስና ባጠቃላይ አንድነታችንን ለመናድ እንዲሁም ሕዝቡን በጎሣና በዘር ከፋፍለው ርስበርስ እያናቆሩ አዳክመው ለመግዛት የከፈቱብንን ጦርነት ሕዝቡ በቆራጥነት እየመከተ ይገኛል›› ዛሬ ዘይት ከከተማ ሲጠፋ በቴሌቪዥን ጀሪካን ይዘው ‹‹ዘይት ሞልቷል››፣ ሕዝቡ ትራንስፖርት አጥቶ ሲሰቃይ ‹‹የትራንስፖርት ችግር የለም›› እያሉ የወያኔን የፈጠራ ወሬ በማስተጋባት የውሸት ምስክርነት የሚሰጡ ግፈኛ ፍርፋሪ ለቃሚ ካድሬዎች የሚያቃጥሉኝን ያህል በደርግ ዘመን ከያንዳንዱ ዜና ጋር የምንትሴ አስተዳደር ክልል የኢሰፓ ዋና ፀሐፊ፣ ምንትሴ እያሉ በሃገሪቱ ያለ ኢሰፓ አባል ሰው የሌለ ሲያስመስሉ ያተክኑኝ ነበር፡፡

ይሁንና ያኔ በደርግ ጊዜ ለመገንጠልና ለማስገንጠል፣ ዳርድንበር ለመቆራረስ፣ እንዲሁም የባህር በራችንን ለመዝጋት ይታገሉ ስለነበሩት ጎጠኛ ቡድኖች ይባል የነበረውን ዛሬም ስመዝነው ውሸት ላገኝበት አለመቻሌ ይገርመኛል፡፡ ርግጥ አልፎ አልፎ ጊዜ በራሱ የሚፈጥረው ተዐምር መኖሩ አይቀሬ በመሆኑ አስገንጣዩ ቡድን (ወያኔ) ፈጣሪውና አለቃው የነበረውን ቡድን (ሻዕብያን) ካጣ በኋላ ከሻዕብያ ሌላ በምድር በሰማይ ጠላት የለኝም በማለት አገር ይያዝልኝ ሲልና ተስፋ በማጣት ከመሸ በኋላ ኢትዮጵያዊ ለመምሰል በተወነው የ10 ዓመታት አድካሚ ትያትር ሲወድቅ፣ ሲነሳ፣ ሲንፈራገጥ ጀርባው ሲገጣጠብ ለማየት በመብቃታችን ወይ ዕድሜ ደጉ ብለናል፡፡ የትያትሩ ደራሲ ራዕይ ይቅርና አቋም የሚባል ነገር ያልተፈጠረበት ለፖለቲካ ጥቅምና ለሥልጣን ሲል ዛሬ በግራ ነገ በቀኝ መሰለፍ የማያሳፍረው መለስ ዜናዊ እንደነበር ‹‹ገድለ-መለስ ወለገስ የህዳሴው መሀንዲስ›› በሚለው መጽሐፍ መለሲዝም የሚለው እምነት ተከታዮች በሆኑት አብዮታዊ ካድሬዎች ተተርኮለታል፡፡ እባካችሁ ለጊዜው መሳቅ ክልክል ነው፤ እሺ@ ከሞተ ገና ዓመቱ እኮ ነው-አይሳቅም፡፡

የሆነ ሆነና በ2004 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ የሞተው መለስ ዜናዊ በርግጥ ኢትዮጵያን ሊወክል የሚችልና ለኢትዮጵያዊያን የመጣ ሰው ነበርን@@@   ይህ ጥያቄ እንቅልፍ ባይነሳኝ ኖሮ ይህን ፅሑፍ መጻፌን ትቼ አርፌ በተኛሁ ነበር፡፡

(ክፍል አንድ በሚቀጥለው ይቀርባል)


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>