-ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት አቅርቤያለሁ ብሏል
‹‹ግብረ ኃይሉ ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ስለማቅረቡ ማስረጃ አላቀረበም›› የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ
የተጠረጠሩበት ወንጀል ግልጽ ሳይደረግላቸው ከመታሰራቸው በተጨማሪ በሕገ መንግሥቱ ‹‹ዜጎች ተጠርጥረው በታሰሩ 48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለባቸው የሚገልጸውን ድንጋጌ ተላልፏል››
በሚል በአንድነት ፓርቲ ክስ የተመሠረተበት፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የፌዴራል ፖሊስ የጋራ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይል፣ ሐምሌ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርቦ ምላሽ ሰጠ፡፡
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ የፓርቲው ምክር ቤት አባል አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ የአረና (ትግራይ) ፓርቲ አመራር አቶ አብርሃ ደስታና የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ የሽዋስ አሰፋ፣ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት በፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውና በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ ተገልጾ ክስ መመሥረቱ ይታወሳል፡፡ ለፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ፍትሐ ብሔር ችሎት ሐምሌ 4 ቀን 2006 ዓ.ም. የተመሠረተበትን ክስ በሚመለከት፣ ግብረ ኃይሉ ሐምሌ 8 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ተገኝቶ ሁሉንም ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ማቅረቡን አስረድቷል፡፡
ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ያዋላቸው ዝም ብሎ ሳይሆን ከፍርድ ቤት ማዘዥያ አውጥቶ መሆኑን የፀረ ግብረ ኃይሉ ተወካይ ፖሊስ አስረድቶ፣ የተመሠረተበት የሐቢየስ ኮርፐስ (አካልን ነፃ ማውጣት) ክስ ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ አቶ ተማም አባቡልጉ እንደተናገሩት፣ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉ ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት አቅርቤያለሁ ባለበት ቀን እስከ ምሽት 11፡30 ሰዓት ድረስ ፍርድ ቤት ግቢ ውስጥ ሲጠብቁ ቢቆዩም ሊቀርቡ አልቻሉም፡፡
የሕግ አማካሪ ሊያገኙ ሲገባ መቼና በስንት ሰዓት እንደቀረቡ ሳይታወቅ ‹‹ቀርበዋል›› መባሉ ተገቢ ባይሆንም፣ ስለመቅረባቸውም ቢሆን ፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉ ለፍርድ ቤቱ ያቀረበለት ማስረጃ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ አንድ ሳምንት ያለፋቸው ቢሆንም፣ የሕግ አማካሪም ሆነ ቤተሰቦቻቸው እስካሁን እንዳላገኟቸው አቶ ተማም አስረድተዋል፡፡ ጠበቃ በእስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪ ደንበኞቹን ማግኘት የሚችለው በሳምንት ሁለት ቀናት ብቻ እንደሆነ በማዕከላዊ እስር ቤት መወሰኑ አግባብ አለመሆኑንም አቶ ተማም ተቃውመዋል፡፡
በተፈቀደው ቀን ጠበቃ ማዕከላዊ እስር ቤት ሄዶ ደንበኛውን ሊያስጠራ ወደ ፖሊሶች ጠጋ ሲል ‹‹ማንን ነው የፈለጉት?›› የሚል ጥያቄ በፖሊሶች መቅረቡ ጥሩ ቢሆንም፣ ጠበቃው የደንበኛውን ስም ሲናገር ‹‹እሱን ለማግኘት አልተፈቀደም›› የሚል ምላሽ በመስጠት ጠበቃው ከደንበኛው ጋር ሳይገናኝ እንዲመለስ መደረጉን ተቃውመዋል፡፡
‹‹በሌላ በኩል ሌሎች ተጠርጣሪዎች ከጠበቆቻቸው ጋር ሲነጋገሩ በተመሳሳይ ቦታ ላይ ይታያሉ፡፡ ጠበቃን ማነጋገር መብት ከመሆኑ አንፃር እየለዩ አልተፈቀደምና ተፈቅዷል›› ማለቱ በሰዎች መካከል ልዩነትን ስለሚፈጥር ጥሩ አይደለም፤›› በማለትም አቶ ተማም አክለዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉ ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ስለመቅረባቸው ማስረጃ እንዲያቀርብ በመንገር፣ ውሳኔ ለመስጠት ለሐምሌ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ፀረ ሽብር ግብረ ኃይሉ ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ማቅረቡን የገለጸ ቢሆንም፣ ከአረና (ትግራይ) አመራር አብርሃ ደስታ በስተቀር የቀረበ ስለመኖሩ እንዳልሰሙና ማስረጃም አለመቅረቡን አቶ ተማም አስረድተዋል፡፡
Source: Ethiopian Reporter