ለሰባዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች!
ለጋዜጠኛ መብት ተከራካሪዎች!
ህሊና ላላቸው ወገኖች በሙሉ!
የዓለም ስደተኞች ቀን ጁን 20 በመላ ዓለም ይከበራል። በየዓመቱ አስደሳች መፈክሮች ይጻፋሉ።ይለጠፋሉ።ስብስባዎች
ይካሄዳሉ።ታላልቅ ሰዎች መልዕክት ያስተላልፋሉ።ስደት በዓለም ላይ እንደኑሮ ውድነት እየጨመረ ነው።ችግሩ የአፍሪቃ
መሆኑ ቀርቶ አውሮፓና ኤዢያንም እያዳረሰ ነው።እኔ እንኳን ከተሰደድኩባት Dec 9,2005 ወዲህ
ኬንያ፥ሊቢያ፥ቱንዚያ፥ሴንትራል አፍሪቃ ሪፐብሊክ፥ቻድ፥ደቡብ ሱዳን፥ሶርያ፥ዩክሬን ወዘተ ፡ተጨማሪ ስደትን የቀመሱ
ሐገሮች ናቸው።ነገ ወደስደት እንደማይገባ ማንም ርግጠኛ መሆን አይችልም።እኔ ከጥቅምት ወር 1998ዓ/ም ስደት
በሕይወቴ ውስጥ ይከሰታል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር።ዛሬ ቅልጥ ያልኩ ስደተኛ ሆኜ የኔ ጦስ ለባለቤቴም
ተርፏል።ሃገር አልቦች ሆነናል።
ባለፉት ስድስት አመታት በዩጋንዳ ካምፓላ በተለያዩ ስፍራዎች “የዩኤንኤችሴር” አጋፋሪ በሆነው “ኢንተር ኤድ”
አስተባባሪነት በተከናወኑ የስደተኞች ቀን በዓል ላይ ኮከብ ተሳታፊ ነበርኩ። ዘንድሮም ዕለቱን ማክበሬ የማይቀር
ነው።
በደም የተቋጨው ምርጫ 97 የበርካት ንጹሃንን ደም ገብሮ ካለፈ ዘጠኝ ዓመታት ተቆጥሮአል።ገዳዮቹ ዛሬም ለፍርድ
አልቀረቡም።ሃገሪቱም በከፋ ሁኔታ ላይ ትገኛለች።ጋዜጠኞችና ጦማሪያን በፈጠራ ክስ እስር ቤት ታጉረዋል።
ዴሞክራሲ በገዢዎች መልካም ፈቃድ የምትሰጥ ብርቅ ስጦታ ሆናለች።የስደተኛው ቁጥር እያሻቀብ ነው።እንኳን የኔ ብጤ
ስደተኛው ወደ ትውልድ ሃገሩ ሊመልስ ይቅርና ሃገር ቤት ያሉትም መውጫ አጥተው ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው።ሃገር
ቤት።
በመጪው 2007 ዓ/ም በኢትዮጲያ ምድር የሚከናወነውን ብሄራዊ ምርጫ በነጻና ፍትሃዊ መንገድ ለማከናውን ቀድመው
መመቻቸት ያለባቸው ጉዳዮች
እስካሁን መተግበራቸውን እጠራጠራለሁ።
ነጻን ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ በአዲስ መልክ አልተዋቀረም።
የሚዲይ በነጻነት የመጠቀም ጉዳይ እልባት አላገኘምም።
ገዢው ቡድን ልቡን ለነጻ ምርጫ ያዘጋጀ ለመሆኑም ከተፈጥሯዊ ባህሪው አኳያ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠም።
ምርጫውን በአስፈላጊው ዘዴ በመጠቀም ዘላለማዊ ገዢ ለመሆን ይጠቀምበታል እንጂ ለማንም 1 ወንበር ማጋራት
