ከዳዊት ሰለሞን
የሙስሊሞችን ሰላማዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተከትሎ ብዛት ያላቸው የእምነቱ ተከታዩች ለእስራት መዳረጋቸው አይዘነጋም፡፡ፈቲያና ያሲንም ይማሩበት ከነበረው ጅማ ዩኒቨርስቲ ተይዘው በቂሊንጦና ቃሊቲ ወህኒ ቤቶች ከታሰሩ አንድ ዓመት ተቆጥሯል፡፡
ወህኒ የተከረቸመባቸው ሁለቱ ወጣቶች በያዝነው ክረምት በጋብቻ ለመጣመር (ኒካህ ለማሰር) እቅድ ነበራቸው፡፡የወህኒ በሮች ቢቆለፍባቸውም ፣ወዳጅ ዘመዶቻቸው ተሰባስበው ድል ባለ ሰርግ ለመጋባት ባይቻላቸውም ልባቸው አንድ በመሆኑ ቀን የቀጠሩላት ጊዜ እንድታልፋቸው አልፈቀዱም፡፡
ኬክ አስጋግረው ፈቲያን እንኳን ደስ አለሽ ለማለት ዛሬ ከቀኑ ስድስት ሰዓት ቃሊቲ የተገኙ ጓደኞቿን፣ቤተሰቦቿንና ታናሽ ወንድሟን የማግኘት ዕድል አጋጥሞኝ ነበር፡፡ለወትሮው ፈቲያን ለመጠየቅ በቃሊቲ የሚፈቀደው ከ6፡00 እስከ 6፡30 ነበር ፡፡
ቃሊቲ በር ላይ ለፍተሻ የተመደቡ ፖሊሶች የፈቲያን ጎብኚዎች ‹‹ቀለበት ይዛችሁ እንደመጣችሁ መረጃ ደርሶናል›› በማለት ጠንከር ያለ ፍተሻ ሲያካሄዱባቸውም ተመልክቻለሁ፡፡
ኬክ ይዘው ፈቲያ ጋር እንደደረሱ የሰርግ ዘፈን ጓደኞቿና ቤተሰቦቿ መዝፈን መጀመራቸው ግን ፖሊሶቹን አላስደሰተም እናም ከአምስት ደቂቃ በላይ ሳያገኟት ግቢውን ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡
‹‹ምን ተሰማሽ››የፈቲያ የልጅነት ጓደኛዋ የሆነች ወጣትን ጠየቅኳት‹‹በዚህ ቀን እንኳን እንድናግራት አልፈቀዱልንም፡፡ፈቲያ ግን አንድም ቀን ስለሆነው ነገር ስታማርር ሰምቼያት አላውቅም፡፡የእርሷ የመንፈስ ጥንካሬ እኔንና መሰሎቼን እንድንበረታ ያደርገናል››ብላለች፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በዛሬው ዕለት ያሲንን በቂሊንጦ በመጎብኘት ወዳጆቹ ‹‹እንኳን ደስ አለህ››ማለታቸውን ሰምቼያለሁ፡፡