የፊታችን ጁሙዓ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከባድ ተቃውሞ ይደረጋል፡፡ ይህ ደግሞ ተምሳሌታዊ አብሮነታችንን በሃገራችን በሁሉም አቅጣጫ ከወትሮው በተለየ መልኩ የምናሳይበት ወሳኝ አጋጣሚ ነው፡፡ የፊታችን ጁሙዓ ህዝባዊነታችን ጎልቶ የሚታይበት፣ ለፍትህ፣ ለሰላም እና ለእምነት ነፃነታችን መከበር ያለንን ቁርጠኝነት እና ፅናት ደግመን ደጋግመን ለዓለም የምናሳይበት ታላቅ ተቃውሞ ነው፡፡ ተምሳሌታዊ አብሮነታችን በአገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም የሚገለጽ ነው፡፡ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንም ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ ሲሆን በሳምንቱ ውስጥም የሚፈጸሙ እንቅስቃሴዎችን አዘጋጅተዋል፡፡
በሃገር ቤት የሚኖረን በሰላማዊ ትግላችን ውስጥ ዋና የሚባሉ አጀንዳዎቻችንን በሙሉ ያካተተ ብርቱና የተቀናጀ ሃገር አቀፍ ተቃውሞ ነው፡፡ ከሃገር ውጭ ደግሞ ጁሙዓን ጨምሮ በቀሪዎቹ ቀናት የተለያዩ መርሃ ግብሮች ለማካሄድ ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆነ መረጃዎች ደርሰውናል፡፡
ይህ አገር አቀፍ ተቃውሞ በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጂድ ይካሄዳል፡፡ (የሚከተለው መርሃ ግብር የአዲስ አበባ ሲሆን ክልሎችም ካሉበት ሁኔታ ጋር አዛምደው ከወትሮው የተለየ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ነው፡፡)
በነገው ጁመዓ ከሚከተሉት 5 መፈክሮች መካከል የገራልንን መፈክር በወረቀት ላይ አስፍረን ይዘን በመምጣት በተቃውሞው ላይ ከፍ አድርገን እናሳያለን፡-
‹‹የአገር መሰረት የሆነውን ህዝብ መናቅ ይቁም!!››
‹‹የህዝብ ድምፅ ይደመጥ!!››
‹‹የሙስሊም ተማሪዎች በነፃነት የመማር መብት ይከበር!!››
‹‹ከትምህርታችን ወይ ከሃይማኖታችን አታስመርጡን!!››
‹‹የሃይማኖት ነፃነትን ማክበር ግዴታ እንጂ ምርጫ አይደለም!!››
> የጁሙዓ ሰላት እንደተጠናቀቀ እጅ ለእጅ ተያይዘን ባለንበት ቦታ በመቆምና በፅሁፍ ይዘን የምንመጣቸውን መፈክሮች ከፍ አድርገን በማሳየት የሚከተሉትን መፈክሮች በድምጽ እናሰማለን፡፡
1. ‹‹አላሁ አክበር!›› ለ 2 ደቂቃ
2. ‹‹ድምፃችን ይሰማ!›› ለ 2 ደቂቃ
3. ‹‹ሕገ መንግስቱ ይከበር!›› ለ 2 ደቂቃ
4. ‹‹ኮሚቴው ይፈታ!›› ለ 2 ደቂቃ
5. ‹‹የታሰሩት ይፈቱ!›› ለ 2 ደቂቃ፤ በየክልልሉና በየማረሚያ ቤቱ ታጉረው የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ፍትህ ብትረሳቸውም ህዝበ ሙስሊሙ እንዳልረሳቸው ለማሳየት፡፡
6. ‹‹ጣልቃ ገብነት ይቁም!›› ለ 2 ደቂቃ
7. ‹‹ኢማሞቻችን ይመለሱ!›› ለ 2 ደቂቃ
8. ‹‹የመንግስት ገዳዮች ለፍርድ ይቅረቡ!›› ለ 2 ደቂቃ
9. ‹‹መማር መብታችን ነው!›› ለ 2 ደቂቃ፤ ህዝበ ሙስሊሙ የመማር መብቱ ህገ መንግስታዊ እና ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ያፀደቁት ሰብዓዊ መብታችን መሆኑን ለማሳየት፡፡
በመጨረሻም ካለንበት ቦታ ሳንንቀሳቀስ እጆቻችንን ወደ አላህ በመዘርጋት ዱዓ በማድረግ ወደየመጣንበት እንመለሳለን – ኢንሻ አላህ!
ትግላችን እስከ ድል ደጃፎች ድረስ ይቀጥላል!
ድምፃችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!