አይፈልግም።የግርማ ሰይፉም በአፓርላማው መኖር ሳያቃጥለው አይቀርም፡
የኔ ስጋት በ2007 ምርጫ ማግስት የከበዱ ሁኔታዎች በሃገሬ ላይ እንደሚከሰቱና የዓለም የስደተኞች ቀን በ2015
ሲከበር የኢትዮጲያዊያን ቁጥር እንደሚያሻቅብ ብገልጽ ማሟረቴ አይሆንም።
ከ1997 ዓ/ም ወዲህ በተፈጠረው ሃገራዊ ቀውስ ምክንያት በርካታ ኢትዮጲያዊያን የፖለቲካ ስደተኞች በኡጋንዳ
የምንኖር ሲሆን ባለፉት 8 ዓመታት “በዩኤንአኤችሴር” ካምፓላና በዩጋንዳ መንግስት ያሉበት የደህንነት ስጋት
ምክንያት ወደ 3 ኛ ሃገር” ሪስትልመንት” አግኝተው የበረሩት “የቶንቦላው ባለዕድሎች” ጥቂቶች ሲሆኑ በርካቶች
አሁንም ደጅ እየጠኑ አሉ።እኔ ደጅ ጥናቴን አላቋረጥኩም።
እኔ ራሴ በቅርበት የማውቃቸው 3 የፖለቲካ ስደተኞች ባለፉት 2 ዓመታት በህመምና ስደቱ ባስከተለባቸው መራራ
ህይወት ተስፋ በመቁረት ወደ አይቀሬው መቃብር ወርደዋል።
3ቱም (UNHCR) ቢሮ ለዘመናት ሲመላለሱ ከርመው የዩጋንዳን አፈር ለብሰው ቀርተዋል።
የኔና የባለቤቴም ጉዳይ ላለፉት 6 ዓመታት ውሳኔ ሳያገኝ በተስፋ ዕድሚያችንን እያቃጠልን ነው።የኔስ የመረጥኩት
መንገድ ስልሆነ ነው።ባለቤቴ ግን ከዱባይ መጥታ ስደተኛ ሆና ያለስራ መጉላላቷ የሚያሳዝን ጉዳይ ነው።
የኔ ሕይወት በኡጋንዳ ምድር ልዩነቱ ሃገር ቤት ከባልደረባዬ እስክንድር ነጋ ጋር ቃሊቲ አለመታሰሬ እንጂ የቁም
እስረኛ ወይም በግዞት እንደሚኖር ሰው ነኝ ብል አልተጋነነም።
ላለፉት 7 ዓመታት በዩጋንዳ ቆይታዬ ገና ለጋ ስደተኛ ሳለሁ የኢትዮጲያን ሚሊኒየም ሲከበር ፕሮግራሙን
ከማስተባበር ጀምሮ በወቅቱ ከወያኔ ቆንስላ ጋር ሚሊኒየሙን በጋር ለማክበር ሲደረግ የነበረውን “መሞዳሞድ”
በመቃውም በዓሉን ወያኔን ባላሳተፈ ሁኔታ በድምቀት እንዲከበር ባደረኩት የጎላ ተሳትፎ “የወያኔ ክልል 16″(
ካምፓላ) ጥቁር መዝገብ ከሰፈሩት “አሸባሪዎች”(ወያኔ ያልተመቹትን ሰዎች የሚለጥፍባቸው ዓለም አቀፍ ታፔላ
ነው)ቁጥር ሁለት መስመር ላይ እንደምገኝ ይታውቃል።
የኢትዮጲያን ማህበረስብ በዩጋንዳ (ethiopian comunity) ከAug,2007 ጀምሮ የበጎ ፈቃድ ተስትፎ
ሳደርግ በመቆየት Nov2010 በተደረገ ጠቅላላ ጉባዔ በቦርድ አባልነት ተመርጬ እስከ አሁን ድረስ በማደርገው
እንቅስቃሴ ያልተደሰቱ ሃይሎች ኮሚኒቲውን ለመቆጣጠር በመፈለግ በሚያደርገው ሴራ አመራሩን ለማዳከም የሚደረገውን
ተግባር በመቃወሜ በጠላትነት ተፈርጄ እንቅስቃሴዬ ስጋት ላይ ወድቋል።
