ፍኖተ ነፃነት
ኤሊያስ ገብሩ
የሰሞኑ የኢትዮጵያችን ሁኔታ ሀዘን፣ ቁጣ፣ ንዴት፣ እልህ፣ ብሎም የደስታ ስሜትን የቀላቀለ ነበር፡፡ የእሰሩ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ ዛሬ እንኳን ከአንድነት ፓርቲ አቶ ሀብታሙ አያሌው እና ከሰማያዊ ፓርቲ አቶ የሺዋስ አሰፋ መታሰራቸውን ሰምተናል፣ አውቀናል፡፡ የዚህ መሰል አካሄድ ግን መዘዘን የሚስከትል ይመስለኛል፡፡
አሁን አሁን ሰዎች እንደጥጃ ከቤታቸው፣ ከየመንገዱ፣ ከሚሰሩባቸው ቦታዎች …እየተወሰዱ መታሰራቸው በሀገራችን እየተለመደ የመጣ አዲስ ክስተት ሆኗል፡፡ ሥልጣን በጨበጡ ኃይሎች ለነገሮች የሚሰጡት ምላሾች የእስር እርምጃ መሆናቸው ከቀጠለ ከትርፉ ይልቅ ኪሳራቸው ማመዘኑ አይቀሬ ነው፡፡ አይንም ጆሮም ያለው መንግሥት ይስማ!
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ሰዎች ለምን ይፈራሉ?›› በማለት ራሴን ደጋግሜ የምጠይቅበት ጊዜ ነበር፡፡ አሁንም እጠይቅና የራሴን ምላሽ ለራሴ እሰጣለሁ፡፡ የምቀርባቸውን ሰዎች ጠይቄም ምክንያቱን ለመረዳት ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ‹‹ፈሪ ለእናቱ›› የሚል መልስ አስተናግጄም አውቃለሁ፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ግን ‹‹እመኑ እንጂ አትፍሩ›› ነው የሚለን፡፡
ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከልባቸው ደፋር የሆኑ ወንድ እና ሴት ኢትዮጵያዊ ወገኖቼን በድፍረት ብቅ ብቅ እያሉ ማየት በመቻሌ ደስ ብሎኛል፡፡
አሁን፣ ሕግን አክብሮ በድፍረት መንቀሳቀስ እንጂ ያለተፈጥሯችን መፍራት በብዙ ችግሮች ለተተበተበችው ሀገራችን አይጠቅማትም፡፡ ‹‹ፍትሕ አጥተናል››፣ ‹‹ተርበናል››፣ ‹‹ነጻነት አጥተናል››፣ ‹‹በኑሮ ተማርረናል››፣ … እያሉ የዳር ተመልካች መሆን መፍትሄ አይደለም፡፡ ‹‹ኢትዮጵኖች የጀግና ሕዝቦች ነን›› እንል የለ? ታዲያ ሕግን ተከትለን በተግባር እናሳየዋ!