አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ የይስሙላውን ምርጫ በመጪው ዓመት እንደተለመደው ግልጽና ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ለማከናወን ሲል ገና ከአሁኑ ለለውጥ የተነሳሱ ዜጎችን በማሰርና በማሳደድ ብሎም ደብዛቸውን እያጠፋ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሠራዊት የወገን ደራሽ ጥቃቱን በጎጠኛው ቡድን ታጣቂዎች ላይ መውሰዱን ቀጥሏል።
በሰኔ 16/2006 ዓ/ም በወልቃይት አድነጣ በተሰኘ ስፍራ በስርዓቱ የሚሊሻ ታጣቂ ላይ በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ አስራ ስምንት(18) ገድሎ ሁለት(2) ማርኳል የምርኮኞቹ ስም1ኛ- ቻለው ሲሳይ 2ኛ- ተጫነ ንጉሱ ሲሆኑ ሠራዊቱ ለሁለቱም ምርኮኞች ስለወቅቱ የኢትዮጵያ ሁኔታና ስለ ድርጅቱ አላማና ግብ በማስተማር ለቋቸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰኔ 18/2006 ዓ/ም ነበልባሉ የኢትዮጵያ ሕዝበ አርበኞች ግንባር ሠራዊት ከወያኔው የልዩ ሃይል ታጣቂ ጋር በወልቃይት አወርቂ በተባለ ቦታ ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ 5 ሰዓት ለአራት ሰዓት ያህል ባካሄደው እልህ አስጨራሽ ውጊያ ሰላሳ ስድስት(36) ገድሎ አርባ ስምንት(48) በማቁሰልና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ከነመሰል ጥይቶቻቸውና ትጥቃቸው ጋር ማርኳል።
ውጊያው በተካሄደበት አከባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችና በ2007 ዓ/ም ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የምርጫ ድራማ ሳቢያ ከፍተኛ እንግልትና ስቃይ እየደረሰባቸው የሚገኙ ወገኖች የተሰማቸውን ደስታ ከመግለጻቸውም ባሻገር የወያኔን ቡድን በጥይት አረር ለመፋለም ግንባሩን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ።
Source: Amharatimes