(ምንጭ ዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 51 ሚኒሶታ)
ባየርን ሙኒክ ለተጨዋቾች ዝውውር ከፍተኛ ወጪ የሚያወጣ ክለብ ሲሆን ቦሩሲያ ዶርትሙንድ በአንፃሩ ከአካዳሚው በሚያፈራቸው ባለተሰጥኦዎች የብዙዎችን ቀልብ መግዛት ችሏል፡፡ የማሪዮ ጎትዘ በ37 ሚሊዮን ዩሮ ወደ ባቫሪያኑ ክለብ ማቅናት አንዳንድ ቅሬታዎችን ፈጥሯል፡፡ አብዛኞቹ ቅሬታዎች ያነጣጠሩት በባየር ሙኒክ ላይ ነው፡፡ ባየርን የገንዘብ አቅሙን እየተጠቀመ ምርጥና ባለተሰጥኦ ወጣቶችን እያሰሰ ያስፈርማል፡፡ ዶርትሙንድ ደግሞ ዋነኛ ተጠቋሚ ነው፡፡
የሁለቱ ክለቦች ፍጥጫ በትልቁ ባየርን እና በወኔያሞቹ የዶርትሙንድ ወጣቶች መካከል ነው ልንለው እንችላለን፡፡ በጥሩውና መጥፎው አልያም በዳዊትና ጎሊያድ መካከል የሚደረግ ፉክክር ሊባልም ይችላል፡፡ በአውሮፓ መድረክ ታላላቅ ቡድኖችን የሚገነዳድሱ ትንንሽ ቡድኖችን ተመልክተናል፡፡ አፖኤልና ባተ ቦሪሶቭን አይተናል፡፡ አፓኤና ባቴ ሲጠፉ ደግሞ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ መጥቷል፡፡
ባየርን ባለፉት አምስት ዓመታት ለዝውውር ያወጣው የተጣራ ወጪ ከዶርትሙንድ በሶስት እጥፍ ይበልጣል፡፡ ነገር ግን ባየርንን ብቻ ከፍተኛ ወጪ የሚያወጣ የቡንደስሊጋው ክለብ አድርጎ መቁጠር ተገቢ አይደለም፡፡ ታሪክን ወደኋላ መለስ ብለን ከቃኘን ዶርትሙንድም ለዝውውር ብዙ ገንዘብ አውጥቶ እናገኘዋለን፡፡ በወጣቶች የተዋቀረው የአሁኑ ዶርትሙንድ የርገን ክሎፕ በ2008 ወደ ኃላፊነቱ ከመምጣታቸው በፊት እጅግ አስቸጋሪ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ ቢጫና ጥቁር በሜዳ ላይ ውጤታቸው ሲዳከም በፋይናንሱ ደግሞ ተንኮታኩተው ነበር፡፡
የቡንደስሊጋው የተጫዋቾች ዝውውር ታሪክ
ባየርን በፋይናንስ በኩል ያለው የፈረጠመ ጡንቻ ሁልጊዜም የቡንደስሊጋው የበላይ ያደርገዋል፡፡ አላማውን ለማሳካት የሚረዳውን የትኛውም ተጨዋች ከማስፈረም ወደኋላ እንደማይል ይገልፃል፡፡ ታሪክ የሚነግረን ግን በቡንደስሊጋው ሪከርድ በሆነ ሂሳብ ተጨዋቾችን ያስፈረሙት ሌሎች ክለቦች መሆናቸውን ነው፡፡ ቬርዴር ብሬመን በ1971 ሪከርድ በሆነ ዋጋ አምስት ተጨዋቾችን አስፈርሞ ነበር፡፡ አምስቱ ተጨዋቾች ግን በጋራ ማስቆጠር የቻሉት 37 ጎሎችን ብቻ ነበር፡፡ ብሬመን ለ10 ዓመታት ከፍተኛ ወጪ ቢያወጣም በ1980 በ34 ጨዋታዎች 93 ጎሎች ተቆጥረውበት ከሊጉ ሊወርድ ችሏል፡፡
