በሁለቱም ወገን የተመረጠው ውህደት አመቻች ኮሚቴ ሰኞ ስራ ይጀምራል
የአራት አመት የድርድርና የምክክር ጊዜ የፈጀው የመላው ኢትዮጵያ ድርጅት (መኢአድ) እና የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ቅድመ ውህደት ባለፈው እሁድ የተፈረመ ሲሆን ሁለቱ ፓርቲዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚዋሀዱ የፓርቲዎቹ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ አንድነት ፓርቲ ነገ ብሄራዊ ምክር ቤቱን ለአስቸኳይ ስብሰባ የጠራ ሲሆን የስብሰባው ዓላማም የጉባኤ አዘጋጅ ኮሚቴን ለመምረጥ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ኮሚቴው በብሄራዊ ም/ቤቱ እንደሚሰየም የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ አያሌው ተናግረዋል፡፡ የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ተስፋሁን አለምነህ ለአዲስ አድማስ እንዳብራሩት፤ የመኢአድ ስራ አስፈፃሚ አምስት አባላት ያሉት የውህደት አመቻች ኮሚቴ መርጦ ለአንድነት በደብዳቤ ያሳወቀ ሲሆን አባላቱ አቶ ወርቁ ከበደ፣ አቶ ተስፋሁን አለምነህ፣ አቶ ሲራክ አጥናፍ፣ አቶ ሙሉ ጌታ አበበና አቶ ካሳሁን አበባው ናቸው፡፡ በአንድነት በኩል ያሉት አዘጋጅ ኮሚቴው ነገ በብሄራዊ ም/ቤቱ ከተመረጡ በኋላ ይፋ እንደሚሆኑ የተናገሩት አቶ ሀብታሙ አያሌው፤ ከሁለቱም ፓርቲዎች የተውጣጡ እና 10 አባላት ያሉት ውህደት አመቻች ኮሚቴ ሰኞ ስራውን እንደሚጀምር ገልፀዋል፡፡
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ውህደቱ እንደሚፈፀም የገለፁት አቶ ሀብታሙ፤ ስለውህዱ ፓርቲ ስያሜ፣ መተዳደሪያ ደንብ፣ ስለ አጠቃላይ የውህደቱ ፓርቲ ፕሮግራም፣ አርማና ድርጅታዊ አወቃቀር ውይይት ተደርጎ ሙሉ በሙሉ ውህደቱ ይጠናቀቃል ብለዋል። ባለፈው እሁድ በተደረገው ቅድመ ውህደት ላይ ስለተነሳው ረብሻና ድብድብ የተጠየቁት የመኢአድ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ፤ ረብሻ በማስነሳት ቅድመ ውህደቱን ለማሰናከል ሙከራ ያደረጉት ሰዎች የኢህአዴግ ካድሬዎች መሆናቸው በማስረጃ ደርሰንበታል” ያሉ ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን ሁሉም ነገር በሰላም እየተከናወነ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
አዲስ አድማስ