Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ጧፍ! (ሥርጉተ ሥላሴ)

$
0
0

ከሥርጉተ ሥላሴ 17.07.2014 (ሲዊዘርላንድ ዙሪክ)

 

Hailemedhin Abera

ካፒቴን አበራ ኃይለመድህን

በርቶ!
ተብራርቶ
ድርጊት ተሰማርቶ
ጀግና ተለክቶ።
ተፍታቶ
ሩቁን አስልቶ
ዛሬን ቀድሞ አይቶ
ትናንትን አውግቶ
ነገን አስተጋብቶ
ጎልቶ!
 

ዛሬ ካፒቴን አበራ ኃይለመድህን በጀግንነት ዚዊዘርላንድ ጄኔባ ላይ የወያኔን ትዕቢት ደርምሶ የገባበት መንፈቅዓዊ ዓመቱ ነው። 6ወር ተቆጠረ። ጀግና አበራ ሃይለመድህን ፍትህ ባለበት ሀገር ስላለ ከታሠረበ በኋላ በእሱ ዙሪያ የተቀነባበሩ ዜናዎች ሆኑ ዘገባዎች ምስሉንም ድምጹንም ማግኘት አልቻሉም። በወቅቱ እጅግ በጣም ብዙ የዓለም ሚዲያዎች ሳይቀሩ እንደቋመጡ ነበር የቀሩት። የሀገሬው የዜና ማሰራጫም ቢሆን ፌስ ቡክ ላይ የተገኘውን ፎቶ ዓይኑን ከተር አድርጎ ነበር ያቀረበው። በሀገረ – ሲዊዘርላንድ እናት ልጆቿን በጡቶቿ ሥር ድብቅ አድርጋ፣ ሽሽግ አድርጋ፣ ከዓይን እንዳይገቡባት እንደምታሳሳው ዓይነት ትንግርት ነው የተፈጸመው።

የወያኔ ጉርዶች – አሸከሮች ከዚህ በከረሙበትም ወቅት ዓይኑን ማግኘት አልቻሉም። ሲንደፋደፉ ባጅተው ማድጋዋ ተስብሮ ወሃ አልባ እንደምትመለስ የሀገሬ ባለጋሜ  ኩም ብለው አፋቸው ኩበት ቅሞ፣ አመድ መስለው፣ አንደበታቸው እንደ ደረቀ ነበር ዬተመለሱት። በዚህ ዙሪያ የነበረው ጫና፣ የነበረው ጉድ መድህኒዓለም ያውቀዋል። የአሸባሪ ተባባሪ እሰከመባል ያደረስ ሰፊ ዘመቻ ነበር። ነገር ግን ለጀግናዬ ለአበራ ሃይለመድህን ደግሞ የሲዊዝ መንግሥት ጥያቄውን ተቀብሎ ቀጣዩ ሂደት በጽሞና እንድንጠብቅ  አደረገ።

መንፈሳችን ረጋ፤ ሁለመናችን ተሰባሰበ፤ በእሱ ዙሪያ የለፉ – የደከሙ – ቀን ከሌት የባዘኑ ወገኖቹ ሁሉ፤ ከአሜሪካን ሀገር ድረስ መጥተው ጉዳዩን ለመከታተተል የቆረጡት የተከበሩ ዶር. ሼክስፔር ፈይሳን ጨምሮ ትንፋሽ አገኙ። አማላካችን ይመስገን። አሜን! እንዲህ ፍትህ ባለበት ሀገር የፍትህ ጥማትን ማግኘት የሰማይ ተግባር ነው።

ሽፍታው ወያኔ በሚመራው አስተዳደር ግን ያፈነውን አንበሳ የተከበሩ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ምስል በአያችሁት ሁኔታ በሸፍጥ ተቀባብቶ አቀረበ። ከዛ በኋላ የተፈጸመው ድርጊት ደግሞ ከአራዊት የሚጠበቀውን ማናቸውንም የጭካኔ አሰቃቂ እርምጃ በመውሰድ የበቀል የደም ጽዋውን ወያኔ ይጎነጫል።

