Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

“አንዳርጋቸው የማይጨበጥ ጽኑ መንፈስ እንጂ አንድ ግለሰብ አይደለም!!!”–ግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል

$
0
0

አንዳርጋቸው የማይጨበጥ ጽኑ መንፈስ እንጂ አንድ ግለሰብ አይደለም!!! ግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል

July 3, 2014

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ከታዩ አርቆ አሳቢ፣ አስተዋይና ብልህ ፖለቲከኞች አንዱ የሆነው ታላቁ የነፃነት ታጋይ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ለሥራ ጉዳይ ሲንቀሳቀስ የመንን እንደመሸጋገሪያ በሚጠቀምበት ወቅት በሰኔ 16 ቀን 2006 ዓ.ም. በየመን ሰንዓ ከተማ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በሀገሪቱ መንግሥት ትዕዛዝ በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል:: ምንም አይነት ምድራዊም ይሁን ሰማያዊ መነሻ ምክንያት ለአቶ አንዳርጋቸው በየመን መንግሥት መታገት እና መታሰር ምክንያት ሊሆን እንደማይችል እንደማይገባም በመግለጽ የየመን መንግሥት የነፃነት ታጋያችንን ባስቸኳይ እንዲለቅ ላለፉት ተከታታይ ቀናት የተደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት ውጤት አላስገኘም:: ከዚህም በመነሳት አቶ አንዳርጋቸው ለዘረኛው እና ከፋፋዩ የወያኔ ቡድን ሊሰጥ ይችላል የሚለው ስጋታችን ቀን በገፋ እና ምላሽ በራቀ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል::
andaregachew-tsege-300x498
በግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል በኩል የነፃነት ታጋዩ ለወያኔ ተላልፎ መሰጠቱን መቶ በመቶ እስከምናረጋግጥበት ቅጽበት ታጋዩን የማስለቀቅ ጥረቱ መቀጠል እንዳለበት በጽኑ እናምናለን:: አንዳርጋቸውን ማሰር ይቻላል፤ ምናልባትም በዚህ ቅጽበት ተችሏል፤አንዳርጋቸውን ማሰቃየት ይቻላል፤ ምናልባትም በዚህ ቅጽበት ተችሏል፤ አንዳርጋቸውን መግደል ይቻላል። ሞትን ፈርቶ ወደ ትግል አልገባምና አንዳርጋቸውን በማሰር የአንዳርጋቸውን እንደ እቶን የሚያቃጥል የፍትህ፣ የነፃነት፣ የዴሞክራሲና የእኩልነት መንፈስ ግን ለሴኮንዶች እንኳን ማሰር አይቻልም። አንዳርጋቸውን በማሰቃየት ያን ዘመን ተሻጋሪ የሆነ የትውልዱን መንፈስ የሚገዛ የሁላችንም የምትሆን የጋራ ኢትዮጵያን የመፍጠር ንጹህ ራዕዩን ግን ፈጽሞ ማቁሰል አይቻልም!!! አንዳርጋቸውን በመግደል ዕንቁ ዓላማውን መግደል ከቶ አይቻልም፤ የታሪክ መዛግብት ገጾች ለዚህ ሃቅ በሚመሰክሩ እውነታዎች የተሞላ ነውና። አንዳርጋቸውን በመግደል “ከአባቶቹ የማይበልጥ ትውልድ እንዳልተፈጠረ ይቆጠራል፣ ልጅ አባቱን ሩጦ መቅደም አለበት፣ ስለዚህ እናንተ ወጣቶች እኛን ሩጡ እና ብለጡ ቅደሙን፣ ቀናዎች ሁኑ፣ ርስ በርስ ተዋደዱ፣ ያለፉት ትውልዶች የሰሩትን ስህተት ላለመድገም ታሪክን ከስሩ ተረዱ፣ ያለማወቅ ጠንቅ ከሚያመጣው ጥፋት ለመዳን ሁሌም ለእውቀት ጉጉዎች ሁኑ። ለማወቅ ጣሩ፣ የማይቀረው ሞታችሁ ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲ እና ለነፃ ኢትዮጵያ ይሁን” እያለ ላለፉት በርካታ አመታት ያስተማራቸው እና የኮተኮታቸው የነፃነት ታጋይ አርበኛ ወጣቶችን እና እሳት መንፈሳቸውን መግደል አይቻልም::

ታሪካዊ ስህተት በመሥራት በአዲሱ ትውልድ ልብ ውስጥ የበቀል እና የቂም ጓዝ ለማስቀመጥ እየተንደረደረ ያለው የየመን መንግሥትም ሆነ ወያኔ ሊያውቁት የሚገባው ተፈጥሯዊ ሃቅ ይህ ነው:: አንዳርጋቸውን በአንድ ካቴና በማሰር፤ በአንድ ክፍል ውስጥ በመዝጋት ወይም በአንድ ጥይት በመግደል “መገላገል” የሚቻል አንድ ግለሰብ አይደለም:: አንዳርጋቸው ለሽህ ካቴናዎች የማይታጠፉ እጆች፤ ለሽህ ማጎሪያዎች የገዘፈ ገላ፤ ለሽህ ጥይቶች የሰፋ እና ሽህ ጥይቶችን የሚተፋ ግንባር እና ደረት ያለው ብርቱ ታጋይ ነው። አንዳርጋቸው አንድ ግለሰብ አይደለም፤ የማይጨበጥ ጽኑ መንፈስ እንጅ!!!