የ‹‹ተምሳሌታዊ አብሮነት›› ሳምንትን ስኬታማ ለማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ዝግጅቶች ተሟሙቀው ቀጥለዋል፡፡ በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነው ከስራ እና ከሰዓት እጥረት ጋር እየታገሉ በአገር ቤት ወንድሞቻቸውን ለማገዝ ሰንፈው የማያውቁት የዳያስፖራው ማህበረሰብ እህትና ወንድሞቻችን ዛሬም እንደተለመደው ከፍተኛ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ በዋሽንግተን ዲሲ፣ በዳላስ፣ በሲያትልና በቺካጎ ለፊታችን ቅዳሜ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ማወቅ የተቻለ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በሚኖሩባት ሳዑዲ ዓረቢያም እንዳለፉት ሁለት ሳምንታት ሁሉ በሶስተኛው ሳምንትም የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑ ታውቋል፡፡
በሌሎች ሃገራት የሚገኙ የዳያስፖራ ማህበረሰቦችም በቀሪዎቹ ጊዜያት የጁሙዓውን ዓለም አቀፍ መርሃ ግብር እና ካሉበት ሁኔታ ጋር የሚጣጣሙ ሌሎች ፕሮግራሞችን ለመተግበር አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳገባደዱ ተስፋ እያደረግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ድምጻችን ጎልቶ እንዲሰማ ለማድረግ ሲያደርጉት የቆዩትን፣ አሁንም እያደረጉ ያሉትን ጥረት አላህ ይቀበላቸው ዘንድ ምኞታችን ነው! እኒህን መሰል ዓለም አቀፍ መርሃ ግብሮችና ዝግጅቶች ሰላማዊ ትግላችንን የበለጠ ዓለምአቀፋዊነት በማላበስ ድምጻችን የበለጠ ጎልቶ እንዲሰማ ያደርጋሉ፡፡ ‹‹ተምሳሌታዊ አብሮነት›› ሊገለጽበት የሚችልበት ሌላ የተሻለ መንገድ ከቶስ ይኖር ይሆን?
ጥቆማዎች
በውጭ ለምትኖሩ ሙስሊሞች ተግባራቱን ማዕከላዊ በሆነ መልኩ ማቀድ ካላችሁበት ሁኔታ ጋር ላይዛመድ ስለሚችል ዋና ዋና ዓላማዎችን እና በሃገር ቤት ያለን ሙስሊሞች በይበልጥ እናንተ ብትሳተፉበት ብለን የምንመኛቸውን አንኳር ተግባራትን ለመጠቆም እንሞክር፡-
1. አለምዐቀፍ መርሃ ግብሮች ሰላማዊ ትግላችን አሁንም በጥንካሬ የመቀጠሉና የሁሉም የህብረተሰብ አንገብጋቢ ጉዳይ የመሆኑ ትልቅ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እንቅስቃሴውም የሚፈጥረው ጫና እና የሚያስተላልፈው መልእክት በራሱ በትልቅ ዓላማነት የሚያዝ ነው፡፡ በመሆኑም በሰፊም ሆነ በአነስተኛ መርሃ ግብር በዚህ ሳምንት ቢያንስ አንድ ተግባር አቅዳችሁ ትተገብራላችሁ ብለን እንጠብቃለን፡፡
2. የዲያስፖራው ማህበረሰብ ዋና ትኩረት እንዲሆን የምንሻው የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት የሚስቡ እና የሚዲያ አጀንዳ የሚፈጥሩ ለየት ያሉ ተግባራት ላይ ትኩረት እንድታደርጉ ነው፡፡
3. ባላችሁበት አካባቢ ለሚኖሩ ማህበረሰቦች እና ተቋማት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ የሚደርሱ ኢፍትሃዊ ተግባራትን እንድታጋልጡ እና የተቻለውን ያክል ለማስቆም ጫና የሚያሳድሩ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ከእናንተ በዋናነት ይጠበቃሉ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኡስታዝ በድሩ ሁሴን ከመታሰሩ ጥቂት ደቂቃዎች አስቀድሞ ከቢቢኤን ሬዲዮ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ የዲያስፖራው ማህበረሰብ ዋነኛ ሚና ምን ሊሆን እንደሚገባ የጠቆመውን በማስታወስ የበኩላችሁን እንድትወጡ ይጠበቃል፡፡
4. ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር መልካም ግንኙነት እና በቀጣይ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት የሚያስችሉ ጤናማ ግንኙነቶችን መፍጠር ይጠበቅባችኋል፡፡
በመሆኑም ከላይ የተቀመጡትን አራት ዋና ዋና ከእናንተ የምንጠብቃቸውን ዓላማዎች ታሳቢ በማድረግ በረመዳን ሶስተኛ ሳምንት ውስጥ በንቃት እና በጠንካራ የአጋርነት ወኔ ወደተግባር የሚያስገባ እቅድ እንድታዘጋጁ እና ወደተግባር እድትገቡ እንጠቁማለን፡፡ እንደመነሻ መሆን የሚችሉ ተግባራት እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡-
• ኮንፈረንስ ብታዘጋጁ እና የተለያዩ ተቋማትን፣ በተለይም የሚዲያ ባለሙያዎችን በመጋበዝ ስለትግሉ፣ በይበልጥም ስለቀጣዩ የትግል አቅጣጫ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ብትሰሩ፤
• በመካከላችሁ አንድነትን የሚያጠናክሩ እና ተባብሮ ቁም ነገር ያለው የሚታይ ስራ ለመስራት የሚያስችሉ የአንድነት የኢፍጣር ፕሮግራሞች ብታዘጋጁ፤
• የጎዳና ላይ ሰልፍ (አመቺ ከሆነ) እና ለየት ያሉ በግል እና በቡድን ሊሰሩ የሚችሉ ትኩረት ሳቢ የጎዳና ላይ ትዕይንቶች እና በእናንተ ተጨባጭ አመቺ የሆኑ መርሃ ግብሮችን በመቅረፅ የታሰበው እንዲሳካ ሰፊ ርብርብ እንድታደርጉ እንጠይቃለን፤
ለምታደርጓቸው እቅስቃሴዎች ስኬት በቂ የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙ በልዩ ትኩረት እንድትሰሩ እየጠቆምን ወደእኛ የምትልኳቸውን ዜናዎች በተሻለ መጠን ሽፋን እንዲያገኙ ለማድረግ የምንጥር መሆኑን እንገልጻለን፡፡
በደማቅ ተምሳሌታዊ አብሮነት ድምጻችንን በዓለምአቀፍ ደረጃ ለማጉላት እንረባረብ!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች ድረስ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!