በጥቅምት 2006 ይጠናቀቃል የተባለው የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ገና አልተጀመረም
የፋብሪካ ግንባታ በመጓተቱ፤ የ100 ሚሊዮን ብር ሸንኮራ አገዳ ያለ ጥቅም ተወግዷል
የፕሮጀክቶቹ የገንዘብ ወጪ በውል አይታወቅም፤ ያለ ጥናትና ዲዛይን የተጀመሩ ናቸው
መንግስት በመቶ ቢሊዮን ብር ወጪ የስኳር ምርትን 23 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ የሚያካሂዳቸው ከአስር በላይ አዳዲስና ነባር የስኳር ፕሮጀክቶች ያለ ውጤት ለአመታት የተጓተቱ ሲሆን፤ የመስኖና የፋብሪካ ግንባታዎቹ ለተቋራጭ ድርጅቶች የተሰጡት በህገወጥ መንገድ ያለጨረታ እንደሆነ የፌደራል ኦዲተር ገለፁ፡፡ አስር የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ህግን ባልተከተለ መልኩ ያለ ጨረታ ሙሉ ለሙሉ ለብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን መሰጠቱን ኦዲተሩ ጠቅሶ፤ የፋብሪካዎቿ ግንባታ እንደተጓተተ ገልጿል፡፡ ያለ ጨረታ የመስኖና የአገዳ ልማት ፕሮጀክቶችን ወስደው ስራ ያጓተቱ ተቋራጮች፤ በአዲስ አበባና በየክልሉ የሚገኙ የውሃ ስራ ድርጅቶች እንዲሁም የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ናቸው፡፡ ፕሮጀክቶቹ የመንግስትን የግዢ መመሪያ ባልተከተለ መልኩ ያለ ጨረታ ለተቋራጮች መሰጠታቸው፣ በታቀደላቸው ጊዜና ወጪ እንዳይጠናቀቁ ያደርጋል ብሏል – የኦዲተሩ የምርመራ ሪፖርት፡፡
ፕሮጀክቶቹ ለተቋራጮቹ የተሰጡበትን አሰራር በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የኮርፖሬሽኑ የስራ ሃላፊዎች፣ በግዢ ክፍሉ በኩል የምናውቀው ነገር የለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የኮርፖሬሽኑን የአምስት አመታት እቅድ አፈጻጸም በተመለከተ የቀረበው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በጣና በለስ እና በኦሞ-ኩራዝ ፕሮጀክቶች፣ የ3 ፋብሪካዎች ግንባታ እስከ ጥቅምት 2005 ዓ.ም እንዲጠናቀቅ እቅድ ወጥቶ እንደነበር የገለፀው የፌደራል ኦዲተር፤ እስከ አመቱ መጨረሻ የተከናወነው ስራ ግን ከ45 በመቶ እንደማይበልጥ ገልጿል፡፡ በጥቅምት ወር 2006 ዓ.ም ይጠናቀቃል የተባለው የወልቃይት የስኳር ፋብሪካ ግንባታም፣ ገና ግንባታው ሳይጀመር የእቅዱ ጊዜ ማለፉ ተገልጧል፡፡
በአገዳ ተክል ልማት፣ በመስኖ ስራና በፋብሪካ ግንባታ በኩል ኮርፖሬሽኑ የሚያዘጋጃቸው የስኳር ፕሮጀክት እቅዶች የሰው ሃይልንና የገንዘብ ምንጭን ያላገናዘቡ፣ ተግባሪ አካላትን ያላሳተፉና በበቂ ጥናት ላይ ያልተመሰረቱ መሆናቸውን በምርመራ እንደደረሰበት ኦዲተሩ ገልፆ፤ በዚህም ምክንያት የኮርፖሬሽኑ ዓመታዊ እቅዶች በአመት ከሶስት ጊዜ በላይ ይከለሳሉ ብሏል፡፡ ይህም ፕሮጀክቶቹ እንዲጓተቱ ማድረጉንና መንግስትን ተገቢ ላልሆነ ወጪ እየዳረገው እንደሚገኝ የኦዲተሩ ሪፖርት ገልጿል፡፡ የተንዳሆ ስኳር ፕሮጀክት የፋብሪካ ግንባታ ስራ በታቀደለት ጊዜ መጠናቀቅ ባለመቻሉ ምክንያት፣ በ5ሺህ164 ሄክታር መሬት ላይ የለማ የሸንኮራ አገዳ ምርት ጥቅም ላይ ሳይውል እንዲወገድ መደረጉን ኦዲተሩ ጠቅሶ፤ በዚህም ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰ አመልክቷል፡፡
ፕሮጀክቶቹ በትክክል ምን ያህል ገንዘብ ወጪ እንደተደረገባቸው በውል ለመለየት አለመቻሉን የገለጸው የኦዲተሩ ሪፖርት፤ ከአገዳ ልማት፣ ከመስኖ ግንባታና ከፋብሪካ ግንባታ ክፍል ጋር የተቀናጀና የተጠናከረ የፕሮጀክት ክትትልና ቁጥጥር አሰራር ባለመኖሩ ምክንያት በየአመቱ ተደጋጋሚ የዕቅድ ክለሳ በማድረግ የዕቅድ አፈጻጸም መጓተትን፣ የወጪ መጨመርን፣ የጊዜ መራዘምንና የሃብት ብክነትን አስከትሏል ብሏል፡፡ ፕሮጀክቶቹ ለአመታት መጓተታቸው፤ የሃብት ብክነትን ከመፍጠር በተጨማሪ በአምስት አመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ የተቀመጠው ግብ እንዳይሳካ ማድረጋቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ የአገሪቱ የስኳር ምርት በየአመቱ እንደሚጨምር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ከ2003 ዓ.ም ወዲህ የስኳር ምርት እየቀነሰ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በአምስት አመት ውስጥ የስኳር አመታዊ ምርት ከ3 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 22 ሚሊዮን ኩንታል እንዲያድግ ታቅዶ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ እስካሁን አራት ሚሊዮን ኩንታል አለመድረሱ ተዘግቧል፡፡
ምንጭ፥ – አዲስ አድማስ