Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የፖለቲከኞቹ እስር እና ያስከተለው ሕገመንግሥታዊ ጥያቄ

$
0
0

በመልካሙ አበበ

ሰንደቅ

Wektawi62ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ሰሞኑን ባደረጉት ቃለምልልስ የግንቦት 7 ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ከየመን ወደኢትዮጵያ ተላልፈው የመሰጠታቸው ጉዳይ በማንሳት “የኢትዮጵያ መንግስት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሽፋንአድርጎ የሚመጣአሸባሪነትንአይታገስም”ማለታቸውን ዘግቧል።

     የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን መያዝ ተከትሎ በሀገር ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ከሆኑት መካከል አቶ ሐብታሙ አያሌው እና አቶ ዳንኤል ሺበሺ ከአንድነት፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ ከሰማያዊ ፓርቲ፣ አቶ አብርሃ ደስታ ከአረና ትግራይ (ዘግይቶም ቢሆን ፍ/ቤት ቀርቧል)፣ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል። የጸረ ሽብር ግብረሃይል የግንቦት 7 ልሳን ከሆነው ኢሳት ቴሌቪዥን ጋር ግንኙነት ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በቁጥጥር ስር ማድረጉን በደፈናው በዕለቱ የገለጸ ሲሆን የተያዙት የአንድነት፣ የሰማያዊና የአረና አመራሮች መሆናቸው ሲታይ መግለጫው እነሱን በቀጥታ የሚመለከት ስለመሆኑ የብዙዎች ግምት ሆኗል።

እስሩ እና የፓርቲዎች ምላሽ

     አንድነትና ሰማያዊ ፓርቲዎች በተናጠል ሰሞኑን ባወጡት መግለጫ እስሩን ከመጪው ዓመት ምርጫ ጋር በቀጥታ አስተሳስረውታል። አንድነት በመግለጫው ኢህአዴግ የአንድነትን ከፍተኛ አመራሮች በማሰር የምርጫ ዘመቻውን ይፋ አድርጓል ብሏል። ሰማያዊ ፓርቲም በበኩሉ እስሩ ኢህአዴግ ቀጣዩን ምርጫ ያለተቀናቃኝ ለማለፍ የሚያደርገው ሕገወጥ እንቅስቃሴ አካል ነው ሲል ነቀፌታውን ሰንዝሯል።

   ጠ/ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ ላይ በሕጋዊ መንገድ በፖለቲካ ፓርቲ በመደራጀት እናሽፋን በማድረግህገወጥ እንቅስቃሴን በማካሄድ መንግስትን በኃይል ለመለወጥ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ግለሰቦች አሁንም ከተጠያቂነት አያመልጡም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሕግ አስከባሪው፤ ሕግ ያለማክበር ጥያቄ ሲነሳበት፣

     የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ የሆነው ኢትዮጵያ ህገመንግስት አንድ ሰው በሕግ ጥላ ስር ከዋለ በኋላ ቢበዛ በ48 ሰዓታት ፍርድቤት መቅረብ እንዳለበት ይደነግጋል። በተለይ የአንድነት እና የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ማክሰኞ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ፍ/ቤት ሳይቀርቡ ሰባት ቀናት ተቆጥረዋል። ይህም ብቻ አይደለም፤ በመረጡት ጠበቃ የመወከል መብታቸውንም ተጠቅመው ከጠበቆቻቸው ጋር የመገናኘት ዕድል መነፈጋቸውን ከፓርቲዎቹ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። አንድነት ይህን ድርጊት ሕገወጥ በማለት አካልን ነጻ የማውጣት ክስ በፍርድ ቤት መመስረቱን አስታውቋል። ይህም ሆኖ እስከትላንት(ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2006) ማምሻውን ድረስ ተጠርጣሪዎቹ ፍ/ቤት ስለመቅረባቸው የታወቀ ነገር የለም።

አንድ የህግ ባለሙያ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት አስተያየት “የሕግ የበላይነት በሚከበርበት ሀገር መንግሥት መረጃ አለኝ እስካለ ድረስ በሽብር ተግባር የተጠረጠሩ ሰዎችን ይዞ ማሰሩ አዲስ ነገር አይደለም። ነገር ግን ህግና ስርዓት እንዲከበር እተጋለሁ የሚል መንግሥት ራሱ ያወጣውን ሕገመንግስትን ጥሶ ያሰራቸውን ተጠርጣሪዎች በወቅቱ ወደፍርድ ቤት ማቅረብ ሳይችል ሲቀር የሕግ በላይነት የሚባለው ጉዳይ ያበቃለታል። በዚህ ምክንያት ዜጎች በመንግሥትና በሕግ ላይ ያላቸው አመኔታ የሚያጡ ሲሆን በቀጣይ ሕግና ስርዓትን አስከብራለሁ ብሎ የሚሞክራቸው ወይንም የሚናገራቸው ነገሮች ሁሉ በሕዝብ ዘንድ ተአማኒነትን ስለማይኖራቸው ትልቅ ችግር ይገጥመዋል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

በሰሞኑ ክስተት፤ የኢዴፓ አቋም

የኢትዮጽያዊያን ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) “በሽብርተኛነት ስም የሚወሰደው እርምጃ ግልጽነት ይኑረው” በሚል ርዕስ ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ የመንግሥት እርምጃ እንዳሳሰበው ጠቁሟል። መግለጫው እንዲህ እያለ ይቀጥላል «በሀገር ውስጥ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም መንግሥት በሽብር ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ማዋሉ በሚዲዎች ተገልጿል። እነዚህ አመራሮች ከ48 ሰዓታት በላይ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ አለማቅረባቸው አመራሮቹ የታሰሩት በሚያራምዱት የፖለቲካ አቋም እንዳይሆን ፓርቲያችን ሥጋት አድሮበታል።