አዎን! የነፃነት ትግሉን፤ የመንፈስ ልጆቹን፤ የአርበኝነት መንፈስ ገድለው ተስፋ ቆራጭነት አዝማች እንዲሆን ታስቦ በደመነ ነፍስ ተተልሞ የቀርበ ነበር ያ ቅጥ አንባሩ የጠፋው የቪዲዮ ቅንብር። ይህ ዓለም ዓቀፍ ወንጀል ነው። ከአፋናቸው – ከውንብድነታቸው - ከበረት ገልባጭነታቸው የዬመኑ የውንብድና ተግባር በላይ ሰሞናዊው ዓለም ጉድ ሊለው የሚገባ የሚዲያ ህግጋትን፣ የእሥረኛ መብትን ሁሉ በማናለብኝነት የዳጣ ገመናው ነው የወያኔ የአደባባይ ሲሳይ ያደረገው። በዚህ ዙሪያ ዓለም ዐቀፉ የሰብዕዊ መብት አስከባሪ ነኝ የሚለው ድርጅት ሆነ ሚዲያዎች ሁሉ ይህን የሰማይ ስጦታ የሆነውን የሰው ልጆችን መብት የረገጠ ገመና እንዴት ሊያዩት እንደሚችሉ አላውቅም። አቅሙ ያላችሁ ተግታችሁ ብትሠሩበት በዚህ ብቻ እራሱን የሚያዞረው መዘዝ ወያኔ ሊመጣበት ይችላል።

እኛ በርትተን ከሰራን ይህ አረም መጥፊያውን ጉድጓድ እራሱ እዬቆፈረ መሆኑን የሚያውጅ ስለሆነ የሂደቱን ጠረኑ ማድመጥ ያስፈልግ ይመስለኛል። ወያኔ ከሰው ውጪ የተፈጠረ እንሰሳ ስለመሆኑ የተገነዘበው ወጣት አበራ ሀይለመድህን ከሀገርም ሲዊዝን መርጠ። ጥቃቱን በጀግንነት አዋራረደ። ለአረሙ ወያኔ የሚፈልገውን ኮሶ አስጎነጨ። ወጣቱ ዬወያኔን ህግ ጣሽነት፤ ጠንቅቆ ምርምሮ የደረሰበት በመሆኑ የዝምታ የበቃኝ ሰላማዊ እርምጃው ፍትህን እንደሚያገኝ አስቀድሞ ተልሞ ነው ነበር የተነሳው።

ዴሞክራሲ በሰፈነበት ሐገር የማይፈጸሙ ህግጋት አይረቁም። አይጸድቁም። አስፈጻሚ አካላቱም ዕውቅና ያለው ተግባር አላቸው። ክንውንና ሚዛን የሚለካከቡት። የቢሮ መኖርም ትርጉም ጠገብ በመሆኑ የተረታው እንኳን የፍርድ ሂደቱን ውሳኔ በጸጋ ደስ ብሎት ይቀባላል። እንዲያውም የተፈረደበት ሰው ውሳኔውን ልክ እንደ ቤተሰቡ አቅርቦና አስጠግቶ ተግባራዊ ለማድረግ ይማስናል። ቅጣቱንም በፍሰኃ ያስተናግዳል። ይቅርታም በመጸጸት ይጠይቃል። የፍትህ አካላቱም ቢያንስ ለህሊናቸውን ለሙያቸው ሥነ ምግባር በመገዛታቸው፤ በመታዘዛቸው ማሃያቸውን ሲጠቀሙበት አይጎርብጣቸውም። ይስማማቸዋል።

በወያኔ ሰፈር ደግሞ የተገለበጠ ውርዴ ነው። እኛም እንዳሻው የምንታረድ፤ እንዳሻው የምንዘለዘለ፤ እንዳሻው የሚከትፈን እርዶች ሆንለታል። የደለብን ሰንጋዎች። ያልገባን ሚስጥር ይህ ነው። ሀገራችን የሚመራት የሚያስተዳድራት ናዚ ስለመሆኑ ፈጽሞ ጭራሽኑ አልገባንም። አልተረዳንም። አጋጣሚና ሁኔታ ካገኜ ለማንምና ለምንም የማይራራ ህጻነትትን ሳይቀር የሚያርድ ጭራቅ መሆኑን አሁንም አልተገለጠልንም። ሆድ አደሩም ሆነ ቀለብ የሚሰፈርለት እሳቱ እስኪደርሰው ድረስ ሽፋን በመስጠት ይቀልዳል። ጥግና ከላላ ሆኖም አብሮ ይዳክራል። በበቀል በጨቀዬ ሥራዓት አብሮ ያረገርጋል። ቀኑ ሲደርስ ግን እዬነጠለ ይለቅመዋል። ጅብ ዘመድ የለውም። ሆዱ ነው ዘመዱ። በቀሉ ነው እስትነፋሱ።