ኮሎኝ በቡንደስሊጋው ታሪክ ለአንድ ተጨዋች ዝውውር 1 ሚሊዮን የከፈለ የመጀመሪያው ክለብ ሲሆን ተጨዋቹ ሮጀር ቫን ጎል ይባላል፡፡ በዚህ ወቅት ሙኒክ 200 ሺ ማርክ (የቀድሞ የጀርመን ገንዘብ) ትርፍ አግኝቶ ነበር፡፡ በ1987 ኤይንትራክት ፍራንክፈርት ለሳድስ ዴታሪ ዝውውር 3 ሚሊዮን ማርክ በመክፈል ሪከርዱን አሻሻለ፡፡ በ1995 ሄይኮ ሄርክን ከሞንቼግላድባኽ ለማስፈረም 10 ሚሊዮን ማርክ በመክፈል የመጀመሪያው የጀርመን ክለብ ሆኗል፡፡ ከስድስት ዓመታት በኋላ ዶርትሙንድ ለማርሲዮ አሞሮሶ ዝውውር 50 ሚሊዮን የማርክ (25 ሚሊዮን ዩሮ) በመክፈል ሪከርዱን ደግሞ አሻሽሏል፡፡ ዶርትሙንድ በ1999 ለሄርሊሽና ፍሬዲቦቢች ግዢ የከፈለው 5.75 ሚሊዮን ዩሮ በቡንደስሊጋው በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከተፈፀሙ 50 ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው ግዢዎች ውስጥ ተካተዋል፡፡ የዶርትሙንድ ውድ ዝውውሮች የተካሄዱት ግን ከ2000-2009 ባሉት ጊዜያት ነው፡፡ ቀሪዎቹ ሶስት ውድ ፈራሚዎች ግን ከ2000 በፊት በነበረው ጊዜ የተፈፀሙ ናቸው፡፡
የቡድንስሊጋው ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው ዝውውሮች ስንመለከት ባየርን ሙኒክ ብዙ ገንዘብ አውጥቶ እናገኘዋለን፡፡ የባቫሪያ ውድ ዝውውሮች የተካሄዱት ግን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ ዶርትሙንድ በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ የፋይናንስ ውስጥ ሲገጥመው ባየርን ደግሞ አስገራሚ የኮሜርሺያል ገቢ አግኝቷል፡፡ ሙኒክ በ2009 በ30 ሚሊዮን ዩሮ ማሪዮ ጎሜዝን ከስቱት ጋርት በማስፈረም የቀደሙትን ሪከርዶች ሰብሯል፡፡ ባየርን ማኑኤል ኑዌርን በ2011 የቡንደስሊጋው ውዱ ግብ ጠባቂ በማድረግ 22 ሚሊዮን ዩሮ ከፍሎ አስፈርሞታል፡፡ ባለፈው ክረምት ደግሞ 40 ሚሊዮን ዩሮ በማውጣት ሃቪ ማርቲኔዝን ወደ አሊያንዝ አሬና አስመጥቶታል፡፡
የተጠና የቢዝነስ አካሄዱ ባየርን አሁን ለሚገኝበት የማይነቃነቅ የፋይናንስ ጥንካሬው አድርሶታል፡፡ ባየርን ለዝውውር ከፍተኛ ወጪ የሚያወጣው በቂ የፋይናንስ አቅም ስላለው ነው፡፡ ዶርትሙንድን ጨምሮ ቀሪዎቹ የቡንደስሊጋ ክለቦች ዘንድ ግን የባየርን አይነት አቅም የላቸውም፡፡
የዶርትሙንድ የፋይናንስ ቀውስ
ከቡንደስሊጋው መስራቾች አንዱ የሆነው ዶርትሙንድ በሊጉ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ቡድን ነበር፡፡ በ1966 በአውሮፓ ጥሎ ማለፍ ዋንጫ ፍፃሜ ሊቨርፑልን በማሸነፍ በኢንተርናሽናል መድረክ ዋንጫ ያነሳ የመጀመሪያው የጀርመን ክለብ መሆን ችሎ ነበር፡፡ በ1970 እና 80ዎቹ ዶርትሙንድ በፋይናንሱ በኩል ተዳከመ፡፡ በአንፃራዊነት በ1960ዎቹ ስኬታማ የነበረ ቢሆንም በ1972 ግን ከሊጉ ወርዷል፡፡ ከአራት ዓመታት በኋላ ደግሞ ወደ ቡንደስሊጋው ቢመለስም በ1986 ወደታችኛው ዲቪዚዮን በድጋሚ ከመውረድ ለጥቂት ተርፏል፡፡