ከጃንዋሪ 2008 ጀምሮ በስደተኛው ህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ በሚመራው የስደተኞች ቤተክርስትያን የሰበካ ጉባዔ ስራ
አመራር ሆኜ በማገልገል ላይ ስሆን ከጁን 2010 ጀምሮ በተፈጠረው ውዝግብ የጥቃት ዒላማ ሆኜ በርካት መከራ
ደርሶብኛል።ድብደባም ተፈጽሞብኛል።(የካዛንቺስ ልጅ ተደብደቦ ዝም ባይልም ባለኝ ማህበራዊ ሃላፊነት ለሌሎችአርአያ
ለመሆንና መሰናክል ላለመሆን በማንም ላይ ዕጄን አላነሳሁም።ወደፊትም አላነሳም።) በተቀነባበረ ወጥመድም በፈጠራ
ክስ እስከ መታሰርና ዲፖርት ለማስደረግ የተሞከረው ደባ በወገኖቼ ርብርብና በአምላክ ፈቃድ እንደከሸፈ በቂ መረጃ
አለ።
አሁንም ክትትሉና ማወከቡ በመቀጠሉ እንድልቤ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ተቸግሬያለሁ።
#ለተወሰነ ጊዜ የብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤቱ የዩጋንዳ ሪፕረዘንታቲቭ ዲፕሎማት ሆኜ በቆየሁበት ወቅት በጣት
ክሚቆጠሩ ወዳጆቼ በቀር አብሮኝ ሻይ የሚጠጣ ወገን እስከማጣት የደረስኩበትና የፖለቲካ ሰው እስክመስል ድረስ(
በወዳጅም በኢ-ወዳጅም)በፖለቲካ አክቲቪስትነት ተፈርጄ መራራ ወቅቶችን አሳልፌያለሁ።አሳዳጆቼ መውጫ መግቢያ
በማሳጣት ሐገር ለቅቄ እንድጠፋ ቢፈልጉም ሃገር አልባው የትም ልሄድ እንድማልችል ግን አላወቁም።
በየጊዜውችግሬን ለሚመለከታቸው አካላት ባቀርብም ዘላቂ መፍትሄ አላገኘሁም።ውሎዬ በጠላት በተወረረ ፈንጂ ወረዳ ውስጥ ነው።
የተለያዩ ጹሁፎችን” በኢትዮጲያን ሪቪው” ኦን ላይን ላይ ፖስት በማድረግ ሃስብን በነጻነት የመግለጽ ነጻነቴን
ኤክሰርሳይስ ሳደርግ ብቆይም ከዲሴምበር 2013 አጋማሽ በሳውዲ የሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን የሰባዊ መብት
ረገጣ በመቃውም ለዓለም ህብረተሰብ ድምጻችንን ለማሰማት ህዝባዊ ስብሰባ በኮሚኒቲ ደረጃ ለማዘጋጀት በማስተባበሬ
የወያኔ ቆንስላ ለዩጋንዳ መንግስት ደብዳቤ በመጻፍ ፖሊስ ጣቢያ ድረስ ከኮሚኒቲ ለቀመንበራችን አቶ ዘለቀ ጀበሮ
ጋር ተጠርተን ስብሰባውን እንድናቆም በከፍተኛ የፖሊስ ኮማንደሮች ጥብቅ መመርያ ተሰጥቶን ስብሰባውን ለመሰረዝ
ተገደናል።
በጉዳዩ ዙርያ ያማከርኩዋቸው “የሰባዊ መብት ተከራካሪ ድርጅትና” “የኢንተሬድ ሌጋል ኦፊሰር” እንደነገሩኝ
የማደርጋቸውን ተግባራት እንዳቆምና በሃገሬ ዙርያ የምጽፋቸውን ስራዎች ማቆም እንድሚገባ በማስጠንቀቃቸው
“ከኢትዮጲያን ሪቪው” ኦን ላይን ድረ ገጽ ዜናዎችናጹሁፎች ማተሜን አቁሜያለሁ።