እውነትን መድፈር የተሳነው ደመነፍሱ የወያኔ አስተዳደር አሁንም በፍትህ ፈላጊያት ላይ የአራዊት ዘመቻውን ተያይዞታል።

ከአንድነት ፓርቲ በተረኝነት እኔ በግሌ እጠብቃቸው የነበሩት ሁለቱ  አቶ ሃብታሙ አያሌውና አቶ ዳንኤልን ሺበሺን ከሰማያዊ ፓርቲ የሺዋስ አሰፋ እንዲሁም ያ የአጭር ግልጽና ጭብጥ አዘል መረጃ ዘጋቢ፤ ንቁው መምህርና ጋዜጠኛ አብርሃም ደስታ ከመቀሌም ባለተራ ሆነዋል። ያው የጭካኔ ቤተ ሙከራነታቸው በተለመደው ሁኔታ ሥጋቸው እዬተቦጨቀ ደም ያዘንባል። ይህ ሥር የሰደደ የፋሽስት የቋሳ ሥርዓት እስካልተወገደ ድረስ አፋናው ይቀጥላል።

ተሰደን እንኳን ሰላም ነሳን፤ ተሰደን እንኳን መቀመጫ ነሳን። ተሰደን እንኳን እረፍት ነሳን። በስደት ሀገር ለመንቀሳቀስ እንኳን ማዕቀብ ተጣለ። ይህ እንግዲህ እኛ የፈቀድንለት አስመችተን የምናሽሞነሙነው ውርዴታችን ነው።

ፍቅር የነጠፈበት ሽፍታ ካፒቴን አበራን አግኝቶ ቢሆን ምን ሊያደርግ ይችል እንደ ነበረ እሰቡት። አስሉት። ስጋው በቁሙ ይቀቀል ነበር። መንፈሱ በኤሌትሪክ ይደነዝዝ ነበር። አካሉ በእሳት ይቃጠል ነበር። አውሮፕላኑን ጣሊያን አሳርፎ ስለምን ሌላ ስደት አልጠዬቀም? የሚሉት ግብዝ ሆድ አደሮች – ተለጣፊ መዥገሮች ጥበቃ አልባ እንዲህ ካንፕ ውስጥ እያለ በጋንግስተር ተጠልፎ አሳሩን ሲይ አብረው ለመደለቅ አስበው ነበር። ግን ወንድና አንበሳነት – ጀግንነትና አድዋ ውል ተዋውለው በድል ላይ ሰላምን አገኙ። አሁንም እንደ ተከደነ ነው። ዘው ተብሎ የሚዛቅ ምንም ብጣቂ ነገር ማግኘት አይቻልም።  በዚህም እንዲቀጥል ምኞቴ ነው።

ጭምቷ ሲዊዝ ለአዲሱ  ለትወልዱ ታላቅ የባለውለታነት ስጦታ ነው ያበረከተችው። የፈጸመችው። ህሊና ያለው ትውልድ ይህን ሊዘክረው ይገባል። ሲዊዝ ታሪካችን ጠብቃልንአለች። አዬነው እኮ የመንን – አዬን እኮ ታላቋ ብርታንያንን – መሪያችን አንዳርጋቸው ጽጌን አሳልፈው ሲሰጡ ለጭራቅ። አሁንም የሚዘገዩበት ምክንያት ተጨማሪው በደል የመንፈሱን ዲታነት እንድናጣ ለወንበዴ ጊዜ ለመስጠት ነው። ሊፈጥኑ  አልቻሉም። ቀኑ በረዘመ ቁጥር መከራውም ያን ያህል መራራ ኮሶ ይሆናል።