አንዳርጋቸው ለአርባ አመታት በሚጠጋ የፖለቲካ ሕይወቱ ሁሉ በረሃ የሚወረወረው አፈር ላይ የሚንከባለለው፤ በእሱ እድሜ በማይታሰብ ሁኔታ እንኳን የበረሃ ሃሩር፣ ጥም እና ረሃብ የሚያንገላታው ነገ ኢትዮጵያን በፕሬዝዳንትነት ወይ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስቴርነት ለመምራት ካለው ሰዋዊ ፍላጎት አይደለም:: የሱ ምኞት የሁላችንም የሆነች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት ነው!!! ይህን በተለይ የግንቦት ሕዝባዊ ኃይል አመራሮች እና መላው አባላት ጠንቅቀን እናውቃለን:: አንዳርጋቸው ሁሌ ለሚያልማት ንጽህት ኢትዮጵያ መሥራት የነበረበትን ፈታኝ እና ታሪካዊ ሥራዎች ቀድሞ አከናውኗቸዋል:: ላለፉት 6 እና 7 ዓመታት ከጥልቅ የፖለቲካ ተሞክሮው እየቀዳ ለወጣት ኢትዮጵያውያን በየበረሃው እየዞረ አስተምሯል:: እያማጠ አደራ ብሏል:: እያለቀሰ ምኞቱን፣ ፍላጎቱን እና ራዕዩን ከውስጡ አውጥቶ መዳፉ ላይ በማስቀመጥ ልቡን ለታዳጊዎች አሳይቷል:: ንጹህ ዓላማው ሽህ ባለ ራዕዮችን ፈጥሯል የተግባር ሰዎችን አምርቷል:: የግንቦት 7 ሕዝባዊ ኃይል አንዳርጋቸው እንደመጥምቁ ዮሃነስ በበረሃ እየዞረ ሲያስተምር እና ሲሰብክ ከፈጠረው ንጹህ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ላይ የበቀለ ኃይል ነው::

ትናንት አብሮ ውሎ ዛሬ በድንገት መተጣጣት የትግል አንዱ ባህሪው ነውና ዛሬ አንዳርጋቸው በአካል አብሮን ላይኖር ይችላል:: ነፍሳችን ውስጥ ያሰረፀው ዘላለማዊ መንፈስ ግን እስከመጨረሻ ህቅታችን ድረስ አብሮን ይዘልቃል:: አንዳርጋቸውን በማስቆም ትግሉን አቆማለሁ ብሎ የሚያስብ ካለ ዓለምን እና ሁኔታዎችን መገንዘብ የማይችል ከራሱ የተጣላ የወያኔ አይነት ቂል ብቻ ነው:: አንዳርጋቸውን በማስቆም ትግሉን ማስቆም አይቻልም:: መንፈስን ማስቆም ከቶ ማን ይቻለዋል?? አንዳርጋቸው እኮ መንፈስ ነው:: ሁሉም ቦታ፣ ሁሉም ጫፍ ፣ሁሉም ልብ ውስጥ የሚገኝ እና የሚንሳፈፍ መንፈስ::

የየመን መንግሥት የፈጸመው ድርጊት እጅግ ስህተት መሆኑን ዘግይቶም ቢሆን ተረድቶ የነፃነት ታጋያችንን ባስቸኳይ ይለቀው ዘንድ አሁንም ደጋግመን እንጠይቃለን:: ይህ ሳይሆ ን ቀርቶ ታጋያችን ወያኔ እጅ ውስጥ ከገባ ግን የትውልዱ የበቀል ሰይፍ ከዛሬ ጀምሮ ከሰገባው መውጣቱን እንዲያውቁት እንፈልጋለን:: ወያኔም ይህ የቂል ድርጊት የነፃነት ታጋዮችን የበለጠ ቁጭት እና የበቀል እርምጃዎች ውስጥ የሚከት መሆኑን አብሮ ሊገነዘበው ይገባል:: ለዚህ ቃላችን ታሪክ ምስክር ይሁንብን::

ድል ለ ኢትዮጵያ ሕዝብ!!!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>