(ዘ-ሐበሻ) የእለተ አርብ ጸሎት ለማድረስ አንዋር መስጊድ የከተመው ሕዝበ ሙስሊም እና የፌድራል ፖሊስ ግጭት መፍጠራቸው ተሰማ። ፖሊስ ትንኮሳ በመፍጠር በተለይ በኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት አካባቢ ሰላማዊውን ሕዝብ መደብደብና በፖሊስ መኪና መጫን ሲጀምር ሕዝቡ ቁጣውን በመግለጽ በፖሊስ ላይ ድንጋይ መወርወሩን ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ አመልክቷል።
የፌደራል ፖሊስ ለአርብ ጸሎት በመስጊድ የተገኘው ሕዝን በመክበብ ከመስጊድ እንዳይወጣ ለማገድ ሙከራ ሲያደርግ ነበር ያሉት የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች በራሱ የመንግስት ካድሬዎች አማካኝነት ብጥብጥ በማስነሳት ጉዳዩን ከሙስሊሞቹ ጋር ለማያያዝ ሙከራ ማድረጉን ጠቅሰዋል። በፖሊስ ላይ ድንጋይ መወረወር የጀመሩት መንግስት ያዘጋጃቸው ካድሬዎች ናቸው የሚሉት ዘጋቢዎቻችን ፖሊስ ይህን ተከትሎ በርካታ ሙስሊሞችን ማሰሩን እና አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙን ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
ፖሊስ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ድብደባ እየፈጸመ እንደሚገኝ የሚገልጹት የዘ-ሐበሻ ዘጋቢዎች አካባቢው በጥይት እሩምታ እየታመሰ እንደሚገኝና ውጥረቱም እንዳየለ አስታውቀዋል።