በዛ ድልዝ ቪዲዮቸው ክብራችን ከነመንፈሱ እንደሆን አይተናል። ነገ ግን ሌላ መርዶ ይኖራል። ይህ ያመረቀዘ የቋሳ ተግባር ከማናቸውም የወያኔ ቅንጥብጣቢ ቅርጥምጣሚ ንክኪዎች ጋር ቆርጠን እንደናቆም የሚያደርግ የበደል ነጋሪት ይመስለኛል። ለዬቶ መታገል። ነጥሮ መውጣት የወቅቱ ግዴታ ነው።

በጨረፍታ ያዳመጥኩት ነገርም አለ። ይህን አቅፈን – ይህን ተቃቅፈን እንድንቀጥል ደግሞ እንሰበካለን። የሚየሳዝነው ደም የሚያስነባው ይሄው ነው። አሁንም „ስክነት“ እያለ የሆዱ ዘመዴ ቱልቱላ በመድረካችን ሲያንባርቅ እንሰማለን። እናዳምጣለን። የነጻነት ትግሉ አቅምን ከማን እግር ሥር ነው ወድቆ ዬሚለምነው? „ከልደቱ?“ „አለም ከተጸዬፋቸው የወያኔ ጋሼ ጃግሬዎች ተላላኪዎች?!“ እንዳልሰማ!

ለረዳት አውሮፕላን አብራሪ አበራ ሃይለመድህን በአካል ለሚያገኙት ቤተሰቦች።

ወገኖቼ የጀግና ቤተሰቦች ዛሬ የሚታመን የለም። ቅይጥ የጎሸ ነገር ይሸተኛል። ጠረኑ በፍጹም አላማረኝም። ጦርነቱ የእርስ በእርስ ነው።  በሁለም ዘርፍ ጥንቃቄ ማድረጉ እጅግ አስፈላጊ ነው። ጥንቃቄ ያተርፋል እንጂ አያከስርም። የሲዊዝ መንግሥት ክድን አድርጎ የያዛቸውን ማናቸውም መረጃዎችን ነፃነታቸውን አደራ ጠብቁላቸው።

የእኔ ክብሮች ልጨርስ። ጊዜያችሁን ሰጥታችሁ ለምትታደሙት ወገኖቼ ሁሉ ፍቅሬን – ናፍቆቴን – ውስጤንም ሳልሳሳ አክዬ ሸልምኳችሁ። በጀግኖቻችን ዙሪያ ዘሃብሻ ላይ የከተብኳቸውን ሌሎችም ታክለው በድምጽ ዛሬ ዕለተ ሃሙስ ከ15 እስከ 16 አዬር ላይ አዬር ላይ እንገናኝ። እርግጥ እንደ እናትነቴ- እንደ አዛኝነቴ – እንደ እርግቡ አንጀቴ አጥንቴን የሰነጠቀው ጥቃትና ውርዴት ምን ያህል አቅም ኑሮኝ ዛሬን እንደማሳካ እርግጠኛ ባልሆንም። ካልቻላችሁ ደግሞ በማግሥቱ አርኬቡ ላይ ፍቀዱና እንገናኝ። የበጋ እረፍት ራዲዮ ፕሮግራሙ ስላለው ደግመን የምንገናኘው ከወር በኋላ ይሆናል በ28.08.2014 ነው። የዛሬው የ17.07.2014 ግን በRadio Tsgaye Aktuell Sendung ወይንም  www.tsegaye.ethio.info ወይንም www.lora.ch.tsegaye በዚህ እንገናኝና መንፈሳችን በናፍቆት እናሟሸው።

 

መፍቻ

* ጎልቶ ላልቶ ነው የሚነበበው። ትርጉሙ አዎንታዊ ነው። ደምቆ፤ ቀለሙ አብርቶ፤ እንደ ጸኃይ አምሮበት ለማለት።

 

ትግል ለነጻነት መስዋዕተነቱም ህይወቱ ነው!

ትግል ለነጻነት መከራው የጽድቅ መንገዱ ነው!

 

እግዚአብሄር ይስጥልኝ።


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>