ዶርትሙንድ ደግሞ ወደ ስኬት የተመለሰው በኦትማር ሂትዝፊልድ አሰልጣኝነት በ1991 ነበር፡፡ ሂትዝፊልድ በችግር ውስጥ የነበረውን ቡድን በማጠናከር 1993 ላይ ለአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ዋንጫ ፍፃሜ አደረሱት፡፡ ወቅቱ የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የአውሮፓ ውድደሮችን ለማስተላለፍ ገንዘብ ማፍሰስ የጀመሩበት ነበር፡፡ በዚያው ዓመት ክለቦች በሚጓዙበት ልክ ገቢ አግኝተዋል፡፡ ዶርትሙንድ በጊዜው በ16ቱ ቡድኖች ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈ ብቸኛው ስለነበር ወደ 25 ሚሊየን ማርክ ገቢ አግኝቷል፡፡
ክለቡ የገንዘብ አቅሙን ማጠናከር ጀመረ፡፡ በተለይ ከጣሊያኖቹ ክለቦች ጋር የመፎካከር ኃይል አገኘ፡፡ በወቅቱ በርካታ ጀርመናዊያን ተጨዋቾች በቡንደስሊጋ የሚያገኙት ደመወዝ ዝቅተኛ በመሆኑ ወደ ሌሎች ሊጎች አምርተው ነበር፡፡ ዶርትሙንድ ባገኘው ገንዘብ እንደ ማቲያስ ዘመር፣ ካርል ሄይንዝ ሪድል፣ የርገንኮለር፣ አንድሪስ ሙለር እና ስቴፋን ሬውተር የመሳሰሉትን ወደ ሀገራቸው መልሷቸዋል፡፡ ከእነዚህ ተጨዋቾች በተጨማሪ የጁቬንቱስ ተጨዋቾች የነበሩትን ሁሊዮ ሌዛር እና ፓውሎ ሶዛን አስፈርሟል፡፡
1990ዎቹ የዶርትሙንድ ወርቃማው ጊዜ ነበር፡፡ ቡድኑ በሂትዝፊልድ እየተመራ ሁለት የቡንደስሊጋ እና በ1997 የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችሏል፡፡ ከ2000ዎቹ በኋላ ደግሞ ቀውስ ውስጥ ለመግባት ተገደደ፡፡ በ1999 በሊጉ አራተኛ ሆኖ ቢያጠናቅቅም በቀጣዩ የውድድር ዘመን ግን ወደ ታችኛው ሊግ ለመውረድ ተቃርቦ ነበር፡፡ ክለቡ ወደ ስኬታማነቱ ጎዳና ለመመለስ ለዝውውር ከፍተኛ ወጪ ማውጣት ምርጫው ሆነ፡፡
ክለቡ ቦቢች (5.8 ሚሊዮን ዩሮ)፣ ቶማስ ሮዚስኪ (145 ሚሊዮን ዩሮ)፣ አሞሮሶ (25 ሚሊዮን ዩሮ)፣ ያን ኮለር (12.75 ሚሊዮን ዩሮ) እንዲሁም ኤቫኒስን (15 ሚሊዮን ዩሮ) ወደ ሲግናል ኤዱና ፓርክ አመጣ፡፡ በ2001/02 የውድድር ዘመን ከፍተኛ ወጪ ያፈሰሰው ዶርትሙንድ የሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከባየር ሌቨርከብን ጋር ከፍተኛ ፉክክር አድርጓል፡፡ በውድድር ዘመኑ የመጨረሻ ጨዋታ በማሸነፍ የቡንደስሊጋውን ክብር ተቀዳጅቷል፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን በዶርትሙንድ መልካም ሁኔታ አልተከሰተም፡፡ የፋይናንስ ችግሩ ተባባሰ፡፡
የባየርን በሌሎች መጠላት