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮምቴ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተለውን አቋም ወስዷል።

  1. 1. መንግሥት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የተያዙበትን ምክንያት ለህብረተሰቡ በዝርዝር እና ግልጽ መረጃ እንዲሰጥ፣
  2. 2. የታሰሩት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በሕገመንግስቱ አንቀጽ 21 መሠረት ለዜጎች የተሰጠው መብት እንዲከበርላቸው፣
  3. 3. በአስቸኳይ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ፣ የፍርድ ሒደታቸውም ተአማኒ፣ ግልጽ እና ፈጣን በሆነ መንገድ እንዲታይ እያሳሰብን ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን አገሪቱ ሕግ አክብረን በሰላማዊ ትግል ከምንቀሳቀስ ፓርቲዎች ይልቅ በተቃራኒ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች የሚያጠናክር፣ ክርክራቸውንም ምክንያታዊ የሚያደርግ እና የዴሞክራሲ ግንባታውን ወደኋላ የሚመልስ በመሆኑ ጉዳዩ በእጅጉ እንደሚያሳስበን እንገልጻለን። ስለዚህም መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ ኢዴፓ ያሳስባል።”

የፍረጃ ፖለቲካ

    የደርግ መንግሥትን በኃይል ለመጣል በተደረገው የትጥቅ ትግል ወቅት ደርግ ታጋዮችን “ገንጣይ፣ አስገንጣይ፣ የእናት ጡት ነካሽ ወንበዴ….” እያለ የህዝብ ድጋፍ እንዳያገኙ ሌተቀን የመንግስት መገናኛ ብዙሃንን መሣሪያ በማድረግ ያወግዝ እንደነበረው ሁሉ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ ኢህአዴግ ተቀናቃኞቹን በተደጋጋሚ በጠላትነት ሲፈርጅ፣ ሲያጥላላ ይታያል። በተቃዋሚ ፓርቲዎችም በኩል ተመሳሳይ ዝንባሌዎች የሚታዩ መሆኑ መቻቻልና በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንኳን አብሮ የመሥራት ባህል እንዳያድግ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።

    በዚህ ምክንያት ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ እና ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግንኙነታቸው በጠላትነት መንፈስ ላይ የተመሰረተና መተማመን የሌለበት፣ ጥላቻ የነገሰበት ሆኖ እስከአሁን ዘልቋል። ኢህአዴግ በ2002 ምርጫ ከ99 በመቶ በላይ ወንበሮችን ካሸነፈ በኋላ ለንባብ የበቃው “አዲስ ራዕይ” መጽሔት በሐምሌ-ነሐሴ ወር 2002 ዓ.ም ዕትሙ ስለተቃዋሚዎች እንዲህ ይላል። “…አንዳንዶቹ ተቃዋሚዎች የተለመደውን የቀለም አብዮተኞች ስልት በመጠቀም የምርጫ ሕጎችን ሆን ብለው በመጣስ በሕጉ መሰረት እርምጃ ሲወሰድባቸው በነጻ መወዳደር አልቻልንም ብለው ኡኡ እንደሚሉ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነበር። እናም ስትራቴጂያችን እንደነዚህ ዓይነት ድርጊት ሲፈጸም መዋቅራችን የተሟላ መረጃ በቪዲዮ ጭምር እንዲይዝ፣ ይህንኑ መሠረት አድርጎ ድርጊቱን በሕዝብ ፊት እንዲያጋልጥና ሆን ተብሎ ምርጫውን ለማበላሸትና ብጥብጥ ለመፍጠር የተደረገ ተግባር መሆኑን እንዲያስረዳ፣ ሕጉ የተፈቀደለትን እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቦ ነገሩን ለበላይ አካል ሪፖርት እንዲያደርግ ነበር የሚያስቀምጠው። በዚሁ መሠረት የተቃዋሚዎች ሕገወጥ ድርጊት በየአካባቢው እንደነገሩ ሁኔታ በአገር አቀፍ ደረጃ በሰፊው የሚጋለጥበት ሁኔታ ተፈጠረ” ሲል የመተጋገሉን ደረጃ ያሳያል።

    እንዲህ ዓይነት አንዱ አጋላጭ ሌላው ተጋላጭ፣ አንዱ ሕግና ስርዓትን አክባሪ፣ ሌላው ጸረ ሕገመንግሥት፣ አንዱ ሽብርተኛ ሌላው የሠላም አቀንቃኝ አድርጎ የመሳሉ ጉዳይ ሞቅ በረድ እያለ አሁን ድረስ መቀጠሉ በሁለቱ ኃይሎች መካከል ያለው የፖለቲካ ልዩነት ወደአላስፈላጊ ጠርዝ የሚገፋ ሆኖ ይታያል።

    ከምንም በላይ ደግሞ መንግሥት በወንጀል ጠርጥሮ የያዛቸውን ሰዎች በወቅቱ ፍርድ ቤት ከማቅረብ መቆጠቡ ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን አክብሮ የማስከበር ኃላፊነቱን አለመወጣቱን ያሳያል። ሕግና ሥርዓትን የማክበር ጉዳይ ደግሞ በምንም ዓይነት ምክንያት ሊስተባበል የማይችል መሆኑንም መንግሥት ይስተዋል ተብሎ ስለማይገመት ስህተቱን በፍጥነት ሊያርም ይገባል።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles