የውህደት አመቻች ኮሚቴውን በማሰር ውህደቱን ማደናቀፍ አይቻልም!!!
ኢህአዴግ ሰሞኑን የጀመረው እስር የአንድነት/መኢአድን ውህደት የማደናቀፍ አቅም እንደሌለው ለኢትዮጵያ ህዝብ ማረጋገጥ እንወዳለን
በኢትዮጵያችን በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ለማምጣት እየታገሉ የሚገኙት አንድነትና መኢአድ ከጥልቅ ውይይት በኋላ ወቅታዊው የፖለቲካ ሁኔታ የሚፈልገውን በመገንዘብ፤ የህዝቡን ጥያቄ መመለስ የሚችል የበተባበረ የፖለቲካ ሃይል ለመፍጠር እንዲቻል ስለ ዴሞክራሲ ሲሉ መስዋዕት የሆኑ ውድ ኢትዮጵያውያን በሚዘከሩበት ሰኔ 1 ቀን ለበርካታ ወራት በጋራ ሲሰሩበት የነበረውን የውህደት ስምምነት ከጫፍ በማድረስ የቅድመ ውህደት ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች ውህደቱን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ የውህደት አመቻች ኮሚቴ በማቋቋም ስራቸውን በእቅዳቸው መሰረት በትጋት እየሰሩ ሲሆን የኮሚቴው ሰብሳቢ ወጣቱ ፖለቲከኛ አቶ ሀብታሙ አያሌው ነበር፡፡ ኮሚቴው እንደሚያምነው ህወሃት/ኢህአዴግ የሁለቱን ፓርቲዎች ውህደት ካለመፈለጉም በላይ የተለያዩ ሁኔታዎችን በመጠቀም ለማደናቀፍ እንደሚሰራ እንገምታለን፡፡ ስለዚህ ሀብታሙ አያሌው በኮሚቴ ሰብሳቢነቱ ስራውን በትጋት እየተወጣ ስለነበር ሆን ተብሎ ውህደቱ ላይ እክል ለመፍጠር በአምባገነኑ ስርዓት ለእስር ተዳርጓል ብለን እናምናለን፡፡
የመኢአድ/አንድነት ውህደት አመቻች ኮሚቴ በጥብቅ እንደሚያምነውና ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማረጋገጥ የምንፈልገው የኮሚቴውን ሰብሳቢ ብቻ ሳይሆን እንዳለ ኮሚቴውን ቢያስር የተጀመረው ውህደት ሊደናቀፍ አይችልም፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግ ሰሞንን የጀመረው አመራሮች ላይ ያነጣጠረ እስር ወሳኙን ምዕራፍ የተሻገረውን ውህደታችንን የማደናቀፍ አቅም እንደሌለው በድጋሚ እናረጋግጣለን፡፡ እስሩ የሚጠቁመው ነገር ቢኖር ህዝባዊ መሰረቱን እያጣ የሚገኘው ገዢ ፓርቲ ህዝባዊ መሰረት እንዳጣና በጭንቀት ውስጥ ወድቆ ወደ ሃይል ርምጃ እንዳመራ ነው፡፡
የውህደት አመቻች ኮሚቴው እንደሚያምነው እንደገና የተጀመረው ሰላማዊ ታጋዮች ላይ ያነጣጠረው የማሰር ርምጃ የፀረ-ውህደት ዘመቻ ከመሆኑም በተጨማሪ በቀጣዩ አመት የሚካሄደውን ሀገራቀፍ ምርጃ በተለመደው ጉልበትና አፈና ለመንጠቅ ያለመ ነው፡፡ ስለዚህ ኮሚቴው ሀብታሙን ጨምሮ ዜጎች በፖለቲካ እምነታቸውና አቋማቸው እየተፈረጁ መታሰራቸውን አሁኑኑ እንዲቆም እየጠየቀ የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላማዊ ትግሉ ላይ የተጀመረውን የመድፈቅ ርምጃ በማውገዝ ሁለቱ ፓርቲዎች የጀመሩት ውህደት ከፍፃሜ እንዲደርስ የተለመደው ህዝባዊ ድጋፉን እንዲሰጥ ጥሪ ያቀርባል፡፡ ሊሎች ፓርቲዎችም ወደ ትብብር በመምጣት ሀገራችንን ከክፉዎች መታደግ እንድንችል ጥሪ እናቀርባለን፡፡
ድል የሕዝብ ነው!!!
የመኢአድ/አንድነት ውህደት አመቻች ኮሚቴ
ሐምሌ 3 ቀን 2006 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