ፍኖተ ነፃነት
ግንቦት በሀገራችን ታሪክ ወሳኝ ፖለቲካዊ ሁነቶች የተከሰቱበት ነው፡፡ ከሌሎቹ ፖለቲካዊ ሁነቶች መካከል፣ ኢትዮጵያን ከአምባገነኖች መዳፍ ነፃ ለማውጣት የተስፋ ጭላንጭል የታየበት የግንቦት 7, 97 ምርጫ ጎላ ብሎ የሚጠቀስ ነው፡፡ በወቅቱ ገዢው ፓርቲ በአንፃራዊነት ከፍቶት በነበረው የውድድር ሜዳ የተጠቀሙት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ዳር እስከዳር ህዝቡን ለማስተባበር የቻሉበት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም ለውጥ እንደሚፈልግና የሰለጠነ ፖለቲካ ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ለኢህአዴግም ሆነ ለመላው የአለም አቀፍ ህብረተሰብ ያረጋገጠበት ነው፡፡
ግንቦት 7 ተደርጎ የነበረው ታሪካዊ ምርጫ በኢህአዴግ አምባገነናዊ አፈናና በተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ፖለቲካዊ ብስለት ማጣት ምክንያት ለውጤት አለመብቃቱ የሚያስቆጭ ነው፡፡ ሆኖም ከስምንት አመታት በኋላም የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት የመጨመር እንጂ የመቀነስ ሁኔታ አይታይበትም፡፡
ኢህአዴግ በግንቦት 97ቱ ምርጫ ያጋጠመውን ኪሳራ ካሰላ በኋላ በሀገር አቀፍም ሆነ በወረዳና በከተማ ደረጃ ካሄዳቸውን ምርጫዎች ሙሉ ለሙሉ ለውድድር የማይመቹ እንዲሆኑ በማድረግ በህዝቡ የለውጥ ፍላጎት ላይ ቀዝቃዛ ውሀ ቸልሷል፡፡
በዘንድሮው የአካባቢና የከተማ ምክር ቤት ምርጫም ኢህአዴግ በከፍተኛ ውጤት ማሸነፉን ገዢው ፓርቲ እንዳሻው የሚዘውረው ብሔራዊው ምርጫ ቦርድባሳለፍነው ሳምንት ለህዝብ ይፋ አድርጓል፡፡ ኢህአዴግ ያለተፎካካሪ ብቻውን የሮጠበትን የምርጫ ሂደትና ያገኘው ውጤት ከግንቦት 7, 97 ምርጫ ጋር ሲተያይ የሀገራችን የዴሞክራሲ ጉዞ ምን ያክል ወደ ኋላ እንደተመለሰ ያመላክተናል፡፡
የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ጉዞ የተሳካ እርምጃ እንዲሄድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ማለትም ዜጎች፣መንግስት፣ገዢው ፓርቲ፣ምርጫ ቦርድ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣የሲቪክ ተቋማትና የሌሎች የጋራ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ መንግስት እና ገዢው ፓርቲ ፀረ ዴሞክራሲያዊ እርምጃዎችን ሲያደርጉ፣ ብሔራዊው ምርጫ ቦርድም የድርጊቱ ተባባሪ ሲሆን ሌሎቹ ባለድርሻ አካላት በዝምታ መመልከት የለባቸውም፡፡ በሀገራችን በገሀድ እየታየ ያለው ሀቅ ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መንግስትና ገዢው ፓርቲ የሚያደርጉትን ፀረዴሞክራሲያዊ ተግባራት ከማውገዝ ያለፈ ተግባራዊ ስራ፣ ሲሰሩ አይታዩም፡፡ ይልቁኑም ገዢው ፓርቲ ያሻውን እንዲያደርግ የተውት እስኪመስል ድረስ ከመግለጫ ያለፈ ተግባራዊ ሰላማዊ ትግል ከማድረግ ተቆጥበዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በምንም አይነት መቀጠል የለበትም፤ በመሆኑም የኢህአዴግን በተለይም የገዢውን ቡድን አምባገነናዊ አፈና ከማማረር ባለፈ ግንቦት 7, 97 የታየውን የለውጥ መነሳሳት ለመድገም ጠንካራ ሰላማዊ ትግል ይኖርበታል፡፡ግንቦት 7, 97ቱን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመድገም ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ለመረዳት የሀገራችንን ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ መመዘን ያስችለናል፡፡
ሀገራችን የገባችበት የማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ከስምንት አመት በፊት ከነበረው እጅግ የባሰ ነው፡፡ ህዝባችን የእምነት፣የመደራጀት፣የመናገር፣በፍትሀዊነት የመዳኘት መብቶቹን ከ1997ዓ.ም በባሰ መልኩ በገዢው ቡድን ተነጥቋል፡፡ የሲቪክ ተቋማትና መንግስት ባወጣው አሳሪ ህግ ለዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ አስተዋፅኦ እንዳይኖራቸው ተደርገዋል፡፡ ነፃውን ፕሬስ በአፋኝ የፕሬስ ህግ በማዳከም እንዲሁም ጋዜጠኞች በፀረሽብርተኝነት ህግ ሰበብ የሚጠበቅባቸውን ያህል እንዳይሰሩ ተደርገዋል፣ በርካታ ጋዜጠኞች በተቀነባበረ የሽብር ክስ ታስረዋል፣ ጋዜጦች አታሚ በማጣት ከገበያ እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡የፖለቲካ ፓርቲዎች ከደጋፊዎቻቸውና ከህዝብ ጋር እንዳይወያዩ አዳራሽ ከመከልከል ጀምሮ አመራሮቻቸውን በተፈበረከ ክስ ታስለውባቸዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ዘርፈ ብዙ አፈናዎች በ1997 ዓ.ም ከነበረው አፈና ጋር ሲተያይ የአሁኑ እጅግ የከፋ ነው፡፡ ይህ ዘርፈ ብዙ አፈና በህዝቡ ውስጥ የፈጠረውን ብሶት ወደ ሰላማዊ ህዝባዊ ዕምቢተኝነት መለወጥ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