ባየርን ሙኒክ በቡንደስሊጋው ታሪክ እጅግ ስኬታማው ክለብ እና የሁልጊዜም የትኩረት ማዕከል ነው፡፡ ከፍተኛ ወጪ በሚያወጣው ክለብ ላይ ብዙዎች ሀሳባቸውን ከመሰንዘር ወደኋላ አይሉም፡፡ ባየርን መልካም ዕድል ያለውና በመጨረሻው ደቂቃ የሚያሸንፍ ቡድን ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሞንቼግሊድባኽ፣ ዶርትሙንድ፣ ሌቨርከብንና ሼልከ በአንፃሩ በ11ኛው ሰዓት ስኬት የሚርቃቸው በመሆን ይታወቃሉ፡፡ አንዳንድ የቡንደስሊጋ ክለቦች ለባየርን ተጫዋቾቻቸውን ላለመሸጥ ባለመፍቀዱ ተጫዋቹን በአነስተኛ ሂሳብ ለጁቬንቱስ አሳልፎ ሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ ባየርን በቅርቡ ያስፈርማቸው ኑዌር እና ጎትዘ የቡንደስሊጋውን ምርጦች ከመውሰድ የሚያቆመው እንደሌለ ያሳያል፡፡ ባየርን ሙኒክ ስኬታማ እንዲሆን ጥሩ እቅድና ግንኙነት ግንባር ቀደምቶቹ ናቸው፡፡ በ1966 ሙኒክ ሮበርት ሻውንን በቡንደስሊጋው የመጀመሪያው ፕሮፌሽናል ቢዝነስ ማናጀር አድርጎ መሾሙ ለወደፊቱ ያለውን ጥሩ ዕቅድ ያመለክታል፡፡ ሮበርት በኡሊ ሆኔሽ ከተተኩ በኋላ የባየርን የዓለም አቀፍ ዝና ይበልጥ ናኘ፡፡ በእርሳቸው ስር 15 የሊግ ዋንጫዎችንና ሌሎች የሀገር ውስጥ ድሎችን አጣጥሟል፡፡
የባየርን ስኬታማነት በሆኔሽ መጎልበቱን ቀጠለ፡፡ የሆኔሽ መምጣት የክለቡን ግንኙነት አስፍቷል፡፡ ሆኔሽ ባየርን ሙኒክ ሆንሽን በተጨዋችነት ያገኘው የ18 ዓመት ልጅ ሳሉ ነው፡፡ ከከተማው ተቀናቃኛቸው 1860 ሙኒክ ጋር ስምምነት ቢኖራቸውም ሆኔሽ ወደ ባየርን አመሩ፡፡ ወደ ባየርን ለማቅናት የወሰኑት በጀርመን ወጣት ቡድን ያሰለጠናቸውን ዑዶ ላዴክ በመከተላቸው ነበር፡፡
በ1979 ሆኔሽ ጫማቸውን ከሰቀሉ በኋላ የክለቡ ጄኔራል ማናጀር ሆነው ተሹመዋል፡፡ ዑሊ ኃላፊነታቸውን እንደጀመሩ ባየርንን ከትክክለኛ ሰዎች ጋር የማቆራኘት ልምዱን አስቀጥለዋል፡፡ ወንድማቸው ዲተር ሆኔሽ ወደ ባየርን እንዲመጣ መንገዶችን አመቻችተውለታል፡፡ ዲተር በባየርን ቆይታው 224 ጨዋታዎች ሲያደርግ 102 ጎሎች አስቆጥሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አምስት የቡንደስሊጋ ክብሮችና ሶስት የጀርመን ጥሎ ማለፍ ዋንጫን ማሸነፍ ችሏል፡፡ ኡሊ ሆኔሽ ከሜዳ ውጭ ያላቸው ተፅዕኖ እጅግ ግዙፍ ነው፡፡
የባየርን ሙኒክ ለጋስነት
ባየርን ሙኒክን በ2000 የለቀቀው ማርከስ ባበል ‹‹በአውሮፓ ውስጥ ከሚገኙ ታላላቅ ክለቦች መካከል ባየርን እጅግ ሰብአዊው ነው፡፡ ችግሮችን ሲመለከት እጁን ከመዘርጋት ወደኋላ አይልም›› በማለት ስለቀድሞ ክለቡ አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ ባበል አልተሳሳተም፡፡ የተቸገሩ ተጨዋቾችም ሆኑ ክለቦች ባየርን እጁን ይዘረጋላቸዋል፡፡ አለን ማክናሊ በጉልበት ጉዳት ከሜዳ ሲርቅ ባየርን ደመወዙን እየከፈለ ኮንትራቱ እስከሚጠናቀቅ ደግፎታል፡፡ በመኪና አደጋ የተጎዳውን ላርስ ሉንድን ሆኔሽ በግላቸው ረድተውታል፡፡ ገርድ ሙለር ከችግሩ እንዲወጣ ወደ አልኮል ማገገሚያ በማስገባት በኋላም በባየርን ስር ስራ እንዲቀጠር በማድረግ ሆኔሽ የበኩላቸውን ተወጥተዋል፡፡ ክለቦችም የባየርን ድጋፍ ተቋዳሽ ናቸው፡፡ በ2003 