(ዘ-ሐበሻ) ሰማያዊ ፓርቲ የጠራው የተቃውሞ ሰለፍ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም እንደሚደረግ ታወቀ። ፓርቲው እንደገለጸው “ከአዲስ አበባ አስተዳደር ም/ከንቲባ በዛሬው እለት በተሰጠ ገለጻ መንግስት 50ኛውን የአፍሪካ ህብረት በአል ለማክበር በአሁኑ ግዜ ከፍተኛ የጸጥታ ሰራተኞች መድቦ በመስራት ላይ በመሆኑ ከፓርቲው የቀረበልንን ጥያቄ ለማስተናገድ የጸጥታ ሰራተኞች እጥረት አለብን። ይህም በመሆኑ የተቃውሞ ሰልፉ ቀንና ቦታ እንዲለወጥ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲም የዚህን ጥያቄ ተገቢነት ከሰላማዊ ሰልፍና የፖለቲካ ስብሰባ ስነስርአት አዋጅ ቁጥር 3/1983 አንጻር በመመርመር ተገቢ ሁኖ ስላገኘው የተቃውሞ ሰልፉ ግንቦት 25/ 2005 አ.ም. በኢትዮ-ኩባ አደባባይ ከጠዋቱ 4 ሰአት- 8 ሰአት እንዲሆን በመወሰን ከመንግስት የእውቅና ማሳወቂያ ደብዳቤውን ተቀብሏል፡፡”
በዚህም መሠረት ሰማያዊ ፓርቲ የጠራው የተቃውሞ ሰለፍ ግንቦት 25 በአዲስ አበባ ስለሚደረግ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንዲገኝ መጋበዙን ፓርቲው አስታውቋል። ፓርቲው ለሰላማዊ ሰልፉ ባገኘው እውቅና መሠረት በከፍተኛ ሁኔታ ቅስቀሳ እያደረገ ሲሆን እየበተነ ያለው ፍላየርም የሚከትለው ነው።