Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

እኔም አንዳርጋቸው ነኝ! እኔም ግንቦት ሰባት ነኝ! (በአበበ ገላው)

$
0
0

የአፓርታይድ ስርአት መገለጫዎች አድልኦ፣ የዘር መከፋፈል፣ ጭቆና፣ ምዝበራ፣ ዝርፊያ፣ የመሬት ንጥቂያ፣ ግድያ፣ እስራት፣ ግርፊያ፣ ሰቆቃ፣…ዋነኞቹ ናቸው። እነዚህም የአፓርታይድ ስርአት መገለጫዎች ከደርግ የከፋው የህወሃቶች ስርወ መንግስት ዋነኛ ባህሪያት መሆናቸው አለም ያወቀው ጸሃይ የሞቀው እውነታ ነው።
abebe
ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ፣ ህወሃት መራሹ ፋሺስታዊ ስርወ መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በርካታ ዘግናኝ ወንጀሎችን ፈጽሟል። በኦሮሚያ ክልል ገበሬዎች ያለ አግባቡ ከመሬታቸው መፈናቀላቸውን የተቃወሙ ተማሪዎች ላይ ተኩስ በመክፈት በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያና የአካል ጉዳት ፈጽሟል። ከዚህም አልፎ በሺ የሚቆጠሩ ተማሪዎች የጅምላ እስር፣ አፈና፣ ሰቆቃና ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀል ገጥሟቸው ህይወታቸው ተመሰቃቅሏል፣ ህልማቸው ጨልሟል።
ህገመንግስታዊ መብታችን ይከበር ከማለት ያልዘለለ ጥፋት ያላጠፉ የዞን ፱ አባላትን ያለምንም ማስረጃና ክስ በህገወጥ መንገድ በእስር ቤት በማጎር ከፍተኛ የአካልና የስነ ልቦና ጥቃት እንዲፈጸምባቸው ተደርጓል። ከወለጋ በሺ የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በኦህዴድ መሪነት በደረሰባቸው ከፍተኛ ጥቃት ሳቢያ ቤትና ንብረታቸውን ትተው እንዲፈናቀሉ ተደርጓል። የቀድሞው የጋምቤላ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኦኬሎ አኳይ እና ሌሎች ሰባት የክልሉ ተወላጆች ከደቡብ ሱዳን በህወሃት የጸጥታ ሃይሎች ታፍነው፣ ከፍተኛ ድብደባና ሰቆቃ ከተፈጸመባቸው በሁዋላ በሽብር ወንጀል ተከሰዋል።
በተመሳሳይ በየመን በኩል ወደ ሶስተኛ አገር ይጓዙ የነበሩት የግንቦት ሰባት ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመንና የህወሃት የደህንነት ሃይሎች ታፍነው ወደ አዲስ አበባ ተወስደው ከፍተኛ ድብደባና ሰቆቃቃ እንደተፈጸመባቸው ለማወቅ ተችሏል። በመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል እንጂ የህወሃቶችና የጋሻ ጃግሬዎቻቸው ወንጀል ተዘርዝሮ አያልቅም።
ህወሃት የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጵያ ገንጥዬ ሪፐብሊክ አቋቁማለሁ በሚል ጠባብና ዘረኛ አላማ ጫካ ከገባ የዛሬ ፵ አመት ጀምሮ በአገራችን እና በህዝቧ ላይ ተዘርዝሮ የማያልቅ ግፍና በደል መፈጸሙ ያደባባይ ምስጢር ነው። ህወሃቶች በየእለቱ በሚፈጽሙት ፋሺስታዊና አንባገነናዊ ወንጀሎች ሳቢያ የኢትዮጵያ ህዝብ ክብሩ፣ ነጻነቱ፣ ሰብአዊ መብቱ፣ ዜግነቱ፣ ክብሩና ማንነቱ ተገፎ በጨቋኞች ጫማ ስር አስከፊ የመከራ ህይወት እንዲገፋ የተገደደ ሲሆን ህወሃቶችና ፍርፋሪ የሚጥሉላቸው ሎሌዎቻቸው ህዝብ በጠራራ ጸሃይ እየዘረፉ፣ እያሰቃዩ፣ በኑሮ ችግር እግር ከወርች አስረው እየገርፉና እየገደሉ ተንደላቀው ለመኖር ሲጥሩ ይታያሉ።
እኔም እንደ በርካታ ኢትዮጵያዊያን በወያኔ የሚፈጸሙ መንጀሎችን ለማጋለጥና፣ የህዝባችንን ብሶትና መከራ አጉልቶ ለማሳየት የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት አቅሜ የፈቀደልኝ ሁሉ በግሌ ጥረት ሳደርግ ቆይቻለሁ። ምንም እንኳ በየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲም ይሁን ንቅናቄ ላለመግባት ውሳኔ አድርጌ የቆየሁ ቢሆንም፣ ከቅርብ ግዚያት ጀምሮ ግን ታግሎ ሊያታግል የሚችል ድርጅት ወስጥ በመግባት የበለጠ አስተማጽኦ ማበርከት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው በመረዳቴ የግንቦት ፯ የፍትህ የነጻነትና የዴሞክራሲ ንቅናቄን ተቀላቅያለሁ።
እንደ ማንም ድርጅት ግንቦት ፯ ድክመትም ጥንካሬም ያለው ሲሆን የድርጅቱን ጥንካሬዎች የበለጠ አጎልብቶ ለመታገል በቁርጠኝነት ተነስቻለሁ። እኔም ድርጅቱ ጥንካሬዎቹን አጎልብቶ ድክመቶቹን አርሞ የበለጠ ህዝባችንን አደራጅቶ ታግሎ እንዲያታግል አስተዋጽኦ ለማድረግ የሚቻለኝን ሁሉ ጥረት አደርጋለሁ።
ህወሃቶችና የወንጀለኛ አፓርታይድ ስርአታቸው ተጠቃሚዎችና አገልጋዮችን በያሉቡትና በየገቡበት አምርረን በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ መታገል የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ፈተና ነው። በተለያዩ ግዚያትና የታሪክ አጋጣሚዎች የተቋቋሙ ድርጅቶች ሁሉም ለጋራ እራእያችን መሳካት በህብረት ህዝባችንን የበለጠ አደራጅተው እንዲታገሉም ያላሰለሰ ጥረት ለማድረግ ቃል እገባለሁ።
እነ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ አንዱ አለም አራጌ፣ ርዮት አለሙ፣ በቀለ ገርባ፣ ኦልባና ሌሊሳ፣ ኡስታስ አቡበከር አህመድ እና በርካታ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ራእያቸው የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነት እውን ለማድረግ እጅ ለጅ ተያይዘን እንታገል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነቱን በትግሉ እንዲቀዳጅ በህብረትና በጋራ አምርረን ለመታገል በያለንበት እንደራጅ። ኑ በጋራ እንነሳ፣ ሀገራችንን ከአውሬዎች ለማታደግ ሁለገብ ትግል በያለንበት እናፋፍም።
እኔም አንዳርጋቸው ጽጌ ነኝ! እኔም ግንቦት ሰባት ነኝ! እኔም አሸባሪዎችን በነጻነት ጥሪ የማሸብር አሸባሪ ነኝ!
ድል ለጭቁኑ የኢትዮጵያ ህዝብ!
ነጻነት! ነጻነት! ነጻነት!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>