ዶርትሙንድ ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ መግባቱን የተመለከተው ባየርን ሙኒክ ለጥቂት ወራት ለተጫዋቾች ደመወዝ ለመክፈል ይረዳው ዘንድ ለዶርትሙንድ 2 ሚሊዮን ዩሮ ሰጥቷል፡፡ በዚያው ዓመት ባየርን ከሴንት ፖሊ ጋር ባደረገው ጨዋታ የተገኘው ገቢ በመስጠት በደካማ ፋይናንስ ለእገዳ ተቃርቦ የነበረውን ሃምቡርግ አድኖታል፡፡ በ2006 ደግሞ 1860 ሙኒክ በአሊያንዝ አሬና ላይ ያለውን ድርሻ ባየርን 11 ሚሊዮን ዩሮ በማውጣት ገዝቶታል፡፡ በዚህ ምክንያት 1860 ሙኒክ ዕዳ ውስጥ እንዳይገባ ታድጎታል፡፡ ኽርታ በርሊን እና ዳይናሞ ድሬሰደን የባየርን እገዛ ያገኙ ሌሎች ክለቦች ናቸው፡፡ በመጪው ክረምት ሃንሳ ሮስቶክን ለመርዳት ባየርን ገቢ ማሰባሰቢያ ጨዋታ ለማድረግ ተስማምቷል፡፡
የዶርትሙንድ ደጋፊዎች በበኩላቸው የባየርን እገዛ የጠቀማቸው በጥቂቱ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ዶርትሙንድ በ2005 መሸጥ የጀመረው ሼር በ80 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን ተከትሎ በተጨዋቾቹ ደመወዝ ላይ የ20 በመቶ ቅነሳ ለማድረግ ተገዷል፡፡ የዶርትሙንድ የፋይናንስ ኦፊሰር ቶማስ ቶስ በወቅቱ እዳቸው 200 ሚሊዮን ዩሮ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ቶሬስ ስለባየርን እገዛ ሲናገሩ ‹‹የባየርን ተግባር ክብር የሚሰጠው ነው፡፡ በአስቸጋሪ ወቅት ሌሎች ክለቦችን መርዳት ድንቅ ተግባር ነው፡፡ የባየርን 2 ሚሊዮን ዩሮ ሁሉንም ችግር ባይፈታም ዶርትሙንድን ደግፏል›› በማለት ያመሰግናሉ፡፡
ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከፋይናንሳዊ ውድቀት በኋላ አካሄዱን በመቀየር ወጣቶች ላይ በማተኮርና ባለተሰጥኦዎችን በማፍራት በአሁኑ ወቅት አውሮፓን ያስገረመ ቡድን ገንብቷል፡፡ ጎትዘ ወደ ባየርን መጓዙና የሮበርት ሌቫንዶቭስኪ መልቀቅ እርግጥ እየሆነ መምጣቱ የዶርትሙንድ ስትራቴጂ በረጅም ጊዜ ምን ያህል እንደሚጠቅመው የሚታይ ይሆናል፡፡ የአሰልጣኝ ክሎፕ በወጣቶች ላይ ያተኮረ ፕሮጀክት ገና እንጭጭ ነው፡፡
የቅርብ ታሪኮችን ተመርኩዘን የዶርትሙንድና የባየርን የቻምፒየንስ ሊግ ፍጥጫ ከተመለከትነው በወጣቶች ላይ ያተኮረውና በከፍተኛ ወጪ ላይ በተመረኮዘ ቡድን መካከል የሚደረግ ጨዋታ ሊባል ይችላል፡፡ ባየርን እና ዶርትሙንድ ታላቅ ክብር የሚገባቸው ቡድኖች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ጥሩ ታሪክ ተንኮለኛ ገፀ ባህሪ ያስፈልገዋል፡፡ ምርጥ ታሪክ ግን በሁሉም ጎን ጀግና ያኖረዋል፡፡ S
በዘ-ሐበሻ ድረ ገጽ የስፖርት ዘገባዎችን በየቀኑ ይከታተሉ
↧
Sport: ባየር ሙኒክ Vs ዶርትሙንድ –የዳዊትና ጎሊያድ ጦርነት
↧