አማካሪዎቼ እንዳሉት ሐገር አልባ ስደተኛ በተሰደደበት ሐገርና በስደት በሚኖርበት ሐገር ጉዳይ ላይ መሳተፍ
እንደማይችል ዩጋንዳ በ2006 ያወጣችው “የሪፊውጂ አክት “ይጠቅሳል።
#ሃገር አልባ(stateless)ዝም ማለት አለበት እንደማለት ነው።
ስደተኞች የራሳቸውን ማህበር መመስረት አለባቸው የሚል ሃሳብ ከጥቂት መሰል ወገኖች ጋር ከMar 2013 ጀምሮ
በርካታ ውይይቶች በማድረግና አስተባባሪ ኮሚቴ በማቋቋም የማስታወቅያ ስራዎችን በመስራቴ ካምፓላ
ለኔ የስጋት ስፍራ ሆናለች።
እንደ ጋዜጠኛና ሰባዊ መብት ተሟጋች እየጻፍኩ ለመኖር አስጊ ሁኔታ ላይ መሆኔን ማን ሊረዳልኝ እንደሚገባ ምላሹን
ከአንባቢ እጠብቃልሁ።
በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኜ ነው አለማቀፉን የስደተኞች ቀን ኡጋንዳ ላይ ለስድስተኛ ጊዜ ለማክበር በዋዜማ ላይ የምገኘው።
የዘንድሮው የስደተኞች ቀንን ለኔ ልዩ የሚያደርገው “ለዓመታት የደከምንበት “በዩጋንዳ የኢትዮጲያዊያን ስደተኞች
ማህበር በዩጋንዳ”የመመስረት ሂደት በጣት የሚቆጠሩ ቀናት በቀሩበት ሁኔታ በመሆኑ የህሊና ዕርካት እንደተሰማኝ
ለመግለጽ እወዳለሁ።
ዓለማቀፉ የሰባዊ መብትና የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ግለስቦች ለኔና መሰል ስደተኛ ወገኖች ተጨባጭ
የሆነ መፍትሄ ይዘው እንዲቀርቡና( ከሙታን በላይ ከቋሚ በታች ) ከሆነው ሕይወታችን እንዲታደጉን የሁሉ መፍትሄ
ምንጭ በሆነው 1አምላክ ስም ጩኸቴን አሰማለሁ።
በምስራቅ አፍሪካ ያለን ጥቂት ያካባቢው ስደተኛ ጋዜጠኞች በዩጋንዳ ጋዜጠኞች ዩኒየን ቢሮ ከ Dec 2012 ጀምሮ
ለመሰባሰብ ብንሞክርም ሁኔታዎች ባለመመቻቸታቸው እንደባለሙያ የጎላ ተግባራት ባናከናውንም በስም ደረጃ
ተደራጅተናል።
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የአለም አቀፉ የስደተኞች ቀን ሊከበር ቀናት በቀሩበት ሁኔታ ለኔና ከኔ ጋር
ከSep2007 ጀምሮ የመከራ ሕይወት የምትገፋውና ለኔ ብላ ስደተኛ ለሆነችው ባለቤቴ ምን አዲስ ተስፋ ይዞ
እንደሚመጣ የምናየው ይሆናል።
ፍትህና መፍትሄ ለኛ በ2014 በአምላክ ፈቃድ ይሁን!!!
ደረጀ በጋሻው(penethiopian)
የምስራቅ አፍሪቃ ስደተኛ ጋዜጠኞች ማህበር ሊቀ መንበርና
የኢትዮጲያ ማህበረሰብ በዩጋንዳ ማህበራዊ ጉዳይ ተጠሪ
ካምፓላ ኡጋንዳ
ሰኔ 11ቀን 2006 ዓ/ም(June 18,2014)
እግዚአብሄር አምላክ የስደትና የመከራ ዘመኔን መፍትሄ ይስጠው።
+256782302124
↧
ግልጽ ደብዳቤ!
↧