የአቶ አንዳርጋቸው መስዕዋትነት ለትግላችን መፋፋም፣ ለትብብራችን ተግባራዊነትና፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነፃነት እውን መሆን ወሳኝ ምዕራፍ ነው!
ጋዜጣዊ መግለጫ
የኢትዮጵያ ወጣቶች ብሄራዊ ንቅናቄ በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ላይ በተፈጠረው ልብ የሚሰብር ክስተት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፀ፤ ይህ ፋሽስት የወያኔ/ኢህአዴግ ሥርዓት የፈፀመውን አሳፋሪና ህገወጥ አፈና በከፍተኛ ምሬት፣ ቁጭትና፣ እልህ አጥብቆ እንደሚቃወም ያሳውቃል። የጎረቤት ሃገራት አቶ አንዳርጋቸውን ጨምሮ በስደት ላይ በሚገኙ አያሌ ኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ የአፈና ወንጀልን በመፈፀም ንፁሃን ዜጎችን ለሰው በላው የወያኔ/ኢህአዴግ ሥርዓት አሳልፈው ሲሰጡ በተደጋጋሚ ሰምተናል አይተናልም። ድርጅታችን ይህ የወንበዴ መንግስታት አይን ያወጣ ወንጀል ነፃነቱንና ህልውናውን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጀግንነትንና ጀብድን በመፈፀሙ፤ ለአለም ጥቁር ህዝቦች ብቸኛው የነፃነት ምሳሌ ሆኖ በአለም አቀፍ ደረጃ ለዘመናት በክብር የኖረው መላው የኢትዮጵያ ህዝብን የናቀና ያዋረደ፤ የሃገሪቱን ሉአላዊነትና ክብር በጅጉ የደፈረ፤ ይቅር የማይባል ብሄራዊ ወንጀል መሆኑን በፅኑ ያምናል። በመሆኑም ሥርዓቱ እየፈፀመ በሚገኘው አስከፊና አሳፋሪ ወንጀል ወደፊት ከመጠየቅ በፍፁም እንደማይድንና ምናልባትም እጅግ የከፋ ዋጋ እንደሚያስከፍለው ተገንዝቦ፤ ከዚህ የወንጀል ድርጊቱ በመታቀብ አቶ አንዳርጋቸውንም ሆነ ሌሎች በተመሳሳይ መልኩ ከጎረቤት ሃገራት ታፍነው በየእስርቤቱ የሚማቅቁ አያሌ ንፁሃን ዜጎችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቅ ከወዲሁ በጥብቅ ያስጠነቅቃል።