ወጣቶች በአልሞ ተኳሽ ግንባራቸው ሲበረቀስና ልባቸውን ሲመቱ ስናስታውስ እንባ ያልተናነቀው ያለ አይመስለኝም፡፡ እነዚህ እውነተኛ መስዋዕትነት የከፈሉ ወጣቶች ደመከልብ ሆነው እንዳይቀሩ ኃላፊነቱ የእኛ ነው፡፡ የእነሱን ደም ልንበቀል የምንችለው የቆሙለትን አላማ እውን ስናደርግ ነው፡፡ ይህንን አላማ እውን ስናደርግ እንደ ሞቱም ላይቆጠር ይችላል፡፡ ሌላኛው የምንበቀልበት መንገድ ደግሞ ህግን በመንተራስ ነው፡፡ በአገራችን ባለስልጣናት በየጊዜው ወንጀል እየፈጸሙ፣ በወንጀል እየተነከሩ፣ ምንም ተጠያቂነት ሳይኖርባቸው ለብዙ ጊዜ ታልፈዋል፡፡ በአገራችን ባለስልጣናት ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ ያለመሆን ባህል በሰፊው የተስፋፋ ነው፡፡
አሁንም ቢሆን ይህን ባህል መስበር ይኖርብናል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ለሰራው ወንጀል ተጠያቂ መሆን አለበት፡፡ በተለይ ባለስልጣናት ከባድ ከባድ ወንጀል እየሰሩ በነጻነት ሳይጠየቁ የሚያልፉበት ጊዜ አለ፡፡ ይህ በእውነት መታረም ያለበት ነገር ነው፡፡ ለሰሩት ወንጀል ተጠያቂነት መኖር አለበት፡፡ በዛ አይነት ነው ወንጀል እንዳይፈጸም ልንገታው የምንችለው፡፡ አንድ ሰው በሰራው ወንጀል ተጠይቆበት ከተቀጣ ለሌላው ማስተማሪያና ምሳሌ ይሆናል፡፡ አሁንም ቢሆን እነዚህ ወጣቶችን ግንባር ግንባራቸውንና ልባቸውን ተኩሰው መትተው የገደሉ ሰዎች ከተጠያቂነት አይድኑም፡፡ ከ70 አመት በፊት በናዚ ዘመን በግፍ ሰው የጨፈጨፉ በቅርብ ጊዜ እስፔን ውስጥ ተይዘው ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያን ወጣቶች የጨፈጨፉትንም በህግ የምንበቀልበት ጊዜ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ ማናችንም ብንሆን ከልባችን የምናወጣው ነገር መሆን የለበትም፡፡ እኔ እንደ ህግ ባለሙያ ይህን ጉዳይ ባመቼ ጊዜ ለማንሳት ቃል እገባለሁ፡፡